Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአዲስ አበባ በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ስድስት በመቶ መጨመሩ ተገለጸ

በአዲስ አበባ በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ስድስት በመቶ መጨመሩ ተገለጸ

ቀን:

በአዲሰ አበባ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በመቶ ሺሕ ሕዝብ የሚመዘገበው የሞት ቁጥር ቢቀንስም፣ በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ስድስት በመቶ መጨመሩ ተገለጸ፡፡

በአገሪቱ ከሚገኙ ተሽከርካሪዎች ውስጥ ከ52 በመቶ በላይ ወይም 728,504 የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች በሚገኙባት አዲስ አበባ፣ በ2014 ዓ.ም. 411 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ22 ሰዎች ወይም ስድስት በመቶ መጨመሩ ታውቋል።

በተጨማሪም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በአዲስ አበባ 1,900 ግለሰቦች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱ የታወቀ ሲሆን፣ በ2013 የደረሰው ጉዳት 1,824 እንደነበርና በአካል ላይ የደረሰው ጉዳት በ76 ወይም አራት በመቶ ጨምሯል ተብሏል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በመዲናዋ የመንገድ ደኅንነት ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ መተግበሩ ያስገኛቸው ውጤቶች ቢኖሩም፣ ነገር ግን የትራፊክ አደጋና መጨናነቅ የከተማዋን ዕድገት እየተፈታተኑት ከመሆኑም በላይ በተለይም የትራፊክ አደጋ በከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡

ስትራቴጂው ተግባራዊ በመደረጉ በተለይም የትራፊክ አደጋ ሞት በመቶ ሺሕ ሕዝብ በ2013 ዓ.ም. ከነበረበት 11.6 በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ወደ 11.4 ዝቅ ማለቱ የታወቀ ሲሆን፣ በአሥር ሺሕ ተሽከርካሪ የሚደርሰው የሞት አደጋ ምን ያህል ነው? የሚለው ላይ ጥናት እየተደረገ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ መንገድ ደኅንነት ምክር ቤት አስታውቋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የመንገድ ትራፊክ ደኅንንት ስትራቴጂውን ለመተግበር ያቋቋመው የአዲስ አበባ ከተማ መንገድ ደኅንነት ምክር ቤት አባል ተቋማት የ2014 ዓ.ም. የዕቅድ ተግባር አፈጻጸማቸውን መስከረም 24 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢንተር ኮንቲኔንታል (ሌግዠሪ) ሆቴል ገምግመዋል፡፡

የመንገድ ደኅንነት ምክር ቤት ቤቱ ፀሐፊና የአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚደቅሳ ባቀረቡት ሪፖርት፣ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በከተማዋ አምስት የመንገድ መጋጠሚያዎች የመንገድ ማሻሻያ ሥራ፣ ደንብ ተላላፊዎች በሲስተም ክፍያቸውን እንዲፈጽሙ ማስቻል፣ ለዕይታ የሚያስቸግሩና ለአደጋ የሚያጋልጡ ቦታዎችን የመለየትና አንጸባራቂ የመትከል ሥራዎች ተሠርተዋል ተብሏል፡፡

በተሠሩት ሥራዎች የተገኙ ውጤቶች ቢኖሩም የምክር ቤት አባል ተቋማት ላይ የሚስተዋለው የቅንጅት ችግር፣ ሪፖርቶችን በወቅቱ አለመላክ፣ ተቋማቱ ተጠሪ ባለሙያዎችን አለመመደባቸው በዓመቱ ያጋጠመ ችግር መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች በከተማዋ ከሚደርሰው አደጋ 80 በመቶ የሚደርሰው እግረኞች ላይ እንደመሆኑ ይኼንን ለመቀነስ እየተሠራ ያለው ሥራ በቂ አለመሆኑን፣ የመንገድ ደኅንነት ማሻሻያዎች ከተሠሩ በኋላ በቂ ክትትል አለመደረጉ፣ በዋና መንገዶች ላይ የሚካሄዱ ግብይቶችና የእግረኛን መንገድ የሚዘጉ የግንባታ ቁሶች፣ የተሽከርካሪ ጥገናዎችና ጎሚስታዎች የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ጥብቅ ቁጥጥር አለማከናወናቸው፣ በጤና ጣቢያዎች የትራፊክ አደጋ ከደረሰ በኋላ የሚሰጠው የተቀናጀ ምላሽ የላላ መሆኑን በማንሳት ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 3,971 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ 23 ቢሊዮን ብር የንብረት ውድመት ደርሷል፡፡ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ የደቡብ ሕዝቦች ክልል እንዲሁም አዲስ አበባ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ የተመዘገበባቸው ክልሎችና የከተማ አስተዳደር መሆናቸው ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የወጪ ንግድ ፖሊሲያችን አገርን የሚጠቅምና ሕገወጥነትን የሚነቅል ሆኖ እንደ አዲስ ሊቀረጽ ይገባል!

ኢትዮጵያ ያልተቋረጠ የውጭ ምንዛሪ ችግር ውስጥ እንድትገባ ካደረጓት የተለያዩ...

የኢትዮጵያ ከአጎአ የገበያ ዕድል መታገድ በኢንዱስትሪዎች ላይ ያስከተለው ጉዳት

የአሜሪካ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ2000 መገባደጃ ላይ ያፀደቀው የአፍሪካ ዕድገትና...

የአብዮቱ ያልተዘጉ ዶሴዎች

‹ዳኛው ማነው› ሒሳዊ ንባብ - ሐሳብና ምክንያታዊነት በዚያ ትውልድ...