Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አራት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ሊቀርብ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኅብረት ሥራ ማኅበራት በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ለሚገኙ ተጎጂዎች ሰብዓዊ ምላሽ የሚሆን ከአራት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የግብርና ምርት፣ ለአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በቀጥታ ሊያቀርቡ ነው፡፡

ሰኞ መስከረም 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተደረገ ውይይት፣ የኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በተያዘው የበጀት ዓመት አራት ሚሊዮን ኩንታል የስንዴና የበቆሎ ምርቶችን ከኅብረት ሥራ ማኅበራት ለመግዛት ማቀዱ ተገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ በተለይ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብና በሲዳማ ክልሎች ውስጥ ከሚገኙ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር የግዥ ስምምነት ሲያደርግ መቆየቱ ተገልጾ፣ ከዚህ ቀደም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝና በአገሪቱ ከተከሰቱ ግጭቶች ጋር ተያይዞ ዘንድሮ ያቀደውን ያህል ምርት አለማቅረቡን፣ የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወ/ሮ አያልሰው ጥሩነህ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ወ/ሮ አያልሰው እንዳስረዱት፣ በተለይም ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ የስንዴ፣ የበቆሎና የማሽላ ምርቶችን የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከፌዴራል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመሆን ያለ ጨረታ በቀጥታ ግዥ ግብይት ሲፈጽሙ ቆይተዋል፡፡

ከላይ ያሉት ጉዳዮች እንደተጠበቁ ሆነው በመሀል የነበሩና በሁለቱም አካላት የሚነሱ ችግሮች እንደነበሩ ተገልጾ ጥራት፣ በጊዜ ምርት አለማቅረብ፣ የፋይናንስ እጥረትና የመጋዘን እጥረት ችግሮች ያጋጥሙ ነበር ተብሏል፡፡

አብዛኛው ችግር እየተቃለለ ቢመጣም የፋይናንስ ችግር እስካሁን ሳይፈታ መቀጠሉ ተመላክቶ፣ በተለይም የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እንደ ሌሎች ተቋማት የግዥ ቅድመ ክፍያን መክፈል የሚችልበት አሠራር አለመኖሩ፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ደግሞ የሚፈለገውን ምርት በወቅቱ ሰብስበው ለማቅረብ የገንዘብ እጥረት ማነቆ ሆኖባቸው መቆየቱን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሯ አክለዋል፡፡

የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ በተለይም ውስን በሆነው የምርት መሰብሰቢያ  ወቅት የፋይናንስ አቅርቦት ካልቀረበላቸው፣ ምርቱን በተባለው ጊዜ ለማቅረብ እንደሚያዳግታቸው ያስረዱት ወይዘሮ አያልሰው፣ የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽኑ የቅድሚያ ክፍያ በመፈጸም ምርትን በወቅቱ ለማድረስ የሚያስችል ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ከኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ጋር የትኛውን ምርት፣ በምን ያህል መጠንና ደረጃ ይቀርባል የሚለውን የሚያካትት ስምምነት እንደሚኖር ተመላክቷል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበሩ የግብይት ሒደቶች ከሚታዩ ችግሮች ውስጥ ምርት ለአደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽኑ ከመጫኑ በፊት ከተከማቸበት መጋዘን ናሙና ተወስዶና ተፈትሾ መጫን ያለበት ቢሆንም፣ ረዥም ኪሎ ሜትሮችን ተጉዞ በኮሚሽኑ ማከማቻ ናሙና ሲወሰድ በሚፈጠር ችግር ተመላሽ መሆኑ ከፍተኛ ኪሳራ ሲያደርስ ቆይቷል ተብሏል፡፡ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ምርት በማኅበራቱ መጋዘን እንዳለ ፍተሻ ተደርጎ የሚጫንበትና በቀጥታ እንደሄደ የሚያራግፍበት አሠራር መዘርጋቱ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል የሚቀርቡ ምርቶች የሚፈለገውን የጥራት ደረጃ ያሟሉ መሆናቸውን መቆጣጠር የተያዘው ዓመት ዋነኛ ተልዕኳቸው እንደሚሆን ያስረዱት ወይዘሮ አያልሰው፣ ከዚህ ጋር በተገናኘ ችግር በተስተዋለባቸው ማኅበራት ላይ ፈቃዳቸውን እስከመንጠቅ የሚደርስ ዕርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡

ለተጎጂዎች ሰብዓዊ ምላሽ የሚሆን የግብርና ምርቶችን ቀጥታ ለማቅረብ ስምምነት በተደረሰበት መድረክ የግብርና ሚኒስቴር፣ የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ የኦሮሚያ፣ የአማራና የደቡብ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲዎች፣ የክልሎቹ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየኖችና ሌሎች የባለድርሻ አካላት አመራሮች መታደማቸው ተጠቅሷል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች