Wednesday, May 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በውጭ ምንዛሪ ፈቃድ ችግር የተያዙ ዕቃዎችና ሰነዶች እንዲለቀቁ ጉምሩክ ኮሚሽን ወሰነ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከባንክ ከተሰጣቸው የውጭ ምንዛሪ ፈቃድና ወደ አገር ውስጥ ካስገቡት ዕቃ ጋር በተያያዘ፣ የተለያዩ ችግሮች የተገኙባቸው አስመጪዎች፣ ዕቃዎቻቸውና ሰነዶቻቸው እንዲለቀቁላቸው የጉምሩክ ኮሚሽን አስተዳደራዊ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

ኮሚሽኑ ውሳኔውን ያስተላለፈው በባንክ ፈቃድ ላይ ከተጠቀሱ የዕቃዎች መጠን በላይ ያልተጠቀሱ ዕቃዎችን ጨምረው ባስመጡ፣ እንዲሁም ከባንክ በተፈቀደላቸው የውጭ ምንዛሪ ሙሉ ለሙሉ የተለዩ ዕቃዎችን ባስገቡ አስመጪዎች ላይ ነው፡፡ የባንክ ፈቃዳቸው፣ ፈቃድ በሌለው ባለሥልጣን ተፈርሞ ወይም በሐሰተኛ የባንክ ፈቃድ ዕቃ ያስገቡ አስመጪዎችም ውሳኔው ይመለከታቸዋል፡፡

ኮሚሽኑ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው ለአንድ ጊዜ ብቻ መሆኑን ለሪፖርተር የተናገሩት የጉምሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አዘዘው ጫኔ፣ ከእነዚህ መካከል ዕቃዎቹና ሰነዶቹ በጉምሩክ ተይዘው ዓመታት የቆዩ እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ አቶ አዘዘው እንደሚያስረዱት፣ የኮሚሽኑ አስተዳደር ይህንን ውሳኔ በቃለ ጉባዔ ያስተላለፈው እንደ አዳማ፣ ሰመራ፣ ሞጆና ቦሌ ኤርፖርት ካሉ የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በመጣ ተደጋጋሚ ጥያቄ የተነሳ ነው፡፡

በቦሌ ኤርፖርት በሚገኘው የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ብቻ በዚህ ውሳኔ ጉዳያቸው የሚታይ ከ250 በላይ አስመጪዎች መኖራቸውን በምሳሌነት አውስተዋል፡፡

እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ፣ በዚህ መንገድ ጉዳያቸው የሚታይ አስመጪዎች ዕቃዎቻቸውን ያስመጡበት የውጭ ምንዛሪ ፈቃድና የዕቃው ዝርዝር ላይ ችግር ቢኖርም፣ ላስገቡት ዕቃዎች የሚጠበቅባቸውን ግብርና ቀረጥ ከፍለዋል፡፡ አብዛኞቹ ዕቃዎችም ወደ አገር ውስጥ እንዲያልፉ ተደርገው ሰነዳቸው ብቻ እንደተያዘ ገልጸዋል፡፡

‹‹ያልተለቀቁት ዕቃዎችም ቢሆኑ ቀረጥ የተከፈለባቸው ናቸው፡፡ ዕቃውን መመለስና የተከፈለውን ቀረጥ ከመንግሥት ካዝና አውጥቶ መልሶ መክፈል አስቸጋሪ ነው፤›› ሲሉ የኮሚሽኑ አስተዳደራዊ ውሳኔ ያስተላለፈበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡

ዕቃው ጉምሩክ ጋር ከመምጣቱ በፊት ባንኮች የፈቀዱትን ‹‹ፕሮፎርማ ኢንቮይስ›› ከመጣው ዕቃ ‹‹ኮሜርሻል ኢንቮይስ›› ጋር ሳያስተያዩ ወደ ጉምሩክ መላካቸው፣ እነዚህ ዕቃዎች ላይ ችግር የተፈጠረበት አንድ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የጉምሩክ ሠራተኞችም ቢሆኑ ቀረጥና ታክስ መከፈሉን እንጂ የገባው ዕቃ መጀመሪያ የተፈቀደው መሆንና አለመሆኑን የማረጋገጥ ሥራ አለማከናወናቸው ሌላው ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የእነዚህ ችግሮች መሠረት የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንደሆነ የሚናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ይህም አስመጪዎች በአነስተኛ ዋጋም ቢሆን የውጭ ምንዛሪ ፈቃድ ካገኙ አያይዘው ሌሎች ዕቃዎች በብዛት እንዲያመጡ እንዳደረጋቸው ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ባንክ በአንድ ሺሕ ዶላር ሁለት ኮንቴይነር ዕቃ እንዲመጣ የሚፈቅድ ከሆነ፣ ለሚመጣው ዕቃ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ የለኝም እያለ ነው ማለት ነው፤›› ካሉ በኋላም፣ አስመጪዎች በዕቃውና በተፈቀደላቸው የውጭ ምንዛሪ መካከል ያለውን ልዩነት ‹‹ከጥቁር ገበያ›› በመሙላት እንደሚያስመጡም ጠቁመዋል፡፡

በዚህ መሠረታዊ ችግር ምክንያት የሚገቡ ዕቃዎች ሰነድ ላይ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት አንደኛው መፍትሔ፣ የውጭ ምንዛሪን በበቂ ሁኔታ ማቅረብ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት አንፃር ይህንን ማድርግ አስቸጋሪ መሆኑን አቶ አዘዘው አውስተዋል፡፡

‹‹[ሌላው አማራጭ] ዕቃ እንዳይገባ መከልከል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለተጠቃሚው ኅብረተሰብ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው፤›› ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ በዚህ ምክንያት ሥርዓታዊ አካሄዶች ላይ ለተፈጠሩ ችግሮች አስተዳደራዊ ውሳኔ መተላለፉን አብራተርተዋል፡፡

ከባንክ ባልተሰጠ ፈቃድ ዕቃዎችን ያስገቡ አስመጪዎች በተገቢውን ታክስና ቀረጥ ከፍለው ዕቃቸውን እንዲለቀቅ፣ የተለቀቀላቸውም ሰነዳቸው እንዲለቀቅ ውሳኔ ቢያሳልፍም፣ አስመጪዎቹ የሕግ ተጠያቂነት እንደሚኖርባቸው ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡ ኮሚሽኑ ውሳኔውን አስመልክቶ መስከረም 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ለቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በጻፈው ደብዳቤ፣ ‹‹የሕግ ተጠያቂነትን በተመለከተ ከሚመለከተው የወንጀል ምርመራ ተቋም ጋር በጋራ የሚሠራ መሆኑ ታውቆ አገልግሎት እንዲሰጥ›› የሚል መልዕክት አሥፍሯል፡፡

ምክትል ዋና ኮሚሽነሩ አቶ አዘዘው፣ ኮሚሽኑ ጉዳያቸውን ወደ ፌዴራል ፖሊስ አስተላልፎ በምርመራ ላይ ያሉ አስመጪዎች እንዳሉ አክለው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች