Wednesday, February 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በዓላት ከውጥረት ተላቀው የአገር ሰላምና ልማት ተስፋ ይሁኑ!

በአራቱም ማዕዘናት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዓላትን ሲያከብሩ ከምንም ነገር በላይ የሚያስቀድሙት የአገር ሰላም ነው፡፡ አገር ሰላም ስትሆን በዓላት ይደምቃሉ፡፡ አገር ሰላሟ ሲቃወስ በዓላትም ይደበዝዛሉ፡፡ በኢትዮጵያ በርካታ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት አሉ፡፡ እነዚህ በዓላት ሲከበሩ ኢትዮጵያውያን አንዳቸው ለሌላቸው መልካም ምኞታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ ጎልማሶችና አዛውንቶች በበዓላት ወቅት ከወትሮ ለየት ያለ የደስታ ስሜት የሚሰማቸው ከምንም ነገር በላይ ሰላም ሲኖር ነው፡፡ ለአገርም ቢሆን ሰላም ሰፍኖ በዓላት ደምቀው ሲከበሩ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በተለይ በአደባባይ የሚከበሩ በዓላት ከውጥረት ተላቀው ሰላማዊ እንዲሆኑ ትኩረት ያስፈልጋል፡፡ በዓላትን ከፖለቲካዊ ትንቅንቅ ማላቀቅ ሲቻል ትልቅ ሀብት ያመነጫሉ፡፡ በዓላት ሲደርሱ በግልም ሆነ በአገር ደረጃ ጭንቀትና ሥጋት ከማስተጋባት፣ ጠቀም ያለ ገቢ እንዲገኝባቸው ዘመናዊ አሠራሮች ላይ ማተኮር ያዋጣል፡፡ በተለይ አገርን የሚያስተዳድረው መንግሥትም ሆነ ሌሎች የግሉ ዘርፍ ተዋንያን፣ የአደባባይ በዓላት ከውጥረት ተላቀው በተለያዩ መስኮች ገቢ እንዲያስገኙ፣ በጥናት ላይ የተመሠረቱ ሥራዎች ላይ ያተኩሩ፡፡ በዓላት በሰላም ሲከናወኑ ለአገር ዕድገትም ያግዛሉ፡፡

በኢትዮጵያ የአደባባይ በዓላት ከሃይማኖታዊና ከባህላዊ እሴቶቻቸው በተጨማሪ፣ ለአገር የሚጠቅሙ በርካታ ፋይዳዎች እንዳሉዋቸው የተለያዩ መገለጫዎች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እነዚህን በዓላት በዩኔስኮ ከማስመዝገብ ባለፈ የቱሪዝም ሀብት አካል ብታደርጋቸው፣ በአፍሪካ ቁጥር አንድ የቱሪስት መዳረሻ እንደምትሆን አያጠራጥርም፡፡ የመስቀል፣ የእሬቻ፣ የጥምቀት፣ የተለያዩ ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላትና የተለያዩ ክንውኖች ወደ ሀብት አመንጪነት እንዲለወጡ ብርቱ ሥራ ይፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ በርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ካሉዋቸው አገሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች፡፡ እነዚህ ብሔርና ብሔረሰቦች የራሳቸው ቋንቋ፣ ባህል፣ አለባበስ፣ አመጋገብ፣ ወግና ልማድ አላቸው፡፡ ከእነዚህ መገለጫዎች በተጨማሪ የሚያከብሯቸው በዓላትና የተለያዩ ሥነ ሥርዓቶችም አሉዋቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ የአገር ሀብቶች በከንቱ ሳይባክኑ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ ያስፈልጋል፡፡ ወደ መጪው ትውልድ በአስተማማኝነት ሊሸጋገሩ የሚችሉት፣ አሁን ያለው ትውልድ ለአገር ሀብት እንዲያመነጩ ሲያደርጋቸው ነው፡፡ በዓላቱን በምግብ ዝግጅት፣ በአልባሳት፣ በአደባባይ ትዕይንቶችና በተለያዩ መንገዶች ቀልብ ሳቢ ማድረግ ሲቻል፣ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ በርካቶችን መማረክ አያቅትም፡፡ ውጥረት ተወግዶ ተስፋ ያብብ፡፡

የተለያዩ የአደባባይ በዓላት ከምንም ነገር በላይ የሚያምሩት በታዳሚዎቻቸው አልባሳት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በአልባሳት ኢንዱስትሪውም ሆነ በፋሽን ዘርፍ ውስጥ ያሉ አካላት ከፍተኛ ትኩረት መስጠት አለባቸው፡፡ በዓለማችን በፋሽን የሚታወቁ ከተሞች የብዙዎችን ቀልብ የሳቡት፣ ከዘርፊ የሚገኘውን ጥቅም ከማንም በፊት ቀድመው በመረዳታቸው ነው፡፡ በጨርቃ ጨርቅ አምራችነት የሚታወቁ አገሮችም የተለያዩ ገበያዎችን የተቆጣጠሩት፣ እነሱም ከአገራቸው አልፈው የሌሎችን ፍላጎትና ስሜት በመገንዘባቸው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከጥጥ ጀምሮ ለአልባሳት ግብዓት የሚሆኑ በርካታ ምርቶችን ማግኘት አዳጋች አይደለም፡፡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ሥፍራዎች የሚከበሩ በዓላት ብዙ በመሆናቸው፣ ወቅቱን የጠበቁ አዳዲስ አልባሳት ለተጠቃሚዎች ማቅረብ ይቻላል፡፡ የአልባሳት ኢንዱስትሪው በዚህ ዕሳቤ በስፋትና በጥልቀት መንቀሳቀስ ሲችል ለበርካቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ፣ አልባሳቶቹንም ከጎረቤት አገሮች ጀምሮ እስከ ዓለም ገበያ ድረስ ተፎካካሪ ማድረግ አያቅትም፡፡ በተለያዩ ኅብረ ቀለማትና ጌጦች ያሸበረቁ አልባሳትና ሌሎች ቁሳቁሶች ከበዓል ታዳሚዎች በዘለለ፣ የሌሎችን ቀልብ በመሳብ ተጨማሪ ገቢ አመንጪ መሆን አለባቸው፡፡ ማደግና መለወጥ የግድ ነው፡፡ በዓላት የሥጋት ምንጭ አይሁኑ፡፡

በምግብ ዝግጅትም በኩል በተመሳሳይ ከፍተኛ ዕመርታ መታየት ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ በጉራጌ ብሔረሰብ ዘንድ በስፋት የሚታወቀው ክትፎ በመላ አገሪቱ ታዋቂ የሆነው፣ ከቤት ውስጥ ምግብነት አልፎ ገበያ ውስጥ ተፈላጊ እንዲሆን በመደረጉ ነው፡፡ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ በተለይ በበዓል ወቅት በክትነት የሚቀርቡ ባህላዊ ምግቦች፣ የየብሔረሰቡን ወግና ልማድ ጠብቀው ራሳቸውን ችለው መመገቢያዎች (ሬስቶራንቶች) ቢከፈቱላቸው ገቢ አመንጪ ይሆናሉ፡፡ እነዚህ ሥፍራዎች የብሔረሰቦቹን ባህሎች፣ ሙዚቃዎች፣ አልባሳትና ሌሎች ኪነ ጥበባዊና ታሪካዊ ፋይዳ ያላቸው መገለጫዎች የሚታዩባቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በኢትዮጵያ በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምዕራብ፣ በምሥራቅና በመሀል አገር ውስጥ የሚዘወተሩ በርካታ የበዓላት ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች የሚሸጡባቸው ሥፍራዎች በጥራትና በብዛት መቅረብ ሲችሉ ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድሎች ይፈጠራሉ፡፡ በግብርናም ሆነ በእንስሳት ዕርባታ ዘርፍ በርካቶች ተሰማርተው ግብዓት አቅራቢ መሆን ይችላሉ፡፡ ከሥራ ቀናት በተጨማሪ በሳምንት መጨረሻ ዕረፍት ጊዜ ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር አማርጠው የሚመገቡባቸው ሥፍራዎችን ሲያገኙ፣ ከውጭ ለሚመጡ ቱሪስቶች ጭምር በማገልገል ጥቅም ያመነጫሉ፡፡ ውጥረት ይወገድ፡፡

በኢትዮጵያ የተወሰኑ ከተሞች ካልሆኑ በስተቀር ብዙዎቹ ፈዘዛ ናቸው፡፡ አንድን ከተማ ከሌላ ከተማ የሚያገናኙ መተላለፊያ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ የላቸውም፡፡ ነገር ግን የክልል፣ የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎችም ሆኑ የከተሞች ከንቲባዎች በአካባቢያቸው የሚከናወኑ በዓላትን ምክንያት በማድረግ ለመጠቀም ካልተጉ፣ ከተሞቹ የአልፎ ሂያጅ መተላለፊያ እንጂ ጥቅም ማግኘት አይችሉም፡፡ በመሆኑም ከተሞቹ ሳቢና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከተፈለገ፣ ለሥራ ፈጠራ የሚያግዙ እንቅስቃሴዎች ላይ ማተኮር ይኖርበቸዋል፡፡ ለዚህ ስኬት ደግሞ ከተሞቹ ማንንም በፍቅርና በእንክብካቤ ሊያስተናግዱ የሚችሉ መሠረተ ልማቶች ያስፈልጋቸዋል፡፡ በከተሞቹ አቅም ልክ ንፁህ ባህላዊ ምግቦች፣ መኝታ፣ መስተንግዶና ሌሎች ተዛማጅ አገልግሎቶች የሚያቀርቡ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ መዝናኛዎችና የመሳሰሉትን ማደራጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንግዶች እንደ መኖሪያ አካባቢያቸው ያለ ሥጋት እንዲንቀሳቀሱ ደኅንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ማንኛውም እንግዳ ገንዘብ ይዞ የሚመጣ በመሆኑ ክብር ያለው እንክብካቤ ማድረግ የግድ ነው፡፡ ከተሞች በዚህ ደረጃ ለእንግዶች የሚመጥኑ ሲሆኑ፣ ከበዓላት በተጨማሪ የእረፍት ጊዜ መዝናኛ መሆን ይችላሉ፡፡ ሥራ የሚፈጠረውና ተጨማሪ ገቢ የሚገኘው በዚህ መንገድ እንጂ፣ ውሉ በማይታወቅ የፖለቲካ መደነቋቆር እንዳልሆነ መታወቅ አለበት፡፡

ኢትዮጵያ ከተሠራባት በርካታ የዕድገት ዕድሎች እንዳሏት በተደጋጋሚ ብዙ የተባለበት ነው፡፡ ዘመን ተሻጋሪ በርካታ አኩሪ ማኅበራዊ እሴቶች ያሏት ኢትዮጵያ የጎደላት ነገር ቢኖር፣ እነዚህን የዘመናት ቅርሶች ወደ ልማት ለመቀየር አለመቻል ነው፡፡ በተደጋጋሚ እንደሚሰማው እነዚህን የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች የዓለም ሀብቶች አካል እንዲሆኑ በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ ጥረት ይደረጋል፡፡ ይህ መልካም ዕሳቤ የበለጠ ውጤታማ መሆን የሚችለው ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ሲያደርግ ነው፡፡ በአገር ውስጥ የሕዝቡን ጨዋነትና እሴቶች ጠብቀው የሚከበሩና ለሥራ ፈጠራ ሊያግዙ የሚችሉ የአደባባይ በዓላትና ሌሎች ሥነ ሥርዓቶች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ የብዙዎችን ትኩረት በመሳብ ለአገር ዕድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ መቻል አለባቸው፡፡ ለዚህ ስኬት ደግሞ የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የክልል ብሔራዊ መንግሥታት፣ የእምነት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና ልሂቃን ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በዓላቱ ከማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ ፍላጎት ተላቀው ሥርዓታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩና አገር እንዲጠቅሙ፣ ኢትዮጵያም በበዓላቱ አማካይነት የሰላምና የመረጋጋት አምባ እንድትሆን ኃላፊነትን መወጣት ያስፈልጋል፡፡ በዓላት ከውጥረት ተላቀው የሰላምና የልማት ተስፋ ይሁኑ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

‹‹ወልቃይት የአማራ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም እስትንፋስ ነው›› አቶ ዓብዩ በለው፣ የልሳነ ግፉአን ድርጅት ፕሬዚዳንት

ለወልቃይት የአማራ ማንነት መከበር የሚታገለው የልሳነ ግፉአን ድርጅት ፕሬዚዳንት...

ሕዝብ በሌለበት ሕዝበ ውሳኔ ይካሄድ መባሉን እንደማይቀበለው የቁጫ ምርጫ ክልል አስታወቀ

በኢዮብ ትኩዬ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ይካሄዳል የተባለውን ‹‹የደቡብ...

የድሬዳዋን ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች ለመመለስ ሪፈረንደም እንዲካሄድ አማራጭ ሐሳብ ቀረበ

የድሬዳዋ አስተዳደር ራሱን የቻለ ክልላዊ መንግሥት እንዲሆን ወይም ከሶማሌና...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...

ንግድ ባንክ ከቪዛና ማስተር ካርድ ጋር ተደራድሮ ያስጀመረው የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂና ፋይዳው

ከውጭ ወደ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መጠን...

ይኼ አመላችን የት ያደርሰን ይሆን?

እነሆ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ። ‹‹አዳም ሆይ በግንባር ወዝ ትበላለህ››...

የፀረ ሙስና ትግሉ ጅማሮና የመንግሥት ሠራተኛው

በንጉሥ ወዳጅነው   በኢትዮጵያ ሁኔታ የመንግሥት ሠራተኛ ወይም በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፈተናው ውጤት የፖለቲካው ዝቅጠት ማሳያ ነው!

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከአጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ 3.3 በመቶ ያህሉ ብቻ ማለፋቸው፣ የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ በሚገባ ያመላከተ መስተዋት እንደሆነ አድርጎ መቀበል ተገቢ ነው፡፡...

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...

ፖለቲካና ሃይማኖትን እየቀላቀሉ በእሳት መጫወት አይቻልም!

ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከሚሹ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሃይማኖት ነው፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ ለተቋማቱና ለምዕመናኑ ብቻ የተተወ ነው፡፡ በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥትም መንግሥትና ሃይማኖት...