Sunday, November 27, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናለ‹‹አፋጣኝ ተኩስ አቁም›› እና ‹‹ድርድር›› አሜሪካ ልዩ መልዕክተኛዋን እንደገና ላከች

  ለ‹‹አፋጣኝ ተኩስ አቁም›› እና ‹‹ድርድር›› አሜሪካ ልዩ መልዕክተኛዋን እንደገና ላከች

  ቀን:

  በሰሜን ኢትዮጵያ ያገረሸው ጦርነት ወደ ተባባሰ ግጭት እንዳያመራ፣ አሜሪካ በአንድ ወር ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛዋን ላከች፡፡ የልዩ መልዕክተኛው የአሁኑ ጉዞ ‹‹አፋጣኝ ተኩስ አቁም›› ተደርጎ ‹‹ድርድር›› እንዲጀመር ነው ተብሏል፡፡

  የፕሬዚዳንት ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመምከር ሰኞ መስከረም 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ናይሮቢ ኬንያ የገቡ ሲሆን፣ ከዚያም ወደ ደበብ አፍሪካና ኢትዮጵያ በማቅናት ለሁለት ሳምንታት እንደሚቆዩ የአሜሪካ መንግሥት ቃል አቀባይ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

  ‹‹የልዩ መልዕክተኛው ጉዞ በሰሜን ኢትዮጵያ አፋጣኝ ተኩስ አቁም እንዲደረግና በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ድርድር እንዲጀመር፣ አሜሪካ እያደረገች ያለችውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለማሳካት ነው፤›› ሲል የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ መግለጫ አትቷል፡፡

  በአዲስ አበባ ቆይታቸው ልዩ መልዕክተኛው ከኢትዮጵያና ከአፍሪካ ኅብረት ባለሥልጣናት ጋር እንደሚመክሩ ሲጠበቅ፣ ከጦርነቱ በተጓዳኝም የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ የታችኛው ተፋሰስ አገሮችን ፍላጎት ያካተተ ስምምነት እንዲደረስና ቀጣናዊ መረጋጋት እንዲፈጠር በሚያስችል ሁኔታ ላይ እንደሚመክሩ መግለጫው ያስረዳል፡፡ ምንም እንኳ ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት መሪነት የሚደረግ ቢሆንም፣ የአሜሪካ መንግሥት በግንባር ቀደምትነት ጥረት እያደረገ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

  የአሜሪካ የሪፐብሊካን ፓርቲ ሴናተር ጂም ኢንሆፍ ባለፈው ሳምንት፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ አዲስ አበባ መጥተዋል፡፡

  ድርድሩን እንዲመሩ የተመደቡት የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ከሁለት ወራት በፊት አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ ተመድና ዓለም አቀፍ አጋሮች በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ለሚደረገው ድርድር ደጋፊና ተሳታፊ እንደሚሆኑ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ማይክ ሐመርም ከሁለት ሳምንት በፊት ለሚዲያዎች በሰጡት የበይነ መረብ መግለጫ፣ አሜሪካ ‹‹ሀቀኛ አደራዳሪ›› እንደምትሆን መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡

  የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ በሰላም ድርድሩ ውስጥ የኬንያና ደቡብ አፍሪካ ተወካዮች በኦባሳንጆ በሚመራው አደራዳሪ ቡድን ውስጥ የሚካተቱ ሲሆን፣ በአዲሱ የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ አስቀድሞ ውክልና የተሰጣቸው ኡሁሩ ኬንያታም፣ ከእንግዲህ በሚደረጉት ድርድሮች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

  ይሁን እንጂ በመሬት ላይ ያለው የጦርነት ሁኔታ መልኩን እየቀየረ መሆኑና ከወር በፊት ወደ ነበረበት ተኩስ አቁም የመመለስ ፍላጎት የቀዘቀዘ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡ ሦስተኛው ዙር ጦርነት ባለፈው ወር ከተጀመረ ወዲህ በአብዛኛው በራያ ቆቦ፣ ሰቆጣና ወልቃይት ሁለት ግንባሮች የነበረ ሲሆን፣ ከዚህ ሳምንት መጀመርያ ጀምሮ ግን የሕወሓት ጦር እነዚህን ቦታዎች ለቆ ለመውጣቱ ተገልዷል፡፡

  የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ‹‹ከሰሜን ወሎ የለቀቅነው በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ያየለውን የኤርትራና ኢትዮጵያ ጥምር ጦር ለመመከት ነው፤›› ቢሉም መሬት ላይ ያለው እውነታ የሚያሳየው የሕወሓት ጦር ተሸንፎ እያፈገፈገ መሆኑን እንደሆነ ተገልጿል፡፡

  ሕወሓት በጦር ሜዳ ያሰበው ስላልተሳካለት አሁን ያለው አማራጭ ወደ ድርድሩ ጠረጴዛ ያለ ቅድመ ሁኔታ መምጣት ነው የሚሉ የፖለቲካ ታዛቢዎች፣ በተለይ የአሜሪካ ከዚህ ቀደም ከምታስፈራራበት የማዕቀብ አማራጭን በመተው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ላይ ማተኮሯ የጦርነቱ መቆሚያ በሕወሓት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በመንግሥት ፍላጎት መሆን እንደሚኖርበት ይገልጻሉ፡፡

  ‹‹የሴናተር ጂም ኢንሆፍ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ለፌዴራል መንግሥት ያላቸውን ድጋፍ ያሳያል፡፡ ከዚህ ቀደምም ድጋፋቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አሳይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በግልጽ ከሩሲያና ከቻይና ጎን እስካልተሠለፈች ድረስ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ለትግራይ ጦርነት ብላ ማዕቀብ አትጥልም፤›› ይላሉ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ስማቸው ሳይገለጽ ለሪፖርተር ሐሳባቸውን ሲያጋሩ፡፡

  ሴናተሩ በአሜሪካ ሴኔት ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪና ስለሩሲያና ስለቻይና አቋም ያላቸው፣ እንዲሁም የአሜሪካ ጦር በአፍሪካ ውስጥ መኖር አለበት በማለት ይታወቃሉ፡፡ በሴናተሩ ጉብኝት ላይ በይፋ የተሰጠ መግለጫ ባይኖርም፣ ከልዩ መልዕክተኛው ማይክ ሐመር የተለየ ተልዕኮ ይዘው እንደሚመጡ ተንታኞች ይገምታሉ፡፡ ‹‹የጥምር ጦሩ በፍጥነት አሸናፊነትን የማይቀዳጅ ከሆነ፣ ድርድሩ የማይቀር ነው፡፡ ድርድሩ ግን የሚሳካው ሁለቱም ወገኖች ግትር ቅድመ ሁኔታዎችን መቀነስ ከቻሉ ነው፤›› ይላሉ ተንታኙ፡፡ የኤርትራ ጦር መውጣት፣ የትግራይ ወሰን ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት መመለስ፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች መጀመርና የሰብዓዊ ዕርዳታ መጀመር ከሕወሓት በኩል በተደጋጋሚ ሲገለጹ የነበሩ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል የፌዴራል መንግሥቱ ሕወሓት ትጥቁን ፈቶ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለሰላም ንግግር ዝግጁ እንዲሆን ሲጠይቅ ነበር፡፡

  ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር መሆኑና ኡሁሩ ኬንያታ በኦባሳንጆ ቡድን ይታቀፋሉ መባሉ ግን ሁለቱንም ወገኖች እንደማይቆረቁር ተንታኙ ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ ደቡብ አፍሪካ በጉዳዩ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ለመሆኗ እስካሁን አልታወቀም፡፡

  ይሁን እንጂ ልዩ መልዕክተኛ በዚህኛው ጉዟቸው ‹‹የመጨረሻውን›› የድርድር ጥሪ እንደሚያደርጉና በሁለት ሳምንት ቆይታቸውም አንድ ዕልባት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...