Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አገር የሚገቡ የግል ዕቃዎችን በሚገድበው መመርያ ምክንያት በርካታ ንብረቶች በጉምሩክ መያዛቸው ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአየር መንገድ ተጓዦች ወደ አገር የሚገቡትን የግል መገልገያ ዕቃዎች በቁጥር ከሚገድበው አዲሱ መመርያ መተግበር በኋላ፣ በርካታ ወደ አገር የሚመጡ ተጓዦች ይዘዋቸው እየመጡ ባሉት አንዳንድ ንብረቶች ላይ ከፍተኛ ቀረጥ እንዲከፍሉ በጉምሩክ ኮሚሽን ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ጽሕፈት ቤት እየተጠየቁና ንብረቶቻቸውም በጽሕፈት ቤቱ እየተያዙ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ከአንድ ወር በፊት በገንዘብ ሚኒስቴር ፀድቆ ተግባራዊ የሆነው ይህ መመርያ፣ የቀረጥ ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ አገር የሚገቡና ከአገር የሚወጡ ዕቃዎች ላይ የቁጥር ገደብ በማውጣት የሚወስን ሲሆን፣ ማንኛውም መንገደኛ ከቀረጥና ታክስ ነፃ ሆኖ ወደ አገር ማስገባት የሚችላቸውን የ16 ዕቃዎች ዓይነት ዝርዝር አውጥቷል።

በዝርዝር በመመርያው የተጠቀሱት ዕቃዎችና ሌሎችም ያልተጠቀሱ ንብረቶችን ተጓዦች እንደ ከዚህ ቀደሙ ወደ አገር ይዘው ሲገቡ ንብረቱን ከገዙበት በላይ ከፍተኛ ቀረጥ እየተጠየቁ በመሆኑ፣ ይህም ከፍተኛ ብዥታ እየፈጠረ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በርካቶች ለመክፈል ባለመቻላቸውና ባለመፈለጋቸውም እዚያው ንብረቶቻቸውን ትተውት እየወጡ እንደሆነ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በርካታ ምንጮች ይገልጻሉ።

ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ ግለሰብ ለጉብኝት አንድ አፍሪካ ውስጥ ወደሚገኝ አገር ከሁለት ሳምንታት በፊት ሄዶ ሲመለስ ለረዥም ዓመታት የተጠቀመበትን ፎቶና ቪድዮ ግራፍ የሚያነሳ ካሜራ 30 ሺሕ ብር ቀረጥ እንዲከፍል መጠየቁን ለሪፖርተር ይገልጻል። ግለሰቡ ካሜራው የግል ንብረት መሆኑን፣ ከዚህ አገር ሲሄድ ይዞት እንደሄደና በአዲሱ መመርያም መክፈል እንደማይጠበቅበት በማስረዳትና ጥቂት ቀናት በፈጀ ክርክር ሊመለስለት እንደቻለ ተናግሯል።

በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የቅሬታ ክፍል ኃላፊ አቶ ዘሪሁን አሰፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የካሜራ ጉዳይ አሳሳቢ እንደሆነና ሁሉንም መፍቀድ እንደሚያስቸግርም ተናግረዋል። መመርያው መውጣቱን ካለማወቅና ብዥታ እንደተፈጠረባቸው የሚገልጹ የተወሰኑ ቅሬታዎች ወደ እሳቸው ክፍል እንደሚመጡም አቶ ዘሪሁን ለሪፖርተር ተናግረዋል።

መመርያው አንድ ወደ አገር የሚመጣ ግለሰብ ከቀረጥ ነፃ ይዞ እንዲገባ ከሚፈቀድለት 16 ዝርዝር ዕቃዎች ውስጥ የፎቶግራፍ ካሜራ አንደኛው ሲሆን፣ በቁጥርም አንድ ማስገባት ይቻላል። መመርያው ስለቪዲዮ ካሜራ የሚገልጸው ባይኖርም፣ አብዛኛዎቹ የፎቶግራፍ ካሜራዎች ግን ቪዲዮም ይቀርፃሉ።

ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ የተፈቀዱት የግለሰብ ንብረቶች ውስጥ ሲጋራ 200 ግራም፣ ሲጋር 20 ፍሬ፣ አልኮል መጠጥ ሁለት ሊትር፣ ሽቶ 500 ሚሊ ሊትር፣ ሁለት ሞባይል ስልክና እንደ ላፕቶፕ፣ ዊልቸር፣ የእጅ ሰዓት፣ ፀጉር መላጫና ፀጉር መተኮሻ ያሉ ዕቃዎች ደግሞ አንድ አንድ ፍሬ ናቸው።

የአየር ማረፊያው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የመንገደኞች ጉዳይ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘራኤል ለዓ በበኩላቸው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ዋነኛው ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ያለው መንገደኛው መመርያውን በአግባቡ አለማወቅ ነው። የንግድ መገልገያ ቁሳቁሶች አስፈላጊው ቀረጥ እንደሚጣልባቸው ሁሉ፣ አንድ ፍሬም የግል መገልገያ ሆኖ የንግድ ባህሪ ያለው ቁስ በጥልቀት በመታየት በመመርያው መሠረት ቀረጥ የሚጣልበት እንደሆነ ስለመመርያውና እሱ ስለወጣበት ደንብ ኃላፊው ያስረዳሉ።

ስለካሜራና ሌሎች ቁሶች ሲያስረዱ አቶ ዘራኤል፣ ከመመርያም ባለፈ የተለያዩ አሠራሮች እንዳሉ የገለጹ ሲሆን፣ አንደኛው መንገደኞች ከአገር ሲወጡ ይዘው የሚወጡትን ቁስ ዓለም አቀፍ መውጫ (Departure) ላይ ካለው የጉምሩክ ቢሮ ውስጥ የቁሱን ሙሉ ዓይነት መረጃዎች ማስመዝገብ ነው።

ካሜራም ሆነ ሌሎች ቁሶችን አስመዝግቦ ያስወጣ መንገደኛ ሲመለስ እንዳለ ይዞት ከመጣ ምንም የሚከፍለው ነገር እንደማይኖርም አክለው ገልጸዋል። ‹‹በእርግጥ አንድ ካሜራ ይፈቀዳል፡፡ ነገር ግን ምን ዓይነት ካሜራ ነው የሚለው መታየት አለበት፤›› ሲሉም አክለው ገልጸዋል።

በተያያዘም ከአንድ ሳምንት በፊት ከዱባይ ወደ አዲስ አበባ 55 ኢንች ሰምሰንግ ቴሌቪዥን ይዞ ወደ አዲስ አበባ የመጣ ሪፖርተር ያነጋገረው አንድ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ግለሰብ፣ ቦሌ አየር ማረፊያ ሲደርስ በአዲሱ መመርያ መሠረት ቀረጥ ከፍሎ ማስገባት እንዳለበት ቢረዳም፣ እንዲከፍል የተጠየቀው ገንዘብ ግን እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ንብረቱን እዚያው ትቶት እንደሄደ ይገልጻል። ቴሌቪዥኑ በዱባይ የሚያወጣው ዋጋ ከ1,500 ድራም (19,500 ብር) እንደማይበጥና እሱ ግን የዋጋውን ሦስት እጥፍ በአጠቃላይ ከ65,000 ሺሕ ብር የበለጠ እንዲከፍል መጠየቁን ይገልጻል።

‹‹ይህን ያህል የተጠየኩት ይዤው የመጣውት ከፍተኛ የምሥል ጥራት ያለው (4K Ultra-High Definition) ቴሌቪዥን ስለሆነ ነበር። አገር ውስጥ ብገዛው እንኳን ያን ያህል አያስወጣኝም ነበር፤›› ሲል የገጠመውን ችግር ለሪፖርተር ገልጿል።

በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፍያ ጉምሩክ ጽሕፈት ቤት የሚሠራና ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ የጉምሩክ ባለሙያ እንደገለጸው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በአየር ማረፊያው ያሉት መጋዘኖች ቀረጥ ሳይከፈልባቸው እዚያው በቀሩ በርካታ ቴሌቪዥኖች እያጨናነቁ እንዳሉ ይናገራል።

‹‹የተተመነባቸውን ቀረጥ አንከፍልም ባሉ ሰዎች እንደ ቴሌቪዥን ዓይነት ንብረቶች የኢትዮጵያ አየር መንገድ አንድ ረዥም መጋዘን እጅግ በጣም ሞልቶ ሌላ ዕቃ ማስቀመጫ ነው የጠፋው። በርካታ ሰዎች ለበዓል ብዙ ዕቃዎች ይዘው መጥተው ነበር፤›› ሲል ባለሙያው ይገልጻል።

እንደ አቶ ዘራኤል ገለጻ፣ ማንኛውም ግለሰብ ንብረቱ በጉምሩክ ከተያዘ በኋላ እስከ 10 ቀናት ድረስ የተጠየቀውን የቀረጥ ተመን እየከፈለ መውሰድ እንደሚችል ነው። ከ10 ቀናት በላይ ከሆነም ቁሶቹ ወደ መንግሥት መጋዘን የሚዞሩ ሲሆን፣ በተዘረጋው አሠራር መሠረት ባለቤቶች አሁንም ቅድሚያ በማግኘት ንብረቱን ቀረጥ በመክፈል ማውጣት እንደሚችሉ ይገልጻሉ። ‹‹ነገር ግን ቁሶቹ የአገርም ንብረት እንደመሆናቸውና እንዲበላሹ ስለማይፈለግ በተገቢው ሒደት ያልፋሉ፤›› ሲሉ፣ ኃላፊው ንብረቶቹ ወደ ጨረታ የሚሄዱበትን መንገድ ያስረዳሉ።

ምክትል ሥራ አስኪያጁ ሲያስረዱ በተለይ በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎች ስለመመርያውና ሌሎች ተያያዥ ሕጎች በደንብ ማወቅ እንዳለባቸው የገለጹ ሲሆን፣ በየአገሮቻቸውም የሚኖሩ ኤምባሲዎቻቸውም ይህን የማሳወቅ ሥራ እንዲሠሩ ሲሉ ያስረዳሉ።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች