Sunday, November 27, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናሶማሌ ክልል የፀጥታ ኃይሉን ለማጠናከር ተጨማሪ 289 ሚሊዮን ብር በጀት አፀደቀ

  ሶማሌ ክልል የፀጥታ ኃይሉን ለማጠናከር ተጨማሪ 289 ሚሊዮን ብር በጀት አፀደቀ

  ቀን:

  • የክልሉ ቢሮዎች ለሥልጠናና ጥናት የያዙት በጀት ለድርቅና ዋጋ ንረት መደጎሚያ እንዲዛወር ተወስኗል

  ከሁለት ወራት በፊት የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን ጥቃት ከፍቶበት የነበረው ሶማሌ ክልል፣ የክልሉን የፀጥታ ኃይል ለማጠናከር የሚውል ተጨማሪ 289 ሚሊዮን ብር በጀት አፀደቀ፡፡

  ተጨማሪ በጀቱን ያፀደቀው የክልሉ ካቢኔ ከትናንት በስቲያ ሰኞ መስከረም 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ላይ ነው፡፡ የፀደቀው 289 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት የክልሉን ልዩ ኃይልና ሚሊሻዎችን በማጠናከር የሚፈጠሩ ሥጋቶችን ለመመከት የሚያስችል አቅም ለመገንባት ያቀደ መሆኑን በክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የኤሌክትሮኒክስና ፕሪንት ሚድያ ዳይሬክተር አቶ አብዱ ሂሎ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

  የአልሸባብን ጥቃት ለመመከት ሲዋጉ የተገደሉ የፀጥታ ኃይሎች ልጆችንና ቤተሰቦች ለመደገፍ እንደሚውልም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

  የሶማሊያ መንግሥት የአልሸባብ ታጣቂዎችን ኦፕሬሽን ማኬድ መጀመሩን የጠቀሱት አቶ አብዲ፣ አሁን ላይ በክልሉ ‹‹ይህ ነው የሚባል›› ሥጋት እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከዚህ ቀደም ድንበር ላይ ችግር አጋጥሞ የነበረ በመሆኑ አሁንም ሌሎች ችግሮች የሚፈጠሩ ከሆነ የፀጥታ ኃይሉን ማጠናከር አስፈላጊ በመሆኑ ነው፤›› ሲሉም ተጨማሪ በጀት የተመደበበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡

  ካቢኔው መስከረም 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ የተወያየበት ሌላኛው ጉዳይ በክልሉ በተከሰተው ድርቅና እየታየ ባለው የኑሮ ውድነት የተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለመደጎም የሚቻልበት መንገድ ላይ መሆኑን አቶ አብዱ ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት በክልሉ የሚገኙ ከ60 በላይ የሚሆኑ በ2015 በጀት ዓመት የመንግሥት ተቋማት ለሥልጠና፣ ጥናትና የመስክ ምልከታ የያዙት በጀት ለድርቅና የዋጋ ንረት መደጎሚያ እንዲውል ካቢኔው መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

  ‹‹ከ60 በላይ የሚሆኑ ቢሮዎች ለዚህ ብለው የመደቡት በጀት አለ፣ አጠቃላይ የገንዘቡ መጠን የሚታወቀው ከእያንዳንዱ ቢሮ ሲሰበሰብ ነው፤›› ብለዋል፡፡

  ለተያዘው የ2015 በጀት ዓመት 31.7 ቢሊዮን ብር በጀት ያፀደቀው የክልሉ መንግሥት፣ በበጀት ዓመቱ የመጀመርያ ሩብ ዓመት ማጠናቀቂያ ላይ ተጨማሪ በጀት ያፀደቀው ሐምሌ 2014 ዓ.ም. የአልሸባብ ታጣቂዎች በክልሉ አፍዴር ዞን ‹‹አቶ›› በተባለ ቦታ ጥቃት ከከፈቱ በኋላ ነው፡፡

  ይህንን ጥቃት ተከትሎ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ለቀናት ከቡድኑ ጋር ውጊያ ያደረጉ ሲሆን ከ20 በላይ የቡድኑ ታጣቂዎች መታገዳቸውን መንግሥት አስታውቆ ነበር፡፡ ቡድኑ በኤልከሬ ወረዳ አልፎ ወደ ኦሮሚያ ክልል በመግባት ከሌላኛው ‹‹ከኦነግ ሸኔ›› ጋር የመገናኘት ዓላማ እንደነበረው የገለጸው የፌዴራል መንግሥት ይህንን ዕቅድ ማክሸፉን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

  አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ በኢትዮጵያ የመጀመርያ ጉብኝታቸውን ባለፈው ሳምንት ሲያካሂዱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር ከተወያዩባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሽብርተኝነትና ፅንፈኝነትን መከላከል ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል፡፡

  በተጨማሪም ሽብርተኝነት፣ ፅንፈኝነትና የጋራ ጠላቶቻቸው ላይ አብረው ለመሥራት፣ የደኅንነት መረጃዎች ልውውጥ ለማድረግና በትብብር የሚሠሩባቸውን ጉዳዮች የበለጠ ለማጠናከር መስማማታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባለፈው ሳምንት ዓርብ መስከረም 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...