Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፖርትየለንደን ማራቶን ባለ ድሏ ያለምዘርፍ የኋላው

  የለንደን ማራቶን ባለ ድሏ ያለምዘርፍ የኋላው

  ቀን:

  በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ደረጃ ያለው የለንደን ማራቶን ባለፈው እሑድ ሲካሄድ፣ ለመጀመርያ ጊዜ  በቦታው የተወዳደረችው ኢትዮጵያዊቷ ያለምዘርፍ የኋላው ድሏን አስደናቂ ያደረገው ውድድሩ ሊያበቃ ዘጠኝ ኪሎሜትር ሲቀረው ከወደቀችበት ተነስታና ሕመሟን አስታማ በስኬት ማጠናቀቋ ነው፡፡

  የዓምናዋን አሸናፊ ኬንያዊቷን ጆይሲሊን ጄፕኮስጌይን ያሸነፈችው የ23 ዓመቷ ያለምዘርፍ፣ 33ኛ ኪሎሜትር ላይ ከወደቀችበት ተነስታ ጥለዋት የሄዱት መሪዎች ላይ ደርሳባቸው ለማሸነፍ የቻለችው በ2፡17፡25 ሰዓት ሲሆን፣ ይህም የውድድሩ ሦስተኛው ፈጣን ጊዜ ሆኖ ተመዝግቦላታል፡፡

  በመስከረም 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ሩጫዋ መውደቋና መጎዳቷ ታሪክን ከመሥራት ያላገታት ያለምዘርፍ፣ የመጨረሻ መስመሩን በቀዳሚነት በማለፍ በዕድሜ ትንሽዋ የለንደን ማራቶን አሸናፊ ሆናለች።

  ከድሏ በኋላ ለጋዜጠኞች ‹‹በዳሌዬና በጉልበቴ ላይ የተወሰነ ስሜት ቢሰማኝም እብጠቱን ግን አላየሁትም፤›› ያለችው ያለምዘርፍ፣ ‹‹በደንብ መሮጥ እንደምችል ተማምኜ ነበር፤ በለንደን ለመጀመሪያ ጊዜ በማሸነፌ በጣም ደስተኛ ነኝ። ተመልካቹም እየጮኸ የሰጠኝ ድጋፍም አነሳስቶኛል፤›› ብላ መናገሯን ስካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡

  የ2021 ሻምፒዮኗ ጆይሲሊን ጄፕኮስጌይ በ41 ሰከንድ ዘግይታ ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ፣ ኢትዮጵያዊቷ መገርቱ ዓለሙ በ2፡18፡32 ሰዓት  በሦስተኛነት ፈጽማለች።

  ያለምዘርፍ ባለፈው ሚያዝያ ለመጀመሪያ ጊዜ በጀርመን የሃምቡርግ ማራቶንን ማሸነፏ ይታወሳል፡፡ የዓለም የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ ባለክብረ ወሰኗ ያለምዘርፍ፣ ዓምና በሃምቡርግ ማራቶን ድሏ ያስመዘገበችው ጊዜ፣ በዓለም ማራቶን ታሪክ ፈጣን ሰዓት ካስመዘገቡ አትሌቶች በሰባተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል።

  በዚሁ የሴቶች ውድድር ከፍተኛ ፉክክር የታየው በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል ሲሆን፣ የመጀመርያዎቹን ስምንት ደረጃዎችን የወሰዱት ሁለቱ አገሮች ናቸው፡፡

  የአትሌቶቹ የመጨረሻ የደረጃ ውጤት…

  1. ያለምዘርፍ የኋላው (ኢትዮጵያ) 2:17:26
  2. ጆይሲሊን ጄፕኮስጌይ (ኬንያ) 2:18:07
  3. መገርቱ ዓለሙ (ኢትዮጵያ) 2:18:32
  4. ጁዲት ኮሪር (ኬንያ) 2:18:43
  5. ጆአን ቼሊሞ ጄሊ (ኬንያ) 2:19:27
  6. አሸተ በከሬ (ኢትዮጵያ) 2:19:30
  7. ሜሪ ንጉጊ (ኬንያ) 2:20:22
  8. ሱቱሜ አሰፋ ከበደ (ኢትዮጵያ) 2:20:44

  በሴቶች ውድድር ካለፉት 12 ዓመታት በ10ሩ ድሉን ተቆጣጥረውት የነበሩት ኬንያውያት ሲሆኑ፣ በ2011 እና 2017 መካከል ከተከናወኑት ሦስቱን ያሸነፈችው ሜሪ ጄፕኮስጌይ ኬይታኒ ናት፡፡

  በሌላ በኩል በወንዶች ማራቶን ላለፉት ሁለት ተከታታይ ውድድሮች በሹራ ኪታታና ሲሳይ ለማ ባለድል የነበረችው ኢትዮጵያ በዘንድሮው ሩጫ ሁለተኛ ነው የወጣችው፡፡

  ኬንያዊው አሞስ ኪፕሩቶ ለመጀመሪያ ጊዜ አሸናፊ የሆነው በ2፡04፡39 ሰዓት በመፈጸም ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ልዑል ገብረሥላሴ ኪፕሮቶን ተከትሎ የገባው በ2፡05፡12 ሲሆን፣ በሦስተኛነት ቤልጂማዊው በሽር አብዲ በሰባት ሰከንድ ልዩነት አጠናቋል፡፡

   የምንጊዜም ፈጣን የማራቶን ሯጭና በታሪክ ከታላላቅ የረዥም ርቀት ሯጮች መካከል አንዱ የሆነው የ40 ዓመቱ ቀነኒሳ በቀለ፣ በ2፡05፡53 በመግባት አምስተኛ ሆኗል።

  ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ብርሃኑ ለገሰ 5ኛ እና 6ኛ ሆነው ሲያጠናቅቁ የዓምናው የለንደን ማራቶን አሸናፊ ሲሳይ ለማ ግን 7ኛ ሆኗል።

  በወንዶቹ ውድድር ከመጀመርያዎቹ ስምንት ደረጃዎች ውስጥ ኢትዮጵያ በኬንያ ከመቀደሟና የቤልጂየም አትሌት ሦስተኛ ሆኖ ከመግባቱ በቀር አምስቱን ደረጃዎች አትሌቶቿ አግኝተዋል፡፡

  ባለፉት ሰባት ዓመታት በተደረጉት የለንደን ማራቶን ውድድሮች አራት ጊዜ ያሸነፈው ኬንያዊው ኢሉድ ኪፕቾጌ በ2019 ክብረወሰን ጭምር የሰበረበት ነበር፡፡  እ.ኤ.አ. በ2013 ጸጋዬ ከበደ ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

  የአትሌቶቹ የመጨረሻ የደረጃ ውጤት…

  1. አሞስ ኪፕሮቶ (ኬንያ) 2:04:39
  2. ልዑል ገብረሥላሴ (ኢትዮጵያ) 2:05:12
  3. በሽር አብዲ (ቤልጂየም) 2:05:19
  4. ክንዴ አጥናው (ኢትዮጵያ) 2:05:27
  5. ቀነኒሳ በቀለ (ኢትዮጵያ) 2:05:53
  6. ብርሃኑ ለገሰ (ኢትዮጵያ) 2:06:11
  7. ሲሳይ ለማ (ኢትዮጵያ) 2:07:26
  8. ብሬት ሮቢንሰን (አውስትራሊያ) 2:09:52
  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...