Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምበዘጠኝ ወር ውስጥ ሁለት መፈንቅለ መንግሥት ያስተናገደችው ቡርኪና ፋሶ

በዘጠኝ ወር ውስጥ ሁለት መፈንቅለ መንግሥት ያስተናገደችው ቡርኪና ፋሶ

ቀን:

ቡርኪና ፋሶን የሚመራው መንግሥት መንበሩ መርጋት አልቻለም፡፡ ዓምና በወርኃ ጥር በሕዝብ የተመረጠው መስተዳድርን ኩዴታ (መፈንቅለ መንግሥት) በማድረግ ያሰወገደው የወታደራዊ መኰንኖች ስብስብ (ደርግ) ለግልበጣው ምክንያት የሰጠው ‹‹መንግሥት የእስላማዊ አክራሪ ቡድኖችን ጥቃት ማስቆም አልቻለም›› በሚል ሲሆን፣ ሥልጣኑንም የጨበጡት ኮሎኔል ፖል ሄኒሪ ዳሚባ ነበሩ፡፡

ከዘጠኝ ወር በኋላ መስከረም 21 ቀን 2015 ዓ.ም. የተሠራጨው ዜና እንደሚያመለክተው የቡርኪና ፋሶ የመከላከያ ኃይል መኰንኖች የወታደራዊ ደርግ መሪውን ኮሎኔል ዳሚባን ከሥልጣን ማስወገዳቸው በብሔራዊ ቴሌቪዥናቸው ይፋ አድርገዋል፡፡

የደርጉ መሪ ሻምበል ኢብራሂም ትራኦሬ ከሥልጣን የወረዱት ኮሎኔል ዳሚባ የተወገዱበትን ምክንያት ከዘጠኝ ወር በፊት የተወገዱት መሪ ላይ የተሰነዘረውን ዳግም ጠቅሰውታል፡፡

ወታደራዊው መሪ ‹‹በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን እስላማዊ አማፂያንን መቆጣጠር አልቻሉም›› በሚል መክሰሳቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ጨብጠው በመፈንቅለ መንግሥት የተወገዱት ዳሚባ ከቀናት በፊት የት እንዳሉ የታወቀ ነገር እንዳልነበር ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

ዶቼቬሌ ትናንትና ባሠራጨው ዜናው ሌተና ኮሎኔል ዳሚባ ወደ ቶጎ መሰደዳቸውን የቶጎን የኮሙዩኒኬሽን ሚኒስቴርን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ ለቀጣናው ሰላም ሲባል ከሥልጣን የተባረሩትን ወታደራዊ ገዢ መቀበሏን ቶጎ አስታውቃለች፡፡

የሃይማኖትና የማኅበረሰብ መሪዎችን የጠቀሰው የቢቢሲ ዘገባ ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን ለመውረድ የወሰኑት ‹‹ከፍተኛ የሰውና የንብረት ጉዳት የሚያስከትል ግጭትን ለማስቀረት›› ብለው ነው ሲሉ መሪዎቹ መናገራቸውን ዘግቧል፡፡

ከዘጠኝ ወራት በፊት የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ሆክ ማርክ ክርስቲያን ካቦሬ ከሥልጣን ያስወገደው መከላከያው፣ መንግሥቱንና ብሔራዊ ሸንጎውን አፍርሶ ሕገ መንግሥቱንም አግዶ ነበር፡፡

ኩዴታውን ተከትሎ የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) ቡርኪና ፋሶን ማገዱንና ይህም ኢኮዋስ ከአባል አገሮቹ መፈንቅለ መንግሥቶች ምክንያት ያገዳቸውን አገሮች ሦስት ማድረሱም ይታወሳል፡፡

የቡርኪና ፋሶ መከላከያ መፈንቅለ መንግሥቱን ለማድረግ የተገደደው ተፈናቃዩ ፕሬዚዳንት ካቦሬ በታጣቂዎችና በአክራሪዎች የሚፈጸም ግድያን ማስቆም አልቻሉም፣ በሥልጣን ዘመናቸውም በሺዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል በሚል እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ጥር 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ሥልጣኑን የያዘውና ራሱን ‹‹ፓትሪዮቲክ ሙቭመንት ፎር ፕሪቬንሽን ኤንድ ሪስቶሬሽን›› ብሎ የሰየመው ወታደራዊ መንግሥት ያደረገውን  የያኔውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ኢኮዋስና የአፍሪካ ኅብረት አገሪቷን ከአባልነት ቢያግዱም፣ በቡርኪና ፋሶ ዋና ከተማ ኡጋዱጉ ነዋሪዎች ለመከላከያው ድጋፍ ለመስጠት ወጥተው ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ዓመት ሳይሞላ ሰሞኑን ዋና ከተማውን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ሕዝቡ ዳሚባ ሥልጣኑን ከተቆናጠጡ በኋላ ያመጡት ለውጥ የለም፣ ደኅንነትም እየተሰማ አይደለም፣ ከሥልጣን ይውረዱ  እያሉ የተቃውሞ ድምፃቸውን አደባባይ በመውጣት ማስተጋባታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ኢኮዋስ ሁለተኛውን ኩዴታ ተከትሎ ባሰማው ድምፅ በአገሪቱ የሲቪል አስተዳደር ለማምጣት እየተጣረ መፈንቅለ መንግሥት መከናወኑ ‹‹ተገቢ አይደለም›› ሲልም ኮንኗል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት በመጪው ሐምሌ ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረገ አመራር ወደ ሥልጣን እንዲመጣ መጠየቁም ተዘግቧል።

አዲሱ ወታደራዊ መሪ ሻምበል ኢብራሂም ትራኦሬ ‹‹አስቸኳይ›› ችግሮችን ለመቅረፍ የካቢኔ ሚኒስትሮች ‹‹በፍጥነት እንዲንቀሳቀሱ›› ማሳሰባቸውን ቢቢሲ በዘገባው አክሏል፡፡

ለኩዴታዎች ሰበብ የሆኑት እስላማዊ ታጣቂዎች ንቅናቄ የተጀመረው በ2007 ዓ.ም. ሲሆን፣ በሰባት ዓመታት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ማጥፋቱን፣ ሁለት ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ  መፈናቀሉ ይወሳል።

የቡርኪናፋሶ መንግሥት በአገሪቱ ከ60 በመቶ በታች ያለ ግዛት ብቻ የሚቆጣጠርና እስላማዊ ታጣቂዎች እያደረሱ ያለው ጉዳትም እየከፋ እንደሄደ ባለሙያዎች መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

እ.ኤ.አ. በ1960 ነፃነቷን የተቀዳጀችው ቡርኪና ፋሶ በስድስት አሠርታት ውስጥ ስምንት ኩዴታዎች ተካሂዶባታል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...