Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የአስጎብኚ ዘርፉ እንዲጠናከር ከተፈለገ የታክስ አዋጁ መሻሻል አለበት› ወ/ሮ አንድነት ፈለቀ፣ የኢትዮጵያ አስጎብኚዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት

የኢትዮጵያ አስጎብኚዎች ማኅበር በ1996 ዓ.ም. ነው የተቋቋመው፡፡ ማኅበሩ ከተቋቋመ በኋላ 272 አስጎብኚ ድርጅቶችን በአባልነት አፍርቷል፡፡ ምንም እንኳን ቱሪዝሙ በሚፈለገው ደረጃ አድጓል ባይባልም፣ አሁን ለደረሰበት ደረጃ የማኅበሩ አባላት ከፍተኛ ሚና ተጫተዋል፡፡ ጎብኚዎች በሚገኙበት የተለያዩ ዓለም አገሮች በራሱ ወጪ እየተዘዋወረ የአገር በጎ ገጽታን በማጉላት፣ ያለውን የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ሀብት በማስተዋወቅና በማሳመን ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መስህቦቿን እንዲጎበኙ የራሱን አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡ ማኅበሩ የኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻዎች ያሉባቸውን የመሠረተ ልማት መሠረታዊ ችግሮች ተቋቁሞ ጎብኚዎችን በማምጣት ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪን ሲያስገኙ መቆየታቸው ይጠቀሳል፡፡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዲሁም በኢትዮጵያ የተከሰተውን የፀጥታ ችግር እየተፈታተነ የሚገኘውን ቱሪዝም ዳግም እንዲያንሰራራ እንቅስቃሴ ላይ የሚገኘው ማኅበሩ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን መንግሥት ማሻሻል እንዳለበት ሲያነሳ ከርሟል፡፡ የማኅበሩን አጠቃላይ እንቅስቃሴና በተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ዳዊት ቶሎሳ ከማኅበሩ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ አንድነት ፈለቀ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በቱሪዝም ላይ የአስጎብኚዎች ሚና ምንድነው?

/ሮ አንድነት፡- አብዛኛውን ጊዜ የአስጎብኚ ድርጅት ሚና በደንብ አይዳሰስም፡፡ የአስጎብኚ ድርጅት ሚና ቱሪስቶች ወደ አገር ውስጥ ከመምጣታቸው አስቀድሞ፣ በራሱ ወጪ ወደ ቱሪስት አመንጪ አገሮች አምርቶ፣ አስተዋውቆ፣ ኢትዮጵያ ስላላት የቱሪስት መስህብ አስረድቶ እንዲሁም የአገር ገጽታ ገንብቶ ነው ጎብኚዎችን የሚያመጣው፡፡ ጎብኚውን ወደ አገር ውስጥ ካመጣ በኋላ ለሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ማለትም ለሆቴል፣ ለትራንስፖርት፣ ለመስህቦች፣ ለአስጎብኚዎች (ጋይዶች)፣ ለጀልባ አከራዮችና በቅሎ ጎታቾች ሥራውን ይበትናል፡፡ የአስጎብኚ ድርጅት ሥራ አንድ ቦታ ላይ ተሰብስቦ የተቀመጠና የሚቆጠር ነገር አይደለም፡፡ ዘርፉ ለተማረውም ላልተማረውም ኅብረተሰብ የሥራ ዕድል የከፈተ ነው፡፡ ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ጂንካ በሚደረግ ጉዞ በርካታ ከተሞችን እያለፈ ይሄዳል፡፡ በዚህም በተለያየ ደረጃ ላለ የኅብረተሰብ ክፍል በቀጥታና በተዘዋዋሪ የተለያየ ሥራ ዕድል እየፈጠረ ያልፋል፡፡ ስለዚህ ሚናው በጣም የጎላ ነው፡፡ በአንፃሩ ዘርፉ እንደ ሆቴል ዓይነት ቆሞ የሚታይ አገልግሎት የሚሰጥ ስላልሆነ፣ እንቅስቃሴውም ሆነ ችግሩ ጎልቶ ሊታይ አልቻለም፡፡

ሪፖርተር፡- በአስጎብኚ ዘርፍ ዕድገት ላይ እንደ ዋና ችግር ሊነሳ የሚችለው ምንድነው?

/ሮ አንድነት፡- የመጀመሪያው ችግር ዘርፉን አለመረዳት ነው፡፡ በትክክል ዘርፉ የሚፈልገውንና ዘርፉን ለማሳደግ ያሉ ክፍተቶችን ለይቶ አለማወቅ ችግር ነው፡፡ ሌላው ዋና ችግር ፖሊሲ ነው፡፡ ወቅቱን ባማከለ መልኩ አይከለስም፣ የማስፈጸሚያ ደንቦች የለውም፣ ፖሊሲው በግልጽ አልተቀመጠም እንዲሁም ፖሊሲውን ለማስፈጸም አቅም አልገነባም፡፡ በተጨማሪ በርካታ የቱሪስት ሀብቶች ከአዲስ አበባ ውጪ ማለትም በደቡብ፣ በሰሜን፣ በምሥራቅ እንዲሁም በምዕራብ ላይ ቢኖሩም ክልሎች በበላይነት የማስተዳደር ኃላፊነት ቢኖራቸውም፣ በፌዴራል ደረጃ ሚኒስቴሩ በበላይነት መቆጣጠሩ ላይ ውስንነት አለ፡፡ አብዛኛውን ሥራ የማስተዋወቅ እንዲሁም የመሸጥ ሥራ አዲስ አበባ ያሉ ድርጅቶች ናቸው የሚሠሩት፡፡ በአንፃሩ ሚኒስቴሩ በመዳረሻዎች ላይ የመቆጣጠር፣ የማዘዝና ሥርዓት የማስያዝ ሥልጣን ያለው ቢሆንም፣ እስካሁን ይህ በሚፈለገው መልኩ አይደረግም፡፡ ሌላው ከድሮ ጀምሮ የነበረው አንዱ ክፍተት፣ መሥሪያ ቤቱና የግል ዘርፉ በአብዛኛው ለየብቻቸው ነው የሚሠሩት፡፡

ሪፖርተር፡- የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ከመሥሪያ ቤቱ ጋር ተደጋግፎ መሥራት እንደሚገባ ይታመናል፡፡ በአንፃሩ ሁለቱም አካላት በየፊናቸው ሲሠሩ መክረማቸውና ክፍተቶችም ሲከሰቱ ተስተውሏል፡፡ ለምን ተቀራርበው መሥራት አልተቻለም?

/ሮ አንድነት፡- ችግሩ ከድሮ ጀምሮ የነበረ ነው፡፡ ለዘርፉ ይሰጥ የነበረው ትኩረት፣ የዘርፉ አመራሮች ቶሎ ቶሎ መቀያየር እንዲሁም እንደገና ዘርፉን አለመረዳት እንደ ዋና ችግር ሊጠቀስ ይችላል፡፡ አሁን ላይ እንደ አዲስ ዘርፉ ሪፎርም ሲደረግ የተለያዩ ተስፋ የሚሰጡ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ለምሳሌ ዘርፉ በሚኒስቴር ደረጃ ተቋቁሟል፡፡ እንዲሁም ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች እየተደረጉ ነው፡፡ ለዚህም የኢትዮጵያ አስጎብኚዎች ማኅበር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ዘርፉ በሚኒስቴር ደረጃ ከመቋቋሙ በፊት የቱሪዝም ቦርድ እንዲቋቋም የጎላ ድርሻ ነበረው፡፡ ዘርፉ ከብዙ ዘርፎችና መሥሪያ ቤቶች ከኢምግሬሽን፣ ከፀጥታ አካላት፣ ከውጭ ጉዳይ እንዲሁም ከአየር መንገድ ጋር ሳይቀር ይገናኛል፡፡ እነዚህን ሁሉ ከግል ዘርፉ ጋር አቀናጅቶ መምራት የሚያስችል ሚኒስቴር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ሁሉንም አቀናጅቶ መምራት የሚያስችል እንዲሁም ቆራጥ የሆነ ሥራን መሥራት የሚያስችል ሚኒስቴር ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ካስቀመጣቸው አምስት የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ውስጥ ቱሪዝም ይገኝበታል፡፡ ስለዚህ ከዚህ ጋር የሚጣጣም፣ መሬት ላይ ወርዶ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ግልጽ የሆነ ማስፈጸሚያና አቅጣጫ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ችግሩን ለመፍታት ከሚኒስቴሩ ጋር ሥራዎች ይጀመራሉ፡፡ ነገር ግን በዋናነት በየጊዜው አመራሮች መለዋወጣቸውንና ቁርጠኝነት ከማጣት ጋር ተከትሎ ጉዳዩ ተንከባሎ ተንከባሎ እዚህ ደርሷል፡፡ ማኅበራችን ከዚህ በፊት ለመጡት አመራሮች በዘርፉ ላይ የሚስተዋለውን ችግር ሁልጊዜ እንደ አዲስ ስናስረዳና ስንጠይቅ ከርመናል፡፡ ነገር ግን በአብዛኛው የመጡት አመራሮች አቅም ያላቸው ቢሆኑም ለዘርፉ ግን አዲስ ናቸው፡፡ ስለዚህ ዘርፉን ለመረዳት ጊዜ ይፈልጋል፡፡ አንዱ ተረድቶታል ብለን ውሳኔ ስንጠባበቅ በሌላ እየተተካ ችግሩ መፍትሔ ሳያገኝ እዚህ ደርሷል፡፡ በተጨማሪም አንደኛው አምኖበት ያፀደቀውን አንደኛው ያፈርሰውና እንደ አዲስ ይጀመራል፡፡ በዚህም ምክንያት እንደ አዲስ ዘርፉ ላይ ተሰማርተው ለመሥራት የሚቀላቀሉትም ተሰላችተው ለመውጣት ይገደዳሉ፡፡ መንግሥት ከላይ ሆኖ ዘርፉ እንዲለወጥ ፍላጎት ቢኖረውም፣ ከታች ግን የማስፈጸም ውስንነት አለ፡፡ ስለዚህ ዘርፉን አሳድጋለሁ ስትል ዘርፉን የሚመጥነውን ድጋፍ ማቅረብና ቆራጥነት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ዘርፉን ለማሳደግ አዲስ ሪፎርም ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ይነሳል፡፡ በአንፃሩ የአስጎቢኚዎች ማኅበር በሪፎርሙ ላይ መሻሻል ያለበት ጉዳይ አልተካተተም የሚል ጥያቄ አለው? ስለእሱ ቢያብራሩልን?

/ሮ አንድነት፡- በአሁኑ ጊዜ መንግሥት ለዘርፉ ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት ሰጥቶታል፡፡ መንግሥት አዲስ ሪፎርም አድርጎ ሥራ ሲገባ፣ ምን ተደረገ ብሎ በደንብ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ አንድ ዘርፍ ይደግ ሲባል፣ በሚገባው ልክ መደገፍና አስቻይ ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ የግል ዘርፉን ሚና ማገናዘብ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ዘርፍ የግሉ ዘርፍ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ዘርፉ ያለ ግል ዘርፍ ማደግ አይችልም፡፡ የሌሎች አገሮችን ልምድን መመልከት ይቻላል፡፡ ስለዚህ መንግሥት አዲስ ሪፎርም ሲያደርግ ትልቅ ሚና ላለው የግሉ ዘርፍ ምን ለመሥራት የሚያችል ሁኔታ ተፈጥሯል ብሎ መጠየቅ ያሻል፡፡ በዘርፉ ውስጥ ዋና ማነቆ ተብለው የሚታወቁ የታክስ ሕግ፣ የመሠረተ ልማትና የማስተዋወቅ ጉዳዮች ላይ የተስተካከለ የታክስ ሕግ፣ ለማልማት የመሬት አቅርቦት፣ የፋይናንስ አቅርቦት ታሳቢ ያደረገ እንዲሁም ከዘርፉ ጋር ተቆራኝተው የሚሠሩ ተቋማትን ታሳቢ ያደረገ ሪፎርም መሆን ይኖርበታል፡፡ በዋናነት ደግሞ ሪፎርሙን መሬት አውርዶ ለመከወን የአቅም መገንባትና አስፈላጊውን ድጋፍ ለግል ዘርፉ ከማቅረብ አንፃር ማጤን ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ መንግሥት አዲስ ባወጣው የቫት የረቂቅ አዋጅና ከታክስ ፖሊሲ ጋር ተያይዞ የሚያነሳው ጥያቄ አለ፡፡ ጥያቄው ምንድነው?

/ሮ አንድነት፡- ለረዥም ዓመታት የተጨማሪ እሴት ታክስ ጉዳይ ዘርፉን ሲፈትን ቆይቷል፡፡ ለአንድ ዘርፍ ተወዳዳሪነት የታክስ ፖሊሲ ወሳኝ ነው፡፡ ዘርፉን ለማሳደግ መቀላቀል ለሚፈልግ አዲስ ድርጅት፣ እንዲሁም ያሉትም እንዲሠሩ የተስተካከለ የታክስ ፖሊሲ ያስፈልጋል፡፡ እስካሁን ላለፉት 18 ዓመታት ማኅበራችን በተለይ ከተጨማሪ የእሴት ታክስ ጋር ተያይዞ፣ መንግሥትም ያለውን ማነቆ እንዲፈታና ግልጽ የሆነ አቅጣጫ እንዲቀመጥ በተደጋጋሚ ወትውቷል፡፡ የእኛ ጥያቄ የጀመረው የኮቪድ-19 ወረርሽኝና የፀጥታ ችግር ከመከሰቱ አስቀድሞ ነው፡፡ አስጎብኚ ማኅበሩ የሚሸጠው ኢትዮጵያ ያላትን ሀብቶች በግል ሰብስበን፣ ጥቅል አድርገን የእኛን ኮሚሽን ጨምረን አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ እኛ በዋናነት ከምንሰበስባቸው አገልግሎቶች ውስጥ የሆቴልና ሬስቶራንት ብቻ ነው መንግሥት ታክስ የጣለበት፡፡ ሌሎችንም እንደ አየር ትራስፖርት፣ የመስህቦች መግቢያ፣ ጋይድ፣ የመሳሰሉት ቫት አይመለከታቸውም፡፡ አንድ አስጎብኚ ድርጅቱ አንድ ጎብኚን ሲያመጣ፣ ለምሳሌ ጎብኚው ባሌ ተራራን መጎብኘት ቢፈልግ፣ አዲስ አባባና በመንገዱ የሚያርፍበትን ሆቴል፣ ትራንስፖርት፣ የፓርኮች መግቢያ፣ በባሌ የበቅሎ ጎታች፣ የበቅሎ አከራይ፣ ምግብ አብሳይ፣ ድንኳን ተካይ የመሳሰሉትን ዋጋ ደምሮ፣ እንደ አስጎብኚ ኮሚሽን ጨምረን እናስከፍላለን፡፡ እነዚህ አገልግሎቶች በአብዛኛው ቫት የላቸውም፡፡ በአንፃሩ እንግዶቻችንን በሆቴል አሳርፈን ለተጠቀሙት ቫት እንዲሰበሰብባቸው ለሚጠየቁ አገልግሎቶች ቫት ከፍለን አናስመልስም፡፡ ለዚህ ገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቱ የሚለው ከላይ የተዘረዘሩትን አገልግሎቶች ሁሉ ከደመርን በኋላ የእኛም ኮሚሽን ተጨምሮበት ከጥቅሉ 15 በመቶ ተጨማሪ እሴት ታክስ ጨምራችሁ ክፈሉ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ከውድድር አንፃር እንዲሁም ‹ደብል ታክሴሽን› በመሆኑ መስተካካል አለበት የሚል ጥያቄ ነው ያነሳነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአስጎብኚዎች ማኅበር ከሆቴል ወጪ ያሉትን አገልግሎቶች ቫት ማስከፈል ለምን አልቻለም?

/ አንድነት፡- የመጀመሪያው ጉዳይ እኛ ከምንሰጣቸው አገልግሎቶች ውስጥ የቫት ተመዝጋቢ ሆቴል ብቻ ነው። በተለየዩ ቦታዎች እንደ ፓርክ፣ ታሪካዊ ቦታዎችና መንደሮች ውስጥ የሚሰጡት አገልግሎቶች ቫት ተመዝጋቢ አይደሉም። ስለዚህ ጎብኚውን ወይም ድርጅቱን ነው የምናስከፍለው። ድርጅቱ ሊከፍል አይችልም። ምክንያቱም ድርጅቱ የኮሚሽን ተወካይ ነው። ጎብኚውን ክፍያ እንጠይቅ ብንል፣ እንደ አገር ከምንሰጠው አገልግሎት አንፃር የበለጠ ወደ መዳረሻ ያደርገናል፡፡ በዘርፉ ላይ የተሰማሩ የተለያዩ አስጎብኚዎች ቢኖሩም የመወዳደሪያ ሜዳው እኩል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ያለ ፈቃድ የሚሠሩና ቫት ያልተመዘገቡ አስጎብኚዎች አሉ። ስለዚህ በዚህ አሠራር ተጎጂ የሚሆነው በትክክለኛው መንገድ የሚሠራውና ለአገር የውጭ ምንዛሪ የሚያመጣውን ድርጅት ነው። አንድ ጎብኚ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ሲዘጋጅ ያሉትን የክፍያ ተመኖች በሙሉ ግልጽ ናቸው። ከጥቅል ቫት እንዲከፍሉ የሚደረጉ ድርጅቶች የሚሰጡት ዋጋ አብዛኛው ቫት ከማይከፍለው ጋር ሲወዳደር ሕጋዊ ሆኖ የሚሠራውን ድርጅት ከሥራ ወጪ ነው የሚያደርገው። ስለዚህ በዋናነት ከዘርፉ የሚፈለገውን የውጭ ምንዛሪ ለማምጣት በትክክል የሚሠሩ ድርጅቶችን የሚጠብቅ ሕግ ሊደረግ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ያስገኛሉ ብሎ ዜሮ ቫት ካደረጋቸው የኢንዱስትሪ ዘርፎች በእኩል ዓይን የመታየት አለብን የሚል ጥያቄም አላችሁ?

/ አንድነት፡- ጥያቄያችን መንግሥት በአሁኑ ጊዜ ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ ስለሆነም በዋናነት የውጭ ምንዛሪ ለሚያመነጩ ዘርፎች የተደረገው ልዩ ድጋፍ ሊደረግ ይገባል፡፡ በተጨማሪ የቱሪዝም ዘርፍ ኤክስፖርት ሴክተር እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ ስለሆነም በድጋሚ ከሰጠው ልዩ ትኩረት አንፃር በዚህ መንገድ እንዲጤን እንፈልጋለን፡፡ እኛ አገልግሎት ሰጪ ሆነን ነው የውጭ ምንዛሪ የምናመጣው። አንድ ጎብኚ ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ ይመጣል፡፡ ምንም ተጨማሪ ልማት ሳናደርግ ተደጋጋሚ የውጭ ምንዛሪ እናገኝበታለን፡፡ በተለይ መንግሥት ሌሎች አገሮች ዘርፉን ለማሳደግ ከተጨማሪ እሴትና ከሌሎች የታክስ ማሻሻያዎች አንፃር የወሰዱትን ዕምጃዎች እንዲያይ እንጠይቃለን፡፡ ማኅበራችንም ይህንን በተመለከተ ለመንግሥት አጋዥ በሆነ መልኩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የሌሎች አገሮች ልምድ የማሳያ ጥናት እያደረግን እንገኛለን፡፡ በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ በርካታ አገሮች የሚያበረታታ አዋጅ አውጥተው ነው ዘርፉን ያሳደጉት። ዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ ካደገ በኋላ አስፈላጊ ማሻሻያና ማስተካከያ ማውጣት ይቻላል። ለምሳሌ በአውሮፓ ቱሪዝማቸውን ማሳደግ ሲጀምሩ የሆቴሎችንና ሬስቶራንቶችን ታክስ ጭምር ዜሮ አድርገው የጀመሩ ብዙ አገሮች አሉ። በሒደት የተወሰነ ማሻሻያ ያደረጉ፣ እንደዚያው የተተው ብዙ ተሞክሮዎችም አሉ፡፡ እኛም አገር ይህ እንዲለመድ እንፈልጋለን። አሁን ደግሞ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ ሁሉም አገሮች ጎብኚዎችን ለመሳብ የተለየ የዋጋ ማሻሻያ አድርገው እንደ አዲስ ጀምረዋል። እኛ ጋ ደግሞ ከኮቪዱ-19 በበለጠ የእርስ በርስ ጦርነቱ ቱሪዝሙን ጎድቶታል፡፡ ስለሆነም በዚህ ሁሉ ውስጥ ጎብኚዎችን ለመመለስ አስጎብኚዎች በሙሉ አቅም እንዲሠሩ ምቹና ተወዳዳሪ ሁኔታ መፍጠር ለዚህም በዋናነት የታክስ አዋጁን መሻሻል አንዱ ዋና መፍትሔ ነው። በቅርቡ መንግሥት አዲስ የቫት ረቂቅ አዋጅ አውጥቷል። ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የእኛ ጉዳይ ዳግም እንዲታይ ከሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶችና የንግድ ማኅበር ጋር እየተወያየን ነው። የእኛ ጥያቄም በዚህ ውስጥ ይመለሳል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

ሪፖርተር፡- ከታክስ ውጪ ዘርፉን እየፈተነ ያለው ምንድነው?

/ አንድነት፡- ሌላው ዘርፉን እየፈተነ የሚገኘው ከወቅቱ ጋር ተያይዞ አገልግሎት ሰጪዎችን በሚገባ መልኩ አለመደገፍ ነው፡፡ ዘርፉ ሲመለስ በብዙ ድካም የተገነባው የተለያየ አገልግሎት ሰጪ ማለትም አስጎብኚ ድርጅቶችን ጨምሮ ጋይዶች፣ የአካባቢ አስጎብኚዎች፣ ሬስቶራንቶችና ሆቴሎች በተለይ በመዳረሻ አካባቢዎች መዘጋትና ከአገልግሎት መውጣት ከፍተኛ ክፍተት ይፈጥራል፡፡ ሌላው የመሠረተ ልማት ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪስት መስህብ በደንብ ማስተዋወቅ ቢቻልም፣ የመሠረተ ልማት ጉዳይ ሌላው ፈታኝ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ ባሌ ተራራ ውስጥ ከ15 ክፍል በላይ ደረጃውን የጠበቀ ማረፊያ የለም። ስሜን ተራራ ከ40 ክፍል በላይ ጠቅላላ የእንግዳ ማረፊያ የለም። አፋር ዋና መስህብ ጋ ምንም ዓይነት ማረፊያም ሆነ ሆቴል የለም። በጎረቤት አገሮች ብንመለከት ከ5,000 በላይ ማረፊያዎች አሉ። በኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎች የሚገኙትም ሆቴሎች በብዛትም በጥቂትም በቂ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው ብሎ ለመናገር ያዳግታል። ሌላው በኢትዮጵያ ያሉት የተፈጥሮ እንዲሁም የታሪክ መስህቦች በጥንቃቄና በተጠያቂነት የሚቆጣጠራቸው አካል አለመኖሩ እንደ ግል ዘርፍ በጣም ያሳስበናል። ፓርኮች ይጠፋሉ፣ በውስጣቸው ያሉ አራዊትም ይገደላሉ፣ ቅርሶች ይጠፋሉ ይህንን እንዲቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው አካል በኃላፊነት ለሕዝቡን ጠቀሜታውን በማስተማርና ኃላፊነትን ወደ ሕዝብ በፍላጎት በማውረድም ጭምር ሊከታተልና ሊጠየቅ ይገባል፡፡ በአጠቃላይ ዘርፉን ለማሳደግ፣ ተወዳዳሪ ለማድረግ ሥርዓት ለማስያዝና ያሉትንና አዳዲስ መንግሥት የሚሠራቸውን ትልልቅ ልማቶች ጨምሮ እንደሚፈለገው ወደ ገቢ ለመቀየር የግል ዘርፉ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ፣ እስከ ታች ድረስ ወርዶ በቅንጅት መሥራት ምንም ምርጫ የሌለው ነገር ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ማኅበራችን እንደ ሁልጊዜው ከግሉ ዘርፍ የሚጠበቀውን ሁሉ ከመንግሥት ጋር በመሆን ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ በማኅበሩ ስም ማረረጋጥ እፈልጋለሁ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግዴታን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን ሥርዓት

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍና የማኅበራዊ ጤና መድኅን ሥርዓቶችን መሠረት አድርጎም ይሠራል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት በኢመደበኛ...

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን...

‹‹በአሁኑ ሰዓት እየፈተነን ያለው እንደ ልብ ተንቀሳቅሰን መሥራት አለመቻላችን ነው›› አቶ ልዑል ሰገድ መኮንንን፣ አይሲዳ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር

አይሲዳ አገር በቀል የዕርዳታ ድርጅት በኤችአይቪ ሥርጭት ቁጥጥር ላይ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከ1998 ዓ.ም. ወዲህ ራሱን እንደ አዲስ አዋቅሮ በተለይ ለሰው ሠራሽና ለተፈጥሮ አደጋዎች ምላሽ...