በየዓመቱ በመስከረም ሦስተኛ ቅዳሜና እሑድ ላይ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል መስከረም 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ፣ በማግስቱ እሑድ በቢሾፍቱ ከተማ ተከብሯል፡፡ የአዲስ አበባው በዓል ‹‹ኢሬቻ ሆረ-ፊንፊኔ›› ሲባል፣ የቢሾፍቱው ‹‹ሆረ አርሰዲ›› ይባላል፡፡ በአባ ገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች ግንባር ቀደምነት ‹‹መሬ..ሆ›› በተሰኘው ዜማ የታጀበው ክብረ በዓሉ፣ ታዳሚያን በተለያዩ የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳትና ጌጣ ጌጦች የተዋቡ፣ ከልጅ እስከ አዋቂ ሴቶችና ወንዶች የታዩበት ነው፡፡ በአዲስ አበባ በአምስቱ መግቢያ በሮች ከተለያዩ የኦሮሚያና ሌሎች ክልሎች የመጡ ታዳሚዎች በተለያዩ ባህላዊ አልባሳት ተውበው በባህላዊ ጭፈራዎች በዓሉን ማድመቃቸው ታይቷል፡፡ የኢትዮጵያን የዓመት መጀመርያ የሆነውን መስከረምን ከሚያደምቁት በዓላት አንዱ የሆነው ኢሬቻ፣ ከክረምት ወደ ብራ መውጣትን ምክንያት በማድረግ ምሥጋና የሚቀርብበት መድረክ መሆኑ ይነገራል፡፡ የሚሞገሰው ልምላሜ ነውና ለምለም ቄጠማና አደይ አበባ የበዓሉ ልዩ መገለጫ ሆነው ታይተዋል፡፡ በዩኔስኮ የተመዘገበው የገዳ ሥርዓት አንድ አካል የሆነው ኢሬቻ፣ ዝማሬና ውዝዋዜ፣ ፉከራን የመሰሉ ክውን ጥበባትን ማቀፉ፣ እንዲሁም የሰው ልጆች ከተፈጥሮ ጋር ተስማምተው መኖራቸውን ማንፀባረቁ የዓለም ሕዝብ ለገዳ ሥርዓት ትኩረት እንዲሰጥ ካደረጉ መካከል እንደሚጠቀስ አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ ያሳያል፡፡ ፎቶዎቹ የክብረ በዓሉን ልዩ ልዩ ገጽታዎች ያሳያሉ፡፡