Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የእንስሳት ሀብት የሚያለሙ ማኅበራትን አደራጅቶ ብድር ለማቅረብ ከልማት ባንክ ጋር ስምምነት ተፈረመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን በመላው አገሪቱ በከተሞች አካባቢ  በእንስሳት ልማት ላይ ብቻ አተኩረው የሚሠሩ 90 ማኅበራትን በማደራጀት የብድር አቅርቦት እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር ተፈራረመ፡፡ 

መስከረም 24 ቀን 2015 ዓ.ም. የተፈራረሙት ሁለቱ ተቋማት፣ በእንስሳት ልማት ዘርፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ቅጥ ያጣውን ገበያ ሥርዓት ለማስያዝ፣ እንዲሁም የውጭ ገበያን ለማሳደግ መታቀዱን የኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ወ/ሮ ፍሬዓለም ሽባባው በፊርማው ሥነ ሥርዓቱ ላይ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚደራጁት ማኅበራትም ተዘንግቶ የቆየውን የእንስሳት ሀብት ልማት  በአዲስ መልክ በባለሙያዎች የሚተዳደሩ፣ በሳይንስ እንዲሁም ተጠያቂነት በሚኖረው ጠንካራ ሥርዓት የሚመሩ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ 

የሚደራጁት ማኅበራትም የሥጋና የዕንቁላል ጣይ ዶሮዎች፣ የበግ፣ የፍየል፣ የዳልጋ ከብቶች፣ እንዲሁም በወተት ምርቶች ላይ አተኩረው የሚሠሩ መሆናቸው ታውቋል፡፡ የማኅበራቱ አደረጃጀትም ከኮሚሽኑና ከሚመለከታቸው የክልል የኅብረት ሥራ ኤጀንሲዎች በጋራ በመሆን የሚከወን ሲሆን፣ ብዛታቸውም እንደ ሥራውና እንደ ክልሉ አቅም የሚወሰን ሆኖ ለአስተዳደር በሚመች መልኩ ይደራጃሉ ተብሏል፡፡

ማኅበራቱ ከተደራጁ በኋላ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሚያስቀምጠው መመዘኛ መሠረት ተለይተውና አስፈላጊውን ቅድመ ሥልጠና ወስደው ወደ ሥራ የሚገቡ መሆኑን የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡ 

በተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚደራጁት ማኅበሮች፣ እያንዳንዱ በአማካይ 10 ሺሕ ዕንቁላል፣ አንድ ሺሒ በግ፣ እንዲሁም 50 የወተት ላሞች ማርባት እንደሚጠበቅባቸውም ተገልጿል፡፡ 

እንደ ባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ (ዶ/ር) አስተያየት ከሆነ፣ ‹‹የፖሊሲ ባንክ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እስከዛሬ ትኩረት ሳይሰጠው የቆየውን ይህንን ዘርፍ አልምቶ ለአገር ጠቃሚ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል፤›› ብለዋል፡፡ 

በዚህም መንገድ ወደ ልማት የሚገቡት ማኅበራት ለባንኩ የመጀመርያ እንደመሆናቸው መጠን ለዘርፉ የተሰነቀውን አዲስ ራዕይ ሳይዘነጉ መሥራት እንደሚገባቸውና ባንኩ የፈቀደላቸውን ገንዘብ በአግባቡ ሥራ ላይ አውለው መመለስ እንደሚጠቡቅባቸው ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል፡፡

በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከ11 ክልሎች፣ ከሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ የግብርና አደረጃጀት ቢሮ ኃላፊዎች፣ የግል ባለሀብቶች፣ የባንክ ኃላፊዎች፣ እንዲሁም የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የኅብረት ሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ በቅርቡም የግብርና ሚኒስቴሩ በተገኙበት ማኅበራቱ ተደራጅተው በይፋ ሥራቸውን እንደሚጀምሩ ተጠቁሟል፡፡        

በመድረኩ ዘርፉን የተመለከቱ ጥናቶች የቀረቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በኢትዮጵያ ያለውን የነፍስ ወከፍ የእንስሳትና የእንስሳት ተዋፅዖ ፍጆታ የተመለከቱ ይገኙበታል። ከቀረቡት ጥናቶች መረዳት እንደተቻለውም፣ በኢትዮጵያ በዓመት የአንድ ሰው የዕንቁላል ፍጆታ ሰባት ሲሆን፣ በአንፃሩ በኬንያ 44 ነው፡፡ በሌላ በኩል የዶሮ ሥጋ በኢትዮጵያ የአንድ ሰው ፍጆታ በዓመት 0.8 ኪሎ ግራም ሲሆን፣ የአፍሪካ አማካኝ የነፍስ ወከፍ ፍጆታ ግን 6.73 ይደርሳል፡፡

በዓለም ጤና ድርጅት ሥሌት መሠረት የአንድ ሰው አማካይ ዓመታዊ የወተት ፍጆታ 200 ሌትር ቢሆንም፣ በአንፃሩ በኢትዮጵያ አንድ ሰው 70 ሌትር ወተት ብቻ በዓመት እንደሚጠቀም በመድረኩ የቀረበ ጥናት አመላክቷል። ለዚህም በኢትዮጵያ ከፍተኛ የእንስሳት ምርት እጥረት እንዳለ በጥናቱ ቀርቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች