Thursday, November 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትና አባል የክልል ንግድ ምክር ቤቶች ተቋማዊ ጤንነት ሲፈተሽ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የኢትዮጵያን የንግድ ኅብረተሰብ በመወከል የሚጠቀስ አገር አቀፍ ተቋም ነው፡፡ በንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጁ መሠረት 18 አባል ምክር ቤቶች አሉት፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ኅብረተሰብን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትም ሆነ አባል ምክር ቤቶች በሕገ ደንባቸው መሠረት ጠቅላላ ጉባዔ አካሂደው ሥራቸውን በተገቢው መንገድ እየሠሩ ያለመሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡ በተለይም ወቅቱን ጠብቆ ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ማካሄድ አለመቻላቸው በንግድ ምክር ቤቶቹ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳረፈ ነው፡፡ አሁን በአመራር ላይ ያለው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በምርጫ ኃላፊነትን የተረከበው ጥቅምት 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ነው፡፡ የተመረጠውም ለሁለት ዓመታት እንዲያገለግል ሲሆን፣ የሁለት ዓመቱ የምርጫ ዘመን እንደተጠናቀቀ ለቀጣይ ሁለት ዓመት የሚያገለግሉትን አዲስ የአመራር አባላት ምርጫ ማካሄድ ነበረበት፡፡ ሆኖም በንግድና ምክር ቤቱ ሕገ ደንብ መሠረት ይህ ምርጫ ሳይካሄድ ለሁለት ዓመታት የተመረጠው ቦርድ አምስተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ በየሁለት ዓመቱ ማካሄድ የነበረበትን ምርጫ ብቻ ሳይሆን፣ በየዓመቱ ማካሄድ የነበረበትን ጠቅላላ ጉባዔም አላካሄደም፡፡ ቦርዱ በተመረጠ በዓመቱ ካካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ውጪ በተከታታይ ሦስት ዓመታት ማካሄድ የነበረበትን ጠቅላላ ጉባዔ ያለማካሄዱ ጥያቄ እያስነሳበት ነው። ንግድ ምክር ቤቱ በሕገ ደንብ መሠረት ጠቅላላ ጉባዔውንና ምርጫ ማካሄድ ያልቻለው በዋናነት በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት እንደሆነ ቢጠቅስም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የፈጠረው ሥጋት ከተቀረፈና በአገሪቱ የተረጋጋ ሁኔታ ከተፈጠረ በኋላም ቢሆን ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔውን ሊያካሂድ አልቻለም፡፡ ከደንብና ከአሠራር ውጭ የዘገየውን የንግድ ምክር ቤቶች ምርጫና ጠቅላላ ጉባዔ ያለማካሄዱ ችግር የአገር አቀፉ ንግድ ምክር ቤት ብቻ ሳይሆን፣ የሁሉም የንግድ ምክር ቤቱ አባል የሆኑ የክልል ንግድ ምክር ቤቶች ችግር ሆኗል፡፡ ሁሉም ንግድ ምክር ቤቶች በሕገ ደንባቸው መሠረት ጠቅላላ ጉባዔ ጠርተው ምርጫ አላካሄዱም፡፡ ሪፖርተር ባገኘው መረጃ መሠረት ከአዲስ አበባና የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ውጪ ጠቅላላ ጉባዔ አድርጎ ምርጫ ያካሄደ የለም፡፡ የአዲስ አበባና የአማራው ንግድ ምክር ቤቶችም ቢሆኑ ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ያካሄዱት ከመተዳደሪያ ደንባቸው ውጪ ከሁለት ዓመታት በላይ ዘግይተው በመሆኑ የንግድ ምክር ቤቶች አጠቃላይ አሠራርና ሒደት ብዙ ችግሮች እንዳሉበት አመላካች ነው የሚል ትችት እንዲጎላ አድርጓል።

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ቦርድ አባል የሆኑት አቶ ታደሰ ገና እንደገለጹት የንግድ ምክር ቤቶቹ ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ በኮቪድ ወረርሽኝ መከሰት በፈጠረው ሥጋትና በአገር ደረጃ በነበረ አለመረጋጋት ምክንያት መዘግየቱ እርግጥ ቢሆንም፣ ዋናው ምክንያት ግን የንግድ ምክር ቤቶች አዋጅ ይሻሻላል ተብሎ ይህንን ማሻሻያ ለመጠበቅ በመገደዳቸው ነው።

አሁንም ቢሆን ሲጠበቅ የነበረው የሕግ ማሻሻያ አለመምጣቱን የገለጹት አቶ ታደሰ ገና፣ ይህ ማሻሻያ ባይረስም ምክንያት የነበሩት ሌሎቹ ሁኔታዎች በመቀየራቸው በየክልሉ የንግድ ምክር ቤቶቹ ምርጫዎቻቸውን ማካሄድ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ግን ከታች ጀምሮ ንግድ ምክር ቤቶችን ከታች አንስቶ የማደራጀት ተግባር ተከናውኖ ምርጫ እንዲያካሂዱ እንደሚደረግም ጠቁመዋል። በዚህም መሠረት በክልል በየደረጃው የሚገኙ የንግድ ምክር ቤቶች ምርጫ አካሂደው ካጠናቀቁ በኋላ የክልል ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ምርጫ ተደርጎ ወደ አመራር እንዲመጡ ይደረጋል ብለዋል፡፡ እንደ ኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አጠቃላይ ምርጫውን በጥቅምት ወር ለማጠናቀቅ መታቀዱንም አቶ ታደሰ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትም ጠቅላላ ጉባዔውን የሚያካሂደው የአባላቱ የክልል ንግድ ምክር ቤቶች ምርጫ ከተጠናቀቀ በኋላ እንደሚሆንና ይህም በዚሁ የበጀት ዓመት ዕውን እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ 

የንግድ ምክር ቤቶቹን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ አስተያየት የሰጡ የንግድ ምክር ቤቶቹ አባላት የንግድ ምክር ቤቶች ወቅታዊ እንቅስቃሴ መዳከሙንና የንግዱን ኅብረተሰብ ጥያቄ ይዘው እየሞገቱ አለመሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡

ከዚህ ቀደም ዓመት ተጠብቆ የሚካሄድ ጠቅላላ ጉባዔ አሁን ላይ እየተደረገ ያለመሆኑ ምክር ቤቶች በአግባቡ ሥራቸውን እየሠሩ ያለመሆኑን ብቻ ሳይሆን የንግድ ማኅበረሰቡ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ተቋም መሆን አለመቻላቸውን የሚጠቁም ነው የሚሉም አስተያቶች እየተሰነዘሩ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ አለማድረጉን በተመለከተ ያነጋገርናቸው አንዳንድ የክልልና ከተማ ንግድ ምክር ቤቶች አመራሮች ችግሩ የሁለቱም ስለመሆኑ ያመለክታሉ፡፡ በወቅታዊ ሁኔታና በኮቪድ ወረርሽኝ እየሳበቡ እስካሁን መቆየት አልነበረባቸውም በሚል ይሞግታሉ፡፡ እንቅስቃሴዎቻቸውም ቢሆን እንደ ቀድሞ ያለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

የአሶሳ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ተሾመ ጽጌ በበኩላቸው አሁን ያሉት ንግድ ምክር ቤቶች በተቋቋሙለት ዓላማ ልክ እየሠሩ ናቸው ብለው እንደማያምኑ ለሪፖርተር ገልጸዋል። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ተጠያቂ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ነው ይላሉ፡፡

የክልል ንግድ ምክር ቤቶች በወቅቱ ጠቅላላ ጉባዔያቸውን እያካሄዱ በየሁለት ዓመቱም ምርጫ እንዲያደርጉ ግፊት ማድረግና ቀን መቁረጥ የነበረበት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ቢሆንም ይህንን ማድረግ አለመቻሉ ችግሩ እንዲፈጠር ምክንያት እንደሆነ ያምናሉ፡፡ እንደውም የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት የክልል ንግድ ምክር ቤትን ዞር ብሎ አያይም በማለት ይወቅሳሉ፡፡ ይህም የንግድ ኅብረተሰቡን ችግር በአግባቡ ተረድቶ መፍትሔ ለመውሰድ ያላስቻለ ነው የሚሉት አቶ ተሾመ ንግድ ምክር ቤቶች አሁን አሉ ለማለት ያስቸግራል ይላሉ፡፡

የክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ወቅቱን ጠብቀው ጠቅላላ ጉባዔ ላለማካሄዳቸው የሚጠቅሱት የየራሳቸው ችግር ቢኖርም በሕገ ደንባቸው መሠረት ጉባዔ እንዲጠሩ ለማድረግ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ዕገዛ አለማድረጉ የንግድ ምክር ቤቶች ህልውና ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉንም ይጠቅሳሉ፡፡

ለምሳሌ የቤንሻንጉል ጉምዝ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ካካሄደ ዘጠኝ ዓመታት ቆይቶ ብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ምንም ያለው ነገር እንደሌለ የጠቀሱት አቶ ተሾመ፣ ሆኖም የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ የቤንሻንጉል ጉምዝ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ወቅቱን ጠብቆ ጠቅላላ ጉባዔ ባለማድረጉ ሊታገድ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡ 

ስለዚህ የክልሉ ንግድ ምክር ቤት የቦርድ አባላት ታግደው ሥራው በጽሕፈት ቤት ብቻ እየተመራ መሆኑ እየታወቀ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራ አለመደረጉ በንግድ ምክር ቤቶች አካባቢ ያለውን ችግር ያሳያል ብለዋል፡፡ ይህንን ዕግድ ለማስነሳት ገለልተኛ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት ምርጫ እንዲደረግ ቢፈለግም ይህንን ማሳካት እንዳልተቻለም አቶ ተሾመ ጠቅሰዋል። ይህ በሆነበት ሁኔታ እንዴት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ይካሄዳል? በማለትም ይጠይቃሉ፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትም የክልሉን ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ የሚያስፈልገውን ወጪ እንዲሸፈን ተጠይቆ አልችልም በማለቱ በእንጥልጥል ላይ እንደሆነም የአቶ ተሾመ ገለጻ ያስረዳል፡፡ 

ሌሎችም የክልሉ ንግድ ምክር ቤቶች ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ያሉ እንደሆነ እየተጠቀሰ ነው፡፡ የደቡብ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትም ጠቅላላ ጉባዔ አራት ዓመታት እንዳለፈው ታውቋል፡፡ ይህ ክልል ግን ከሌሎች የተለየ ምክንያት ስላለኝ ጠቅላላ ጉባዔም ሆነ ምርጫ ማካሄድ አልቻልኩም ብሏል፡፡

የደቡብ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔውን ማካሄድ ያልቻለበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ በክልሉ የተፈጠሩ የአዳዲስ ክክሎችና አሁንም በተመሳሳይ ጥያቄ ላይ ከሚገኙ ዞኖች ጉዳይ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ የደቡብ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አሸናፊ ፈለቀ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ሸናፊ ገለጻ 2010 ዓ.ም. የሲዳማ የክልልነት ጥያቄን ተመርኩዞ አባሎቻችን በሙሉ መዋጮዋቸውን ከፍለው ጠቅላላ ጉባዔ ሊያደርጉ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ አልነበሩም፡፡ በዚህ ምክንያት ጠቅላላ ጉባዔ ማድረግ አለመቻላቸውን ለክልሉ ንግድ ቢሮና በወቅቱ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ማሳወቃቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚያም በኋላ በደቡብ ክልል የክልልነት ጥያቄ የሚያነሱ ሌሎች አሥር ዞኖች መምጣት የደቡብ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ጉዳይ ውስብስብ አደረገው ስለዚህ ይህንኑ አሳውቀው እንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ እያለን ጠቅላላ ጉባዔውን መጥራት ያለመቻላቸው ትልቅ ፈተና እንደሆነባቸው የሚገልጹት አቶ አሸናፊ ፈተናው የምክር ቤቱን አቅም እያደከመው ጭምር መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ እንደውም ምክር ቤቱን እናፍርስ ወይ? እስከማለት ተደርሷል ይላሉ፡፡

በክልላቸው የተፈጠረው ክፍተት የንግድ ምክር ቤታቸውን የገቢ ምንጭ ጭምር የጎዳ ሲሆን፣ በተለይ ሲዳማ ራሱን ችሎ ከወጣ በኋላ በሐዋሳ ከተማ ከዚህ ቀደም ንግድ ምክር ቤቱ ያካሂደው የነበሩት የንግድና ባዛር ዝግጅት እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡

የምክር ቤቱ ዋነኛ ገቢ ይኸው ባዛር ቢሆንም ይህንን ለማድረጋችን ችግር ገጥሞናል በማለት ያለባቸውን ችግር አውስተዋል፡፡ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ እንዲህ ያለው ችግር በሁሉም ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች የሚስተዋል ሲሆን፣ የንግድ ምክር ቤቶችን ወቅታዊ ሁኔታ የሚከታተል አካል መጥፋቱም ችግሩን እንዳባሰው የሚናገሩ አሉ፡፡ ብዙዎቹ ንግድ ምክር ቤቶች በስም ብቻ ያሉ ሲሆን ሕገ ደንባቸውን ተመርኩዘው እየሠሩ ያለመሆናቸውን የሚጠቅሱ አሉ፡፡ እንደ አቶ ታደሰ ገለጻ እንዲህ ያሉ አስተያየቶች የሚሰነዘሩት ምርጫ በወቅቱ ካለመካሄዱ ጋር የተያያዙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን አሳማኝ ምክንያቶች ስለነበሩ የተፈጠረ ክፍተት እንደሆነ በመግለጽ የሚሰነዘሩትን ትችቶች አይቀበሉዋቸውም፡፡ 

በተለይ ንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ይሻሻላል በሚል የተፈጠረው መዘናጋት ችግሩን ያባባሰው ቢሆንም አሁን ግን በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ቦርድ በተሰጠው ውሳኔ መሠረት የምርጫ ሒደቱ ተፈጻሚ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

ይህም ቢሆን ግን ዘንድሮ ሁሉም ክልሎች ከታች ጀምሮ ምርጫ በማድረግ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ጠቅላላ ጉባዔ ምርጫ የሚካሄድ ስለመሆኑ አረጋግጠዋል፡፡ 

አቶ ተሾመ ግን ብሔራዊ ምክር ቤቱም ሆነ የክልል ምክር ቤቶች ለከተማ ንግድ ምክር ቤቶች ምንም ዓይነት ዕገዛ የማያደርጉ በመሆኑ ህልውናችን አደጋ ላይ ነው ይላሉ፡፡ የንግዱን ኅብረተሰብ መብት ለማስጠበቅ አልተቻለም፡፡ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ለአገር ውስጥ የንግድ ኅብረተሰብ ከማሰብ ይልቅ ከውጭ የንግድ ልዑካን ጋር መታየት የሚፈልግ በመሆኑ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ምርጫ አድርጎ አዲስ አመራር ቢሰየምም ታች ተወርዶ የማይሠራ ከሆነ ጥቅም የለውም የሚል አቋም አላቸው፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ውቤ መንግሥቱ ለሪፖርተር እንደገለጹት ደግሞ ምርጫን በተመለከተ በቦርድ የተወሰነው ውሳኔ የከተማና የክልል ንግድ ምክር ቤቶች  ምርጫዎችን እንዲያካሂዱ ማድረግ አንድ ጉዳይ ሆኖ የሁሉም ንግድ ምክር ቤቶች ፕሬዚዳንቶና ዋና ጸሐፊዎች በተገኙበት አንድ ውይይት ይካሄድ የሚል ነው፡፡

የዚህን ውይይት ውጤት መሠረት አድርጎ የምርጫ ቀኑ ይወሰን፡፡ እስከዚያ ግን 18ቱም አባል ምክር ቤቶች በየደረጃው ጠቅላላ ጉባዔያቸውንና ምርጫቸውን እንዲያካሂዱ መወሰኑን አቶ ውቤ ገልጸዋል፡፡ ይህም ውሳኔ እንዲደርሳቸው ተደርጓል ይላሉ፡፡ የአባሎቻቸውን መረጃም ለኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እንዲያቀርቡም ተወስኗል፡፡ በዚህ የቦርድ ውሳኔ መሠረት በቅርቡ የሁሉም ንግድ ምክር ቤቶች ፕሬዚዳንቶችና ዋና ጸሐፊዎች በምርጫው ዙሪያ ውይይት በማድረግ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ምርጫ በዚህ ዓመት ለማካሄድ እንቅስቃሴ መጀመሩንና የከተሞች ምርጫዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም ምክር ቤታቸው ዕገዛ እያደረገ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡

ለመዘግየቱ ምክንያቶች ቢኖርም አሁን በከተሞች እየተደረገ ያለው ምርጫ በክልል ደረጃ ከተካሄደ በኋላ የብሔራዊ ምክር ቤቱ ተመሳሳይ ምርጫ ያደርጋል በማለት ገልጸዋል፡፡

ብሔራዊ ምክር ቤቱ እንዲህ ያለ ዕቅድ ያለው ቢሆንም የደቡብ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ግን የተለየ አቋም እንዳለው አስታውቋል፡፡ ይህም የደቡብ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አሁን ባለበት ችግር ጠቅላላ ጉባዔውን ማካሄድ ባልቻለበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔውን ማድረግ የለበትም የሚል ነው፡፡

ይህ እንዲታገድልን እንጠይቃለን ያሉት አቶ አሸናፊ የትግራይና የደቡብ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የሌለበት ጠቅላላ ጉባዔ ማካሄድ ተገቢ ስለማይሆን እንዲታገድልን እንጠይቃለን ብለዋል፡፡

ለደቡብ ንግድ ምክር ቤት ወቅታዊ አቋም ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ውቤ፣ ይህ ውሳኔያቸው ከአባልነት የሚያግዳች ነገር አይኖርም፡፡ ሕጉ በሚፈቅድላቸው ድረስ በምርጫ የመሳተፍ፣ የመምረጥና የመመረጥ መብቱ አላቸው፡፡ ነገር ግን የጠቅላላ ጉባዔ ሕግ 50+1 በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሂዳል፡፡ ይህ በአዋጅ የተደነገገ በመሆኑ አብዛኛው አባላት ከተገኙ ጠቅላላው ጉባዔ ይካሄዳል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 

ነገር ግን የመጨረሻው ውሳኔ የሚሰጠው ግን በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንደሚሆን አቶ ውቤ አመልክተዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች