- ክቡር ሚኒስትር እጅግ የሚያስደስት ነገር ነው። እንኳን ደስ አለዎት፡፡
- ምኑ? ምን ተገኘ?
- ባለፈው የነገሩኝ ስልት በጣም ውጤታማ ነው።
- የቱ ስልት?
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር ባለፈው ያጫወቱኝ ነዋ? ለማንኛውም በኃይል ከያዙት አካባቢ እግሬ አውጪኝ ብለዋል።
- እውነት፡፡
- አዎ። አልሰሙም እንዴ?
- እኔ ምንም የሰማሁት ነገር የለም።
- የምርዎትን ነው ክቡር ሚኒስትር?
- አልሰማሁም ስልህ?
- የካቢኔ አባል ሆነው ምንም ካልሰሙ ተግባራዊ የሆነው ስልት በጥብቅ ዲሲፕሊን የሚፈጸም ነው ያሰኛል።
- የቱ ስልት?
- ባለፈው የነገሩኝን የውጊያ ስልት ማለቴ ነው።
- የውጊያ ስልት? እኔ ነኝ የነገርኩህ?
- አዎ!
- ምን ብዬ?
- ምታ በዝምታ!
- በጭራሽ አላስታውስም… እርግጠኛ ነህ እኔ ነኝ የነገረኩህ?
- አሃ …ገባኝ ገባኝ!
- ምን?
- በዘዴ እየነገሩኝ እንደሆነ ገባኝ።
- በዘዴ የገባህ ምንድነው?
- ማስተካከያ እንደተደረገበት።
- ምኑ?
- ምታ በዝምታ።
- ምን ተባለ?
- ምታ በዝምታ ጠላት እስኪምታታ፡፡
- ኦሆሆ… አንተ መቼም…
- እውነቴን ነው እንደዚያ እኮ ነው ያደረጋቸው?
- ምኑ?
- ምቱ!
- እንዴት?
- መጀመሪያ ለቀን ነው የወጣነው አሉ።
- እሺ፡፡
- ቀጥሎ ደግሞ ተሸንፈን አይደለም ስትራቴጂክ የቦታ ለውጥ ነው አሉ።
- ማን ተሸንፋችሁ ነው አለ?
- እሱን እኮ ነው የምልዎት፡፡
- እሺ፡፡
- ቀጥሎ ደግሞ መንግሥት ራሱ መግለጫ አለመስጠቱ የሚያረጋግጠው ተሸንፈን አለመውጣታችን ነው አሉ።
- መንግሥት አሁንም በዝምታው ሲቀጥል ደግሞ ምን አሉ መሰሎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እህ…
- እንገናኛለን፡፡
- ኪኪኪ… ወይ አንተ!
- በዚህ ከቀጠሉ ወደፊት ምን የሚሉ ይመስልዎታል?
- እ…?
- እጅ በእጅ!
- እጅ በእጅ ምን?
- እጅ በእጅ ይዋጣልን!
[ክቡሩ ሚኒስትሩ ከዓብይ የሰላም ኮሚቴው ጋር ድርድሩን የተመለከተ ሪፖርት ተቀብለው ተጨማሪ መረጃ እየጠየቁ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በእኛ በኩል ማድረግ የሚገባንን ዝግጅት አድርገናል ነገር ግን …
- ነገር ግን ምን?
- ክቡር ሚኒስትር ሌላኛው ተደራዳሪ አቋሙን የቀየረ ይመስላል?
- እንዴት? ምን ተፈጠረ?
- እኛን ቅርቃር ውስጥ ለማስገባት አልሞ የዘመን መለወጫ ቀን ላይ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን አሳውቆ አልነበር?
- አዎ።
- የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነትን መቀበል ብቻ ሳይሆን ያለ ቅድመ ሁኔታ ለመደራደርም ዝግጁ መሆኑን ለማሳየት ቅድመ ሁኔታ የሌለው ጥሪ ነበር ያቀረበው።
- አዎ። አስታውሳለሁ፡፡
- አሁን ወደ ድርድር ለመግባት ጥረቶች ሲጀመሩ ወደ ቀደመ አቋሙ ተመልሷል።
- ወደ ቀደመ አቋሙ ማለት?
- የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነትን ብቀበልም ዋና አደራዳሪውን አልቀበልም እያሉ ነው።
- እንደዚያ አሉ?
- እሱ ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲል ያስቀመጣቸውን ሁሉንም ቅድመ ሁኔታዎች ዳግም በቅድመ ሁኔታነት እያቀረበ ነው።
- እርግጠኛ ነህ?
- አዎ። ተደራዳሪ ተብለው የተመደቡት ሰዎዬ ናቸው በይፋ የተናገሩት።
- እንደዚያ ከሆነ እኚህን ተደራዳሪ መንግሥት እንደማንቀበል ለአደራዳሪዎቹ እሳውቁ፡፡
- እንዴት? ለምን ብለው ቢጠይቁንስ?
- በመጀመሪያ ሕጋዊ ዕወቅና ያለው የክልል መንግሥት ባለመኖሩ ድርድሩን የምናደርገው ከክልሉ ፓርቲ ጋር እንደሆነ አሳውቋቸው።
- ጥሩ። ከዚያ በኋላስ?
- ሰውዬው የክልሉ ፓርቲ አባል እንዳልሆኑ ጠቅሳችሁ እንደማንቀበል አሳውቁ።
- እሺ። ጥሩ መላ ነው።
- ሌላ የገጠማችሁ ችግር አለ?
- ትልቅ ችግር አለ ክቡር ሚኒስትር።
- ምንድነው?
- በድርድሩ መሳተፍና ሚና እንዲኖራቸው የሚፈልጉ አገሮች ቁጥር እየጨመረ ነው።
- የትኞቹ አገሮች ናቸው።
- የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አለ። አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረትም መሳተፍ አለብን እያሉ ነው።
- የተባበሩት መንግሥታት አይበቃም እንዴ?
- እኛ የሌለንበት ድርድር አይታሰብም እያሉ ነው። እነሱን ተከትሎ ደግሞ ሌሎች አገሮችም ጥያቄ አቅርበዋል።
- የትኞቹ አገሮች?
- ሩሲያ፣ ቻይናና የዓረብ አገሮች ናቸው። በዚህም ምክንያት ማን ታዛቢ መሆን አለበት የሚለው ላይ ስምምነት ጠፍቷል።
- ሌላ ድርድር ገጥሞናል ማለት ነዋ?
- አዎ።
- ጥሩ ነው፡፡
- እንዴት?
- እነሱ እስኪስማሙ እኛ ፈትተን እንጠብቃቸዋለን።
- ምኑን ፈትተን?
- የውስጥ ችግራችንን!