የአፍሪካ ሕብረት በፌደራል መንግስትና በህወሃት መካከል የሰላም ንግግር እንዲጀመር ቀንና ስፍራ ቆርጦ ያቀረበውን ጥሪ፣ የፌደራል መንግስት መቀበሉን የሰላም ኮሚቴው አባል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን አስታወቁ፡፡
ሕብረቱ ያቀረበው ጥሪ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ጦርነቱን በሰላም ለማጠናቀቅና ያለቅድመ ሁኔታ ንግግር ለመጀመር ከያዘው መርህ ጋር የሚጣጣም እንደሆነ አምባሳደር ሬድዋን በቲውተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን በበኩሉ ዛሬ ባወጣው መግለጫ መንግስት ንግግሩ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ብቻ እንዲሆንና ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲደረግ አቋሙን ሲገልጽ መቆየቱን አስታውሶ፣ የአፍሪካ ህብረት ያቀረበው ኦፊሴላዊ ጥሪ ይሄንን አቋም የጠበቀ ሆኖ እንዳገኘው አስታውቋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ለኢትዮጵያ መንግስትና ለሕወሓት የላከው የጥሪ ደብዳቤ፣ የሰላም ንግግሩን የፊታችን እአአ ኦክቶበር 8 ቀን 2022(መስከረም 28 ቀን 2015 ዓም) በደቡብ አፍሪካ ለማካሄድ ቀን እንደተቆረጠ ያስረዳል፡፡ ሁለቱ አካላት በሚጀምሩት ንግግር የድርድሩን አካሄድና ድርድር ሚደረግባቸውን አጀንዳዎች እንዲሁም የንግግሩን ቅርፅና የጊዜ ሰሌዳ ይወሰንበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ህብረቱ በደብዳቤው ላይ አስፍሯል፡፡
በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የሚደረገው ንግግር ሁለቱ አካላት የሚያደርጉት ድርድር ቅርፅን ለመሰወሰንና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ መሰረት እንደሚጥልም ተጠቅሷል፡፡
የህብረቱ ደብዳቤ እንደሚገልጸው ንግግር የሚመቻቸው በአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ነው፡፡
በተጨማሪም በቅርቡ ከስልጣናቸው የወረዱት የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እንዲሁም የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንትና በአሁኑ ወቅት የሕብረቱ የሰላምና ደህንነት ምክር ቤት አማካሪ (ፓነል ኦፍ ዘ ዋይዝ) አባል የሆኑት ፉምዙሌ መላምቦ ንጉካ አወያይ በመሆን የንግግር ሂደቱን ለማካሄድ እገዛ እንደሚያደርጉ ደብዳቤው አስታውቋል፡፡