Sunday, May 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በቅጣት ምክንያት የተሽከርካሪዎችን ሰሌዳ የመፍታት ዕርምጃ እንዲቆም ጥያቄ ቀረበ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሜትር ታክሲ ዘርፍ ለሚሰማሩ ይሰጥ የነበረው ከቀረጽ ነፃ ዕድል ቀሪ ተደረገ

የትራፊክ ደንብ በተላለፉ አሽከርካሪዎች ላይ ለቅጣት በሚል ምክንያት የተሽከርካሪዎችን ሰሌዳን የመፍታት ዕርምጃ ሕግን ካለማስከበሩ ባሻገር፣ ለአገር ሀብት ብክነት ምክንያት በመሆኑ ዕርምጃው ሊጤንና ሊቆም እንደሚገባ ጥያቄ ቀረበ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ደኅንነት ምክር ቤት የተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸሙን አስመልክቶ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ከተነሱ አስተያየቶች መካከል፣ ከሰሌዳ መፈታት ጋር በተገናኘ የተነሳው ይጠቀሳል፡፡

የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን መንግሥቱ ሰጡት አስተያየት የትራፊክ ደንብ ተቆጣጣሪ አካልም ሆነ የትራፊክ ፖሊሶች ሰሌዳዎችን በመፍታት ሪፖርት የሚያደርጉበት አሠራር፣ በትራፊክ ማኔጅመንትም ሆነ በአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ባለሙያዎች የሚወሰዱት ተመሳሳይ ዕርምጃዎች ተገቢ አይደሉም ብለዋል፡፡

ሰሌዳ ከተሽከርካሪዎች ላይ የሚፈታበት መንገድ ሥርዓት የለውም ያሉት አቶ መስፍን፣ አድራሻ ለመያዝ ብቻ ተብለው ተቆርጠው የሚወጡ ሰሌዳዎች በርካታ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የሰሌዳ ከተሽከርካሪዎች ላይ መፈታት ሕግን ካለማስከበሩም በተጨማሪ፣ ለሌላ አደጋ ስለሚዳርግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ መፍትሔ ሊያበጁለት ይገባል ብለዋል፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ ከተሽከርካሪ አካል ላይ ምንም ዓይነት ክፍል መፈታት የለበትም፡፡ የደንብ ጥሰት የፈጸመ አካል አድራሻው ስለሚታወቅ አስተማሪና ከፍተኛ ቅጣት መቅጣት ተገቢ መሆኑን አስረድዋል፡፡

አገሪቱ በተጠናቀቀው ዓመት በግብዓት እጥረት ሳቢያ ሰሌዳ ለማምረት ተቸግራ መቆየቷን በማስታወስ፣ በተለይ ጉዳዩን አስመልክቶ ከሕግ አንፃር የተቀመጠ ነገር ካለም አጣጥሞ መሄድ እንደሚገባ በውይይቱ ላይ ተገልጿል፡፡

ሰሌዳው ተፈቶ አደጋ ያደረሰ ተሽከርካሪ በቁጥጥር ሥር የሚውልበት ሁኔታ አስቸጋሪነቱን በመግለጽ፣ ሰሌዳ የሚወገድበትን አግባብ መሠረት አድርጎ ሌላ በመጠየቅ ምርቱን ዳግም ማግኘት የሚቻልበትም መንገድ ሳይረሳ፣ በጉዳዩ ላያ ሰፋ ያለ ጥናት ተደርጎ ተገቢውን ዕርምጃ መውሰድ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን በመድረኩ ተመላክቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ በማጠቃለያ ላይ እንደተናገሩት፣ የትራንስፖርት ሥርዓቱን ለማዘመንና የመንገድ ደኅንነት ለማስተካከል ሦስት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል፡፡ አንደኛው የተሽከርካሪ ሥርዓቱን ማዘመን ሲሆን፣ ተሽከርካሪዎች ከግዥ ሥርዓት ጀምሮ ሰሌዳ እስከሚያወጡበት ያለውን ሥርዓት ዘመናዊ ማድረግን ይመለከታል፡፡

ሁለተኛው ከአሽከርከሪ ጋር በተያያዘ ሲሆን፣ የመንጃ ፈቃድ ማውጣት ሒደቱ ምን ይመስላል የሚለው ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ሦስተኛው ቅጣትን የሚመለከት ሲሆን አንድ ቦታ የተቀጣ ሰው ሌላ ቦታ ሄዶ የሚወጣበትን አሠራርና የመሳሰሉ ጉዳዮችን የሚያስቀር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ በከተማዋ በሜትር ታክሲ ዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ ግለሰቦችና ማኅበራት የቀረጥ ነጻ ድጋፍ ማቆሙን ታውቋል።

ቢሮው ከዚህ ቀደም በሜትር ታክሲ አገልግሎት ዘርፍ ለመሰማራት ጥያቄ ሲያቀርቡ ለነበሩ ማኅበራትና ግለሰቦች ተሽከርካሪዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ ለገንዘብ ሚኒስቴር የድጋፍ ደብዳቤ ሲጽፍ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ነገር ግን በዚህ ወቅት በከተማ ያለው የሜትር ታክሲ ተሽከርካሪዎች ቁጥር በቂ ሆኖ በማግኘቱ፣ የቀረጥ ነፃ ድጋፍ መስጠት ስለማቆሙ የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል ተብሏል።

የቀረጥ ነፃ መብት ሳይጠይቅ ተሽከርካሪዎችን በማስገባት በሜትር ታክሲ ዘርፍ መሰማራት የሚፈልግ ማንኛውም አካል ፈቃድ ማግኘት እንደሚችል ተገልጾ፣ በብዙኃን ትራንስፖርት ዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ ግለሰቦችና ማኅበራት ግን የቀረጥ ነፃ መብት እንዲያገኙ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች