Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሰብል ምርት ላኪዎች በአዲሱ የምርት ግብይት አፈጻጸም መመርያ ላይ ቅሬታ አሰሙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማኅበር፣ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የወጣው በውልና በኢንቨስትመንት እርሻ የተመረቱ ምርቶች ግብይት መመርያ አሠራሩን ‹‹የሚያከብድ ነው›› የሚል ቅሬታ አቀረበ፡፡

ኢንቨስተሮች በአዲሱ መመርያ የተጣሉባቸው ግዴታዎች፣ ላኪዎች ከአርሶ አደሮች ጋር ያላቸውን ግንኙነትና በገጠሩ ክፍል ያለውን ሁኔታ አላገናዘበም ሲል ትችቱን አቅርቧል፡፡ የማኅበሩ አመራሮች ረቡዕ መስከረም 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በነበራቸው ውይይት ላይ ይኼንን ሐሳብ ማንጸባረቃቸውን የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤዳዎ አብዲ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት መስከረም 19 ቀን 2015 ዓ.ም. የጸደቀው ይኼ መመርያ፣ ኢንቨስተሮች በኮንትራት እርሻ ምርት ለማስመረት የሚገቡት ውል ሰነድን ለማረጋገጥ በሕግ ሥልጣን በተሰጠው አካል የተረጋገጠ መሆን እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ በፌዴራል ደረጃ ይኼንን አግልገሎት የሚሰጠው የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ሲሆን በክልሎች በፍትህ ቢሮዎች ሊሰጥ ይችላል፡፡

በተጨማሪም መመርያው ኢንቨስትሮች በውል እርሻ ያስመረቱትን ምርት ግብይት ሲፈጽሙ ክፍያውን በባንክ መፈጸም እንዳለባቸው አስቀምጧል፡፡

አቶ ኤዳዎ፣ ማኅበራቸው ምርት በሚመረትበት የገጠሩ ክፍል ሁለቱንም ግዴታዎች ለመፈጸም የሚያስችል ሁኔታ አለ ብሎ እንደማያምን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ውል የማረጋገጡን ሥራ የሚሠሩት ተቋማት ያሉት ከተሞች ላይ ነው›› ያሉት አቶ ኤዳዎ፣ ገበሬውን ወደ ውልና ማስረጃ ለማጓጓዝ ፍቃደኝነቱን ማግኘት ምን ያህል ‹‹ከባድ ሥራ›› ነው የሚል ሐሳብ አንስተዋል፡፡ በአገሪቱ ያለው የባንክ ተደራሽነትና አርሶ አደሩ ጋር ያለው ባንክ ተጠቃሚነት ልምድ ማነስ የግብይት ሥርዓቱ ላይ ‹‹ተጨማሪ ጫና›› ይፈጥራል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም አዲሱ መመርያ ያመረቱትን ምርት በአካባቢው በሚገኝ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የምርት መረከቢያ ማዕከል በማስመዘንና በማረጋገጥ መረጃ እንዲያቀርቡ የሚያዝ ነው፡፡

ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ኤዳዎ፣ አብዛኛው ላኪ በመንግሥት የሥነ-ልኬት ባለሙያ የተረጋገጠ ሚዛን እያላቸው፣ ተደራሽነት በሌለው የምርት ገበያ ሚዛን ብቻ እንዲመዘን መደረጉ አግባብነት የለውም የሚል ቅሬታ አንስተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የሚዛን ብዛት በቅርንጫፎቹ ቁጥር 25 መሆናቸውን በመጥቀስም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ኢንቨስተሮች አመቺ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በመመርያው ላይ ይኼንን ግዴታ ያስቀመጠው፣ የሚንቀሳቀሱ ምርቶችን ትክክለኛ መጠን ለማወቅና ይኼንም ለማረጋገጥ ነው፡፡ ለዚህም ሲል ሁሉም ኢንቨስተሮች ምርታቸውን የመንግሥት ተቋም በሆነው ምርት ገበያ ማስመዘን እንዳለባቸው አስቀምጧል፡፡

ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር ባለሀብቶች በራሳቸው ሚዛንና ይኼንን አገልግሎት በሚሰጡ የግል ባለሚዛኖች ያስመዝኑ እንደነበር የገለጹ ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ከቀበሌ ጀምሮ ያሉ የንግድና የግብርና ቢሮዎች ደግሞ በአካባቢው በአንድ ሔክታር ምን ያህል ምርት እንደሚመረት ካስቀመጡት የባለሙያ ግምት ጋር በማስተያየት ማረጋገጫ እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ኤዳዎ ገለጻ፣ የሚዛን አገልግሎት በምርት ገበያ በኩል ግዴታ በመሆኑ ላኪዎች ለማስመዘን ብቻ ሳምንት ለሚደርስ ጊዜ ወረፋ ለመጠበቅ እንደሚገደዱ አስረድተዋል፡፡ ምርቱን ለኢንቨስተሮች የሚያጓጉዙ የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢዎችም፣ ምርት ጭነው ለሳምንት መቆም ስለማይፈልጉ የምርት ማጓጓዝ ሒደቱ ይጎዳል የሚል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ነጻነት ተስፋዬ፣ ተቋማቸው ኢንቨስተሮች እንዲህ ዓይነት ችግር ያጋጥማቸዋል የሚል ሥጋት እንደሌለው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከሁመራና ሽራሮ ውጪ ያሉት 23 ቅርንጫፎች በሙሉ በሥራ ላይ እንደሚገኙና በመብራት መጥፋት ምክንያት ካልሆነ የሚዛን አገልግሎታቸው እንደማይስተጓጎል አስረድተዋል፡፡

የምርት መሰብሰቢያ ጊዜ ምርት ስለሚበዛ ወረፋ መጠበቅ ሊኖርባቸው እንደሚችል የጠቀሱት አቶ ነጻነት፣ ‹‹ይኼም ቢሆን ተደውሎ መኪናቸው የሚመጣበት ቀን ስለሚነገራቸው ችግር አይፈጥረም፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች