Wednesday, February 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሳፋሪኮም 5ጂ ለማስጀመር ቢያንስ እስከ ሦስት ዓመት እንደሚጠብቅ አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮ ቴሌኮም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በሁለተኛ ከተማ 5ጂ ሊያስጀምር ነው

አዲስ አበባን አሥራ አንደኛ ከተማ አድርጎ በአገር አቀፍ ደረጃ ሥራ መጀመሩን ይፋ ያደረገው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፣ የ5ጂ አገልግሎት ለማስጀመር ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት ጊዜ እንደሚጠብቅ አስታወቀ፡፡

ኩባንያው አልግሎት በጀመረባቸው አካባቢዎች እስካሁን ያቀረበው 4ጂ ድረስ ያለውን የኢንተርኔት አገልግሎት ሲሆን፣ የ5ጂ አገልግሎት ለማስጀመር የሚያስችለውን ስፔክትረም ምደባ ለማግኘት ለኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ጥያቄ ማቅረቡ ተሰምቷል፡፡ ባለሥልጣኑ፣ ሳፋሪኮም ያቀረበውን የምደባ ጥያቄ በማየት ላይ እንደሚገኝና ማብራሪያ የሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ ማቅረቡን ገልጿል፡፡

ሳፋሪኮም አዲስ አበባን ጨምሮ አገልግሎት ባስጀመረባቸው አካባቢዎች የዘረጋው ሥርዓት 5ጂን ማስጠቀም እንደሚያስችል ቢያስታውቅም፣ አገልግሎቱን ያስጀመረው በ4ጂ የኢንተርኔት አገልግሎት ነው፡፡

እንደ ኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንዋር ሶሳ ገለጻ፣ ሳፋሪኮም 5ጂ የሚያስጀምርበት ጊዜ የሚወሰነው በአገሪቱ ውስጥ ምን ያህል 5ጂ የሚያስጠቅሙ መሣሪያዎች (Device) አሉ በሚለው ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ 5ጂ የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ለዚህም ሲባል 5ጂ የሚያስጠቅሙ መሣሪያዎች በብዛት እስከሚገኝ ድረስ እንደሚጠብቅ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም. የ5ጂ የሞባይል ቴክኖሎጂ በቅድመ ሙከራ በአዲስ አበባ መጀመሩን ይፋ ባደረገበት ጊዜ፣ በኔትወርኩ ካሉት አጠቃላይ ደንበኞች 110 ሺሕ ያህሉ አገልግሎቱን መጠቀም የሚችሉበት የሞባይል ቀፎ ባለቤት እንደሆኑ አስታውቆ ነበር፡፡

ሳፋሪኮም 5ጂ የሚያስጠቅሙ መሣሪያዎች ብዛት ስንት እስከሚሆን እንደሚጠብቅ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ትክክለኛውን ቁጥር መናገር እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡ ጊዜውን በተመለከተ ግን አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት “ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት” እንደሚጠብቅ ተናግረዋል፡፡

‹‹እናስጀምረው ብለን እስካልወሰንን ድረስ ከሁለት ዓመት በፊት ባለ ጊዜ ውስጥ 5ጂ አንጀምርም፡፡ የተጠቃሚዎች ቁጥር አነስተኛ ስለሆነ ነው 5ጂ ማስጀመር ላይ ትኩረት ያላደረግነው፤›› ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የ5ጂ አገልግሎት ለማስጀመር የስፔክትረም ምደባ ማግኘት እንደሚኖርበትና ይህንንም ለማግኘት ንግግር ማድረግ እንደሚጠበቅበት፣ ኩባንያው በአዲስ አበባ አገልግሎት ማስጀመሩን ለማስታወቅ ሐሙስ መስከረም 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ባደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ (ዶ/ር)፣ ሳፋሪኮም የስፔክትረም ምደባ ለማግኘት ጥያቄ ማቅረቡን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ለኢትዮ ቴሌኮም የ5ጂ ሙከራ የስፔክትረም ምደባ ማድረጉን ያስታወሱት ባልቻ (ዶ/ር)፣ ‹‹ማሟላት የሚጠበቅባቸው ነገሮች ይታያሉ፣ ያቀረቡት መጠይቅ ላይም ማብራሪያ የተጠየቀባቸው ጉዳዮች አሉ፣ እነሱን እንዳሟሉ ምደባው ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡

 በቅድሚያ የሚሰጠው ምደባ የሙከራ መሆኑንና ይህም በጊዜ የተገደበና ክፍያ የማይጠየቅበት ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮምም ሆነ ሳፋሪኮም ትርፍ ማግኘት ባልጀመሩበት ሁኔታ ለ5ጂ ስፔክትረም ምደባ ክፍያ እንደማያስከፍል ገልጸው፣ የሙከራው ጊዜ አልቆ መደበኛው ምደባ ሲደረግ ክፍያም እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡

ከሳፋሪኮም ጋር በሚደረገው ንግግርም በየትኛዎቹ ከተሞች የሙከራ ሥርጭት ማስጀመር እንደሚፈለግ፣ የሙከራ ጊዜው ለስንት ጊዜ ይቆያል የሚሉትና ሌሎች ጉዳዮች ላይ መግባባት እንደሚደረስ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ባለፈው ዓመት የ5ጂ ስፔክትረም ምደባ የተደረገለት ለአንድ ዓመት የሙከራ ጊዜ እንደሆነና የሙከራ ምደባው የተሰጠውም በአዲስ አበባ፣ በአዳማና በሐዋሳ ከተሞች ሙከራ እንዲያደርግ መሆኑን ባልቻ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ መሳይ መኮንን፣ በአገሪቱ 5ጂ የሚጠቀሙ መሣሪያዎች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም በራሱ የስልክ ቀፎዎችና ሌሎች 5ጂ የሚጠቀሙ መሣሪያዎችን በማስመጣት የተጠቃሚዎችን ቁጥር ለመጨመር እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ዓላማችን 5ጂ የሚያስጠቅሙ መሣሪያዎችን (ዲቫይሶችን) ማስመጣት የሚችሉ ተቋማትን ማነሳሳት ነው፤›› ያሉት አቶ መሳይ፣ ኩባንያው የ5ጂ አገልግሎትን በተመለከተ መንቀሳቀስ የሚፈልገው ከመደበኛ ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ይልቅ በተለያዩ ዘርፎች ያሉ ተቋማት እንዲጠቀሙ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የትራፊክ ማኔጅመንትና የማዕድን ዘርፎችን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

አቶ መሳይ ኩብንያው ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ የጀመረውን የ5ጂ አገልግሎት በሌላ ሁለተኛ ከተማ እንደሚያስጀምር ገልጸዋል፡፡ አገልግሎቱ የሚጀመርበትን ከተማ ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ የ5ጂ አገልግሎትን ያስጀመረው የ5ጂ ዞን ናቸው ባላቸው እንደ ወዳጅነትና አንድነት ፓርኮች፣ ሸራተን ሆቴል አካባቢ፣ ቸርችል ጎዳናና የኩባንያው ዋና መሥሪያ ቤት አካባቢዎች ነው፡፡

በወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ከሚመራው ኢትዮ ቴሌኮም ጋር ውድድር ያደርጋል ትበሎ የሚጠበቀው ሳፋሪኮም፣ አገልግሎቶቹን ከኢትዮ ቴሌኮም ባነሰ ዋጋ በማቅረብ የዋጋ ፉክክር ውስጥ እንደማይገባ አስታውቋል፡፡ ይሁንና በተለይ የኢንተርኔት አገልግሎቱን “በላቀ” ጥራት ደረጃ በማቅረብ ደንበኞችን ለመሳብ ማቀዱን አስታውቋል፡፡

ኩባንያው በኢትዮ ቴሌኮም የሚቀርቡ የአገልግሎት ዓይነቶችን በሙሉ ለደንበኞች እንደሚያቀርብ ቢያስታውቅም፣ ቢያንስ እስከሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ድረስ ያልተገደበ የኢንተርኔት አገልግሎት እንደማያቀርብ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አንዋር ሶሳ ተናግረዋል፡፡

ያልተገደበ የኢንተርኔት አገልግሎት ማቅረብ በኢንተርኔት መስመሩ ላይ ጫና በመፍጠር የአገልግሎቱን ፍጥነት እንደሚቀንስ ያስረዱት አንዋር፣ “ለጥቂት ተጠቃሚዎች” ሲባል ሁሉም ተጠቃሚዎች ላይ ተፅዕኖ እንዲፈጠር ማድረግ ተገቢ ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

የድሬዳዋ ከተማን የማስጀመሪያ አገልግሎት መስጫው ያደረገው ሳፋሪኮም አገልግሎቱን በአገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አባባ ይፋ ከማድረጉ በፊት በ11 ከተሞች ላይ አገልግሎቱን አስጀምሯል፡፡ እስከ ሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥም በተጨማሪ 14 ከተሞች አገልሎቱን ለማስጀመር አቅዷል፡፡

ኩባንያው ሐሙስ መስከረም 26 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሥራ ከማስጀመሩ በፊት፣ በሌሎቹ ከተሞች የተጠቃሚዎቹ ቁጥር 200 ሺሕ እንደደረሱ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች