Monday, January 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲመረምር የተቋቋመው የባለሙያዎች ኮሚሽን የሥራ ጊዜ ተራዘመ

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲመረምር የተቋቋመው የባለሙያዎች ኮሚሽን የሥራ ጊዜ ተራዘመ

ቀን:

ኢትዮጵያ ውሳኔውን እንደማትቀበል አስታውቃለች

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት፣ ከሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲመረምር ላቋቋመው የባለሙያዎች ኮሚሽን የፈቀደውን የሥራ ዘመን፣ ለተጨማሪ አንድ ዓመት የሚያራዝም ውሳኔ አሳለፈ።

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ባለፈው ዓርብ መስከረም 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው 51ኛው ስብሰባ ከተመለከታቸው ጉዳዮች መካከል፣ የሥራ ዘመኑ የተገባደደውን በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር የተቋቋመው የባለሙያዎች ኮሚሽን የሥራ ዘመን ለማራዘም የቀረበውን ጥያቄ መርምሮ መወሰን፣ እንዲሁም ከሰሜን ኢትዮጵያ ገጭት ጋር የተያያዙ ጥስቶችን የተመለከተ የውሳኔ ሐሳብ ማሳለፍ ነበር። 

በዚህም መሠረት ከሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ጋር ተያይዥነት ያላቸውን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ የተመለከተ ውሳኔ ሐሳብ ያጸደቀ ሲሆን፣ ባጸደቀው የውሳኔ ሐሳብም በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር የተቋቋመው የባለሙያዎች ኮሚሽን የሥራ ዘመን ለአንድ ዓመት እንዲራዘም ፈቅዷል። 

ምክር ቤቱ ላሳለፈው የውሳኔ ሐሳብ መነሻ የሆኑት ጉዳዮች የተዘረዘሩ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል እ.ኤ.አ. በኅዳር 3 ቀን 2021 የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤትና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የጋራ ምርመራ ሪፖርት፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል ተፈጽመዋል የተባሉ በርካታ ጥሰቶችና የመብት ጥሰቶች ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያስፈልግ የጠቆመ መሆኑ ይገኝበታል። 

እንዲሁም እ.ኤ.አ. ኅዳር 3 ቀን 2020 እና ሰኔ 28 ቀን 2021 እና ከባድ የሆኑ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ዓለም አቀፍ የስደተኞች ሕግ ጥሰቶች አሁንም በኢትዮጵያ ውስጥ አፋርን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች እየተፈጸሙ እንደሚገኙ ከግምት በማስገባት እንደሆነ ይገልጻል።

በተጨማሪም ቀደም ሲል የተካሄደው የጋራ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምርመራና በቅርቡ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን የምርመራ ከባድና አሳሳቢ ግኝቶችን አመላክቶ የበለጠ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሄድ የሚጠይቅ መሆኑን ግንዛቤ በመውሰድ እንደሆነ የውሳኔ ሐሳቡ ያመለክታል።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን በኢትዮጵያ ሥራውን ለማከናወን በጀትና የሰው ኃይል አቅርቦት ላይ የገጠመው ውሱንነት ተልዕኮውን ሙሉ በሙሉ የመወጣት አቅሙን በእጅጉ የገደበው መሆኑን በማጤንና ኮሚሽኑ የተቋቋመው በጋራ መርማሪ ቡድኑ የተከናወኑ ተግባራትን ለማሟላትና ቀጣይ የተጠያቂነት ሒደቶችን ለማረጋገጥ መሆኑን ከግንዛቤ በመውሰድ እንደሆነ የኮሚሽኑ የሥራ ጊዜ ለአንድ ዓመት እንዲራዘም መወሰኑን ይገልጻል።

በዚህም መሠረት ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን በኢትዮጵያ በተጨማሪ ጊዜው የሚደርስበትን ውጤት ለተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት 52ኛ ስብሰባ የቃል ገለጻ እንዲያቀርብና በሪፖርቱ ላይም በበይነ መረብ አማካይነት ውይይት እንዲደረግ ወስኗል። በማከለም ኮሚሽኑ ለተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት 54ኛ ስብሰባ የጽሑፍ ሪፖርት እንዲያቀርብና ውይይት እንዲደረግ፣ እንዲሁም በ78ኛው የምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ውይይት እንዲካሄድ ወስኗል። በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ጉዳይ ለሚቀጥለው አንድ ዓመት የምክር ቤቱ አጀንዳ ሆኖ እንደሚቆይ በተላለፈው የውሳኔ ሐሳብ ተገልጿል።

ሁሉም በግጭቱ ተሳታፊ አካላት በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽንና ለአባላቶቹ ያለምንም እንቅፋት ተልዕኳቸውን እንዲወጡ፣ ያለ ገደብ ቦታዎችን እንዲጎበኙና የፈለጉትን በነፃና በግል አግኝቸው እንዲነጋገሩ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን የውሳኔ ሐሳብ ምክር ቤቱ ከማሳለፉ አስቀድሞ ለምክር ቤቱ የቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ውድቅ እንደሚያደርግ በይፋ አሳውቋል።

በቤልጂየም ብራሰልስ የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ አምባሳደር ዘነበ ከበደ ለምክር ቤቱ በጻፉት ደብዳቤ፣ በአውሮፓ ኅብረት ተዘጋጅቶ የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ የኢትዮጵያ መንግሥት የተፈጸሙ ጥሰቶች ተቀብሎ በማጣራት ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ዕርምጃዎችን በሚወስድበት ጊዜ የመጣና በኢትዮጵያ መንግሥት፣ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር የተሸረበ የፖለቲካ ሴራ በመሆኑ ተቀባይነት እንደማይኖረው አስታውቀዋል።

የአፍሪካ ኅብረት የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭትን በሰላም ለመፍታት ሁለቱንም ወገኖች በአሁኑ ወቅት ለድርድር ጋብዞ ባለበትና የኢትዮጵያ መንግሥትም ድርድሩን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተቀበለ መሆኑን አስታውሰው፣ የኢትዮጵያ ወዳጅ አገሮች ትኩረት መሆን ያለበት የሰላም ድርድሩንና መንግሥት ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ጥረቶች በደጋፊነት መርህ ማገዝ ነው ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...