Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በፍራንኮ ቫሉታ ለሚገቡ ዕቃዎች የውጭ ምንዛሪን ምንጭ ማሳወቅ ግዴታ እንዲሆን ተወሰነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት የተወሰኑ ምርቶች ወደ አገር እንዳይገቡ ክልከላ ሊጥል ነው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በፍራንኮ ቫሉታ አማካይነት ዕቃዎችን ወደ አገር የሚያስገቡ ግለሰቦች፣ የሚጠቀሙበት የውጭ ምንዛሪ የራሳቸው ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ የባንክ ስቴትመንት እንዲያቀርቡ የሚያስገድደውን አሠራር እንደገና መጀመሩን አስታወቀ፡፡

ብሔራዊ ባንክ ይህንን ዕርምጃ የወሰደው በፍራንኮ ቫሉታ ዕቃ እናስመጣለን በማለት ከጥቁር ገበያ ዶላር እየገዙ መልሰው በማስወጣት እየሠሩ ያሉ መኖራቸውን ማረጋገጥ በመቻሉ እንደሆነ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪው የራሳቸው መሆኑን ማረጋገጥ ሳያስፈልገው ዕቃዎችን በፍራንኮ ቫሉታ እንዲያስገቡ የሚፈቅደው አሠራር ችግር ያለበት መሆኑን በማረጋገጡ፣ ከዚህ በኋላ እንደ ቀድሞው በፍራንኮ ቫሉታ ለሚገቡ ዕቃዎች ግዥ የሚውለው የውጭ ምንዛሪ ላይ ማጣራት ይደረጋል ብለዋል፡፡

‹‹በመሆኑም የጥቁር ገበያ ምንዛሪን ለመቆጣጠር ብሔራዊ ባንክ በፍራንኮ ቫሉታ ተጠቃሚዎች ላይ ያደርግ የነበረውን ቁጥጥር እንደገና ይጀምራል፤›› ያሉት ገዥው፣ ከዚያ በኋላ ፍራንኮ ቫሉታ ተጠቅመው ለሚያስገቡት ዕቃ መግዣ የሚያውሉት የውጭ ምንዛሪ የራሳቸው ስለመሆኑ፣ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪው በሚታወቅ ባንክ የተቀመጠ መሆን አለመሆኑ ይጣራል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ዕቃ የሚያስመጡበት ዶላር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የጥቁር ገበያ ጋር የተያያዘ አለመሆኑም ይጣራል ተብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ብሔራዊ ባንክ በፍራንኮ ቫሉታ ለሚገቡ ዕቃዎች የሚውለው የውጭ ምንዛሪ፣ በትክክል ዕቃዎቹን ያስመጡ ግለሰቦች በውጭ ባንክ አካውንታቸው ውስጥ መኖር አለመኖሩን ያረጋግጥ ነበር፡፡ ገንዘቡ ከጥቁር ገበያው ጋር የተያያዘ አለመሆኑን በማረጋገጥ ዕቃውን ማስገባት እንደሚችሉ፣ ብሔራዊ ባንክ ለጉምሩክ ኮሚሽን በመጻፍ ይከናወን እንደነበርም ይናገር (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ይህ አሠራር ተመልሶ ሥራ ላይ እንዲውል መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡

ይህ አሠራር ተቋርጦ የነበረው ብሔራዊ ባንክ የሚጠይቀው የባንክ ስቴትመንት ትንሽ የቢሮክራሲ ይዘትና ባህሪ የያዘ ነው በሚል ይቅር ተብሎ እንደነበር የገለጹት ገዥው፣ አሁን ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ዶላር በጥቁር ገበያ እየገዙ በሕገወጥ መንገድ የሚሠሩ መኖራቸው በመረጋገጡ፣ ወደ ቀድሞው አሠራር መመለስ አስፈላጊ እንደሆነ ታምኖበት በሥራ ላይ እንዲውል ይደረጋል ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዋጋ ንረቱንና ሕገወጥ የውጭ ምንዛሪ ዝውውርን ለመከላከል፣ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪን በአግባቡ ለመጠቀም ሲባል፣ ብሔራዊ ባንክ የተለያዩ ዕርምጃዎችን እንደሚወስድ ተገልጿል፡፡ በተለይ ከውጭ ወደ አገር የሚገቡ አንዳንድ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ የሚወስን መመርያ በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚሆን ይናገር (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓመት ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው በርካታ ምርቶች ከውጭ የምታስገባ መሆኑን ያስታወሱት ገዥው፣ እነዚህ ምርቶች መግባታቸው ጥሩ ቢሆንም አሁን ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ከአስፈላጊነታቸው አንፃር ታይቶ፣ አንዳንድ ምርቶችን ከውጭ እንዳይገቡ ክልከላ ይደረግባቸዋል ብለዋል፡፡ ምርቶቹም በቅርቡ በሚወጣ መመርያ በዝርዝር የሚቀርቡ መሆናቸውን፣ በዚህ መሠረት አንዳንድ ምርቶች ላልተወሰነ ጊዜ እንዳይገቡ ክልከላ እንደሚጣልባቸው አስረድተዋል፡፡

ከአስፈላጊነታቸው አንፃር ተመዝነው ክልከላ ይደረግባቸዋል የተባሉ ምርቶች ባይገለጹም፣ የትኞቹ ምርቶች በዚህ መመርያ ውስጥ እንደሚካተቱ በቅርቡ ይታወቃል ተብሏል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች