Tuesday, April 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የውጭ ባንኮች እንዲገቡ የሚፈቅደው ረቂቅ አዋጅ ማሻሻያ ተጠናቀቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ለውጭ ተወዳዳሪዎች ክፍት እንዲሆን ከተወሰነ በኋላ፣ በ2009 ዓ.ም. የወጣው የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅ ማሻሻያ ተጠናቆ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀርብ ነው፡፡  

ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀርብ ዝግጁ የሆነው ረቂቅ አዋጅ፣ በጥቂት ወራት ውስጥ ለፓርላማ ቀርቦ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሪፖርተር ያገኘው ረቂቅ አዋጅ እንደሚያመለክተው፣ አብዛኛው ለውጥ የተደረገው ባለፈው ወር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ካፀደቀው የባንኮች ለውጭ መከፈት ከፖሊሲ ጋር ለማጣጣም ነው፡፡ የውጭ ባንኮች እንዴት ወደ ኢትዮጵያ ገብተው መሥራት እንደሚችሉ ረቂቅ አዋጁ በዝርዝር ይደነግጋል፡፡

የውጭ ባንኮች እንዲገቡ አራት ተደጓሚ (Subsidiary)፣ ቅርንጫፍ (Branch)፣ የውክልና ቢሮ (Representative Office) እና በሥራ ላይ በሚገኙ የአገር ውስጥ ባንኮች ውስጥ አክሲዮን መግዛት አማራጭ ሆነው ቀርበዋል፡፡ የውጭ ባንኮች ከአራቱ አንዱን አማራጭ ወይም ሁሉንም መጠቀም ይችላሉ ተብሏል፡፡

አንድ የውጭ ባንክ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ባንኮች ውስጥ አክሲዮን መግዛት ከፈለገ የሚፈቀድለት እስከ 30 በመቶ ብቻ ነው፡፡ የውጭ ዜጋና ባንክ ያልሆነ የውጭ ድርጅትም እያንዳንዳቸው አምስት በመቶ የአገር ውስጥ ባንክ አክሲዮን መግዛት ይችላሉ፡፡ ይህ ማለት አንድ የአገር ውስጥ ባንክ ለውጭ ዜጋ፣ ለውጭ ባንክና ድርጅት መሸጥ የሚችለው ጠቅላላ አክሲዮን ከ40 በመቶ መብለጥ የለበትም፡፡ ቀመሩ የአገር ውስጥ ባንኮች በውጭ ሰዎች እንዳይዋጡና የአገር ውስጥ ባለአክሲዮኖች ዋነኛ ባለድርሻ ሆነው እንዲቀጥሉ ያስችላል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ምንም እንኳ እንደ አዋሽና ዳሸን የመሳሰሉ ጠንካራ የሚባሉ ባንኮች አክሲዮናቸውን ለነባር ባለአክሲዮኖች ብቻ የመሸጥ አዝማሚያ ያላቸው ቢሆንም፣ ቶሎ ለማደግ የሚውተረተሩ የ‹‹ሦስተኛ ትውልድ ባንኮች›› ግን ቀመሩን ለመጠቀም አያመነቱም ተብሎ ይጠበቃል፡፡

‹‹ረቂቅ አዋጁ የውጭ ባንኮች ከአገር ውስጥ ባንኮች አክሲዮን እንዲገዙ ፈቅዷል፡፡ ነገር ግን እንደ አዋሽና ዳሸን ያሉት አቅም ያላቸው ባንኮች ከትንንሾቹ ባንኮች ድርሻ እንዲገዙ አልፈቀደም፤›› ሲሉ በእንግሊዝ አገር ለአሥርት ዓመታት በፋይናንስ ዘርፍ ያገለገሉት አብዱልመናን ሙሐመድ (ዶ/ር) ይተቻሉ፡፡

የውጭ ባንኮች፣ ዜጎችና ድርጅቶች በውጭ ምንዛሪ ብቻ ይዘው እንዲገቡ የሚፈቅድላቸው ሲሆን፣ይህም መንግሥት የባንክ ዘርፉን ቀስ በቀስ እንዲከፈት የወሰነበት ምክንያት አንዱ ነው፡፡ ሌላው የባንክ ሥራ አመራር ልምድ፣ ቴክኖሎጂና ቅልጥፍናን ለማስፈን ታስቦ ነው፡፡ አንዳንድ የዘርፉ ተንታኞች ግን፣ መንግሥት ዘርፉን የሚከፍተው በምዕራባውያን ፍላጎትና በኢኮኖሚ ጫና አጣብቂኝ ውስጥ በመግባቱ ነው ይላሉ፡፡

ባለሙያዎች እንደሚሉት የውጭ ባንኮች ቅርንጫፍ መክፈት አማራጫቸው ከሆነ ግን፣ በአንድ ቅርንጫፍ የቁጠባና የብድር አገልግሎቶችን እንዲሰጡ አይፈቀድላቸውም፡፡ ስለዚህ ለቁጠባና ለብድር አገልግሎቶች የተለያዩ የባንክ ቅርንጫፎች መክፈት ይኖርባቸዋል፡፡ የውጭ ባንክ ቅርንጫፍ ከአገር ውስጥ የሰበሰበውን ቁጠባ መልሶ እያበደረ የሚሠራ ከሆነ፣ እንደ ማንኛውም የንግድ ባንክ ይሆናል ማለት ስለሚሆን፣ ከአገር ውስጥ ተቀማጭ የማይሰበስብ ከሆነ ደግሞ የኢንቨስትመነንት ባንክ ይሆናል ይላሉ፡፡

‹‹የኢንቨስትመንት ባንኮች በውጭ መጥተው ተቀማጭ አይሰበስቡም፡፡ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሚያበድሩትን ገንዘብ ከሌሎች ምንጮች ያገኛሉ፡፡ በእርግጥ የኢንቨስትመንት ባንኮች ብዙ ጊዜ ችግር ያመጣሉ ተብሎ ስለሚታሰብ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፤›› ሲሉ አብዱልመናን (ዶ/ር) ያሳስባሉ፡፡

በውጭ ባንኮች የተያዙ ንብረቶች (Mortgaged Property) ከአምስት ዓመት በላይ የራሳቸው አድርገው ማቆየት አይችሉም ብለው፣ ‹‹የውጭ ባንኮች ሲመጡ ከአምስት ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ሕንፃ እንዳይከራዩ መደረጉ የባለቤትነት ስሜት እንዳያመጣ ለማድረግ የሚጠቅም ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ የሕንፃውን ኢንሹራንስ ወጪ፣ ጥገናና ሌሎች ወጪዎችን የሚሸፍነው አከራዩ ይሆናል፡፡ በውጭ አገሮች እስከ 25 እና 50 ዓመታት ሕንፃ ሲከራዩ እነዚህን ወጪዎች ተከራዩ ወይም ባንኩ ይሽፍናል፡፡ የኢትዮጵያ ባንኮችም ለራሳቸው ጥቅም ካልሆነ ሕንፃዎችን በባለቤትነት መያዝ አይፈቅድላቸውም፡፡ ይህ ብዙ ካፒታል በሕንፃ ግንባታ እንዳይባክን ይረዳል፤›› ይላሉ አብዱልመናን (ዶ/ር)፡፡

የውጭ ባንኮች የሚያገኙን የትርፍ ድርሻ፣ የአክሲዮን ሽያጭ ገንዘብና ማንኛውንም ካፒታል ወደ ውጭ መውሰድ የሚችሉት፣ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ሕግ መሠረት ነው፡፡ የአገር ውስጥ ባንኮች ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚ፣ ከፍተኛ ማኔጅመንት ቦታዎችና የተመረጡ ቦታዎች ላይ የውጭ ዜጎችን ከሦስት ዓመታት ላልበለጠ ጊዜ መቅጠር ይችላሉ፡፡ በሦስት ዓመታት ውስጥ የውጭ ዜጋው የዕውቀት ሽግግር አድርጎ መውጣት ይጠበቅበታል፡፡

ባንኮች ድንበር ዘለል ብድር እንዲሰጡ አይፈቀድም፡፡ ነገር ግን ባንኮች የራሳቸውን ገንዘብ ማስተላለፍና ከውጭ ብድር መውሰድ ይችላሉ፡፡ በ2000 ዓ.ም. የወጣው የባንክ ሥራ አዋጅ መጀመርያ የተሻሻለው በ2011 ዓ.ም. ሲሆን፣ ይህም የወለድ ነፃ ወይም እስላሚክ ባንክን ለመፍቀድ ነበር፡፡ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ግን በ2011 ዓ.ም. የተሻሻለውን አዋጅ ይሸራል፡፡ ስለዚህ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎትን በተመለከተ አዳዲስ አንቀጾች በረቂቁ ውስጥ ተካተዋል፡፡ ረቂቁ አዋጅ የተሻሻለውን የ2012 ዓ.ም. የኢንቨስትመንት ደንብም ሽሯል፡፡ የባንክ አከፋፈት አሠራር የአገር ውስጥ ባንኮችን ላለማጋለጥ ከመጠንቀቁም ባሻገር፣ የሸማቾች መብት ጥበቃንም ከግምት አስገብቷል፡፡ ለዚህም ብሔራዊ ባንክ ከአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት ጋር መግባቢያ ሰነድ እንደሚፈራረም፣ መረጃ እንደሚለዋወጥ፣ የተሳለጠ ሱፐርቪዥንና ውጤታማ የቀውስ ጊዜ አያያዝ እንደሚተገብር ረቂቁ ይገልጻል፡፡

‹‹የውጭ ባንክ ኢትዮጵያ ውስጥ መጥቶ ሲሠራ አፈጻጸሙ በእናት ባንኩ ይወሰናል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የግድ ውጭ ያለውንም እናት ባንክ መቆጠጣጠር መቻል አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ በየጊዜው ከውጭ ብሔራዊ ባንኮች ጋር መረጃ መለዋወጥ አለበት፡፡ ካልሆነ ግን የውጭ ባንኮች ከፍተኛ ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ ጉዳዩ በረቂቅ አዋጁ ላይ መነሳቱ ጥሩ ነው፡፡ ግን ጥያቄው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በተግባር ማሳየት ይችላል ወይ ነው?›› ይላሉ አብዱልመናን (ዶ/ር)፡፡

በርካታ ጉዳዮች ረቂቅ አዋጁ ከፀደቀ በኋላ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣቸው መመርያዎች እንዲወሰኑ በክፍተት ተትተዋል፡፡

ለውጭ ባንኮች ፈቃድ መስጠት የሚጀመረው ተሻሽሎ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ በፀደቀ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚሆን፣ ባለፈው ወር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባፀደቀው ውሳኔ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ በዚህ መሠረት የውጭ ባንኮች እ.ኤ.አ. በ2023 የመግባት ዕድላቸው ሰፊ ይሆናል ማለት ነው፡፡

አዋጁ ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ ባለው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁለት ዋና ዋና ሥራዎች ይጠናቀቃሉ ተብሏል፡፡ የመጀመርያው ብሔራዊ ባንክ ብዛት ያላቸውንና አዋጁን ለማስፈጸም የሚረዱ መመርያዎች ያወጣል፡፡ ሁለተኛው የአገር ውስጥ ባንኮች የዝግጅት ጊዜ ይኖራቸዋል፡፡ ሁሉም የአገር ውስጥ ባንኮች በአንድ ዓመት ውስጥ በብሔራዊ ባንክ የቅርብ ክትትል የመወዳደሪያ ዕቅድና ስትራቴጂ እንዲነድፉ ይገደዳሉ፡፡ ግዴታ የሆነ ውህደት (Mandatory Merger) ሊኖር እንደሚችልም በብሔራዊ ባንክ ተገልጿል፡፡

‹‹ረቂቅ አዋጁ በጥንቃቄ ከተተገበረ ስኬታማ ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ብሔራዊ ባንክ የአገር ውስጥ ባንኮችን እንደሚቆጣጠረው ሁሉ፣ የውጭ ባንኮችንም መቆጣጠር መቻል አለበት፤›› ሲሉ አብዱልመናን (ዶ/ር) ያሳስባሉ፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች