Sunday, February 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትአዲስ የአሠራር መመርያዎችን ያፀደቀው የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን

አዲስ የአሠራር መመርያዎችን ያፀደቀው የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን

ቀን:

  • የዘንድሮን የውድድር መርሐ ግብር ይፋ አድርጓል

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በ2014 ዓ.ም. በሐዋሳ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የፀደቁና የተሻሻሉ መመርያዎች ላይ ግንዛቤን የሚፈጥርና ለተግባራዊነቱም ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

ፌዴሬሽኑ መስከረም 24 ቀን 2015 ዓ.ም. በመድረኩ አቅርቦ የተወያየባቸው አምስት መመርያዎችና ደንቦች ሲሆኑ፣ እነሱም የባለድርሻ አካላት ድጋፍ አሰጣጥ መመርያ፣ የአሠልጣኞች ደረጃ መስጫ ሰነድ፣ የውጭ ጉዞ ሥርዓት፣ የአትሌት ተወካዮችና የማናጀር ፈቃድ እንዲሁም የአትሌቶች የውጭ ጉዞ መመርያ ሰነድ ናቸው።

በተጨማሪም የብሔራዊ ቡድንና የብሔራዊ ቡድን አትሌቶች መምረጫ እንዲሁም አትሌቶች የሚያሠለጥኑ አሠልጣኞች የሚመረጡበት መመርያ የቀረበ ሲሆን፣ የባለድርሻ አካላት የሥነ ምግባር መመርያ ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ እንግዳ ለሪፖርተር አስረድተዋል።

ከአሠልጣኞች ሰነድ ጋር በተያያዘ ከሕፃናት እስከ ብሔራዊ ቡድን ያሉ አሠልጣኞች ሊኖራቸው የሚገባ ደረጃ የተመለከተ ሲሆን የትምህርት ደረጃቸውን፣ ባፈሩት አትሌት በመመልከትና ዓለም አቀፉን ተሞክሮ በመወሰድ ደረጃ እንዲወጣላቸው አቅጣጫ ያስቀመጠ ነው።

በሥነ ምግባር መመርያው መሠረት አሠልጣኝ፣ አትሌት፣ ክለብ፣ ክልል እንዲሁም አመራሩ ሥነ ምግባር ቢያጎድል ምን ዓይነት ዕርምጃዎች ይወስድበታል? የሚለውን በግልጽ የሚያስቀምጥ መመርያ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ስምምነት ላይ ተደርሷል። መመርያው የወጣው ዓለም በአትሌቲክስ ከደረሰበት ደረጃ ጋር ተመጋግቦ እንዲጓዝ ታቅዶ መዘጋጀቱን ኃላፊው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉና የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መስፍን ቸርነት በተገኙበት መድረክ፣ የክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች፣ የማሠልጠኛ ማዕከላት፣ ክለቦች፣ አሠልጣኞች፣ ማናጀሮች፣ የሙያ ማኅበራት ተሳትፈውበታል፡፡

በሌላ በኩል ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ዘንድሮ ከዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች መርሐ ግብር ጋር ተመጋጋቢ የሆኑ የተለያዩ ውድድሮች ለማከናወን፣ እንዲሁም ከዓለም አትሌቲክስ ጋር በመነጋገር  ለአሠልጣኞችና ለዳኞች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለማሰናዳት ማቀዱንም አስታውቋል፡፡

 በተጨማሪም የተለያዩ የአትሌቲክስ ልማቶች ላይ እንደሚሠራና የተጀመሩ የማዘውተሪያ ሥፍራዎች ተጠናቀው ለልምምድና ለውድድር ዝግጁ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግም ማሰቡንም ለሪፖርተር ገልጸዋል።

ፌዴሬሽኑ ያለውን የአትሌቲክስ አቅም ወደ ገበያ አውጥቶ መሸጡ ላይ ውስንነት መኖሩ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በዚህም በቀጣይ የገበያ ሪፎርም በማድረግ ካሉት ስፖንሰሮች ጋር ውል እንደሚያስርና ተጨማሪ ስፖንሰሮችን ለማምጣት የሥራ አስፈጻሚው እንቅሰቃሴ እያደረገ እንደሚገኝም አቶ ዮሐንስ አልሸሸጉም።  

በሌላ በኩል ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የዘንድሮን የውድድር መርሐ ግብር ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ይፋ ማድረጉንና በአዲስ አበባና በተለያዩ  ከተሞች እንደሚያከናውን አስታውቋል፡፡

በዚህም መሠረት የውድድር ዓመቱን ጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ በሚከናወነው በ9ኛው የኢትዮጵያ 30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ ይጀምራል፡፡ 18ኛውን የኢትዮጵያ ማራቶን ሪሌ ውድድርና የ5 ኪሎ ሜትር ሕዝባዊ ሩጫ ኅዳር 11 ቀን በሰመራ ከተማ ያከናውናል፡፡ ዕድሜ ጠገቡን 40ኛው ጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር ጥር 7 ቀን በአዲስ አበባ እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡

ዓመታዊ የአትሌቲክስ ውድድሩን ተቀብላ የምታስተናግደውና በርካታ የአትሌቲክስ ተመልካች ያላት አሰላ ከተማ፣ 11ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከጥር 23 እስከ 28 እንደምታስተናግድ ይፋ ተደርጓል፡፡

ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰናዳው የኢትዮጵያ ፕሮጄክቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከየካቲት 15 እስከ 19 ቀን በድሬደዋ ከተማ፣ 16ኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ውድድር መጋቢት 3 ቀን በደብረ ብርሃን እንደሚከናወን ቀጠሮ ተይዞለታል፡፡

የኢትዮጵያ የአጭር፣ መካከለኛና 3,000 ሜትር መሰናክል፣ የሜዳ ተግባራትና የዕርምጃ ውድድር ከመጋቢት 13 እስከ 17፣ እንዲሁም 52ኛው የአትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሚያዝያ 17 እስከ 22 ቀን በአዲስ አበባ የሚካሄዱ መርሐ ግብሮች ናቸው፡፡

ሦስተኛው የኢትዮጵያ ማሠልጠኛ ማዕከላት አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሰኔ 1 እስከ 4 ቀን በአምቦ፣ እንዲሁም 39ኛው የሻምበል አበበ ቢቂላ ኢንተርናሽናል ማራቶን ውድድርና የ10 ኪሎ ሜትር ሕዝባዊ ሩጫ ሰኔ 18 ቀን በባህር ዳር ከተማ ይከናወናሉ፡፡

እንደ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ማሳሰቢያ ከሆነ የውድድር መረሐ ግብሩ እንደ አስፈላጊነቱ ሊሻሻል ወይም ሊስተካክል ይችላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...