አገሬ ውስጥ ሁሌም ከሚቆጩኝ ነገሮች መካከል አንዱ ይህችን የመሰለች አገር ይዘን ለምን እንራባለን የሚለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቶች የታደለች ሆና ለምን የረሃብ ምሳሌ ሆነች ብንል መልሱ ቀላል ነው፡፡ የሥራ ባህላችን ደካማ በመሆኑና ውስን ሀብት ላይ ስለምንራኮት ነው፡፡ በርካታ ሚሊዮን ካሬ ሜትር መሬቶች ሳይታረሱ ፆማቸውን እንዲያድሩ በማድረጋችን፣ ዳቦ ማግኘት አቅቶን ረሃብ ይቆላናል፡፡ በአፍሪካ በቀንድ ከብት ሀብት አንደኛ እየተባልን አንዲት ብርጭቆ ወተት ማግኘት ይከብደናል፡፡ ሥጋው፣ ዕንቁላሉ፣ ቅቤውና ዓይቡማ እንደ ሰማይ ይርቁናል፡፡ ከዓመታት በፊት ኡጋንዳ ለሥራ ሄጄ አንድ ቀን ምሽት ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፣ ‹‹ኡጋንዳ ወተት እንደ ውኃ የሚቀዳባት ሀብታም አገር ናት…›› ሲሉ ሰምቼ ነበር፡፡ እውነቱን ለማረጋገጥ ካምፓላ ውስጥ ያሉ የምግብ መደብሮችን ሳስስ የተናገሩት ትክክል ነበር፡፡ ወተት ጎርፍ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ጎረቤት ኬንያም ሆነ ታንዛኒያ የዶሮና የዓሳ ጥብስ ጎዳና ላይ እንደ ድንች ነው በርካሽ ዋጋ የሚቀርቡት፡፡ እኛ ግን የክት ምግብ ናቸው፡፡ ያውም ከተገኙ፡፡
እኛ አገር ሠርቶ ከሚያሠራ ምሁርና ፖለቲከኛ ይልቅ በታሪክ ሰበዞች ላይ የሚወዛገበው በመብዛቱ፣ ለም አፈርና የውኃ ማማ ላይ ተቀምጦ መራብም ሆነ መጠማት እርግማን ካልሆነ ምን ሊባል ይችላል? እኛ ኢትዮጵያውያን ታሪካችን እንደሚነግረን ሊወሩንም ሆነ ቅኝ ሊገዙን የመጡትን በአንድነት ተሠልፈን ድል መንሳት ከቻልን፣ ፈጣሪ የሰጠንን የተፈጥሮ ፀጋዎች ገርተን ደልቶን መኖር ለምን አቃተን? ድሮ ንግድ ሥራ ትምህርት ቤት ስማር በአባቱ ጣሊያናዊ በእናቱ ኢትዮጵያዊ የነበረ የክፍል ጓደኛዬ የነገረኝ አይረሳኝም፡፡ ‹‹አባቴ ጣሊያን ውስጥ የሲሲሊ አካባቢ ተወላጅ ነው፡፡ እሱ እዚያ ድህነት የተንሰራፋበት ሥፍራ ስለተወለደ፣ የኢትዮጵያ ጉዳይም ያበሳጨዋል፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን የመሰለ የተፈጥሮ ፀጋ ይዛ ተቸገረች ሲባል ይናደዳል፡፡ ሁልጊዜ እኛ ጣሊያናውያን ኢትዮጵያ ውስጥ የመሥራት ዕድል በስፋት ብናገኝ፣ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ከአውሮፓ አገሮች የበለጠች ሀብታም ትሆን ነበር እያለ ይቆጫል፡፡ ኢትዮጵያውያን ከማይረቡ ነገሮች ውስጥ ወጥተው ለሥራ ቆርጠው ካልተነሱ በስተቀር ድህነቱ ይቀጥላል እያለ ይነግረኛል…›› ያለኝ አይረሳኝም፡፡
ከኢትዮጵያ ሕዝብ 80 በመቶ ያህሉ በግብርናና በእንስሳት ዕርባታ እንደሚተዳደር ይነገራል፡፡ ይህንን ያህል መጠን ያለው ሕዝብ 20 በመቶ ለሚሆነው ከተሜ ምግብም ሆነ ወተት ማቅረብ አይችልም፡፡ በሠለጠኑት አገሮች ግን አምስት በመቶ የማይሞላው ነው ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነውን ሕዝብ አብልቶ ለዓለም ገበያ የሚተርፈው፡፡ ለምን ቢባል በግብርና የተሰማራው ኃይል ከፍተኛ የሆነ የባንክ ብድር፣ የኢንሹራንስ አገልግሎት፣ የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ አቅርቦት፣ የቴክኖሎጂ ድጋፍና ሌሎች መሠረታዊ የሚባሉ ዕገዛዎች ስለሚደረጉለት አትራፊ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ለግብርናው ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት ሲታይ፣ ሌላው ቀርቶ ከባንክ ጋር ትውውቅ የለውም፡፡ የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ ወጪ ወገቡን ያጎብጠዋል፡፡ የባንክ ብድሮች በሙሉ ለአስመጪዎችና ለሕንፃ ገንቢዎች ብቻ እየዋሉ ጥቅማቸው ሊታወቅ አልቻለም፡፡ ዘመናዊ እርሻ ለመጀመር የሚፈልጉ የሚያተጋቸው ነገር የለም፡፡ መሬት እንደ አንድ የምርት መገልገያ መሣሪያ ሳይሆን የፖለቲካ መሣሪያ ስለሆነ፣ ሕዝብን ከችግር የሚያላቅቅ ሊሆን አልቻለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መሬት የምርት መገልገያነቱ ካልተረጋገጠ በስተቀር ድህነቱ ይቀጥላል፡፡
የግብርና ባለሙያዎች እንደሚሉት የኢትዮጵያ የመሬት ይዞታ ሥርዓት ቢቀየር በትንሹ በሁለት ዓመት ውስጥ ገበያው በምርቶች ይጥለቀለቃል፡፡ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ አተር፣ ባቄላ፣ ምስር፣ ጎመን፣ ቲማቲም፣ ድንችና የመሳሰሉ ምርቶች በብዛትም በጥራትም ለሸማቹ መድረስ ይችላሉ፡፡ የቅባት እህሎች በብዛት ተመርተው ኢትዮጵያ የምግብ ዘይት ሐይቅ መሆን አያቅታትም፡፡ መንግሥት በብቁ ባለሙያዎችና የፖሊሲ አውጭዎች ድጋፍ አሠራሩን ቢያስተካክል፣ ከምግብ ምርቶች በተጨማሪ እንደ ሲሚንቶና መሰል ግብዓቶች በብዛት ተመርተው ወደ ውጭ ሳይቀር መላክ ይቻላል፡፡ በውጭ ምክርና ዕርዳታ ላይ የተመሠረቱ ብልሹ አሠራሮችና ፖሊሲዎች ተስተካክለው፣ የስግብግብ ባለሥልጣናትና የደላሎች መጫወቻ የሆነው ኢኮኖሚ ፈር መያዝ አያቅተውም፡፡
በዚህ ረገድ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ጠቃሚ ምልከታቸውን የሚያጋሩ መልካም ሰዎችን ሐሳብ መቃረም ጥሩ ይመስለኛል፡፡ በተለያዩ ሚዲያዎችም ጠቃሚ ምክረ ሐሳቦችን የሚያቀርቡትንም ማዳመጥ ይጠቅማል፡፡ በቅርቡ አንድ አንጋፋ የግብርና ኢኮኖሚ ባለሙያ የሰሞኑን የዶላር የጥቁር ገበያ አስደንጋጭ ግብይት አስመልክተው፣ ለመሆኑ ይህ ሁሉ ዶላር በጆንያ እየተሞላ ነው የገባው ወይስ ከየት መጥቶ ነው ኢኮኖሚውን ከማናጋት አልፎ መንግሥት ሊያስገለብጥ ደረጃ ላይ የደረሰው ብለዋል፡፡ እኔም የእሳቸውን ሐሳብ እጋራለሁ፡፡ ይህ ሁሉ ጥሬ ዶላር ከየት መጥቶ ነው ኢኮኖሚውን በየቀኑ የሚያርበደብደው ተብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ የዋጋ ግሽበት የዜጎችን ኑሮ ምስቅልቅሉን እያወጣው፣ ኢኮኖሚው በጥቁር ገበያ የሚመራ እስከሚመስል ድረስ መንግሥት ምን እየሠራ እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ የመኪና ዋጋ በአንዴ የአንድ ሚሊዮን ብር ለውጥ ሲያሳይና ከዚህ ጀርባ ያለው ደባ ምን ይሆን ካልተባለ፣ አገር እንዴት ነው እየተመራ ያለው መባልም አለበት፡፡
በቀደም ዕለት አንድ የመኪና ደላላ አግኝቼ እየሆነ ስላለው ነገር እውነቱን እንዲነግረኝ ጠየቅኩት፡፡ አጅሬው የእንጀራ ነገር ሆኖበት እውነቱን አፍርጦ ሊነግረኝ ባይፈልግም፣ የመኪናም ሆነ የዶላር ንግድ ውስጥ የመንግሥት ሹማምንት ጭምር ከበስተጀርባ እንዳሉ መጠርጠር ይገባል ነው ያለኝ፡፡ አይሆንም ብዬ ልከራከር የማልችልባቸው በርካታ ምክንያቶች ስላሉኝ፣ የደላላውን ጥቆማ እንደ ዋዛ ለማየት አልፈለግኩም፡፡ ፍራንኮ ቫሉታ የሚባለው የኢኮኖሚ ጠላት የተፈቀደበት ምክንያትና ያስገኘው ውጤት በቅጡ ከተጠና፣ ዞሮ ዞሮ ወደ ደላላው ጥቆማ እውነትነት መጠጋት አያቅትም፡፡ ከቀረጥ ነፃ ዕድል እንደ ሽልማት ለጥቅም ተጋሪዎች በሚታደልባት ኢትዮጵያ፣ በፍራንኮ ቫሉታ ሽፋን ጥቁር ገበያው አገር ላይ ቢፈነጭ ምንም አይገርምም፡፡ እንግዲህ ወደ ሥራ ተገብቶ ፖሊሲን በማስተካከል መነሳት ካልተቻለ ድህነቱ ይስፋፋል፣ የሌባ ሠራዊት ደግሞ አገሪቱን መቀመቅ እየከተተ ጥቂቶች ሁሉንም ነገር ይቆጣጠራሉ፡፡ ይህ ጥንቆላ ወይም ትንቢት ሳይሆን ነገ በገሃድ የሚታይ እውነት ነው፡፡ ሚሊዮኖች እየተራቡ ጥቂቶች ሲያገሱ ደግሞ መቅሰፍት ነው የሚከተለው፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡
(ሰይፈ ሚካኤል አማኑኤል፣ ከልደታ)