Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉትኩረት ሊቸረው የሚገባው አካታች የካፒታል ገበያ

ትኩረት ሊቸረው የሚገባው አካታች የካፒታል ገበያ

ቀን:

በአብዱ ሰኢድ (ዶ/ር)

ገበያዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ዓይነታቸውና ቅርፃቸው እየተቀያየረ ቢሄድም፣ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል እየተጫወቱም ይገኛሉ። ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን በማቅረብ ምርታማነት፣ ሥርጭትና ፍጆታን በተገቢው መንገድ ማሰናሰል የገበያዎች ሚና ሆኖ ለረዥም ጊዜ ቆይቷል፡፡ ለገበያ የሚቀርበው ምርትና አገልግሎት መጠን፣ ዓይነት፣ ዋጋና የሥርጭት ሁኔታ በገበያ ኃይሎች (Market Forces) የሚወሰን ሲሆን፣ ይህም በጊዜው ባለው የፍላጎትና (Demand) አቅርቦት (Supply) መሠረት ይሆናል (ምንም እንኳ በገበያ ኃይሎች ላይ ብቻ መተማመን አከራካሪ ቢሆንም)፡፡ በዓለማችን በርካታ የገበያ ዓይነቶች ሲኖሩ በፋይናንስ ገበያ ሥር ከሚመደቡት ውሰጥ የአክሲዮን (Stock)፣ የዕዳ ሰነድ (Bond)፣ የውጭ ምንዛሪ (Foreign Exchange)፣ የሌላን ንብረት መሠረት ያደረጉ ስምምነቶች (Derivative Instruments) ገበያዎች፣ ወዘተ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ባለፈው ግንቦት ወር የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስና የኤፍኤስዲ አፍሪካ ተወካዮች የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅን ለመመሥረት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ይህም ቡድን የካፒታል ገበያውን ለማቋቋም የሚያስፈልገውን ቅድመ ሥራ የሚያከናውን ፕሮጀክት ቡድን ሲሆን፣ ገበያውን ለማቋቋምም እስከ ሁለት ዓመት እንደሚወስድ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ተናግረዋል። ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉ ግዙፍ የአክሲዮን ገበያዎች በአዲስ አበባ በሚመሠረተው ተቋም መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳሳዩም ተነግሯል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የአክሲዮን ገበያ መኖሩ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል፡፡ የአክሲዮን ገበያ በእጃቸው ትርፍና ሥራ ላይ ያልዋለ ገንዘብ ያላቸውን ባለሀብቶች ገንዘብ ከሚፈልጉት ጋር በማገናኘት፣ እንደ አንድ የካፒታል ምንጭ በማገልገል የረዥም ጊዜ ኢንቨስትመንትና ንብረት ላይ በማዋል የአገሮች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ ያደርጋል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የፋይናንስ ምንጭ በዋናነት በመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ቁጥጥር ሥር ባለበት አገር፣ የካፒታል ገበያ ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ካፒታል በማመንጨት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። በተጨማሪም ካፒታል ገበያዎች በአገሮች ኢኮኖሚ ላይ የሚከተሉትን ሚናዎች ይጫወታሉ።

ገንዘቦችን በባንኮች ውስጥ በማስቀመጥ እዚህ ግባ የሚባል ጥቅም በማያስገኙበት ሁኔታ ሰዎች የቆጠቡትን ገንዘብ አክሲዮን ለመግዛት ሲያውሉት፣ የሚሰበሰበው ገንዘብ ለንግድና ኢንቨስትመንት ማስፋፊያና ማጠናከሪያ እንደ ጥሩ ግብዓት ከማገልገሉም ባሻገር የአጭርና የረዥም ጊዜ ትርፍ ያስገኛል። በተጨማሪም ዜጎች በተለያዩ የተመዘገቡ ድርጅቶች ውስጥ የአክሲዮን ድርሻ ሲኖራቸውና ሌሎች ባቋቋሙት ድርጅቶች ውስጥ የባለቤትነት ዕድል ሲያገኙ፣ ድርጅቱ ከሚያከፋፍለው ትርፍ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህም በኢኮኖሚው ውስጥ የሀብት ሥርጭት ፍትሐዊ እንዲሆን በር ይከፍታል።

ሌላው ጥቅም ደግሞ የአክሲዮን ገበያ በርከት ያለ ገንዘብ ላላቸው ባለሀብቶች ብቻ ሳይሆን፣ መካከለኛ ገቢ ላላቸውም በተለያየ መንገድ በካፒታል ገበያው በሚሳተፉ የጋራ ፈንድ (Mutual Fund) እና የጡረታ ፈንዶች (Pension Funds) ላይ የመሳተፍ ዕድል ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ የካፒታል ገበያ ለመሠረተ ልማትና ለግዙፍ ፕሮጀክቶች የሚውሉ የገንዘብ ምንጮችን በማቅረብም መንገዶች፣ ድልድዮች፣ የውኃ አቅርቦት፣ የኃይል ማመንጫ፣ የመገናኛ አገልግሎት፣ የትራንስፖርት አገልግሎትና የመሳሰሉትን በረዥም ጊዜ ቦንድ (Long-term Bonds) እና ንብረትን መሠረት ባደረጉ ሰነዶች (Asset-Backed Securities) ሥራ ላይ በማዋል ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ልማቶች እንዲኖሩ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

ሌላውና ዋናው ጥቅም ደግሞ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ በጥምረት የሚሠሩበትን (Public Private Partnership) ዕድል ያመቻቻል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በኢኮኖሚው ዘርፍ የመንግሥት ሚና ከፍተኛ በሆነባቸው አገሮች፣ ይህ ጥምረት የግሉ ዘርፍ ቀስ በቀስ በኢኮኖሚው ላይ መጫወት ያለበትን ሚና ከፍ ያደርገዋል።

አካታች  የፋይናንስ  ሥርዓ

እነዚህን ሁሉ ጥቅሞች ለመቋደስ ግን አካታች የፋይናንስ ሥርዓት መዘርጋት ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆን ይኖርበታል። ከአካታችነት መርሆች አንዱ የሆነው ከእምነት ጋር በተያያዘ ምክንያት ከፋይናንስ ሥርዓት ተጠቃሚነት የተገለሉ የማኅበረሰብ  ክፍሎችን ለማቀፍ፣ በመንግሥት ፖሊሲ አውጭዎች በኩል የሚያስመሠግን ተግባር ተፈጽሟል፡፡ አሥር ዓመታት ሊደፍን ጥቂት የቀረው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በ11 መደበኛ ባንኮችና በሦስት ሙሉ በሙሉ አገልግሎቱን በሚሰጡ ባንኮች አገልግሎቱን ለማኅበረሰቡ በማዳረስ ላይ ይገኛል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በአዋጅ የተፈቀደው ተካፉል (ከሸሪዓ መርህ ጋር የሚጣጣም የኢንሹራንስ አገልግሎት) በጥቂት የመደበኛ የኢንሹራንስ ደርጅቶች በመስኮት እየተሰጠ ሲገኝ፣ ሙሉ በሙሉ የተካፉል አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች በቅርቡ ገበያውን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይገመታል፡፡

ከወለድ ነፃ የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት ደግሞ በአንድ ሙሉ በሙሉ የባንክና የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎትን በጣምራ በሚሰጥ ተቋምና በጥቂት በተጓዳኝ በሚሰጡ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት አገልግሎት እየተሰጠ ሲሆን፣ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በቅርቡ ይመጣሉ፡፡ ምንም እንኳ በአገራችን ከወለድ ነፃ የባንክ፣ ተካፉልና ማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎቶች ለጥቂት ዓመታት ቢዘልቅም የፖሊሲና ሕግ ማዕቀፍ ክፍተት፣ በዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል በቂ አለመሆን፣ የግንዛቤ እጥረት ከዋና ዋና ተግዳሮቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

እንደ ባንክ፣ ኢንሹራንስና ማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎቶች ሁሉ በቅርቡ ሊቋቋም የታሰበው የካፒታል ገበያም፣ አካታችና አሳታፊ መሆን እንዳለበት ይታመናል፡፡ አካታችና አሳታፊ የካፒታል ገበያ የግለሰቦችንና ድርጅቶችን ተሳትፎ በማሳደግ በገበያ ስፋት (Market Cap) እና ባቀፉት ድርጅቶች ብዛት (The Number of Listed Companies) የተሻለ እንዲሆን፣ በጣም ጥቂት የገበያ ተሳታፊዎችና አልፎ አልፎ በሚደረግ ግብይት የተገደበ የቀዘቀዘ ገበያ (Illiquid Market) እንዳይሆንና ለአገራችን አስፈላጊውንና ያሰብነውን ጥቅም እንዲያመጣ ተገቢው ትኩረት ሊቸረው ይገባል፡፡

የሸሪ  መርሆች  የተከተለ  የአክሲዮን  ኢንዴክስ

የአገራችንን የካፒታል ገበያ አካታችና አሳታፊ ከምናደርግባቸው መንገዶች አንዱ የሸሪዓ ኢንዴክስ (Shariah Index) እንዲያካትት ማድረግ ነው፡፡ ይህ ኢንዴክስ በካፒታል ገበያው ውስጥ የሚሳተፉ ድርጅቶች የተሰማሩበት የሥራ እንቅስቃሴ፣ ከሃይማኖታዊ መርሆች ጋር የማይጋጩ መሆናቸውን የተለያዩ መሥፈርቶችን አውጥቶ የሚያጣራ (Shariah Screening and Filtering Process) ዘዴ ነው፡፡ በአገሪቱ ግዙፍ የሆኑ ድርጅቶችን ማለትም እንደ ባንኮች፣ የኢንሹራንስ፣ የማኑፋክቸሪንግ፣ የግንባታና የሪል ስቴት፣ የአገልግሎት ተቋማት፣ ወዘተ አክሲዮኖች የሚገበያዩበት ሥርዓት ነው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች የተለያዩ ምርቶችንና አገልግሎቶችን ለተጠቃሚዎች ያቀርባሉ፡፡

እንደሚታወቀው ከኢስላሚክ ፋይናንስ መርሆች ውስጥ አንዱ ያልተፈቀዱና የተወገዙ ተግባራትን ለምሳሌ ወለድ/አራጣ፣ አስካሪ መጠጦች፣ የትምባሆ ምርቶች፣ የአሳማ ሥጋና ማቀነባበሪያ፣ የጦር መሣሪያዎችና የመሳሰሉ ምርቶችንና አገልግሎቶችን የሚሸጡ ድርጅቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግም ሆነ መሳተፍ የተከለከለ መሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም የአገራችን የካፒታል ገበያ ከአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ በሃይማኖት ጉዳይ ስሱ የሆኑ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ፣ የረዥም ጊዜ ፋይናንስ ለማሰባሰብና አገርን የሚጠቅሙ ኢንቨስትመንቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ከሚኖረው የተለያዩ ኢንዴክሶች ውስጥ፣ የሸሪዓ ኢንዴክስ መኖር ላቅ ያለ ሚና ይጫወታል፡፡

የሸሪዓ ኢንዴክስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ባላቸው የአክሲዮን ኢንዴክስ አውጪ ድርጅቶች ወደ ተግባር ከገባ ሰነባብቷል፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካዎቹ ዳዎ ጆንስና ኤስኤንድፒ ግሎባል (Dow Jones Islamic Market Indices, S&P 500 Shariah Index) ሲኖራቸው፣ እንግሊዝ ለንደን መሠረታቸውን ያደረጉት (FTSE and HSBC  FTSE Shariah Indexes) HSBC Islamic Global Equity Index Fund በካፒታል ገበያዎቻቸው ውስጥ አካተዋል፡፡ በማሌዥያ (MSCI Malaysia Islamic Index) ሲኖር፣ በአኅጉራችን አፍሪካ ደግሞ በናይጀሪያ አክሲዮን ገበያ (NSE Lotus Islamic Index) ሲገኝ፣ በደቡብ አፍሪካ ደግሞ በአፍሪካ ግዙፉ የአክሲዮን ገበያ በሆነው በጁሃንስበርግ አክሲዮን ገበያ (FTSE/JSE Shariah Indices) የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡

ለማጠቃለል ያህል በአገራችን የሚቋቋመው የካፒታል ገበያ አገራዊ ፋይዳው የጎላ እንዲሆን አሳታፊና አካታች መሆን እንዳለበት አጠያያቂ አይደለም፡፡ ለአገራችን ኢኮኖሚ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ተገቢውን የመዋቅር፣ የሕግ፣ የመረጃና የትምህርት፣ እንዲሁም የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ ተገቢውን የመሠረተ ልማት ማሟላትና በአቅራቢያችን ከሚገኙ አገሮች ገበያዎች ጋር ትብብረና ጥምረት ከመፍጠር ጎን ለጎን ፖሊሲ አውጪው አካል የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅን ለማቋቋም በሚያደርገው ጥረት፣ ከሸሪዓ መርህ ጋር የሚጣጣም ኢንዴክስ (Shari’ah-compliant Index) ማካተት አስፈላጊና ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በማክስብሪጅ የትምህርትና ልማት አክሲዮን ማኅበር የወለድ ነፃ ፋይናንስ ክፍል ኃላፊ፣ በፋይናንስ ጉዳዮች ደግሞ አማካሪና አሠልጣኝ ሲሆኑ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...