በንጉሥ ወዳጅነው
መንግሥት የሕዝብ አደራ የተሸከሙ ተቋማት ስብስብ መገለጫ ነው፡፡ በአገር ደረጃ በየደረጃው ያሉ ሕግ አውጭ፣ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚዎች ብሎም የፀጥታና የደኅንነት መዋቅሮች መንግሥት የሚለውን ሰፊ ማዕቀፍ የሚወክሉ ናቸው፡፡ ለነገሩ እንደ ፋይናንስና የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት መንግሥታዊ ተቋማትም የተጣለባቸው ኃላፊነት ከመንግሥትነት ድርሻ የሚያወርዳቸው አይደለም፡፡
ያም ሆኖ በተለይ የእኛን አገር በመሳሰሉ ታዳጊ አገሮች የፖለቲካ አመራሩን የሚመሩት አስፈጻሚ አካላት እንደ ፖሊሲ አውጭና አቅጣጫ አመላካች ስለሚወሰዱ፣ መንግሥት ሲባል ጫፍ ላይ ያሉ የአስፈጻሚው መሪዎች ናቸው የሚታወሱት፡፡ ብቻ ምንም ይባል ምን መንግሥት የአገር ዋልታና ማገር መሆኑን መዘንጋት አይቻልም፡፡ ሕዝብ እንዲሁ ጨፈቃ፣ ግድግዳ፣ ጭቃ፣ ጣሪያ… ሆኖ ቤት ያቆም እንደሆን እንጂ የመንግሥትን ድርሻ ሊሸፍን አይችልም፡፡
ለዚህም ነው እንደ አገር ለገጠመን ፈተናም ሆነ መልካም ዕድሎች መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት፣ ታሪካዊ አደራውንም መወጣት ግድ እንደሚለው ደግሜ ደጋግሜ ማሳሰብ የምሻው፡፡ ከዚህ አንፃር ከቀናት በፊት በተቀበልነው የ2015 አዲሱ ዓመት በሥልጣን ላይ ያለው አካል ትኩረት ቢሰጣቸው የምላቸውን ቁምነገሮች በማንሳት፣ በአፅንኦት መወያያ እንዲሆኑ ነው የምመኘው፡፡
መንግሥት የሰላምና አገራዊ መረጋጋት ቀንዲል ይሁንልን
አሁን በምንገኝበት አገራዊ ሁኔታ ኢትዮጵያ ከለውጥ ማግሥት የገጠማት ከፍተኛ የሚባል የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የአማፅያን ጦር ሰባቂነትና ለዘመናት የተከማመሩ የአዋሳኝ አገሮች የድንበር ፍጥጫዎች፣ ወዘተ ቀላል የማይባል የፀጥታና የደኅንነት ሥጋት ፈጥረውብናል፡፡ በአንድ በኩል የውስጥ ኃይሎች ተስማምተውና ተደማምጠው የፖለቲካ ፍላጎታቸውን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማራመድ አለመቻላቸው፣ ከዚያም ብሶ ንፁኃንን የሽኩቻው ማገዶ አድርገው ለመጠቀም መሞከራቸው ይታያል፡፡
በሌላ በኩል በውስጥ ያሉ አኩራፊ ኃይሎችን አገራችንን ለማዳከም እንደ መሣሪያ መጠቀም የሚሹ የውጭ ኃይሎች፣ መንግሥትን ጫና ውስጥ ለመክተት ችግሮች እንዲባባሱ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት ከሟቹም ከገዳዩም በመሆን አንድ ጊዜ ገላጋይና አደራዳሪ በመምሰል ጫና ለማሳደር ይሻሉ (አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረትና ሸሪኮቻቸውን ልብ ይሏል)፡፡ ሲያሻቸውም በተፈጥሮ ሀብታችን እንዳንጠቀም ለማወክ ሁሉም መፍትሔዎች በጠረጴዛ ዙሪያ እንደሚያልቁ ቢያውቁም፡ በሁከት እንድንታመስ ይሠራሉ (ሱዳን፣ ግብፅና ሸሪኮቻቸውን መጥቀስ ይቻላል)፡፡
እነዚህን ነባራዊ ፈተናዎች ለመመከትና አገርን ለመታደግ ታዲያ መንግሥት ብልህ፣ ጠናካራና ሕዝቡን ከጎኑ ያሳለፈ ሆኖ መገኘት ይኖርበታል፡፡ በእርግጥ በኃይልና በጦር የመጣን ግትር ሁሉ በመለማመጥና ተስፋ በሌለው ድርድር ብቻ መርታት አይቻል ይሆናል፡፡ ወይም ሁሉንም ችግሮች በጉልበትና በጦር ብቻ ማሸነፍም እንዲህ እንደሚታሰበው ሊቀል አይችልም፡፡ ስለዚህ መጠነኛ ጉዳት ቢኖርም፣ አገር የከፋ ኪሳራ ውስጥ በማትወድቅበትና ሳትበተን መልሳ በምትነሳበት መንገድ መፍትሔዎችን ለማምጣት፣ ዙሪያ ገባውን መፈተሽ ዋነኛ የመንግሥት ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡
በየትኛውም መለኪያ ቢሆን የጠላትና ባላንጣዎችን ቁጥር በመቀነስ፣ የወዳጅና የአጋር ኃይሎችን መጠን ማብዛት ብልህነት ነው፡፡ በየትኛውም ፈተናና ችግር ውስጥ አገር ብትወድቅም የሕዝብን መብትና ጥቅሞች መጠበቅ፣ ዜጎችን በተቻለ መጠን ከጎን ለማሳለፍ መሞከር፣ የመንግሥትነት ትንሹ ኃላፊነት ነው፡፡ አንድ ተገዳዳሪ በጦርነት ሲገጥም በጦር ብቻ ሳይሆን፣ በአሉባልታና በውዥንብር ጭምር በመሆኑ የመንግሥትና የሕዝብን ግንኙነት የሚያበላሹ አካሄዶችንና ፕሮፓጋንዳዎችን እየመከቱ ለእውነትና ለፍትሕ መቆም ያስፈልጋል፡፡
ከዚህ አንፃር አገራችን በዚህ ወቅት የገጠማትን የሥነ ልቦና ጦርነት፣ የኑሮ ውድነትና የምጣኔ ሀብት ፈተና፣ እንዲሁም የመንግሥትን ቅቡልነት የመናድ ተግዳሮት ለመመከት ከፍተኛ ሥራ መኖሩን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት በሰላማዊውና በአዘቦት ጊዜ ከሚሠሩት በላይ ትጋትና ተቆርቋሪነት፣ ብሎም ፍትሐዊነት ቀጥተኝነት፣ አልፎ ተርፎም ግልጽነትና ተጠያቂነትን የተላበሰ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
በእርግጥ የትኛውም የመንግሥት ተቋም የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት የሚመራበት ራዕይ፣ ተልዕኮና እሴቶች አሉት፡፡ የአብዛኛው ተቋም ራዕይ ቀልጣፋ፣ ውጤታማ፣ ፍትሐዊ፣ ነፃ፣ ተደራሽ፣ ተጠያቂና የሕዝብ አመኔታ የተቸረው ተቋም መሆን ነው፡፡ ተልዕኮው ደግሞ የሕግ የበላይነት መርህን መሠረት ያደረገ ፍትሐዊ፣ ቀልጣፋ፣ ተደራሽ፣ ጥራት ያለው አገልግሎት ለሁሉም በእኩልነት መስጠት መሆኑም ይታወቃል፡፡ እነዚህን እሴቶች እየሸራረፉ ሕዝቡን ማስመረር ከጠላትነት አይለይም፡፡
አሁን አሁን በመርህ ደረጃ ብዙዎቹ ተቋማት የሚመሩባቸው እሴቶች ግልጽነት፣ ሀቀኝነት፣ ተደራሽነት፣ እኩልነት፣ ነፃነትና ተጠያቂነት፣ ውጤታማነት፣ አክብሮትና ቅንነት፣ ፍትሐዊነት፣ ዕውቀትና ቅልጥፍና፣ ጥራት ያለው አገልግሎት ለሕዝብ መስጠት የሚሉት ቢሆንም፣ በተግባር ሲናዱ መታየታቸው አሳሳቢ ነው፡፡ አንዳንዱ አካባቢ በብሔር፣ በቡድንና በጥቅም ትስስር ሲሠራ፣ ሌላው አካባቢ ፍትሕ በገንዘብ ሲለወጥ፣ ትንሽ በማይባል ሥፍራም የመንግሥትና የሕዝብ ንብረት ያላግባብ ሲዘረፍና ሲድፋፋ… መታየቱ የሚናፈቀውን ሰላምና ዕድገት ያርቀዋል እንጂ አያቀርበውም፡፡
በመሆኑም የመንግሥት ራዕይ ከድህነት የተላቀቀች፣ በመልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲ ፅኑ መሠረት ላይ የቆመች የበለፀገች ኢትዮጵያን መገንባት መሆኑን ደጋግሞ መናገር ብቻ ሳይሆን፣ እዚያ ለመድረስ መረባረብም ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በዋናነት በመንግሥት የተሾሙና ኃላፊነት የተሰጣቸው፣ ብሎም የተቀጠሩና የተመደቡ ባለሙያዎች ተቀዳሚ ተግባርና ኃላፊነት ነው፡፡ አንዱ ወደ ቀኝ ሲጎትት ሌላው ወደ ግራ እየሳበ፣ ባልተናበበ መንፈስና ተግባር የአገርን ችግር እቀርፋለሁ ማለት ዘበት ነው፡፡
መንግሥት ብሔራዊ ጥቅምን ያስተሳስር
በአንድ አገር የሚኖሩ ሕዝቦች ብሔራዊ ጥቅማቸው በዋናነት የሚመነጨው፣ ከአገር ሉዓላዊነትና ከግዛታዊ አንድነታቸው ነው፡፡ ሰላም፣ ልማትም ይባል ዴሞክራሲ ሊመጡ የሚችሉት የአገር ህልውና ከተረጋገጠ ብቻ ነው፡፡ አንዱ ሰላም ሆኖ ሌላው እየታመሰ፣ ወይም የአገሪቱ አንድ ክፍል ያላግባብ ተቆርጦና የሕገወጥነት መተራመሻ ሆኖ የሕዝብ ጥቅም ተከበረ ሊባል አይችልም፡፡ ይከበራል ቢባልም ምልዑነት ይጎድለዋል፡፡
ከዚህ አኳያ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል፣ በምዕራብ ኦሮሚያና መሰል አንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው የሰላም መደፍረስ እንደ ዋነኛ እንቅፋትና የሕዝብ ጥቅም ፈተና መወሰድ ይኖርበታል፡፡ ዛሬ በደሃ አገር ምጣኔ ሀብት በቢሊዮን ዶላር ለጦርነት ልናወጣ አይገባም፣ አንችልምም፡፡ በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአንድ አገር ዜጎች እየሞቱና እየቆሰሉ፣ በሺዎች የሚቆጠሩትም እየተፈናቀሉና ለችግር እየተጋለጡ ብሔራዊ ጥቅም ብሎ ነገርም ሊመጣ አይችልም፡፡ ከሁሉ በላይ አምራቾችና አገር ሊቀይሩ የሚችሉ ወጣቶች በዚያም በዚህም ሆነው የሚፋለሙ ጦረኛ መሆናቸው፣ በየትኛውም መለኪያ የሕዝብ ጥቅም አያስከብርም፡፡
እናም ምንም ተባለ ምንም አሁን የተገባበትን የእርስ በርስ ግጭት ፈጥኖ መቋጨት፣ ካልሆነም የተወሰነ መስዋዕትነት ተከፍሎም ወደ ድርድር መግባት በዋናነት የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ አክራሪና ፅንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎችንም በየትኛውም መንገድ ሕዝብና አገርን ከሚበድሉበት የጥፋት ጎዳና የማስቆም ታሪካዊ ኃላፊነት የወደቀው በዚሁ ትውልድ ላይ ነው፡፡ ምንም እንኳን ሴራውና ውስብስቡ ችግር ሥር የሰደደ ፈተናችን ቢሆንም፡፡
መንግሥት ሁሌም ተግቶ እንዲሠራ ያሉትን ሀብቶችና ግብዓቶች በአግባቡ ተጠቅሞ ከጊዜ ጋር አገናዝቦ እንዲሠራ ግዴታን የሚጥል፣ ሕዝባዊ አደራና መንግሥታዊ ኃላፊነት አለበት የሚባለው ይህ ዓይነቱን ኃላፊነት ሲወጣ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ያለበት የቤት ሥራ እጅግ በጣም ከባድ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ የመንግሥትነት ሥራ ራስ የሚያዞር፣ ወገብ የሚያጎብጥ፣ ተጠያቂነትን የሚያስከትል፣ ከሕዝብ ዓይንና ጆሮ የማይሰወር በግልጽ የሚታይና ከፍተኛ ሥራ ቢሆንም፣ ለአገር ሲባል መሸነፍም ሊኖር እንደሚችል ታሳቢ መደረግ አለበት፡፡
መንግሥት በፈተናዎች ውስጥም ቢሆን አገር መገንባቱን ሊዘነጋ አይገባም
ከአምስት ዓመታት ወዲህ አገሪቱን እየመራ ያለው መንግሥት በብዙ ፈተናዎች ውስጥም ቢሆን ያመጣቸው አንዳንድ የዕድገት ምልክቶች አሉ፡፡ ለአብነት ያህል በግብርና ዘርፍ የበጋ ስንዴና የትርፍ አምራች አካባቢዎችን በቴክኖሎጂ የታገዘ ምርታማነትን እያሳየ ነው፡፡ የወጪ ንግድ ከገቢ ንግድ ጋር ባይጣጣም፣ የኑሮ ውድነትና የገበያ ብልሽትን ማስተካከል ፈተና ቢሆንም፣ የመንገድ መሠረተ ልማትና የታላቁ ህዳሴ ግድብን የመሰሉ ግንባታዎችን በተሻለ ደረጃ መፈጸም እየቻለ ነው፡፡
የኮንስትራክሽን ዘርፍ የሥራ ዕድል ፈጠራው ላይ ያለው ጫና ገና እንደ መርግ የከበደ ቢሆንም፣ በቱሪዝም ረገድና በቴሌኮም ኢንዱስትሪው ረገድ አዲስ አብዮት ለመቀስቀስ እየተደረገ ያለው ጥረት ተስፋ ሰጪ ሆኖ እየታየ ነው፡፡ እንደ ሕዝብ ለእነዚህ ውጤቶች ዕውቅና፣ ክብርና ምሥጋና መስጠትም ያስፈልጋል፡፡
በቀጣዩ ጊዜ ግን መንግሥት በዋናነት በምግብ እህል ራሳችንን ለመቻል ብዙ ርቀት ይሄድ ዘንድ መወትወታችንን አንተውም፡፡ አቅም በፈቀደው መጠን በአገሪቱ ለምና የልማት ኮሪደር ተብለው የተለዩ አካባቢዎች፣ ግብርናውን በሜካናይዜሽንና በአግሮ-ፕሮሰሲንግ እያደራጁ ምርታማነትን ለማሳደግ ባለሀብቱን የሚያበረታታ ፖሊሲና የልማት አቅጣጫ መከተል ያስፈልጋል፡፡ አርሶ አደሮችም ከየአካባቢው ምርጥ ተሞክሮዎችን እየቀመሩ በአካባቢያቸው እንዲያስፋፉ ማድረግ ለነገ የማይባል ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡
የግብርና ውጤቶችን ገበያ ተኮር እንዲሆኑ ተወዳዳሪ ሆነው ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡና የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኙ፣ ገበሬው የግብርና ምርቶቹን በጥሬው ከሚያመጣ እሴት ጨምሮ እንዲያቀርብ ለማስቻልና የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ፣ ሁሉም የልማት ኃይሎች ሊረባረቡ ግድ ይላል፡፡ መሠረታዊው ከድህነት መውጫ ብቻ ሳይሆን ከተረጅነትና ከጥገኝነት መፋቻው ቀዳሚ አማራጭ ይህ መሆኑን በመገንዘብ፣ መንግሥት በጥናት ላይ የተመሠረተ ዕርምጃ መውሰድ ዋነኛ ኃላፊነቱ ሊሆን ይገባል፡፡
በዚህ ረገድ በግብርናው ዘርፍ አንዳንድ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያስከትሉ ችግሮች ለይቶ መፍታት የተግባሩ ቀደሚ ዕርምጃ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ የግብዓቶችን ችግር መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንደ ማዳበሪያ፣ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችና ምርጥ ዘሮች የግብርና ኬሚካሎችና መሰል ግብዓቶች ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተገናኙ እንደ መሆናቸው፣ በአገር ውስጥ የሚመረቱበትና እንዳስፈላጊነቱም ቅድሚያ ከውጭ የሚገቡበት ሥልት በትጋት መቀየስ አለበት፡፡
ሌላው መሠረታዊ ጉዳይ የኢንዱስትሪው መስክ መጠናከር ነው፡፡ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋትና መጠናከር የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ፣ የብድር፣ የግብዓት አቅርቦት፣ የገበያ ትስስርና የውጭ ገበያ ግኝትን ማሳደግ ትኩረት ሊያገኙ ይገባል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በየልማት ኮሪደሩ ባለሀብቶች ዋስትና አግኝተው ምርታማነታችውን እንዲያሳድጉ በመሠረተ ልማት፣ በመልካም አስተዳደርና በሕዝብ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ማጠናከር አስፈላጊ ነው፡፡
በኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚስተዋለው ሴራና አሻጥር ተወግዶ፣ ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጠራና የአገር ግንባታ ሒደት እንዲሳለጥ ማድረግም ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ ሲሚንቶን በመሳሰሉ የአገር ውስጥ ምርቶች ላይ የተፈጠረውን የገበያ አሻጥርና የማናለብኝነት እንቅስቃሴ ማስወገድ፣ የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር መሆን አለበት፡፡ በብረት፣ በአሉሚኒየምም ሆነ በእንጨት ገበያው ውስጥ ያለው የቀን ተቀን ጭማሪም ቢሆን ከገንዘብ የመግዛት አቅም ጋር የተፈጠረ በመሆኑ አጠቃላይ ምጣኔ ሀብታዊ ሪፎርም ይፈልጋል፡፡ እነዚህና መሰል ተግባሮችን ደግሞ ከመንግሥት ጫንቃ ላይ ማውረድ የሚቻል አይሆንም፡፡
መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳዮች ናቸው
በአገር ግንባታ ሒደትና በሕዝብ ተጠቃሚነት ረገድ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም አስተዳደርን በተቻለ መጠን ለማስፈን ከመረባረብ በላይ ትልቅ የመንግሥት ኃላፊነት የለም፡፡ ዜጎች የመምረጥና የመመረጥ፣ የፖለቲካ መብታቸውን የመጠቀም፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን የማስከበር ፍላጎታቸው እያደገ መጥቷል፡፡ ዛሬ እንደ ትናንቱ አውቅልሃለሁ በሚል ብሂል በሕዝብ የጋራና የተናጠል ጥቅም ላይ መወሰንም እንዲህ ቀላል አይደለም፡፡
በዚህ ረገድ ቢያንስ ፍትሐዊነት፣ አሳታፊነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የተላበሰ መልካም አስተዳደርን የማስፈን ተግባርን መንግሥት በትኩረት ሊሠራው የግድ ይላል፡፡ ለአብነት ያህል ከዚህ ቀደም ሕዝብ በመንግሥት ላይ ቅሬታ ካሳደረባቸው ጉዳዮች በዋነኛነት የሚጠቀሰው የፍትሕ ሥርዓቱ ነበር፡፡ እርግጥ እንደ መሬት፣ ገቢና ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎትም ሕዝብ አስለቃሽ ዘርፎች ነበሩ፡፡
እነዚህና መሰል መስኮች አሁንም ቢሆን ስለመሻሻላቸው በቂ ማሳያ ማቅረብ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ዛሬም ፍትሕን በሚመለከት በሐምሌ የታየ ጉዳይ ለታኅሳስ የሚቀጠርበት ሁኔታ ተደጋግሞ ይታያል፡፡ ያለ በቂ መረጃ እየተያዘ ያለ ፍርድ ታስሮ የሚለቀቀውን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ አሁንም ቀጠሮ ይበዛል፡፡ ቶሎ የሚፈጸም አቤቱታ የለም፡፡ ሌብነቱ ቀነስ ቢልም፣ ሁሌም እሮሮ ነው፡፡
በሌላ በኩል በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ያለው የሲቪል ሰርቪስ በየጊዜው ባለመረጋጋት ሲታመስ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ዘወትር መዋቅር መሥራት፣ ፈጻሚና አመራር መፐወዝ ይበዛል፡፡ ነባሩ እየጠፋ በአዲስ ፈጻሚ ሥራን ማተረማመስ ተለምዷል፡፡ የባሰው ደግሞ ቢሮክራሲው በእከክልኝ ልከክልህና በመሳሳብ መጠመዱ የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡
ይህ አካሄድ ደግሞ በአፋጣኝ ካልታረመ እንደ ወደቀው የቀድሞው ሥርዓት በአጭር ዓመታት እየተስፋፋ ሥርዓቱንና ሕዝቡን ወደ የማይታረቁበት ደረጃ ሊያደርሳቸው ይችላል፡፡ ይህ ችግር በደንብና በጥራት ተመርምሮና በቁርጠኝነት ተይዞ መስተካከል አለበት፡፡ መተሻሸት ይቅር፣ መሳሳብ ይቅር፣ አለመነካካት ይብቃ፡፡ ይቅርታ የሚለው ቃል እንደ ቀላል መታየት የለበትም፡፡ ሕግና ሥርዓት፣ ዕውቀትና ችሎታ መከበር አለባቸው፡፡
ከዚህ አንፃር በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊ አካላትና የገዥው ፓርቲ ብልፅግና አመራሮች ለሕዝቡ ብለው ሳይሆን ለራሳቸው ህልውና ሲሉ ዜጎችን ያዳምጡ፡፡ በተዘዋዋሪም ቢሆን ሕዝቡ መርጦ ለሥልጣን አብቅቷቸዋልና እንደ መንግሥት ደግሞ ይህን አደራ በላቀ ቁርጠኝነት መወጣት ይጠበቃል፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻለ በሚቀጥለው ምርጫ ሕዝቡ በምርጫ ካርዱ ሊቀጣው እንደሚችልም ግልጽ ነው፡፡ ይህንን መዘንጋት ዋጋ ያስከፍላል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡