Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትዝም ብሎ አንድ ዓመት የሞላው የተመድ የኢትዮጵያ ጉዳይ!

ዝም ብሎ አንድ ዓመት የሞላው የተመድ የኢትዮጵያ ጉዳይ!

ቀን:

በገነት ዓለሙ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት ከመጀመርያው የታኅሳስ 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ስብሰባው ወዲህ በኢትዮጵያ ላይ (ስለኢትዮጵያ ከማለት ይልቅ በኢትዮጵያ ላይ ማለትን የመረጥኩበት ምክንያት ግልጽ ነው ብዬ እገምታለለሁ) ሊቀመጥ እስካሁን ድረስ የመጨረሻ ወይም የቅርቡ ከሆነው ከመስከረም 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ስብሰባው ድረስ ለአሥራ አራተኛ ጊዜ መሆኑን በከፍተኛ የአገር ፍቅር፣ የአገር ጉዳይ ያገባኛል ባይነት ስሜት የምንቆጥረው አለዚያም የምንጠይቀው ብዙዎቻችን ነን፡፡ ከእነዚህ የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባዎች መካከል ሁለቱ ማለትም ኦክቶበር 1 እና 6 ቀን 2021 ዓ.ም. (የዛሬ ዓመት መስከረም 21 ቀንና መስከረም 26 ቀን 2014 ዓ.ም.) የተጠሩት ኢትዮጵያ መስከረም 20 ቀን በዚያው ዓመት ሰባት የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች፣ በ72 ሰዓታት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ የሰጠችውን ውሳኔ ምክንያት በማድረግ በዚያ ውሳኔ በመቆጣት ነው፡፡ ሁለቱንም ስብሰባዎች የጠሩትን ኤስቶንያን፣ ፈረንሣይን፣ አየርላንድን፣ ኖርዌይን፣ ዩኬን፣ ዩኤስን፣ ስብሰባው በመጨረሻ ላይ የሚሰጠውን የውሳኔ ረቂቅ ከወዲሁ ለማዘጋጀት ‹‹እኔ አለሁ›› ያለችው ኖርዌይን ጨምሮ፣ በስብሰባዎቹ ላይ እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው ቁጣቸውን ያሰሙት የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ጭምር ናቸው፡፡

የመንግሥታቱ ድርጅት ሰባቱ ሠራተኞች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባታቸው፣ የዓለም አቀፋዊው የሲቪል ሰርቪስ ሙያና ኃላፊነት የሚጠይቀውን መታመን በመክዳታቸው ነው ቢባል የሚሰማ ጠፋ፡፡ ይልቁንም ዜናውንና የኢትዮጵያን ‹‹ጥፋት›› የሚያስተጋባው ጩኸት በረከተ፡፡ ልክ በዚህ ጊዜ ኦክቶበር የመጀመርያ ሳምንት ውስጥ (2021) ወይም መስከረም የመጨረሻ ሳንምት አካባቢ በተለያዩ የዩቲዩብ ቻናሎች ላይ ጄፍ ፒርስ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥራ ባልደረቦች መካከል የተደረገ ውይይት የኦዲዮ (የድምፅ) ቅጂ ተለቅቆ በሰፊው ተሰማ፡፡ በዚህ 13 ደቂቃ ሊሞላው ጥቂት በቀረው የውይይት/የሐሳብ መለዋወጥ የድምፅ ቅጂ ውስጥ፣ ሁለት የመንግሥታቱ ድርጅት አባላት ለጄፍ ፒርስ የሚናገሩትና ከእሱ ጋርም የሚያወሩት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥርዓት የኢትዮጵያ መዋቅር ውስጥ ከተመድ ሥርዓት፣ ሕግና አሠራር ውጪ በደል፣ ጥፋትና ሴራ እየተሠራ መሆኑን እየገለጡ ነው፡፡ የዚህ ውይይት የድምፅ ቅጂ በሰፊው በመሠራጨቱ መንግሥታቱ ድርጅት ጆሮም ይሰማል፡፡ የሰዎቹ በተለይም የተመድ ሠራተኞች/የተመድ የሥራ ባልደረቦች ማንነትም በድምፃቸው በመታወቁ ኬንያዊቷ ማውሪን አቺን (Maureen Achieng) እና ኮስታሪካዊቷ ዲንያ ጌል (Dennia Gayle) የተባሉት ሁለት ከፍተኛ የተመድ ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ ከየእናት ድርጅታቸው ጥቅምት 1 እና 2 ቀን 2014 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ ‹‹ሪፖርት›› እንዲያደርጉ ይጠራሉ፡፡ ዕጣ ፈንታቸውና አሁን ያሉበት ሁኔታም ምን እንደሆነ በጭራሽ አይታወቅም፡፡  

- Advertisement -

ከዚህ በላይ የተገለጸው በአጭሩና በግርድፉ የሁለት ዓይነት የተመድ ሠራተኞች ‹‹ወግ›› ነው፡፡ አንደኛው ኢትዮጵያ በ72 ሰዓታት ውስጥ ከአገር ውጡልኝ ያለቻቸው፣ ውጡልኝ በተባሉበት ጊዜ እንዲባረሩ የተሰጠው ውሳኔ በተሰጠ ጊዜ ከሰባቱ የተመድ ባለሥልጣናት መካከል አንዳቸውም ኢትዮጵያ ውስጥ የሌሉና ገና ድሮ የወጡ፣ የተቀሩት ደግሞ ለደኅንነታቸው ሲባል ዘወር እንዲሉ የተደረጉ የተመድ ባልደረቦች ታሪክ ነው፡፡ ይህ አሉባልታ ሳይሆን በተመድ ዋና ጸሐፊ ምክትል ቃል አቀባይ ፈርሀን ሀቅ የተናገሩት ነው፡፡ እነዚህ የተመድ ሠራተኞች የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ የጠራላቸው/የተሰበሰበላቸው ናቸው፡፡ ተመድ በዋና ዋና ፕሪኒሲፓል በሚባሉ የሥልጣን አካላቱ አማካይነት (ቢያንስ ቢያንስ በፀጥታው ምክር ቤትና በዋና ጸሐፊው አማካይነት) እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ ያዙኝ ልቁቁን ያለላቸው የተመድ ባልደረቦች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን በተመድ ጥቅም ላይ ብርቱ ጥፋት ፈጽመዋል፣ ለተመድ ለመሥራት የመታመን ብቃትና ክብር የሌላቸው ሰዎች ናቸው አሰናብቻቸዋለሁ፣ በሌላ ተኩልኝ ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡

ተመድ፣ ወይም በተመድ ሥርዓት ውስጥ የሚገኙ ‹‹እናት›› ድርጅቶች በደብዳቤ ከደንበኛው ምድብ የሥራ ቦታቸው ከኢትዮጵያ በ‹‹አዋራጅ›› ደብዳቤ፣ ለጊዜው አድሚኒስትሬቲቭ ሊቭ (አስተዳደራዊ ዕረፍት) በሰጠ መጥሪያ ከሥራ ያነሷቸው ማውሪን አይቺንና ዴንያ ጌል ግን እውነቱን ወይም እነሱ እውነት ያሉትን፣ የሚመጣውን ጣጣና መዘዝ፣ ጠንቅና አደጋ እያወቁና ሳይፈሩ፣ ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ጥቅም ሳይራሩና ሳያዳሉ ኢትዮጵያ ዩኤን ሲስተም ውስጥ ሥርዓት ተዛብቷል፣ ሕግ ተጥሷል፣ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ዩኤን ካንትሪ ቲም ላይ መፈንቅለ አስተዳደር ተፈጽሟል በማለታቸው፣ የራሱ የተቋሙ ‹‹የዊስልብሎወርስ›› ፖሊሲ እንኳን የይስሙላ መከላከል ሳያደርግላቸው ምስኪንና ብኩን ሆነው ቀርተዋል፡፡ እነዚህን ሰዎች የበላ ጅብም እነሆ ሳይጮህ አንድ ዓመት ሞልቶናል፡፡

የእነዚህ ሰዎች የራሳቸው ጉዳይ በገዛ ራሱ ምክንያት ራሱን ችሎ የሚቆም የመብት ጉዳይ ነው፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅትን የመሰለ አሠሪ የሥራ ሁኔታና የሥራ ሕግ እንዲህ ለጅብ የሚሰጥ ሆኖ ስለመገኘቱ ካልተመረመረ፣ እንዴት ተመድ ለዓለም ሰላም የመቆም ባህርይ ይኖረዋል? ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለእውነትና ለሰው ልጆች ክብር የቆመ ማኅበር እውነት መናገርን የሚፈራና የሚከላከል ከሆነ፣ እውነት አልናገርም ካለ፣ እውነት ተናገራችሁ ብሎ ከመደበኛ ሥራ ቦታ ጠርቶ እንዲህ ደብዛ፣ አድራሻና ድራሽ ‹‹የሚያጠፋ›› ከሆነ፣ ራሳቸውን የግል ተበዳዮችንም፣ ባልደረባ ሠራተኞችንም እንዲህ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በሚሠሩ ሠራተኞች እንዳደረገው ዓመት ሙሉ ፀጥና ረጭ ማድረግን ከቻለ፣ ተመድ ሲስተም ውስጥ እውነትን ለባለሥልጣንና ለሥልጣን መናገር መኗኗሪያ ካልሆነ፣ እውነት መከላከያና መከራከሪያ ካልሆነ፣ ተመድ ኖረ አልኖረ ምን ያደርጋል? የተመድን የሥራ ሁኔታ የሚገዛው የሥራ ሕግ ብቻ ሳይሆን፣ እሱን የመሰለ ታላቅ ዓለም አቀፋዊ ተቋም አምኖ እኩይ ሥራን፣ አደጋን፣ ሴራን አጋልጣለሁ ማለት የሕግ ጥበቃ ያጣል፡፡ ይህ አንደኛው ራሱን የቻለ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ደግሞ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ተመድን ራሱን ለጥቃት፣ ለአደጋና ለጉልበተኛ ሴራ የዳረገ መፈንቅለ ተመድ ያልነው ተግባር አለ፡፡

ጉዳዩን በዝርዝር መረዳት ይረዳ ዘንድ በተለይም ኢትዮጵያ ውስጥ ተመድ ላይ ስለተፈጸመው ወይም ተፈጸመ ስለሚባለው የኃይል ሥራ (መፈንቅለ ተመድ) በደንብ ማወቅ እንዲያግዝ፣ መጀመርያ ከተቋሙ ፍጥርጥርና አሠራር እንጀምር፡፡ ይህም የዩኤን ሲስተም የሚባለው ነው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥርዓት ወይም የዩኤን ሲስተም የሚባለው፣ እሱኑ ጨምሮ በስም በስማቸው ለይተን ለየብቻ የምናውቃቸውን ፈንድና ፕሮግራም እየተባሉ የሚጠሩትን፣ እንዲሁም ስፔሻላይዝድ ኤጀንሲስ የሚባሉትን ድርጅቶች ያካትታል፡፡ ራሱ ተመድ ዋና ዋናና አውራ ወይም ፕሪንሲፓል ኦርጋን የሚባሉ የሥልጣን አካላት አሉት፡፡ ጠቅላላ ጉባዔው፣ የፀጥታ ምክር ቤቱ ወይም ሴኪዩሪቲ ካውንስሉ፣ የኢኮኖሚና የሶሻል ካውንስል የሚባለው፣ ሴክሬታርያቱ (ጽሕፈት ቤቱ)፣ ኢንተርናሽናል ኮርት ኦፍ ጀስቲስ የሚባለው ሄግ የሚገኘው የተመድ የዳኝነት አካል/ፍርድ ቤቱ፣ እንዲሁም እ.ኤ.አ. በ1994 ሥራውን የገታው ትረስትሽፕ ካውንስል የሚባለው እነዚህ ስድስቱ የተመድ ዋና አውራ አካላት ናቸው፡፡ ፈንድ ወይም ፕሮግራም የሚባሉት እነ ‹‹UNDP – UNEP UNFPA, UN Habitat, UNICEF, WFP›› ናቸው፡፡ እነዚህ በጠቅላላ አነጋገር በመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ/ሪዞሉዩሽን የተቋቋሙ ናቸው፡፡ ስፔሻላይዝድ ኤጀንሲስ የሚባሉት 15 ያህል ድርጅቶች ከላይኞቹ የተለዩ (በአቋቋማቸው የሕግ መሣሪያ ዓይነት) ከተመድ ጋር በውል የሚሠሩ ናቸው፡፡

በእያንዳንዱ አገር ውስጥም ተመድ ያለው፣ የሚኖረው ቁጭ ቁጭ ባሉ በእያንዳንዱ ተቋሙ አማካይነት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ተመድ የሚኖረው፣ የሚሠራው በዩኤን ሲስተም አማካይነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የተመድ አባል አገር ናት፣ መሥራችም ናት፡፡ የተመድ ሲስተም በኢትዮጵያም በዓለም ውስጥ ግዙፍ ናቸው ከሚባሉት መካከል አንዱ ነው፡፡ በየአገሩ ያለው የተመድ ሲስተም ወይም የዩኤን ሲስተም የዩናይትድ ኔሽንስ ካንትሪ ቲም (UNCT) የሚባል አመራር አለው፡፡ ከ193 አባል አገሮች መካከል በ180 አባል አገሮች ውስጥ ያለውን የተመድ ሥርዓት የሚያስተባብረው 136 አገሮች ውስጥ የተቋቋሙ ‹‹UNCT››ዎች ወይም ካንትሪ ቲሞች ናቸው፡፡ እያንዳንዱን የተመድን ካንትሪ ቲም የሚያስተባብረውና የበላዩ ሆኖ የሚመራው የዚያ አገር ቲም ‹‹UNRC›› ዩኤን ሬዚደንት ኮኦርዲኔተር ወይም ‹‹UNRC››ም ‹‹UNHC››ም ማለትም ዩኤን ሬዚደንት/ሒዩማኒቴሪያን ኮኦርዲኔተር ጭምር የሚባለው ሹም ነው፡፡ በአንድ አገር ደረጃ የተመድ ሥርዓት (የዩኤን ሲስተም ከፍተኛው ባለሥልጣን ‹‹UNRC/HC›› ነው፡፡ የአንድን አገር የመንግሥታቱን ድርጅት ሲስተም የሚመራውና የሚያስተባብረው ይኼው የተመድ ሬዚደንት ኮኦርዲኔተር (RC or R/HC) እና ወይም ሒዩማኒቴሪያን ከኦርዲኔተር የሚባለው ኃላፊ ነው፡፡ ይህን ከፍተኛ የሥልጣን ቦታ የሚመለምለውና የሚሾመው (የሚሾምበትን አገር መንግሥት ስምምነት መኖሩን አረገግጦ) በተመድ ዋና ጸሐፊ ነው፣ ተጠሪነቱም ለእሱ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ያለው የተመድ ሥርዓት አመራር የ28 የተመድ ፈንዶችን፣ ፕሮግራሞችና ስፔሻላይዝድ ኤጀንሲዎችን ሥራ የሚያስተባብሩት የእነዚህ እንደራሴዎች በሙሉ የተካተቱበት አመራር ነው፡፡ የዚህ አመራር ቁንጮ ማለትም የኢትዮጵያ ዩኤንሲቲ ካንትሪ ቲም ‹‹UNCT›› አርሲ/ኤችሲ (RC/HC) አሁንም ዶ/ር ካተሪን ሶዚ የሚባሉት ኡጋንዳዊ ሲሆኑ፣ በዚያ ጄፍ ፒርስና ሁለቱ የተመድ የሥራ ባልደረቦች በሚነጋገሩበት፣ በሚወያዩበት የድምፅ ቅጂ ውስጥ ‹‹ስማቸው›› ሳይሆን ማንነታቸው የሚነሳውና በግልጽ የሚነገረው እኚህ ሴትዮ ናቸው፡፡   

ማውሪን ኤቺንግ በኢትዮጵያ የአይኦኤምና የኢንተርናሽናል ኦርጋናይዜሽን ፎር ሚግሬሽን (IOM) ተጠሪ፣ ዴንያ ጌል የዩኤን ኤፍ ፒኤ (UNFPA) የተመድ ፖፑሌሽን ፈንድ (የተመድ የሕዝብ ጉዳዮች ድርጅት) ተጠሪ ሆነው በሚሠሩበት ወቅት በአፍሪካም ኅብረት፣ በኢጋድም፣ እንዲሁም በኢሲኤ (ECA) የየእናት ተቋማቸው ተጠሪ ሆነውም ያገለግሉ ነበር፡፡  ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በተመድ ሥርዓት ውስጥ የኢትዮጵያ ካንትሪ ቲም አመራር የ28 ፈንዶች፣ ፕሮግራችሞና ስፔሻላይዝድ ኤጀንሲዎች ወኪሎች/ተጠሪዎች የተገነባ በመሆኑ፣ እነዚህ ሁለት የተመድ ሠራተኞች/ባለሥልጣናት የኢትዮጵያ ካንትሪ ቲም አመራር አካል አባላትም ነበሩ፡፡

የተሰረቀውና ሆን ተብሎም አፈትልኮ እንዲወጣ (Leak) የተደረገው ‹‹ነገረኛው››፣ ‹‹መከረኛው›› እና አወዛጋቢም ሊባል የሚችለው የጄፍ ፒርስ የኦዲዮ ቅጂ (ወይም በድሮ ቋንቋ ‹‹ቴፕ››) ውይይት ይዘትና ቁም ነገር የሚገባንም ከዚህ ከፍ ሲል ከገለጽኩት ዳራ፣ የተመድ አሠራር ግንዛቤ ጋር ነው፡፡ ወደ እዚህ ‹‹ቴፕ›› ይዘትና ዝርዝር ወይም ጠቋሚ ቁምነገሮች ውስጥ ከመግባታችን በፊት ግን የዚህን ‹‹ነገረኛ››፣ ‹‹መከረኛ›› ያልኩትን ውይይት አመጣጥ የምናውቀውን ያህል አረጋግጦ ማስቀመጥና መጨበጥ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ፒርስ ፕራይም ሎግ በተባለ የዩቲዩብ ቻናል ላይ ከልደት ሙለታ ጋር ጥቅምት 6 ቀን 2014 (ኦክቶበር 16 ቀን 2021) በተላለፈ ዝግጅት ባደረገው ውይይት (ቃለ ምልልስ) እንደገለጸው፣ ካነጋገራቸው ሁለት ሰዎች መካከል መጀመርያና ከዚያ ብዙ ቀደም ብሎ ከአንደኛዋ ጋር በ‹‹ሶሻል ሚዲያ›› አማካይነት እንደተገናኘ፣ እሳቸው ጄፍ ፒርስን እንዳገኙ፣ እንደቀረቡት፣ ‹ለምን አንነጋገርም፣ የማናግርህ የምነግርህ፣ የምንነጋገረው ነገር አለ› ዓይነት ነገር እንዳሉት፣ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ምንም ነገር እንደማያውቅ፣ ምንም ዓይነት ፍንጭ የሌለው መሆኑን ገልጾ፣ ኋላ ላይ ኦውገስት 2021 አዲስ አበባ በመጣ ጊዜ አሁን አዲስ አበባ ነህ፣ ለምን አንነጋገርም እንደተባለ፣ በዚህ ሳቢያ ተገናኝተው አንደኛዋ ከሌላዋ ጋር እንዳስተዋወቁት፣ በዚህ ትውውቅ አማካይነት ከእነሱ ጋር ሊነጋገር እንደቻለ፣ የተባለውን መረጃ እንዳገኘ፣ እንደቀዳ፣ እንደቀረፀ ይነግረናል፡፡ ጋዜጠኛው/ደራሲው ከእነዚህ የመረጃ ምንጮች ጋር ያደረገው ውይይት/ንግግር ረዥም ጊዜ የወሰደ መሆኑን ከመግለጽ ጋር ዲጂታል ሪከርደሩ ላይ የቀረፀው ግን የ22 ደቂቃ ርዝመት ያለው እንደሆነ፣ ይህንንም ወደ ላፕቶፑ እንደገለበጠው፣ ከዚያም ትራንስክራይብ እንዳደረገውና እንደተገለገለበት ጭምር ይነግረናል፡፡

ከኢትዮጵያ ወደ አገሩ ሲወጣ ግን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ እንደተሰረቀበት ይገልጻል፡፡ ተሰረቀ እንጂ ሆን ተብሎ እንዲነዛ/እንዲባዛ አልተደረገም ይላል፡፡ ይህንንም ሲያስረዳ ቦሌ ኤርፖርት ሴኪዩሪቲ ቼክ (የፍተሻ ሒደት ውስጥ) የመጀመርያው ፍተሻ ነጥብ ላይ ዲጂታል መቅጃውን ከኪሱ አውጥቶ ዕቃዎች በፍተሻ ማሽን ውስጥ ሲያልፉ በሚቀመጥበት ትሬ ላይ እንዳስቀመጠው፣ እዚህ የመጀመርያ ፍተሻ ላይ ተፈትሾ አልፎ ወጥቶ ሁለተኛው የፍተሻ ነጥብ ላይ ከደረሰ በኋላ ዲጂታል ሪከርደሩን እንዳጣው፣ በሁለቱ የፍተሻ ነጥቦች መካከል ንብረቱን የት ቦታ እንዳጣው በደንብ እንደማያስታውስ ይገልጻል፡፡ ከሁለተኛው የፍተሻ ነጥብ ወዲህ ያሉ የአውሮፕላን ማረፊያው ሠራተኞችን ስለጉዳዩ ማስረዳቱን፣ ሊረዳው የሚችል ሰው ማጣቱን፣ እንዲያውም ከሠራተኞቹ መካከል አንዱ ሞገደኛ (Belligerent) እንደሆነበትና ወደኋላ ብትመለስ የሴኪዩሪቲ ሒደት ውስጥ እንደገና ሀ ብለህ ትጀምራለህ ብሎ ያላሰበውን አማራጭ እንደገለጸለትና እንዳስጠነቀቀው ይናገራል፡፡ ከተወሰደበት/ከጠፋበት ዲጂታል ሪከርደር ውስጥ ከነበረው ባለ 22 ደቂቃ ውይይት ውስጥ መቅጃውን በወሰዱት ሰዎች አማካይነት አደባባይ የወጣውና የተሠራጨው የ12 ደቂቃ ርዝመት ያለው ንግግር መሆኑንም ይገልጻል፡፡

በጄፍ ፒርስ በራሱ ትረካ መሠረት የነገሩ አመጣጥ ይህንን ይመስላል፡፡ ኢትዮጵያ የተመድ ሥርዓት (ዩኤን ሲስተም) ውስጥ፣ ለዚያውም ከፍተኛው የአመራር ጉልላት ውስጥ ካሉ ቁልፍ ሰዎች መካከል አንደኛዋ ቀረቡት፣ ሁለት ሆነው አነጋገሩት፡፡ እዚያ ‹‹ቤት›› ምን እንደሚሠራ ነገሩት፡፡ የቀረፀውን የድምፅ መረጃ እንዲጠቀምበት ፈቀዱለት፡፡ ወደ አገሩ ሲወጣ ዲጂታል ሪከርደሩና እሱም የያዘው መረጃ ወጣ፡፡ የምናውቀው ይህንን ያህልና ጄፍ ፒርስ የነገረንን ያህል ብቻ ነው፡፡

ወደ ዋናው ጉዳይ፣ የጄፍ ፒርስ ምንጮች ወደ‹‹አፈነዱት›› ወደ አጋለጡት ጉዳይ እንመለስ፡፡ መጀመርያ ይዘቱን በአጭሩ እንመልከት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘው የተመድ ሥርዓት አደጋ ውስጥ መውደቁን ያጋልጣል፡፡ በእያንዳንዱ አገር የመንግሥታቱ ድርጅት የተዋቀረውና የተደራጀው በዚያ አገር ለሚገኘው ለመላው የተመድ ሥርዓት፣ ተመድን ወክሎና አክሎ እንድ ሰው እንዲመራውና እንዲናገር በሚያስችል አኳኃን ነው፡፡ ያ ሰው ደግሞ ‹‹RC››ው ነው፡፡ የኢትዮጵያ የተመድ የአገር ቤት ቡድን (UNCT) እና የዚህ የበላይ አስተባባሪ (RC/HC) አደጋ ውስጥ ወድቋል፡፡ ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው ሁኔታ ‹‹ስኬል አፕ›› ከመደረጉ፣ ከማደግ ከመመንደጉ ጋር የክልሉን የአደጋ ጊዜ አስተባባሪዎች ከፍ ያለ ርብርብ ይጠይቃል፡፡ እነዚህ የክልል አስተባባሪዎች ግን ቀጥታ ሪፖርት የሚያደርጉት ያለ ኢትዮጵያ የአገር ቤት ቡድንና ያለ ኃላፊዋ ዕውቀት፣ ይልቁንም ከእሳቸው ትዕዛዝና ቃል ውጪ አዲስ አበባ ውስጥ ሠፍረውና ‹‹ወረው›› ለተቀመጡ ኢመርጀንሲ ዳይሬክተርስ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የሰሜን ኢትዮጵያ (የክልሉ) ግንኙነት ቀጥታ ከኒውዮርክ፣ ከጄኔቫና ከሮም ጋር ነው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኤን (ተመድ) ወደ ጎን ተትቷል፡፡ ይህንንም ማን እንዳደረገው ‹‹ምንጮቹ›› አይጠራጠሩም፡፡ ይመስለናል እንኳን አይሉም፡፡ በቀጥታ ይከሳሉ፡፡  ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) በየቦታው ከሚገኙ አቻ ባልደረቦቻቸውና ምክትል ዋና ጸሐፊዎች ጋር የሠሩት/የሚሠሩት ሥራ ነው ይላሉ (ይህ ባለ 12 ደቂቃ የድምፅ ቅጂ ከእነ ትራንስክሪፕቱ ዌብሳይት ላይ አለና አንባቢያን እንዲሰሙትና እንዲያዩት የምጠይቀው በአክብሮትና በትኅትና ነው)፡፡

እንደ ማንኛውም ከፍተኛና ቁም ነገር ያለው ‹‹ጥቆማ›› መጣራት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ የጠላት ወይም የ‹‹ምቀኛ ወሬ ነው ብሎ ነገር ካለ የሚጣራው አብሮ ነው፡፡ የመንግሥታቱን ድርጅት የመሰለ ለሰው ልጆች ሰላም፣ ለሰው ልጆች መብትና ክብር የቆመ ድርጅት ግን ሌላው ቢቀር ከወሰደው ዕርምጃ ጋር ጉዳዩ ይጣራ አላለም፡፡  የወሰደው ዕርምጃ ደግሞ እነዚህን በኢትዮጵያ የአይኦኤም (IOM) እና የዩኤንኤፍፒኤ (UNFPA) የበላይ ኃላፊዎች ብቻ አይደለም በኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ድርጅት ቁንጮ አመራር አባላት በድምፃቸው ብቻ ለይቶ፣ ጥቅምት 1 እና 2 ቀን 2014 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ ወደ ጠቅላይ መምርያው ጠራ፡፡ ከዚያ በኋላ እዚህን ዘመናዊ ሥልጣኔና ተመድ ራሱ ‹‹ዊስልብሎወርስ›› ብሎ የሚጠራቸውንና የሕግ ጥበቃም አደርግላቸዋለሁ የሚላቸውን ሰዎች መብት (ድርብርብ መብት) ረግጦ የአገራችን ሰው እንደሚለው፣ ‹‹እንደ መፋቂያ እንጨት ከመንገድ ቆረጣቸው››፡፡ በአንፃሩ እነዚህ የከፍተኛ አደጋ ጠቋሚዎችና አጋላጮች የተናገሩት ስሞታ፣ ውንጀላ ወይም ክስ የሚነካካቸውና የሚመለከታቸው የሚመስሉ ሰባቱ የተመድ ሠራተኞች ጉዳይ የፀጥታውን ምክር ቤት የሁለት ስብሰባዎች ትኩረት አገኘ፡፡ ይህም ኢትዮጵያን የፀጥታው ምክር ቤት አጀንዳ የማድረግ እንጂ፣ ለተመድ ሠራተኞች መብት/ወይም ለተመድ ሥራ ነፃነት የተባለው አለመሆኑን የ77 ዓመት የድርጅቱ ታሪክና ተሞክሮ ያረጋገጠው አሠራር ነው፡፡ ተመድ በተቋቋመበት ዓላማና ይረማመድባቸው ዘንድ በተዘረጉ ሕጎች ማዕቀፍ ውስጥ ደህናና ጥሩ ነገር መሥራት የሚችለው ጉልበተኛና ኃይለኛ አገሮች፣ በተለይም አሜሪካ በፈቀዱለትና ሸምቀቆውን ባላሉለት ልክ ብቻ ነው፡፡

በዚህ ወሳኝና ቀውጢ ጊዜ፣ የራሱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትንና አጠቃላይ የተመድን ሥርዓት ተጨባጭ አሠራር ‹‹መታዘብ›› ባስቻለን በዚህ ገና ዕልባት ያላገኘ የጦርነት ሁኔታ ውስጥ ሆነን፣ የተመድ ሠራተኞችን እነዚህን ሁለት ዓይነት ወጎች በዓመቱ/በክብረ በዓሉ ብቻ ሳይሆን መልሰን መላልሰን ማስታወስና ተገቢውን ጥያቄ እያነሳን ትርጉም ያለው ውይይት ማድረግ ያለብን ለእያንዳንዳችንና ለየራሳችን መኗኗሪያ ላደረግነው ሕግና ሥርዓት ስንል ነው፡፡ እነዚህን ሁለት የተመድ ሹማምንት እንደ ቀልድና እንደ ዘበት ‹‹የበላ ጅብ›› ምነው ድምፁ ጠፋ ብሎ መጠየቅ በስምና በአካላቸው እገሌ ተብለው የሚጠሩ የእነዚህ ግለሰቦች መብት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ እውነትንም የመናገር ጉዳይ ነው፡፡ ተመድን ራሱን የማጠናከር ነገር ጭምር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ‹‹UNCT›› ውስጥ፣ እዚያ በሚሠሩ፣ ሲሠሩ በኖሩ ሠራተኞች በተራ የሥራ ሁኔታ ስምና አማካይነት ሊነሳና ሊጠየቅ፣ ሊወያዩበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ የአገራችን ሚዲያ ራሱ የእነዚህን ሰዎች ጉዳይ አንስቶ ሰፊና ጥልቅ ሥራ ውስጥ መግባት ያለበት፣ የእነዚያ የሁለት ሰዎች ጉዳይ የኢትዮጵያ ጉዳይ፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ ደግሞ የሚዲያው ጉዳይ ከሚል ረቂቅ ሎጂክ ብቻ ሳይሆን፣ ይህ የራሱ የሚዲያው ጉዳይ ስለሆነ ጭምር ነው፡፡ ጄፍ ፒርስ የድምፅ መረጃ ላይ የደረሰው አደጋ፣ ወይም ይህን መረጃ ያጋጠመው አደጋ፣ ወይም ሌላ ነገር እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ሕጎች ብቃትና ጥራት ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን የባለሙያዎችን ንቃትና ግንዛቤ ጭምር የምንመረምርበት ‹‹መልካም›› አጋጣሚ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...