Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አገራዊ የምክክር መድረኩ ኢትዮጵያን የምናፀናበት እንዲሆን እንፈልጋለን›› አቶ ግርማ ሰይፉ፣ የኢዜማ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የትይዩ ካቢኔ ተወካይ

ግርማ ሰይፉ የኢዜማ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የትይዩ ካቢኔ ተወካይ ሲሆኑ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነርም ናቸው፡፡ ዮናስ አማረ  በወቅታዊ የአገሪቱ ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከእሳቸው ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ሙስናና ምዝበራን መከላከል በተመለከተ ዘንድሮ የመንግሥት ዋና የትኩረት አቅጣጫ ተብሎ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው በጀት ዓመት መገባደጃ ላይ የቀረበ ነገር አለ፡፡ ሙስናና ምዝበራን እርስዎ በግልዎም ሆነ ኢዜማ በኢትዮጵያ ምን ዓይነት ገጽታ የያዘ ችግር ነው ትላላችሁ? የኢትዮጵያ የሙስና ተጋላጭነትስ ምን ይመስላል?

አቶ ግርማ፡- አበረታችና እያደገ ያለ (ሳቅ)፡፡ እንደ አገር ቀስ በቀስ እየሸረሸረን የሄደ ጉዳይ ነው፡፡ ምናልባትም የህልውና አደጋ ነው፡፡ እንደ አገር የሆነ ጉዳይ ከፈለግን አንዱ ሌብነት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ችግሩን መከላከል አንድ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን በተለያዩ መንገዶች እንዲስፋፋ ድጋፍ የሚሰጠው ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ችግር ለመከላከል ቁርጠኛ የሆነ የፖለቲካ አመራር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጠንካራ የሰብዕና ግንባታ ሥራ በልጆች ላይ እየሠራን የማንሄድ ከሆነ፣ እንደ አገር የህልውና አደጋ ችግር ይገጥመናል፡፡ ወረራን እኮ በጦርነት ትዋጋዋለህ፡፡ ይህ ግን ለውጊያም ምቹ ያልሆነ ከወረራ በላይ አደጋ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ በራሱ ጊዜ ቀስ በቀስ ጠልፎ የሚጥል ችግር ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሙስናን ሰዎች ገንዘብ ባለውና በባለሥልጣን መካከል የሚደረግ የጥቅም ግንኙነት አድርገው ይመለከቱታል፡፡ በመሠረታዊነት መገለጫው እሱ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ችግሩና ውጤቱ በዋናነት የሚታየው በደሃ በዜጎች ላይ ነው፡፡

      አሁን የሚታየው የኑሮ ውድነት በደሃ ዜጎች ላይ ተፅዕኖው እንደሚከብድ የምናየው ነገር ነው፡፡ ለአብነት የመኖሪያ ቤት ኪራይና ግዥ ውድነትን ብታይ የሚሰርቁ ሰዎች በፈለጉት ዋጋ መሬት ገዝተው ቤት ይሠራሉ፡፡ የሚሰርቁ ሰዎች በፈለጉት ዋጋ ተከራይተው መኖርም ይችላሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ግን በሀቁ ሠርቶና ለፍቶ የሚኖር ሰው ተከራይቶ የሚኖርበት ቤት እንኳ ያጣል፡፡ በመሀል በኢኮኖሚው ውስጥ ሰርቆ አዳሪዎች ሲገቡ የገበያ መናጋት ሁሌም ይፈጠራል፡፡ ሰርቆ አዳሪ ለፍቶ ያመጣው ባለመሆኑ በአንድ ቀን አምስት ሚሊዮን ብር በትኖ ቢያድርም ምንም አይመስለውም፡፡ ይህ በቀን የሚበተን ሚሊዮን ብር ግን ተመልሶ በደሃው ላይ በዕዳነት መጫኑ የማይቀር ነው፡፡ ጉቦ ሲሰጥህም ደሃ ላይ ነው ዕዳው የሚጫነው፡፡ ሸቀጣ ሸቀጥ ከውጭ ይምጣም ሆነ እዚህ ይመረት መጨረሻ ላይ ዕዳውን የሚሸከመው ምስኪኑ ሸማች ዜጋ ነው፡፡ ይህ የምዝበራና የሙስና እሽክርክሪት ደግሞ በደንብ እየተስፋፋ ነው፡፡ ከሥር ከመሠረቱ አረሙን ነቅለን ካልጣልነው በስተቀር አንድ ቀን ተብትቦ ሁላችንንም ይጥለናል፡፡ ጤነኛውን ከታማሚው አይመርጥም፡፡ ጨዋ ስለሆንክ ከሙስና መቅሰፍት አትድንም፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፈው መንግሥትም ሙስና የሥርዓቱ መገለጫ ዋነኛ ችግር ሲባል ነበር፡፡ ለውጥ ከመጣ ወዲህም ባለው አስተዳደር ዓመታትም ሙስና አገሪቱን እየፈተነ ያለ ከባድ ችግር ሆኖ ሊቀጥል የቻለበት ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ ግርማ፡- ሰዎቹ እኮ አልተቀየሩም፡፡ የባህሪ ለውጥም ያስፈልጋል፡፡ ሙስናን መዋጋትም ቢሆን ቀላል ሥራ አይደለም፡፡ ‹ሙስና ይውደም!› ስላልክ በቀላሉ የሚወድም ነገር አይደለም፡፡ አንዳንዶች አሁንም ከደምና ከአጥንታቸው ጋር አስተሳስረው የተለመደ ባህላቸው አድርገውታል፡፡ ወጣቶች ስትቀጥር እኮ ‹ምን የሚገነጠል ነገር አለ?› ብለው ነው ወደ ሥራው የሚገቡት፡፡ እንደ ማኅበረሰብ እኮ ሙስናን እያወገዝነው አይደለም፣ እያበረታታነው ነው፡፡ በጣም አደገኛው ነገር ሠርቶ ሳይሆን፣ ለመበልፀግ መስረቅ መሠረታዊው መንገድ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ሀብት ለማፍራት ሰዎች የሚሄዱበት ሁሉም የነውር መንገድ አይደለም፡፡ አሁን አሁን ግን ሰዎች ካልሰረቁ አይበለፅጉም በሚል እምነት እየተኬደ ነው፡፡ ወጣቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዴት ገንጥለው መኪና እንደሚገዙና የቤት ባለቤት እንደሚሆኑ ማሰብ ላይ እየተጠመዱ ነው፡፡ ሙስናን እንደ ባህል እየተቀበልነው እንገኛለን፡፡ ስለዚህ ይህን ነገር እንደ ማኅበረሰብ ማነወር አለብን፡፡ ፀረ ሙስና የሚባሉ ተቋማት ትልቁ ሥራቸው መሆን ያለበት ሙስናን የማነወር፣ ሥራን ወጣቶችን ማዕከል ባደረገ መንገድ ማከናወን ሊሆን ይገባል፡፡ አባት ሰክሮ ቤት እንዳይገባ ብቻ ሳይሆን፣ አባት ሰርቆም ቤት እንዳይገባ መደረግ አለበት፡፡ ለልጆችና ለቤተሰብ የወላጆች ግልጽነት በደንብ ያስፈልጋል፡፡ ከየት አመጣህ ተብሎ ወላጅም መጠየቅ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ሙስና የፖለቲካ መገልገያ መሣሪያ ሆኗል ይባላል፡፡ ቀደም ሲል መንግሥት ሰዎች ሙስና ውስጥ እንዲነከሩ በማድረግ ለፖለቲካ ተፅዕኖ ማሳደሪያነት ይጠቀምበታል ሲባል ቆይቷል፡፡ ይህ ሙስናን መገልገያ የማድረግ ዝንባሌ አሁንስ በፖለቲካው የቀጠለ አይመስልዎትም?

አቶ ግርማ፡- በፊት ይደረግ ነበር፡፡ አሁን በአመራር ደረጃ እንደ እሱ ይደረጋል ብዬ ላምን አልችልም፡፡

ሪፖርተር፡- ሙስናን ለመዋጋት ቁርጠኝነቱ የጠፋው በዚህ ምክንያት ነው የሚሉ አሉ፡፡

አቶ ግርማ፡- ሙስናን ለመዋጋት ቁርጠኝነት ብቻውን በቂ ነው ማለት አይደለም፡፡ ሥርዓት መዘርጋት አለብህ፡፡ የምትመድባቸው ሰዎችም ለቦታው የሚመጥኑና ችግሩን በተጨባጭ የሚዋጉ መሆን አለባቸው፡፡ በፊት በነበረው መንግሥት ሙስናን ለፖለቲካ የመገልገል ዝንባሌ ነበር፡፡ በሙስና ማኖ ትነካለህ፣ ከዚያ የተፈለገውን የፖለቲካ ሥራ እንድትሠራ ትታዘዛለህ፡፡ አሁን ያለው ሥርዓት ግን የማትፈልገውን የፖለቲካ ሥራ እንድትሠራ በሙስና ተጠቅሞ የሚያስገድድ ነው ብዬ አላምንም፡፡ የብልፅግና አባል ሆነህ እንድትቀጥልና እንድታገለግለው፣ በሆነ የሙስና ታክቲክ ይጠቀማል ብዬ አላምንም፡፡ የዋህ ሆኜ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን አልፈልግም ብለህ ብልፅግናን ብትለቅ ማንም የሚከለክልህ የለም፡፡ በኢሕአዴግ ጊዜ ግን ይህ ሲሆን አይታይም ነበር፡፡   

ሪፖርተር፡- በቀበሌ፣ በወረዳና በተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮች ሰዎችን ለፖለቲካ ድጋፍ ማግኛ በአበልና በጥቅማ ጥቅሞች የመደለል ሙከራ አሁንም ቢሆን ቀጥሏል ይባላልና ይህ ሙስናን መገልገያ የማድረግ መገለጫ አይባልም?

አቶ ግርማ፡- እሱ ሌላ ነገር ነው፡፡ ንቅናቄ እያሉ የሚያደርጓቸው እንዲህ ዓይነት ሥራዎች የፖለቲካ በሽታቸው ዋና መገለጫዎች ናቸው፡፡ ሥራቸውን የሠሩ የሚመስላቸው ይህንን ዓይነት ነገር ሲያደርጉ ነው፡፡ ሆኖም ዳቦ የሚገዙበት ለሌላቸው ሰዎች ሠልፍ እንዲወጡልህ አበል ብትከፍላቸው ሰዎቹ ጉቦ ተቀበሉ ብሎ ለመፍረድ ያስቸግራል፡፡ ገንዘብ ሰጪዎቹ ፖለቲከኞች ሥራቸውን የሚሠሩበት መንገድ የተሳሳተ ስለሆነ እንጂ፣ እነዚያ ምስኪኖች ግን አበሉን የተቀበሉት ለዕለት ጉርሳቸው ነው፡፡ ካልተሠለፉ በሚቀጥለው ቀን ከሥራ ሊሰናበቱም ይችላሉ፡፡ ሲቪል ሰርቪስ ውስጥም ያለው ሠራተኛ ቢሆን ብዙኃኑ በዚህ ደረጃ የሚገኝ ነው፡፡ ይህ በኑሮ አስገዳጅነትና በፖለቲከኞች የተዛባ አመለካከት የመጣ ነው፡፡ አሁን በገንዘብ ገዝቶ የፖለቲካ ሥራ ላሠራህ የሚልህ ኃይል የለም፡፡ አሁን ያለው ከዚያ ይልቅ መሄጃ የሌለው ተሿሚ ነው፡፡ የሆነ ሥራ ሠርቶና አሳክቶ ሳይሆን፣ ሹመትን ዋና ግቡ አድርጎ የሚመጣ ተሿሚ አለ፡፡ የፖለቲካ ሹመት በሥራ ወይም በልፋት የሚገኝ ስኬት አይደለም፡፡ በሌላ አገር ሹመት ሁሉን ነገር ጨርሰህና የግል ኑሮህን አሳክተህ ሕዝብ ለማገልገል የምትይዘው ቦታ ነው፡፡ እዚህ ግን ሹመት የኑሮ መሠረት ነው፡፡

ከሹመት በኋላ ሲሰናበት ብዙ ሰው መሄጃ ያጣል፡፡ አንዳንዱ ከሹመት በኋላ ኤክስፐርት ሆኖ ለመሥራትም ዝግጁ ላይሆን ይችላል፡፡ ሹመት በጥረት የሚገኝ ባለመሆኑ፣ ከሹመት ስነሳ ምን እሆናለሁ ብሎ ሹመቱን ለሌብነት የሚጠቀምበት አለ፡፡ ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› ከእነ አባባሉ እንደሚባለው፣ ሹመት የጥቅም ቦታ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ለአገልግሎት ሳይሆን ለሌብነት ይውላል፡፡ ሹመት ሕዝብ ማገልገያ ቢሆን ግን፣ ልክ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ሲያልቅ ወደ ቤትህ እንደምትሄደው ሁሉ ስትሻርና አገልግሎትህ ሲያበቃም ምንም ሳይመስልህ የመሰናበት ባህል ይኖረን ነበር፡፡       

ሪፖርተር፡- እርስዎ አሁን ባሉበት የአዲስ አበባ ከተማ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን በቅርበት ለመታዘብ ይረዳል ተብሎ ይታመናል፡፡ በፓርቲዎ ኢዜማ በኩልም ቢሆን የመሬት ወረራን ጨምሮ የሙስና ተጋላጭ የሆኑ ዘርፎችን ስታጠኑ ነበር፡፡ ሙስና በከተማው ውስጥ አሁን ያለው ገጽታ ምን ይመስላል የሚለውን በማሳያዎች ቢያስረዱ?

አቶ ግርማ፡- ያለሁበት ዘርፍ ለሌብነት ምቹ የሆነ ነው፡፡ እየቆለፍክና መንገድ እየዘጋህ የዜጎችን ጥቅም አሳጥተህ የራስህን ጥቅም ልታጋብስበት የምትችልበት ዘርፍ ነው፡፡ እኛ ጋ የነበሩ አብዛኞቹ ችግሮች ከአሠራር ጋር የተያያዙ ነበሩ፡፡ ሥርዓት የተበጀለትና ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝንበት ብልሹ አሠራር የሠፈነበት ነበር፡፡ አንዳንዴ ምንም እሴት የማይጨምር የአገልግሎት ቅድመ ሁኔታ ይጠየቅ ነበር፡፡ ደንበኞች እነዚህን ነገሮች ለማሟላትና ልፋት ለመቀነስ ሲሉ፣ በሕገወጥ መንገድ ለማስፈጸም ሲሉ ሙስና ተቀባይ ለመሆን ይገደዳሉ፡፡ የሚጠየቁትን ለማሟላት መንገድ የሚጠቁም ወገን ይኖራል፡፡ በዚህ ሒደትም የሚጠየቁትን እንዲከፍሉ ይገደዳሉ፡፡ በዚህ መሰሉ የተቆላለፈ መንገድ ነው ሙስናው የሚፈጸመው፡፡ እኔ ወደ እዚህ ቢሮ ስመጣ እንዲህ ዓይነት አካሄዶችን ቀይረናል፡፡ ግልጽ የሆኑ አሠራሮችን መፍጠር ብቻ ሳይሆን የተዘረጋውን አሠራርም እንዲታወቅ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ግልጽ አሠራርም ተዘርግቶ አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች ሥራቸውን ቶሎ መገላገል ስለሚፈልጉ የሕገወጥነት ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ አገልጋዮችም ይህን የተገልጋዮችን ጉጉት በመመልከት በኋላ ተመለስ፣ ቶሎ እንዲያልቅልህ፣ ወዘተ እያሉ ገንዘብ ማግኛ መንገዶችን ይፈጥራሉ፡፡ በየትም ተቋም እንግልት ካለ በመጨረሻ ሌብነት አለ፡፡ ገንዘብ ስጠኝ አይልህም፡፡ እንግልቱን ሰዎች ሲያጋጥማቸው በመጨረሻ ሌላ አማራጭ መንገድ መፈለጋቸው አይቀርም፡፡

ሰዎች የሚጠበቅባቸውን አሟልተው ከመጡ አገልግሎቱን ለምን አያገኙም? ሰዎች መብታቸውን ለማግኘት ለምን ይሠለፋሉ? አንዳንድ ጊዜ ሠልፉን የሚያበዙብን አውቀው ነው፡፡ ተሠልፈህ እንድታመሽ ለማድረግ በሥራ ሰዓት ሻይ ቤት ይሄዳሉ፡፡ እዚህ ቤት ለምሳሌ የሥራ ወይም የሻይ ሰዓት የሚባል የለም፡፡ ደንበኛ እያለ ለሻይ ወይም ለምሳ ብለህ ልትወጣ አትችልም፡፡ መዝገብ ቤት ለማኅተም ስትሄድ ማንም ‹ምሳ ሰዓቴ ነው› ሊልህ አይችልም፡፡ ከሥራው በኋላ ምሳውን ይበላል፡፡ መብቴ ነው ወይም ሰዓቴ ነው አይሠራም፡፡ አገልጋይ ስትሆን ትንሽ መብትህንም መሽረፍ አለብህ፡፡ ይህን ዓይነቱን ልምምድ ደግሞ እኔው ነኝ በራሴ ማሳየት ያለብኝ፡፡ እኔ ካሳየሁኝ ሌላው ሠራተኛ አያደርገውም፡፡

ሪፖርተር፡- አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞች የሚያገኙት ጥቅማ ጥቅምና ገቢ የማያበረታታ መሆኑ ወደ ሙስናና ምዝበራ እንዲገቡ ይገፋፋል ይባላል፡፡

አቶ ግርማ፡- ይህ አንዱ ለሌብነት ምክንያት ተደርጎ የሚቀርብ ነገር ነው፡፡ የማገኘው ጥቅም የማያበረታታ መሆኑ ለሌብነት ፈቃድ ሊሆን ይችላል፡፡ አያበረታታም ይባላል፡፡ ካላበረታታ ሥራውን ጥሎ መሄድ ነው መፍትሔው፡፡ በነገራችን ላይ ብዙ ሚዲያዎች ዘንድ ያለው ችግር እኮ ይኸው ነው፡፡ ለመግለጫ ወይም ለዘገባ ሲጠራ ጋዜጠኛው ሁሉ አበል ከሌለው አልሄድም ይላል፡፡ መኪና ካልቀረበና አበል ካልተመደበ አልሄድም ይላል፡፡ ካላዋጣ ሥራውን መተው ነው እንጂ ደመወዙ ስለማይበቃና የማገኘው ስለሚያንሰኝ ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ ደመወዙ አልበቃ ያለውና የተሻለ ጥቅም እፈልጋለሁ ያለ በግሉ ነው መሥራት ያለበት፡፡ እኛ መሥሪያ ቤት ለምሳሌ ማንም ሰው የሚከፈለው በቂ ነው ብዬ አላምንም፡፡ እኔም ብሆን ደመወዙ አይበቃኝም፡፡ ሆኖም ግን ለሕዝብ አገልግሎት ነው ብዬ አምኜበት ነው የገባሁበት፡፡ ይሁን እንጂ ሌላው ሠራተኛም ቢሆን በሚያገኘው ደመወዝ አገለግላለሁ ብሎ ፈቅዶ እስከገባ ድረስ፣ በሚያገኛት ገቢ ሥራውን አክብሮ መሥራት ነው ያለበት፡፡ ደመወዙ ስለሚያንሰኝ መስረቅ ይፈቀድልኝ ማለት አይቻልም፡፡ ሁሉም ሰው በሥራ ገበያው ላይ ተወዳድሮ ነው የሚቀጠረው፡፡ ሌሎች ሥራ ያላገኙና ዕድል አጥተው የሚንከራተቱ ብዙ ዜጎች እያሉ፣ ደመወዙ ስለማይበቃኝ ብሎ ሙስና ለመፈጸም ምክንያት ማቅረብ አያስኬድም፡፡

እዚህ ቤት ለምሳሌ 150 ሠራተኞች አሉ፡፡ ነገር ግን ከዚህ ባነሰ የሰው ኃይልም ቢሆን አሁን ከሚሠራው ሥራ በጣም ውጤታማ የሆነ መሥራት እንደሚቻል አምናለሁ፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ የሥራ ሰዓት የሚያከብር የለም፡፡ ሌብነት ከዚህ ነው የሚጀምረው፡፡ አይደለም ስምንት ሰዓት፣ አራት ሰዓት በትክክል ለሥራ የሚያውል የለም፡፡ ሌላው ደግሞ በየተቋሙ ውጤታማ ሆኖ የሚሠራውና ተቋሙን ቀጥ አድርጎ የሚይዘው አራትና አምስት ሰው ቢሆን ነው፡፡ አብዛኛው ፈጻሚና ተከታይ እንጂ ውጤታማ ሥራ የሚሠራው ጥቂት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አገሪቱ ለሚገጥሟት የኢኮኖሚ ቀውሶችና የገበያ መናጋቶች ተደጋግመው ከሚነሱ ምክንያቶች ውስጥ የደላላ መብዛትና የኢኮኖሚ አሻጥር ይጠቀሳሉ፡፡ በተጨባጭ እነዚህ ነገሮች ችግር ናቸው ወይ? የመንግሥት ሥጋትስ ከየት ነው የሚመነጨው?

አቶ ግርማ፡- በመጀመሪያ አብዛኞቹ የኢኮኖሚ ችግሮቻችን ምንጭ እጥረት ነው፡፡ እጥረት ካለ በመሀል ገዥና ሻጭን የሚያገናኙ ሰዎች ይበዛሉ፡፡ በየደረጃው አገናኞቹ የየራሳቸውን ድርሻ ሲወስዱ፣ በመጨረሻ የሸቀጡ ዋጋ ተጠቃሚው ላይ መጨመሩም የማይቀር ነው፡፡ መፍትሔው ደላላን መስደብና ማውገዝ ግን አይደለም፡፡ ግብይት ፈላጊና ተፈላጊን የሚያገናኝ ድልድይ ያስፈልገዋል፡፡ የማታውቀውን ነገር ለመግዛት ስትነሳ የሚያውቁ፣ ስለምርቱና አገልግሎቱ የሚነግሩህ ሰዎች ያስፈልጉሃል፡፡ ለገዥ ብቻ ሳይሆን ለሻጭም ያስፈልገዋል፡፡ ይህ በተለምዶ ድለላ እየተባለ ከሚገፋ መደበኛ የሆነ ሥርዓት ቢዘረጋለትና እንደ አሊባባና አማዞን ዓይነት ‹‹ፕላትፎርም›› ቢፈጠርለት መልካም ነው፡፡ በድለላ ስም በግብይቶች መካከል የሚገባው ሰው ከበዛ ግን ችግር ነው፡፡

በእኛ አገር ያለው ከሸቀጣ ሸቀጦች ጋር የሚታየው ችግር ግን ከእጥረት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ መፍትሔው እጥረቱን ማስወገድ ነው፡፡ አሻጥር የለም እያልኩ አይደለም፡፡ ነገር ግን እጥረት ካለ ሁሌም በገበያው አሻጥር ይኖራል፡፡ ዘይት ብትደብቅ ዘይት በብዛት ማምጣት የሚችል ሰው ካለ አንተ የደበቅከው ይበላሻል፡፡ ለምሳሌ ሲሚንቶ መጋዘን ውስጥ አከማችተህ ለረዥም ጊዜ ልትደብቀው የምትችለው ምርት አይደለም፡፡ ሲሚንቶ ከተወሰነ ወራት በኋላ ይበላሻል፡፡ ባቆየኸው ቁጥር ትከስራለህ፡፡ ሲደረግ የሚታየው፣ እጥረት ስላለ ለቀናት ደብቆ ዋጋ ጨምሮ በድብቅ የመሸጥ አሻጥር ነው፡፡

ትልቁ ችግር እጥረት በመሆኑ እጥረትን መፍታት ለኢኮኖሚው ጤናማነት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ እጥረት በሚኖር ጊዜ ምርትን በኮታ (በራሽን) ማከፋፈል አስገዳጅ ይሆናል፡፡ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች በተለየ መንገድ አቅርቦት ይደረጋል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በሲሚንቶ እጥረት ተብሎ ሊቆም አይችልም፡፡ ሌሎችም አገራዊ ፕሮጀክቶች የሚባሉና ቅድሚያ የሚሰጣቸው አሉ፡፡ ለእነዚህ ስታከፋፍል እጥረት ይባባሳል ማለት ነው፡፡ ከእነሱ የተረፈችዋን የተወሰነች ምርት ነው ሰፊው ሕዝብ ይከፋፈል የምትለው ማለት ነው፡፡ እሱንም ያለው ስለሚወስድ ደሃው አያገኝም፡፡ ደሃ ደግሞ መቼም ቢሆን መቸገሩ የማይቀር ነውና ይህ የትም የሚከሰት የእጥረት አመጣሽ ችግር ይጫነዋል፡፡ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ባስከተለው እጥረት ጀርመን ውስጥ ጭምር በኮታ ጋዝ መሸጥ ተጀመረ መባሉን እየሰማን ነው፡፡ እጥረት ሲፈጠር ሁሌም ወደ ራሽን መገባቱ የማይቀር ነው፡፡ ስለዚህ እጥረቱን እንዴት እንፍታው ከማለት ባለፈ፣ አሻጥረኛ ነጋዴ ወይም ደላላ እያሉ በመርገም ችግሩን መፍታት አይቻልም፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ለሚታየው የገበያና የኢኮኖሚ ችግር ኢዜማ ምን መፍትሔዎች አሉት? ሙስናን በተመለከተስ?

አቶ ግርማ፡- እስካሁን ከተናገርኩት የተለየ አይደለም፡፡ እጥረትን መፍታት፣ የአቅርቦት ሰንሰለቱን ማስተካከልና ምቹ የግብይት ሁኔታዎችን መፍጠር ነው፡፡ ሙስናን በተመለከተም ቁርጠኛ ነው መሆን ያለብን፡፡ ለሌብነት ምቹ የሆኑ ቀዳዳዎችን መዝጋት፣ ለሌብነት ይቅርታ ማድረግም አያስፈልግም፡፡ ትንሽ መስረቅም ሆነ ትልቅ መስረቅ አንድ ነው፡፡ እዚህ ቢሮ ሌብነት ካለ በአሠራር የሚፈታውን በአሠራር መፍታት፣ የባህሪ ከሆነ ችግሩ እያንዳንዱ ሠራተኛ ኃላፊነት ወስዶ መፍታት፣ የድሮ ልምምድ ከሆነ ደግሞ እሱን ለይቶ ቆርጦ ማስቀረት የኃላፊዎች ሥራ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህንን ሁሉ አልፎ የሰረቀ ግን፣ ደመወዜ ትንሽ ስለሆነ ብሎ ምክንያት መደርደር አይችልም፣ ይቀጣል፡፡ እስከ መባረር ድረስም ሊሄድ ይችላል፡፡ ትንሽ ያላትንም ደመወዝ ያጣታል ማለት ነው፡፡

የተለየ ኤክስፐርት ወይም ልዩ ችሎታ አለው ተብሎ የተቀመጠ ሰው ካለ እሱ ሊሰርቅ ብቻ ነው የተቀመጠው ማለት ነው፡፡ ይህንን ሥራ በትንሽ ደመወዝ እየሠራሁ የመስረቂያ ቦታ አደርጋለሁ ማለትም አይችልም፡፡ በአገልግሎት ዘርፍ ለምሳሌ በሆቴል ኢንዱስትሪው ውስጥ ደመወዝ ብዙ ላይከፈል ይችላል፣ ሥራው ጉርሻ (ቲፕ) አለው ተብሎ ስለሚታመን፡፡ በመንግሥት ሥራ ግን መስረቅ ይቻላል የሚሉ ወይም ስርቆቱን መደበኛ ጉርሻ (ቲፕ) ቢያደርጉት ነው የሚሻለው፡፡ መንግሥት ደመወዝ በደንብ አልከፍልም፡፡ ቲፕ እየከፈላችሁ ተገልገሉ የሚል ሥርዓት መዘርጋት አለበት፡፡ ይህን ዓይነቱ ሥርዓት እስከ ሌለ ድረስ ግን መስረቅ አይቻልም፡፡ ደመወዙ ያንሰኛል ብሎ ጉርሻም ሆነ ጉቦና ጥቅማ ጥቅም መጠየቅ አይቻልም ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቁርጠኝነቱ ያለው የፖለቲካ አመራር ሊያስቆመው የሚችለው ችግር ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሌብነትን የሚፀየፍና ሀቀኝነትን ባህል ያደረገ ማኅበረሰብ የመገንባት ሥራ ይጠይቃል፡፡ ይህ ደግሞ በዋናነት የሚሠራው በትምህርት ቤቶች ከታች ከታዳጊዎች ጀምሮ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንዴ አገልግሎት የማቋረጥ ዕርምጃ ይወሰዳል፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማን የመዝጋት ዕርምጃ እንደተወሰደው፣ በተለያዩ ዘርፎችና ተቋማት ችግሩ እስኪፈታ አገልግሎት ማቆሙ ሙስናን ለመከላከል መፍትሔ ይሆናል?

አቶ ግርማ፡- ሙስናውን አይገታውም፣ ነገር ግን ሙስናውን ለመግታት የሚያስችል ሥራ ለመሥራት ይረዳል፡፡ በሩን ለአገልግሎት ከፍተኸው መዝገቦችህ የተበታተኑና መረጃዎችህ ያልተደራጁ ከሆነ አገልግሎት መስጠት አትችልም፡፡ ላገልግልህ ብለህ ያስገባኸውን ሰው ማገልገል ካልቻልክ ለሌብነት በር ይከፈታል፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ የውክልና ውል አገልግሎትን የመዝጋት ዓይነት ዕርምጃዎች ዜጎችን በጅምላ መቅጣት አይሆኑም ወይ? ሙስናን ለመከላከል በሚል አንድ ሥራ ሲቆምና ቢሮ ሲዘጋ ብዙዎች በጅምላ አይቀጡም ወይ?

አቶ ግርማ፡- እሱ በሕግ ልክ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ነገር ግን ለምሳሌ የመቶ ሰዎችን ውክልና ይዞ ውሎና አዳሩን አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ያደረገ ሰው አለ፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ናቸው ለሙስና መስፋፋት አስተዋጽኦ የሚያደርጉት፡፡ እነዚህን ሰዎች እከሌ ከእከሌ ብሎ ለይቶ አገልግሎት አታገኙም ብሎ መቅጣት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በሙስና መገልገል ምንም ፍላጎት የሌለውና በሀቅ ሠርቶ የሚያድር ውጭ አገር የሄደን ሰው፣ በውክልና መገልገል አትችልም ማለት ግን ምን ማለት ነው? ነቃ ያለ ዜጋ ፍርድ ቤት ሄዶ ቢሟገት እኮ ያሸንፋል፡፡ በሕግ ያገኘሁትን መብት በደብዳቤ ልትነጥቁኝ አትችሉም ብሎ ሊከስ ይችላል፡፡ ይህ ዓይነት ቅጣት በሕግ መብት አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች እናምራ፡፡ ድርድሩና የሰላም ጥረቱ ወዴት የሚያመራ ይመስልዎታል?

አቶ ግርማ፡- የዚህ ጦርነት መቋጫ በስተመጨረሻ ድርድር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ግን ‹‹ከሕወሓት ጋር የሚደረግ ድርድር ምን ዓይነት መሆን አለበት?›› የሚለው መታየት አለበት፡፡ ስለሕወሓት ታሪካዊ ትንተና የምትሠራ ከሆነ፣ ድርድሩ ለራሳቸው ጥቅም በሚሆን መንገድ እንዲቋጭ እንደሚፈልጉ በእርግጠኝነት መናገር ትችላለህ፡፡ በነገራችን ላይ ድርድርን በተመለከተ ራሳቸው ያለ ኃፍረት የጻፉት ነገር አለ፡፡ ‹ድርድር ሰዎችን ወደ ጠረጴዛ አምጥተህ የእነሱን የምትቀማበት እንጂ፣ ሰጥተህ የምትቀበልበት አይደለም› ይሉታል፡፡ ስለዚህ አሁንም ድርድሩን ለሰጥቶ መቀበል ይጠቀሙበታል ተብሎ አይታመንም፡፡ በተለይም ደግሞ ድርድሩን የትግራይ ሕዝብ እረፍት እንዲያገኝ ሳይሆን፣ የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ይጠቀሙበታል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ሆኖም  በማንኛውም ሁኔታ በሞራልም ሆነ በሕግ ቢሆን፣ ድርድርን አልፈልግም የምትልበት ሁኔታ የለም፡፡ መሣሪያ ተይዞ ግን ድርድር አይሆንም፡፡ ጠረጴዛ ላይ ተቀምጠን እናውራ ተባብለን ሽጉጥ አውጥቼ ከጎኔ ባስቀምጥና ወዮውልህ ብል ድርድር አይሆንም፡፡ ስለዚህ ሕወሓት መሣሪያ ታጥቆ በምንም ዓይነት ሁኔታ ድርድር ላይ መቀመጥ አይችልም፣ ተገቢም አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ድርድር ባለመግባት የሚፈጠረውን ዓለም አቀፍ ጫና መቋቋም እንዴት ይቻላል?

አቶ ግርማ፡- መንግሥት ብቻ እኮ አይደለም ጫናውን የሚቋቋመው፣ እያንዳንዳችን ነን፡፡ ለዚያ ደግሞ መዘጋጀት አለብን፡፡ ከክብርና ከውርደት ምርጫ ሲቀርብልህ ከሁለቱ አንዱን መምረጥ አለብህ፡፡ ጫና ለሚያደርጉብህ ወገኖች ካጎነበስክ የበለጠ ይጭኑብሃል እንጂ የተሻለ ነገር አይሰጡህም፡፡ ለምሳሌ ሕወሓት መሣሪያ እንደ ታጠቀ ድርድሩ ላይ ቢቀርብ፣ ቀጥሎ ደግሞ የሚፈልገውን ስጡት የሚል የውጭ ጫና እኮ ነው የሚከተለው፡፡ ስለዚህ የሚፈልገውን ልትሰጠው ከሆነ ድርድሩም ሆነ የውጭ ጫናው ሳያስፈልግ መስጠት አይሻልም ታዲያ? የውጭ ጫና የምትፈልገውን ነገር የምታገኝበት መንገድ አይደለም፡፡ የውጭ ጫናን የመቋቋም ብቃት የእኛው ነው፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ልንጎዳ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ከክብራችን አይበልጥም፡፡ የውጭ ጫናን በመቀበል እኮ ከውርደት አንድንም፡፡

ሪፖርተር፡- የኤርትራ መግባትም ቢሆን እንደ የውጭ ጣልቃ ገብነት መታየት አለበት የሚሉ አሉ፡፡

አቶ ግርማ፡- እኔ በግሌ የኤርትራን መግባት የውጭ ጣልቃ ገብነት ነው ብዬ አልወስድም፡፡ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ለዲፕሎማሲ ብሎ የፈለገውን ነገር ቢናገር እንኳን፣ እኔ በግሌ ጣልቃ ገብነት አልለውም፡፡ ሕወሓት መንገድ ቢያገኝ የኤርትራ መንግሥትን ከመገልበጥ ይመለሳል? ይህ አቅምና ፍላጎት እንዳላቸው በደንብ አይታወቅም፡፡ ስለዚህ የኤርትራ መንግሥት ሕወሓት እንዳይነሳ የሚያደርግ ማንኛውንም ቀዳዳ ቢጠቀም፣ ከኤርትራ መንግሥት አኳያ ስታየው ትክክል ነው፡፡ ኢትዮጵያ በውጭ ኃይል ስትወረር ዝም አሉ ይሉሃል፡፡ እንከላከል ብንል ግን በየት በኩል አልፈን ነው የምንከላከለው? እነሱ መሀል ላይ ደንቃራ ሆነው እንዴት አድርገን እንከላከል? ሕወሓትን የሚዋጋ እንጂ ኢትዮጵያን የወረረ ኃይል አይደለም ያለው፡፡ ሕወሓትን የሚመታልህ ሰው ስታገኝ ደግሞ እንዴት ዝም ትላለህ? እኔ አሁን ለምሳሌ ኦነግ ሸኔን የሚመታልኝ ኃይል ከደቡብ ሱዳን ባገኝ ቅሬታ የለኝም፡፡ ኦነግ ሸኔ የሆነ ነገር ለማድረግ ሲንቀሳቀስ የኬንያ መንግሥት አንገቱን እያነቀ አምጥቶ ቢያስረክበኝ ደስታውን አልችለውም፡፡ እንዲያውም በድንገት መቀሌ ገብተው ጌታቸውንና ሌሎች አመራሮችን ይዘው ቢሰጡን፣ ወይም አንቀው አስመራ ይዘው ቢሄዱ ለምነን ከመቀበል በቀር ጣልቃ ገባችሁ ልንላቸው ነው? ጌታቸውን ወሰዳችሁብን ብለን ጣልቃ ገባችሁ አንላቸውም፡፡

ስለዚህ የጣልቃ ገብነት አተረጓጎሙ መስተካከል አለበት፡፡ የኤርትራ መንግሥት የአገሩን ጥቅምና ደኅንነት የማስከበር መብት ያለው መንግሥት እኮ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሶማሊያ የገባችው ለኢትዮጵያ ደኅንነት ሥጋት የሆኑ ኃይሎች በመፈጠራቸው ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ባይመጡም የደኅንነት ሥጋት ደቅነዋል በሚል ነበር መንግሥት ወደ ሶማሊያ ጦር በማሰማራት የተዋጋቸው፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ሲሆን መብት ለኤርትራ ሲሆን ግን ጣልቃ ገብነት ተብሎ ሊተረጎም አይገባም፡፡ ሕወሓት ለኤርትራ ሥጋት ብቻ ሳይሆን፣ መድፍና ሚሳኤል ወደ አስመራ እየተኮሰ በተጨባጭ በኤርትራ ላይ ውጊያ የከፈተ ኃይል ነው፡፡ ይህ ለኤርትራ መግባት በቂ ምክንያት ነው፡፡ አሜሪካ ባህር ተሻግራ፣ እዚህ ሞቃዲሾ መጥታ፣ ጎረቤቷ ያልሆነ ኃይልን ስትደበድብ ነበረ፡፡ ሚሳኤል የተኮሰብህ ኃይል አንገቱን ቀና ካደረገ ነገ ደግሞ አደጋው ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ ጥቅምና ደኅንነትህ ላይ ያነጣጠረ አደጋ የደቀነ ኃይልን ድንበር ጥሰህም ቢሆን መምታት በምንም መንገድ ሊኮነን አይችልም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ትገኛለች፡፡ በምክክር ሒደቱ ላይ ምን አስተያየት አላችሁ? በምን መንገድ ለመሳተፍ እየተዘጋጃችሁስ ነው?

አቶ ግርማ፡- የአገራዊ ምክክሩን ጉዳይ እንደ ኢዜማ በትኩረት የያዘው ኃይል ያለ አይመስለኝም፡፡ በአጋጣሚ እኔም በፓርቲው የአገራዊ ምክክር ኮሚቴ አባል ነኝና በትኩረት ነው ጉዳዩን የየዝነው፡፡ እኛ አገራዊ ምክክሩን አገር የመገንቢያ መንገድ አድርገን ለመጠቀም ዝግጁ ነን፡፡ በምንም ዓይነት የፖለቲካ ጥቅም (አድቫንቴጅ) የምናገኝበት አድርገን መጠቀም አንፈልግም፡፡ ወደ አገራዊ ምክክር መድረኩ ጠረጴዛ ስንመጣ ከሆነ ቡድን፣ የሆነ ነገር ቀምተን የምንወጣበት የዘረፋ መድረክ አድርገን መጠቀም አንፈልግም፡፡ እኛ ማዕከል የምናደርገውን ዋና ጉዳይ አስቀምጠናል፡፡ እሱም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ አገረ መንግሥትን ህልውና የተቀበለ አጀንዳ ላይ እንጂ፣ ‹ኢትዮጵያን እንዴት እናፍርሳት?› በሚል ስብሰባ ላይ አንቀመጥም፡፡ ኢትዮጵያን እንዴት እናፍርሳት የሚል አጀንዳ ተቀርፆ፣ ‹‹እኛ ደግሞ አይ ኢትዮጵያን እኮ ባናፈርሳት ይሻላል›› የሚል ልምምጥ ልናደርግ አይደለም እዚያ የምንገኘው፡፡ በመሠረታዊነት ኢትዮጵያ የምትባል አገር መኖሯን አምኖ ከሚመጣና ኢትዮጵያን የተሻለች አገር አድርገን እንዴት እንገንባት በሚል ጉዳይ ላይ ነው የምንወያየው፡፡ ገዥ በሆነው በኢትዮጵያ ህልውና ላይ ከተስማማን በኋላ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት ምን መሆን አለበት? በሚለው ላይ ውይይት እናደርጋለን፡፡ እኛ የማንፈልገው ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እስከ ወሰነ ድረስ ማንኛውንም ዓይነት የፌዴራላዊ ሥርዓት ለመቀበል ዝግጁ ነን፡፡

ሪፖርተር፡- የማንነት ወይም የብሔር ፌዴራሊዝም ቢሆንም?

አቶ ግርማ፡- የፈለገው ይሁን፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁንልኝ ካለ ለውሳኔው እንገዛለን፡፡ እኛ በዋናነት የብሔርም ይሁን ሌላ ፌዴራላዊ ሥርዓት ጥቅሙና ጉዳቱ ይህ ነው ተብሎ ሕዝቡ መረጃ ማግኘትና በነፃነት መምረጥ አለበት ነው የምንለው፡፡ ሕዝቡ ትክክለኛው ምርጫ ሊሰጠው ይገባል፡፡ እኛ በዚህ ችግር የለብንም፡፡ ኢትዮጵያን እናፍርሳት ወይስ ትቀጥል? የሚል ድርድር ላይ ግን አንቀመጥም፡፡ ኢትዮጵያ አለች/የለችም? የሚል ጥያቄ ያለው ሰው፣ ሌላ ቦታ መኖሯን ጠይቆ ያለች መሆኑን አምኖ ነው ወደ መድረኩ መምጣት ያለበት፡፡ ይህን በተመለከተ ገዥው መንግሥትም ከዚህ መሠረታዊ ሐሳብ ጎን ይቆማል ብለን እናምናለን፡፡ ሌሎች ኃይሎችም ቢሆኑ ይህንን እንደሚደግፉ ነው የምንገምተው፡፡ በዚህ ሁላችንም ተግባብተን፣ ኢትዮጵያን የተሻለች አገር እንዴት እናድርጋት በሚለው ላይ ለመምከር፣ ጎን ለጎን እንቆማለን ብለን ነው የምንገምተው፡፡

ይህ ከሆነ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ሥርዓተ መንግሥት ይኑራት በሚለው ላይ እንመክራለን፡፡ ፓርላሜንታዊ፣ ፕሬዚዳንታዊ፣ ወይስ ቅልቅል ይሁን የሚለውን እንመክራለን፡፡ እኛ የምንፈልገውና ይበጃል የምንለው ቢኖረንም፣ በመጨረሻ የፈለገው ቢወሰን ችግር የለብንም፡፡ የማንፈልገው ሆን ብለን ጠብመንጃ ይዘን ጫካ መግባት ሳይሆን፣ ሌላ ጊዜ ዕድሉን ስናገኝ ይበጃል የምንለውን አስረድተን ሕዝቡ እንዲቀበል ማሳመን ይሆናል የእኛ ሥራ፡፡ በሌሎች ጉዳዮችም ተመሳሳይ አካሄድ ነው የምንከተለው፡፡ እኛ ወደ መድረኩ የምንገባው በአገራዊ አጀንዳዎች ላይ ለመስማማትም ላለመስማማትም ነው፡፡ አንድ ለመሆን አይደለም የምንሄደው፡፡ ልዩነት ቢኖረን በሐሳብ ልዩነት እንጂ፣ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ ፀብ የሌለን መሆናችንን ለማረጋገጥ ነው የምንሄደው፡፡ በሐሳብ አንድ የምንሆን ከሆነማ ወደፊት የመድበለ ፓርቲ ፖለቲካ አያስፈልገንም ማለት ነው፡፡ የሐሳብ ልዩነቶች ዘላቂ ናቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ የሐሳብ ልዩነቶች በየአምስት ዓመቱ ምርጫ ሲካሄድ ለፉክክር የሚቀርቡ የምርጫ ካርኒቫሎች እንጂ፣ የሐሳብ ልዩነቶችን በአገራዊ ምክክር መድረኩ አጥፍተን ጨርሰን የምናልፍበት አጋጣሚ ነው አንልም፡፡ አገራዊ የምክክር መድረኩ ኢትዮጵያን የምናፀናበት እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ከዚያ ውጪ ግን የፈለገው ዓይነት ጥያቄ ቀርቦ የሚመከርበት እንዲሆን እንጠብቃለን፡፡ ይህ ሲካሄድ ደግሞ የዜጎች ደኅንነት አደጋ ውስጥ በማይወድቅበት መንገድ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ኢዜማ በቅርቡ የአመራር ምርጫ በማድረግ የአመራር መተካካት ማድረጉ ይታወሳል፡፡ በዚህ ምርጫ ሒደት ደግሞ በተፎካካሪዎች መሀል የሐሳብ ልዩነት መታየቱ ይታወሳል፡፡ ከምርጫው በኋላ የሐሳብ ልዩነቱ ተፈቶ ሁሉንም ወገን ባቀፈ ሁኔታ ነው ፓርቲው እየተጓዘ ያለው?

አቶ ግርማ፡- የሐሳብ ልዩነት ያለውን ሰው የግዴታ እዚህ ውስጥ ካልገባህ አትለውም፡፡ ለዚህ እኮ ነው ውድድር የሚያስፈልገው፡፡ ሐሳብ ታቀርባለህ፣ ውድድር ታደርግና ያሸነፈው ኃላፊነቱን ይረከባል፡፡ የኢዜማን አመራርነት የሚይዘውና ሥራ የሚያስፈጽመው በምርጫ ያሸነፈው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ ሰዎች ከአባልነት ወጡ የሚባለውስ?

አቶ ግርማ፡- ከአባልነት መውጣት ልክ እንደ መግባት መብት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም ልክ ነው እላለሁ፡፡ እንዲያውም የማታምንበት ፕሮግራምና ፖሊሲ የሚፈጸምበት ፓርቲ ውስጥ ምን ታደርጋለህ? አጠቃላይ በፓርቲው ማዕቀፍ ውስጥ መቆየት ይስማማኛል፣ በሐሳብ ብሸነፍም በሌላ ዙር አሳምኜ እመረጣለሁና እስከዚያው ግን የፓርቲውን ሥራ እፈጽማለሁ የሚል ሰው ከፓርቲው ጋር ለመጓዝ አይቸገርም፡፡ የፓርቲው ዲሲፕሊንም ይኸው በመሆኑ፣ በፓርቲው ውስጥ ያለው ስብስብም ይህን የተቀበለ ነው፡፡ አንዳንዱ ራሱ የሣላቸው አንጋፋ ሰዎች አሉት፣ ግን ይህ ልክ አይደለም፡፡ እኔ አሁን ከኢዜማ ብወጣ ማን ነኝ? አንድ ስንጥር ማለት ነኝ፡፡ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ቢወጣ ሁላችንም አንድ ስንጥር ነን፡፡ እከሌ ከወጣ ፓርቲው የሆነ ነገር ይሆናል የሚባል ሥጋት ትክክል አይደለም፡፡ ኢዜማ የተሠራበትና የተገመደበት ገመድ ብዙ ነው፡፡ እያንዳንዱ የኢዜማ አባል በተናጠል የየራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ይህን አስተዋጽኦ በአግባቡ ማስቀመጥ ችግር የለውም፡፡ ሆኖም በሆነ አጋጣሚ ወይም በሐሳብ ልዩነት አንዳንዶች ቢወጡም ሆነ ሳይወጡ ትችት ቢያቀርቡ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ፓርቲው ተንገራገጨ ማለት ግን አይደለም፡፡ ጠቅላላ ጉባዔው ያሳለፈው ውሳኔ አለ፣ አመራር ተመርጧል፡፡ ይህ አመራርም ጠቅላላ ጉባዔው የወሰነውን ይፈጽማል፡፡ የሐሳብ ልዩነት ያለው ሰው በልዩነቱ መቀጠል ይችላል፡፡ ያልተስማማው ሰው ካለም አይገደድም፡፡ ሰው ቢወጣም ፓርቲው ተከፈለ ማለት አይደለም፡፡

የተወሰኑ ሰዎች ከኢዜማ ወጥተው ፓርቲ ቢያቋቁሙም መብታቸው ነው፡፡ እኛ አገር እንጂ ብርቅ የሚሆነው ሌላ አገር እኮ የተለመደ ነው፡፡ እስራኤልን ብትመለከት ያልተስማሙ ሰዎች ከአንድ ፓርቲ ወጥተው ሌላ ፓርቲ መሥርተው በምርጫ ሲፎካከሩ ማየት የተለመደ ነገር ነው፡፡ ኢዜማ በዚህ ወጥቶ፣ ኢዜማ እንዲህ ሆኖ የሚልና ያልተመቸው ሰው ካለ እንዲያውም የራሱን አሪፍ ፓርቲ አቋቁሞ ሠርቶ ማሳየት ነው ያለበት፡፡ እኛ የሠራነውን ሩብ የሚሠራ ሰው ካለ ሠርቶ ማሳየት ነው ያለበት፡፡ እኔ የምችለውንና የማውቀውን ነው እየሠራሁ ያለሁት፡፡ ሠርቶ ማሳየት እንጂ መተቸቱ ምን ያደርጋል? ሂስ መቀበል ይኖራል፣ ትችት አንቀበልም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን በኢዜማ ላይ የሚቀርቡ አንዳንድ ትችቶች የማይጠቅሙ ናቸው፡፡ ኢዜማ ተልዕኮ አለው፡፡ ኢዜማ ተልዕኮው በኢትዮጵያ ጠንካራ የመድበለ ፓርቲ ፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር ነው፡፡ ይህንን ለመፍጠር ደግሞ ተደራራቢ ኃላፊነት ነው የተሸከምነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ነው የሚባል ዓይን ውስጥ የሚገባ የፖለቲካ ሥራ የሚሠራ ፓርቲ የለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመንግሥት ዝም ተብሎ የሚተው አይደለም፡፡ ኃላፊነታችንን ወደን ብቻ ሳይሆን ተገደንም ነው የወሰድነው፡፡ ሰርተፊኬት መውሰድ አንድ ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ በሰርተፊኬት ሁሉም እኩል ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በእኛ ልክ እንኳ ተደራጅቶና የፓርቲ ቁመና ይዞ አማራጭ የፖለቲካ ኃይል ሆኖ በመቅረብ በኩል ከኢዜማ የተሻለ ፓርቲ ነኝ የሚል ማነው? ኢዜማን መተቸት ሳይሆን ፈጥሮ ማሳየት አለበት፡፡

እኛ ትከሻ እንለካካ ካልን ከገዥው ፓርቲ ጋር እንጂ ከማንም ጋር ትከሻ አንለካካም፡፡ ርቀታችንን እናውቀዋለን፡፡ ለምሳሌ እኛ 11 ሚሊዮን አባላት ለማፍራት አንችልም፣ ለማፍራትም አንፈልግም፡፡ ነገር ግን ይህን በማካካስ በተሻለ ጥራትና ብቃት ራሳችንን ገንብተን ተፎካካሪ ኃይል ለመሆን አስበን እየሠራን ነው የምንገኘው፡፡ በዚህ ልክ እየሠራ ያለ ፓርቲ ካለ አደንቃለሁ፡፡ በመኖራቸው አልቀናም፡፡ መኖራቸው ጠቃሚ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ግን የፓርቲ መብዛት ሳይሆን፣ ጠንከር ብሎ የሚቆም ሦስትና አራት ፓርቲ ነው የሚያስፈልጋት፡፡ የብሔር ሲቪክ ማኅበር እንጂ የብሔር ፓርቲ ግን ምንም አያስፈልጋትም፡፡ የእከሌ ብሔር ተበደለ ወይም እንዲህ ዓይነት ጥቅም ይከበርለት ብሎ ለመጠየቅ፣ ሲቪክ ማኅበራት በብሔር ቢደራጁ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በብሔር የሚያዝ ሥልጣን መኖር የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካ አያስፈልጋትም፡፡ የብሔር ፓርቲ ነን የሚሉ በሒደት መክሰማቸው አይቀርም፡፡ ይህ ምንም ትንቢት አይደለም፡፡

ጉባዔና ስብሰባ ሲጠሩ ‹አበል አለው ወይ?› ብለው የሚጠይቁ አመራሮች ያላቸው ፓርቲዎች አገር ሊረከቡ አይችሉም፡፡ እኛ የኢትዮጵያን መድበለ ፓርቲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት ጠንክሮ የሚታገል ፓርቲ ካለና ድጋፋችንን ከፈለገ እናግዛለን፡፡ በተረፈ ግን ጠንክረን ሠርተን በሐሳብ የበላይነት ማሸነፍ እንጂ፣ ማንንም ምንም አንለምንም፡፡ ሕዝብ አገልጋይነትንና የፖለቲካ ሥራን የሚደባልቁ ሰዎች አሉ፡፡ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ ጥቂት የኢዜማ አባላት በመቀመጣችን የተለየ ትርጉም ሊሰጠው አይገባም፡፡ እኔ ለምሳሌ እዚህ ቢሮ ውስጥ ተቀምጫለሁ፡፡ ነገር ግን በምንም ዓይነት የብልፅግና አሸከር ሆኛለሁ ማለት አይደለም፡፡ የተሾምኩበት ቦታ የመንግሥት ኃላፊነት በመሆኑ፣ ለመንግሥትነት ተራውን ያገኘው ብልፅግና ያስቀመጣቸውን ፖሊሲዎችና ዕቅዶች እፈጽማለሁ፡፡ ይህ ግን በከተማው ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ፣ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር፣ እንዲሁም ቀልጣፋ የኢንቨስትመንት አገልግሎት እንዲቀርብ የማደርገውን አስተዋጽኦ ሊከለክለኝ አይችልም፡፡ እዚህ ቤት ባልመደብ ከዚህ ሥራ የማገኘውን ሌላ ቦታ ሠርቼ አገኘዋለሁ፡፡ እሱም ቢሆን ግን ግብር ከፋይ በመሆኔ በተዘዋዋሪ አገልግሎት ነው፡፡ ስለዚህ ሹመቱ የፖለቲካ ነው፡፡ ነገር ግን ደግሞ ኃላፊነቱ ሕዝብን ማገልገል ነው፡፡     

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...