Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መንግሥት የኑሮ ውድነትን አንድ ይበልልን!

የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት መንስዔ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉት በተደጋጋሚ ሰምተናል፡፡ ችግሩ ዛሬ የጀመረ ሳይሆን ለዓመታት ተጠረቃቅሞ አሁን ላይ ገዝፎ የወጣ መሆኑም በተደጋጋሚ ሰምተናል፡፡ ቅጥ ያጣው የግብይት ሥርዓት ብልሽት፣ የደላሎች ጡንቻ ፈርጥሞ መውጣት፣ ገበያን ለማረጋጋት ኃላፊነት የተሰጣቸው መንግሥታዊ ተቋማት መልፈስፈስ፣ አልጠግብ ባይ ነጋዴዎች እንዳሻቸው መሆንና የመሳሰሉት ችግሩን ስለማባሳቸውም ጆሯችን እስኪደክም አዳምጠናል፡፡

የውጪ ምንዛሪ እጥረትና የባንኮች የማበደሪያ ወለድ መጠን ገደብ ማጣት ለዋጋ ንረቱ መባባስ ሌላው ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ችግሩ ጠማማ የፖለቲካ አመለካከት ካላቸው ወገኖች ጋር የተያያዘም እንደሆነ ይታመናል፡፡ መንግሥትን ለማጠልሸት ገበያ ውስጥ የሚፈጸሙ ሸፍጦች ገበያውን አበላሽተዋል ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ ይደመራል፡፡

የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት መንስዔዎች ምንድናቸው ብለን ወደ ውስጥ ገብተን እንመርምር ከተባለም በሐላል እየነገሠ ያለው ሙስና መዘንጋት የሌለበትና መጠቀስ ያለበት ይሆናል፡፡ ሙስና ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከታች እስከ ላይ ያሉ ባለሥልጣናት የሚመለከት ይሆናልና በዚህ የገንዘብ ቅብብል ውስጥ የሚፈጠር የግብይት ሥርዓት ብልሽት ይታያል፡፡ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማካሄድ የሚፈጸም ያልተገባ ክፍያ ወይም ጉቦ በሰጪው ዘንድ ወጪ ተደርጎ የሚሰላ በመሆኑ ይህንን ‹‹ዕዳ›› በሚሰጠው አገልግሎት ወይም ምርት ላይ በማከል ሸማቹ ወይም ተገልጋዩ እንዲሸከም ያደርጋል፡፡

እዚህ አካባቢ ያለው ተያያዥ ችግር አልጠግብ ባዮች ከባለሥልጣናት ወይም አስፈጻሚ ከሚባሉ አካላት ጋር በመመሳጠር የሚፈጥሩት ቀውስም ለችግሩ መባባስ ምክንያት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡

ከዚህ ባሻገር ግን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ትንታኔ ሳያሻው ለዋጋ ንረት ትልቁ ምክንያት በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ያለው ልዩነት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ እጥረት ያለበት ምርት ዋጋው መናሩ አይቀርም፡፡ በእኛ አገር ሁኔታ ግን እጥረት አይኖርበትም የተባለው ምርት ሁሉ እንደ ሌላው ተመሳስሎ ቁጭ ይላል፡፡ ወረርሽኝ ይሆናል፡፡

ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች የሚፈጥሩት ችግርም ዋጋን ያንራሉ፡፡ ለምሳሌ የዩክሬንና የሩሲያ ጦርነት ይዞብን የመጣው ጣጣ በእርግጥም ሸክማችንን አብሶታል፡፡ ችግሩ በዚህ ሰበብ የተፈጠረውን ክፍተት አባብሶ ያለ ይሉኝታ የሚጠየቀው ዋጋ እላይ መድረሱ ነው፡፡

ለማንኛውም ለዋጋ ንረትና ለኑሮ ውድነት መባባስ አሳማኝ ምክንያቶች ሊኖሩ ቢችሉም በአመዛኙ ግን ልክ የሌላው የትርፍ ምጣኔና አጋጣሚዎችን በመጠቀም የሚፈጸም ሸፍጥ ከገባንበት አዙሪት እንዳንወጣ አድርጎናል፡፡ ዛሬ የምርቶች ዋጋ ጭማሪ በሳምንት በወራት የሚከሰት መሆኑ ቀርቷል፡፡ በአንድ ቀን ውስጥ ዋጋ ይለዋወጣል፡፡ ይጨምራል፡፡ ቀነሰ የሚል መረጃ የለም፡፡ ተጋነነ ካልተባለ ጠዋት አንድ ዕቃ ለመግዛት የሄደ ሸማች ገንዘብ ጎድሎት ከሰዓት ቢመለስ ጠዋት የተነገረውን ዋጋ ሊያገኝ የማይችልበት አጋጣሚዎች ሁሉ እየተፈጠሩ ነው፡፡ ይህ አደገኛ አካሄድ እየተለመደ ነው፡፡ በግብይታችን ውስጥ ከፍተኛ የዲሲፒሊን ችግር ያለ በመሆኑ ከወራት በፊት በነበረ የውጭ ምንዛሪ የገባ ዕቃ በተባራሪ የዶላር ጭማሪ ወሬ በዕለቱ ጥቁር ገበያ የውጪ ምንዛሪ ዋጋ ተሰልቶ ይሸጣል፡፡ እንዲህ ያለው አሠራር አሁን ላይ በሰፊው ተንሰራፍቷል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ስሌቱ ደግሞ በሕጋዊ መንገድ በባንክ የሚደረግ የምንዛሪ ዋጋን መሠረት ያደረገ ሳይሆን የጥቁር ገበያን ዋጋ ያገናዘበ ነው፡፡ ይህ ማለት ገበያው እየተመራና ዋጋ እየተሰላ ያለው በጥቁር ገበያው እየሆነ መምጣቱ የዋጋ ንረቱን መገመት አያቅትም፡፡

በሕጋዊ መንገድ በ52 እና በ53 ብር ዋጋ ተሰልቶ ከባንክ በተወሰደ የወጭ ምንዛሪ የሚገባ ዕቃ ዋጋ የሚተመንበት ጥቁር ገበያን መነሻ አድርጎ ለመሆኑ አስረጂ የሚሆነን አንዳንድ ደፋሮች በጥቁር ገበያ አንድ ዶላር 100 ብር እየተመነዘረ እኔ በ53 ብር አስልቼ አልሸጥም እስከማለት መድረሳቸው ነው፡፡

አንዳንዱም በ90 እና በመቶ ብር አንድ ዶላር ገዝቼ ያስመጣሁት ዕቃ እኮ ነው ማለት መጀመሩ ምን ያህል የግብይት ሥርዓታችን እንደተበላሸ ማሳያ ይሆናል፡፡

ራስ ወዳድነትና ስግብግብነት ገበያ ማበላሸቱንም እንዲህ ያሉ ዓይን ያወጡ ድፍረቶችን ምስክር ሊሆኑን ይችላሉ፡፡ መንግሥት ቁርጥ ዋጋ ያውጅ የትርፍ ምጣኔም በሕግ ይገደብ የሚባለው፡፡

የአገር ኢኮኖሚ ጥቁር ገበያን እያሰላ የማካሄድ ከሆነ ሕጋዊ የግብይት ሥርዓት እንዴት መፍጠር እንደሚቻል ግራ ያጋባል፡፡ ግራ ማጋባት ብቻ ሳይሆን ውንብድናው ሥር እየሰደደ ከሄደ የሆነ ጊዜ ተነስቶ አሁንስ በቃ ዕርምጃ ልወስድ ቢባል ላይሆን የሚችልበት ዕድል መኖሩን ሳስብ ያስፈራኛል፡፡

ስለዚህ ኑሯችንን የመረረ እያደረገ ያለው ሕገ ወጥነት መንሰራፋት ብሎም ሕገወጥነትን ለመከላከል ዳተኝነቱ ከበዛ አገር የባለ ፍራንካዎች ብቻ ልትሆን ነው ማለት ነው፡፡ ጥቂት የሚባሉ አካላት በሚያጦዙት ገበያ ሲተረማመስና ከደጃፋችን የምናገኘው ምርት ሁሉ ዋጋው አልቀመስ ካለ የደሃው ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ነው? ይህንን አደገኛ አካሄድ ማስቆም ለሁሉም የሚበጅ ይሆናል፡፡ በተለይ ጥቁር ገበያን መሠረት ያደረገ የዋጋ አተማመን እጅግ አደገኛ በመሆኑ ችግሩ ከዚህም በላይ ቀውስ እንዳይሆን መላ ሊበጅለት ይገባል፡፡

ይህንን ችግር ለመቅረፍ አሁንም መንግሥት ቀዳሚው ቢሆንም አሁን ከምናየው ሁኔታ አንጻር ግንለመፍትሔው መንግሥትን ብቻ መጠበቅ ተገቢ አይሆንም፡፡

መንግሥት በሕገወጦች ላይ ክንዱን ለማንሳት ቆርጦ ከተነሳ ሸማቹ በአጠቃላይ ኅብረተሰቡ ተባባሪ መሆን አለበት፡፡ ለኑሮ ውድነቱ መባባስ በተጨባጭ ምክንያት የሆኑ አካላትን ማጋለጥ ይገባል፡፡ ከልክ በላይ የትርፍ ህዳግ ይዘው እንዳሻቸው የሚሆኑ አካላትን ማስጠንቀቅ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሸማቹም መሆን አለበት፡፡ እንብኝ አልገዛም ማለትንም እንደ ሸማቹ መልመድ አለብን፡፡ በነገራችን ላይ ስለሸማች የሚሞግቱ ማኅበራት የት ደረሱ? ለማንኛውም ንረቱን የሚያንሩ አዳዲስ ክስቶች እየታዩ ነውና ይህንን በጋራ እንከላከል፡፡  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት