Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአገር ውስጥ መድኃኒት አምራች ኢንዱስትሪ ፈተናና ቀጣይ ዕጣ ፈንታ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በጤና ተቋማት የሚያጋጥመው የመድኃኒት፣ የሕክምና መገልገያዎች አቅርቦት ችግር ከመዲናዋ አንስቶ ጠረፍ እስከሚገኙት የአገሪቱ ክፍሎች የዘወትር ዕሮሮ መሆኑ ይታወቃል፣ በተደጋጋሚም ሲገለጽ የቆየ ጉዳይ ነው።

የመድኃኒትና ጉዳይ ከሁሉም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ አንገብጋቢ ጉዳይ ቢሆንም የአገር ውስጥ የመድኃኒት አምራቾችና አጠቃላይ ዘርፉ ያጋጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ተያያዥ ችግሮች ሳይፈቱ ለረዥም ጊዜ መክረማቸው ከዘርፉ አልፎ የማኅበረሰብን ጤና እየፈተነ የሚገኝ ራስ ምታት ሆኗል። በዘርፉ ያለው ችግር በተደጋጋሚ የሚነሳ ቢሆንም፣ እስካሁንም ሊፈታ ያልቻለ ስለመሆኑ የሚናገሩ ዜጎች ቁጥራቸው በርካታ ነው፡፡ 

በሌላ በኩል 70 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱን የመድኃኒት ፍላጎት እየገዛ የሚያሠራጨው የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት 90 በመቶ የሚሆነውን የመድኃኒት ፍላጎት በውጭ ምንዛሪ ከሌሎች አገሮች ሲገዛ፣ አሥር በመቶ የሚሆነውን ብቻ ከአገር ውስጥ አምራቾች ገዝቶ እንደሚያቀርብ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ አንጋፋና በቅርቡ ዘርፉን የተቀላቀሉ አምራቾች የተሰባሰቡበት የኢትዮጵያ መድኃኒትና ሕክምና መገልገያ አምራች ኢንዱስትሪዎች ዘርፍ ማኅበር በተጠናቀቀው ሳምንት ባከናወነው 19 ዓመታዊ ጉባዔ ላይ በቀረበ ጽሑፍ ላይ እንደቀረበው፣ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ለአገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች ብቻ ውስን የውድድር ጨረታ (ኮምፒቲቲቭ ቢዲንግ) ካለ ምንም የውጭ አገር ተወዳዳሪ ሲያቀርብ ቆይቷል። ይሁን እንጂ የአገር ውስጥ አምራቾች ድርሻ በአሳዛኝ ሁኔታ እየቀነሰ መምጣቱን ባለፉት አምስት ዓመታት የነበረው የግዥ መረጃ ያሳያል።

ለአገር ውስጥ አቅራቢዎች እንዲያቀርቡ ኮንትራት ተሰጥቷቸው ባጋጠማቸው ከአቅም በላይ ችግር ምርቱን ማቅረብ ባለመቻላቸው በ2013 ዓ.ም. 72 የሚጠጉ መድኃኒቶችን 23 ሚሊዮን ዶላር ከፍሎ ወደ አገር ውስጥ ማስገባቱን የመድኃኒት አቅርቦት አገልግሎቱ ይገልጻል፡፡ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ደግሞ 82 የሚጠጉ መድኃኒቶችን 32 ሚሊዮን ዶላር አውጥቶ ለመግዛት ተገዷል፡፡

የአገር ውስጥ የመድኃኒት አምራቾች ጨረታ አሸንፈውና እንዲያቀርቡ ዕድሉ ተሰጥቷቸው በገጠማቸው ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ ችግር ምክንያት ብቻ ባለማቅረባቸው፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የመድኃኒት ግብዓት እጥረት መከሰቱና በዚህም የተነሳ በጤና ተቋማት ከሕይወት ሕልፈት ጀምሮ፣ የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት የሚወስደው ጊዜ መራዘምና ከዚያም አልፎ ዜጎች ከፍተኛ የሆነ ወጭ በማውጣት ከውጭ አገሮች መድኃኒቶችን በግለሰብ ደረጃ እስከማስመጣት ደረጃ እንዲደርሱ ማስገደዱ ይነገራል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ደረጀ ዱጉማ (ዶ/ር) መድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 60 በመቶ የሚሆነውን የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት ዕቅድ ተይዞ እንደነበር አስታውሰዋል። ይሁን እንጂ የዕቅዱ ትግበራ በተቃራኒው ውሎ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑ መድኃኒቶችና አብዛኛው የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ከውጭ አገር ተገዝተው የገቡ መሆናቸውን ሚኒስቴር ዴኤታው ይገልጻሉ፡፡ 

የአገር ውስጥ አምራቾች መልካም የአመራር ሥርዓቶች እንዲከተሉ ከጤና ሚኒስቴርና ተጠሪ ከሆኑ ተቋማት ጋር በመሆን ድጋፍ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ጥረቶቹ እንደጠበቁ ሆነው፣ በዚህ ወቅት ይህ ዘርፍ ትልቅ ችግር ውስጥ እየገባ መሆኑን ደረጀ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም 20 በመቶ የሚደርሰው የመድኃኒትና የሕክምና መሣሪያ አቅርቦት በአገር ውስጥ አምራቾች የሚሸፈን ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግን በከፍተኛ ደረጃ አሽቆልቁሎ ወደ ስምንት በመቶ ዝቅ ማለቱን ሚንስትር ዴኤታው ጠቁመዋል፡፡ 

የአገር ውስጥ አምራቾች ድርሻ በዚህ ደረጃ ዝቅ ማለት አስደንጋጭነቱን የሚልጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በዚህ ወቅት ፋብሪካዎች ወደ መዘጋት የሚያንደረድራቸውን የተመናመነ ሥራ ብቻ እየሠሩ እንደሆነ በምልከታ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ 

ከብዙ ምክንያቶች ዋነኛው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በሚፈለገው ልክ አለመገኘቱ ሲሆን፣ ይህንንም መንግሥት አምኖ ተቀብሎ እየሠራበት ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ 

በየጊዜው የጤናው ዘርፍ ግምገማ ዋነኛ ችግር ሆኖ የሚቀርበው የመድኃኒት እጥረት ነው፡፡ የማኅበረሰቡን ከፍተኛ የሆነ የመድኃኒት አቅርቦት ጥያቄ መፍታት የሚቻለው በአገር ውስጥ ማምረት ሲቻል ብቻ እንደሆነ ፣ ለአብነትም የጎረቤት አገር ኬንያ ተሞክሮ እንደሚያሳየው ለአገሪቱ ከሚያስፈልጉ ወሳኝ መድኃኒቶች ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው የሚመረተው ኬንያ ውስጥ ባሉ አምራቾች መሆኑን ሚንስትር ዴኤታው ደረጀ (ዶ/ር) ይገልጻሉ፡፡ 

የኢትዮጵያ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራቾች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ዳንኤል ዋቅቶሌ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ በአገሪቱ ውስጥ ለመድኃኒት አምራች ዘርፉ መስፋፋት በመንግሥት የሚደረገው ድጋፍ እንደተጠበቀ ሆኖ የመድኃኒት አምራቾች የአቅርቦት መጠን ግን እየተዳከመ መጥቷል፡፡ 

አገሪቱ ለመድኃኒት አቅርቦት ዘርፉ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር እንዳለበት ያስታወሱት አቶ ዳንኤል፣ መንግሥት የአገሪቱን ውስን የውጭ ምንዛሬ ሀብት መድቦ መድኃኒቶችንና የሕክምና መገልገያዎችን ከውጭ መግዛት በመቀነስ ከአገር ውስጥ አምራቾች እንዲረከብና ዘርፉን እንዲያበረታታ ማኅበሩ መጠየቁን ያስረዳሉ፡፡ 

አርባ በመቶ የሚሆነውን የአገር ውስጥ የፋርማሲዩቲካልስ ፍላጎት ማሟላት (ማቅረብ) የሚችሉ ፋብሪካዎች በአገር ውስጥ እንደሚገኙ፣ ይህንን አቅም አሟጦ ለመጠቀም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከመንግሥት ጋር ንግግሮችና መግባባቶች ላይ በመደረሱ በቅርብ ጊዜ ለውጥ ይኖራል የሚል እምነት እንዳላቸው የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ይናገራሉ፡፡ 

አቶ ዳንኤል እንደሚሉት በዘርፉ የሚስተዋለውን ክፍተት ለመቅረፍ መደረግ ከሚገባቸው ጉዳዮች ውስጥ የሕክምና ግብዓቶች ግዥ ሥርዓቱ መስተካከል አለበት፡፡ ለአብነትም የአገር ውስጥ አምራቾች ለማቅረብ የሚወዳደሩበት ዋጋ በብር ሲሆን፣ የውጭ አገር አምራቾች ግን በዶላር ነው፡፡ ነገር ግን የአገር ውስጥ አምራቾች የሚያቀርቧቸው ግብዓቶች ዋጋ በዶላር ሆኖ ክፍያው ሲከፈል ግን በብር ይከፈላቸው የሚል ጥያቄ ለመንግሥት መቅረቡንና ይህንንም ለማስተካከል መንግሥት ይሁንታ መስጠቱ ተጠቅሷል፡፡ 

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ከውጪ አገሮች ለሚገዛው ምርት የሚወጣውን የውጪ ምንዛሪ ለአገር ውስጥ አምራቾች ጥሬ ዕቃ መግዣ ሰጥቶ መድኃኒቱ በአገር ውስጥ የሚቀርብበት ሁኔታ እንዲፈጠር እንዲሁ ማህበሩ ለመንግሥት ጥያቄ አቅርቦ መልካም ምላሽ እንዳገኘም ተሰምቷል፡፡ 

በጤና ሚኒስቴር የአገር ውስጥ ምርት ዘርፍ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አቶ ፋሲካ መከተ ለሪፖርተር እንደሚገልጹት፣ ከዚህ ቀደም በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሥር የነበረው የአገር ውስጥ ፋርማሲዩቲካልስ ዘርፉን የማበረታት (የመደገፍ) ሥራ ለጤና ሚኒስቴር ከዞረበት ጊዜ ጀምሮ ለዘርፉ አመቺ የሆነ ሥነ ምኅዳር መፍጠር ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል፡፡ 

ሥነ ምኅዳር ማመቻቸት ሲባል የባለ ድርሻ አካላትን ማቀናጀት የመጀመርያው ሲሆን፣ ከዚህም ባሻገር ድጋፍ ለማድረግ የሕግ ማሻሻያ የሚጠይቁ ጉዳዮችም ይገኙበታል፡፡ ለአብነትም የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪው ጥሬ ዕቃ እንዲመቻችለትና በተለይ መልክ እንዲቀርብለት የሕግ ማሻሻያዎችን ማድረግ ይጠይቃል፡፡ 

የአገር ውስጥ መድኃኒት አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ችግር ላይ እንዳሉና የማምረት አቅማቸው መቀነሱ ይታወቃል የሚሉት አቶ ፋሲካ፣ በቅርቡ የተሻለ ነገር እንደሚመጣ፣ መንግሥት ጉዳዩን ሲያሻሻል ተቋማቱ ደግሞ አቅማቸውንና የሚያመርቱበትን የጥራት ደረጃ ማሻሻል ግድ እንደሚል ያብራራሉ፡፡

አቶ ፋሲካ እንደሚሉት፣ ለዘርፉ የታክስ ማበረታቻ የተፈቀደ ቢሆንም የተፈለገውን ለውጥ አላመጣም፡፡ በተደረገው የታክስ ማበረታቻ ምክንያት ለምን ኢንዱስትሪው አላደገም? የሚለው ጉዳይ እየተፈተሸ ይገኛል፡፡ 

ከታክስ ማበረታቻ በተጨማሪ ምን ዓይነት ማበረታቻዎች ሥነ ምኅዳሩን አመቺ ያደርጉታል? የሚለውን ጉዳይ የተመለከቱ ጥናቶች መኖራቸውን (መደረጋቸውን) የሚገልጹት ከፍተኛ አማካሪው፣ የፋርማሲዩቲካል ኢንዲስትሪው ያሉት (የሚጠቀማቸው) መገልገያዎች (ኢክዩፒመንት) በተወሰነ ጊዜ የሚፈተሹ (ካሊብሬት የሚደረጉ) መሆናቸውን በማስታወስ፣ ይህንን ሁሉ መፈተሽ የሚያስችል መሣሪያ አለ ወይ? የሚለውን በመፈተሽ፣ በጥናትና ምርምር አሊያም በሥልጠና፣ የገበያ ዕድል በማመቻቸት መደገፍ እንደሚገባ ይገልጻሉ። መንግሥት ለተጠቀሱት ጉዳዮች ምላሽ የሚሰጥበትና አጠቀላይ ዘርፉን የሚደገፍበት (ኢንተርሺን የሚደርግበት) ሁኔታ ይኖራል ይላሉ፡፡ 

አቶ ፋሲካ እንደሚናገሩት፣ ለፋርማሲዩቲካልስ ኢንዱስትሪ የሚያገለግሉ ጥሬ ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ (ዲዩቲፍሪ) ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ቢሆንም፣ ነገር ግን ለዚህ ኢንዱስትሪ የሚሆነው ጥሬ ዕቃን (ኬሚካል ሪኤጀንት) ሌላው ኢንዱስትሪ ይጠቀማል፡፡ የጉምሩክ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች ከዘርፉ ጋር የተዛመደ የግብይት ዓይነት ስለሆነ የማይለዩበት ዕድል ስለሚኖር ግልጽ በሆነ መንገድ ለፋርማሲዩቲካልስ ኢንዱስትሪዎች ግብይት ናቸው የተባሉ መዘርዝሮች ተዘጋጅተው ለጉምሩኩ ባለሙያዎች በቀላሉ ለሥራ እንዲያመች ሆኖ የማቅረብ ሥራ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀትና የፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ፣ የኢንዱስትሪና ማዕድን ቋሚ ኮሚቴ፣ የጤናና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችን፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ሌሎች የባለድርሻ አካላት የዘርፉን ማነቆዎች ከመገንዘባቸው አንጻር በተያዘው ዓመት የአገር ውስጥ አምራቾቹ ከዚህ ቀደም ከነበራቸው ድርሻ የተሻለ ቢያንስ 15 ከመቶ ፍላጎት ለማሟላት የሚሠሩ መሆኑን የማኅበሩ ፕሬዚዳንት እንዲሁ ያስረዳሉ፡፡ 

የጤና ሚኒስቴር ከአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት እንዲሁም ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን ፎረም መሥርተው በዘርፉ ላይ ሊደረግ የሚገቡ ድጋፎችን ለማቅረብ የጀመሩት ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አምራቾች በጥራት ፈዋሽነታቸው በተረጋገጠና ዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ማሟላት በሚችሉበት መንገድ መድኃኒቶችን ማምረት እንደሚገባቸው የጤና ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች