Monday, March 4, 2024

የድርድር ወይስ የጫና ድግስ?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ሳምንቱ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለመቋጨት የሰላም ጥረት ይጀመራል የሚል ተስፋ ሰጪ ዜና የተደመጠበት ነበር፡፡ ተስፋውን የበለጠ ያጠናከረው ደግሞ ሁለቱን ተፋላሚዎች ማለትም መንግሥትና ሕወሓትን በደቡብ አፍሪካ ፊት ለፊት አገናኝቶ ለማነጋገር ቀጠሮ እንደተቆረጠለት መነገሩ ነበር፡፡ ይህ ተስፋ ሰጪ ዜና ግን በቀናት ልዩነት የሚያደበዝዝ ጉዳይ ሲገጥመው ታይቷል፡፡ ዓርብ ዕለት ረፋድ ላይ እንደተሰማው ከሆነ በደቡብ አፍሪካ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የገጽ ለገጽ ድርድር በሎጂስቲክስ ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ መሸጋገሩ ተሰምቷል፡፡ ይህን ተከትሎ ደግሞ ድርድሩ የምር ሊካሄድ የተወጠነ ወይስ ላይ ላዩን የሚነገር መርሐ ግብር እየሆነ ነው የሚል ጥያቄ እየተነሳ ነው፡፡

ከዚህ የሰላም ጥረት መጀመር ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ በርካታ ዜናዎችና ግምቶች እየወጡ ነው፡፡ የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ውሳኔ፣ የአፍሪካ ኅብረት መግለጫ፣ የሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔና የውጭ ዲፕሎማቶች የኢንተርኔት ውይይት፣ እንዲሁም የሕወሓት መግለጫዎች ድርድሩ በምን መንገድና ሁኔታ ሊቀጥል ይችላል በሚለው ጉዳይ ላይ መነጋገሪያ ምክንያቶች ሆነው ነው የሰነበቱት፡፡ በተለይ በአውሮፓ ኅብረት ተወካዮች መለቀቁ የተነገረው ባለ አራት ገጽ ሰነድ ስለሰላም ንግግሩ ሒደት ብዙ ግምቶች እንዲሰጡ መነሻ ሆኖ ነው የከረመው፡፡

ይህ ሰነድ ለሰብዓዊ ረድኤት መተላለፊያ ከሱዳን ጋር የሚያገናኝ ኮሪደር መከፈቱ ለሕወሓት እጅግ ወሳኝ ጥያቄ መሆኑን ያስቀምጣል፡፡ ይህ ሰነድ ከዚህ በተጨማሪም እንደ ሩሲያና ቻይና ያሉ ኃይሎችን ጨምሮ የዓረብ አገሮች በሰላም ሒደት ሊሳተፉ እንደሚችልም ይጠቅሳል፡፡ የአውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካና የአፍሪካ ኅብረት የድርድሩን ሒደት እንዴት እንደያዙት ከዚህ ቀደም ያልተሰሙ አዳዲስ ጉዳዮችን ይፋ የሚያደርገው ይህ ሰነድ አስገራሚ ነጥብም ያነሳል፡፡

በኦገስት (ነሐሴ) በተደረገው ግንኙነት በተደረሰው መግባባት መሠረት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት በድርድሩ የሎጂስቲክስ ድጋፍ ከማድረግ በዘለለ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ እንደሚፈለግ በሰነዱ ተጠቅሷል፡፡ ተመድ፣ አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት ከአፍሪካ ኅብረት ጋር የድርድር ስትራቴጂውን በማርቀቅ ጭምር ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ሐሳብ መኖሩን ይህ ሰነድ በግልጽ ይጠቅሳል፡፡

ሔሪቴጅ ፋውንዴሽን አዘጋጅቶታል በተባለው የኢንተርኔት ውይይት ላይ ደግሞ ለዲፕሎማቶች ማብራሪያ ሲሰጡ የተደመጡት ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ በበኩላቸው ስለድርድሩና ስለሒደቱ ብዙ ተናግረዋል፡፡

ጦርነቱን ቀጣናዊ ሲሉ የጠሩት ሌተና ጄኔራል ፃድቃን፣ ‹‹ሰላም ለትግራይ ኃይሎች ስትራቴጂካዊ አማራጫቸው ነው፤›› በማለት ነበር የተናገሩት፡፡ ከዚህ ቀደም በሦስት አጋጣሚዎች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ግንኙነት መደረጉን የተናገሩት ጄኔራሉ ‹‹በሦስቱም አጋጣሚዎች ልንፈጽም ተስማምተን የወጣናቸውን ቅድመ ሁኔታዎች መንግሥት አልፈጸመም፣ ተክደናል፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

እነሱ ተዓማኒነት ያለውና በገለልተኛ አደራዳሪዎች በኩል የሚካሄድ ድርድር በእጅጉ እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡ በዚህ የኢንተርኔት ውይይት ጥያቄ አቅራቢ የነበሩት የአማራ አሶሴሽን በአሜሪካ ተወካዩ ቴዎድሮስ ትርፌ የወልቃይትን ጉዳይ አንስተው ነበር፡፡ ጄኔራሉ ለዚህ በሰጡት ምላሽ ወደ ድርድሩ ከመገባቱ በፊት የወልቃይትም ሆነ ሁሉም ጉዳይ ጦርነቱ ከጀመረበት ቅድመ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ወደ ነበረበት ይዞታ መመለስ ይኖርበታል የሚል ቅድመ ሁኔታ አንስተው ነበር፡፡

ድርድሩ በገጽ ለገጽ ግንኙነት በደቡብ አፍሪካ ሊቀጥል መሆኑ በተነገረ ማግሥት የኬንያ አዲሱ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸው፣ ሰውየው በድርድሩ ሒደት ጉልህ ሚና ካላቸው መሪዎች አንዱ እንደሆኑ ብዙ ያስባለ ነበር፡፡ የአፍሪካ ኅብረትም ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ በድርድሩ እነማን የሸምጋይነት ሚና እንደሚኖራቸው አስታውቆ ነበር፡፡ ዋና የኅብረቱ የምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞው የናይጄሪያ መሪ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የሚመሩት ፓናል መዋቀሩን መግለጫው ያትታል፡፡ በዚህ ፓናል ውስጥ ደግሞ የኬንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ፉምዚሌ ምላምቦ (ዶ/ር) እና የኅብረቱ ሸምጋዮች ይወከላሉ ሲል ነበር መግለጫው ያስቀመጠው፡፡

ነገር ግን የኬንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ በፕሮግራም መጣበብ ምክንያት እንደማይገኙ ለአፍሪካ ኅብረት አሳውቀው ነበር፡፡ በተጨማሪም ወደፊት የሚካሄደው ስብሰባ የመነጋገሪያ ነጥቦቹና አሠራሩ እንዲገለጽላቸው ጠይቀዋል፡፡

የሰላም ንግግሩ በምን መንገድ እንደሚካሄድ ስለሒደቱ ተከታታይ ዘገባዎች ይወጣ በነበረበት ወቅት ግን ይሰምራል ወይ የሚለው ጥያቄ ጎልቶ ሲነሳ ነበር የከረመው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሰጡ ታዛቢዎችም ቢሆን ንግግሩ በተለያዩ ምክንያቶች ሊሰናከል እንደሚችል ነበር ግምታቸውን የተናገሩት፡፡

የኢዜማ ከፍተኛ አመራርና የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የቢሮ ኃላፊ  አቶ ግርማ ሰይፉ፣ ከሕወሓት ባህሪ በመነሳት ንግግሩ አይሰምርም ይላሉ፡፡

‹‹ድርድር ሰዎችን ወደ ጠረጴዛ በማምጣት የእነሱን የሆነን ነገር የምትነጥቅበት መንገድ ነው ብሎ የጻፈው ሕወሓት፣ በፍፁም ለሰጥቶ መቀበል ድርድር ዝግጁ አይሆንም፤›› በማለት ነበር አቶ ግርማ ድርድሩን ያሰናክላል ያሉትን የሕወሓት ባህሪ ያስቀመጡት፡፡ በእሳቸው እምነት ሕወሓት የሰላም ንግግሩን ሒደት ለትግራይ ሕዝብ ሰላም ማግኛ ሳይሆን ለራሱ ፖለቲካዊ ትርፍ ይገለገልበታል ተብሎ ነበር የሚገመተው፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ አሰፋ አዳነ (ዶ/ር) በተመሳሳይ፣ ‹‹በሕወሓት በኩል በሰጥቶ መቀበል መርህ ድርድር የማድረግ ፍላጎት የለም፤›› ሲሉ ነው የሚናገሩት፡፡ ‹‹ከሰሞኑ የሕወሓትና የምዕራባውያን ኃይሎች ለድርድር ሽር ጉድ ያበዙበትና ሲሯሯጡ  የሰነበተው የጦርነቱ ሚዛን በመለወጡ ነው፤›› የሚሉት አሰፋ (ዶ/ር)፣ ከዚህ ውጪ ሀቀኛ የድርድርም ሆነ የሰላም ፍላጎት እንደሌለ ነው የተናገሩት፡፡

የሰላሙን ሒደት እንደሚደግፍና በድርድሩ ሒደትም ንቁ ተሳትፎ እንደሚኖረው ያስታወቀው የአውሮፓ ኅብረት፣ ከሰሞኑ ባንፀባረቃቸው አቋሞች ኅብረቱ እውነትም የሰላም ሒደቱን ይፈልገዋል ወይ? የሚለውን ጥያቄ ጎልቶ እንዲነሳ የሚጋብዝ ነበር፡፡ የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ከቀናት በፊት በጠራው ስብሰባ የማዕቀብ ናዳ በኢትዮጵያ ላይ ለማውረድ ያለውን ፍላጎት በግልጽ ያንፀባረቀ ነበር፡፡

የፓርላማው አንዳንድ አባላት ያለ ቅድመ ሁኔታ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲጀመር፣ እንዲሁም ወደ ድርድሩ እንዲገባ ግፊት ሲያደርጉ ታይተዋል፡፡ ከፓርላማ አባላቱ ብዙዎቹ በጦርነቱ ለደረሰው ዕልቂት ተጠያቂነት እንዲኖር የጠየቁ ሲሆን፣ በሁሉም የጦርነቱ ተካፋይ ኃይሎች ላይ ማለትም በኤርትራና በኢትዮጵያ ላይ  የጦር መሣሪያ ዕቀባን ጨምሮ አስገዳጅ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጫናዎች እንዲደረጉ ያላቸውን ሰፊ ፍላጎት ሲያንፀባርቁም ተሰምተዋል፡፡ የአሜሪካ የምሥራቅ አፍሪካ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመርም ማዕቀቡን ጨምሮ ሁሉም አማራጭ ጠረጴዛ ላይ እንዳለ ከዚህ ቀደም መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

ይህ ሁኔታ ደግሞ የአውሮፓ ኅብረትም ሆነ አሜሪካ እውነተኛ ፍላጎታቸው ማደራደርና በሰላማዊ መፍትሔ የኢትዮጵያን ችግር የመፍታት አይደለም የሚለውን ግምት የበለጠ የሚያጠናክር ነበር፡፡ ምዕራባውያኑ ድርድር ሲሉና የሰላም ሒደትን በተመለከተ ግፊት ሲያደርጉ በእርግጥም ገለልተኛና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ችግሩን ለመዳኘት ፈልገው ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ ጫና ለማሳደር ነው የሚለውን ጥርጣሬ የሰሞኑ አቋማቸው እንደሚያጭር ብዙዎች ይገምታሉ፡፡

በአንድ ወገን ድርድር ካልተካሄደና በድርድሩ ንቁ ተሳትፎ ካላደረግን እያሉ፣ በሌላ በኩል በማዕቀብ ቅጣት ማስፈራራት ምዕራባውያኑ ለአንድ ወገን ባጋደለው አካሄዳቸው የተፈጠረ መሆኑን የሚናገሩ በርካታ ናቸው፡፡

ይህን ሐሳብ የሚጋሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው አሰፋ አዳነ (ዶ/ር)፣ ‹‹ሕወሓቶች አቅም ያጡ ሲመስላቸውና ተዳክመዋል ብለው ሲያስቡ ነው ምዕራባውያኑ እየተረባረቡ ያሉት፤›› ይላሉ፡፡ ይህን ዘዴ ደግሞ ምዕራባውያኑ ለሦስተኛ ጊዜ እየሞከሩት መሆኑን የሚጠቅሱት አሰፋ (ዶ/ር)፣ ‹‹ሕወሓቶች በዕርዳታ ስም መሣሪያ እስኪገባላቸው ራሳቸውን አደራጅተው ለዳግም ጦርነት እስኪዘጋጁ ጊዜ ለመግዛት ነው፡፡ ዳግም አቅም አግኝተው የአማራንና የአፋርን ሕዝብ፣ እንዲሁም የትግራይን ወጣት ለማስጨፍጨፍ እንዲችሉ ድጋፍ እያደረጉላቸው እንጂ ድርድሩ እንዲሳካ በመፈለግ አይደለም፤›› የሚል ማብራሪያቸውንም ያክላሉ፡፡

የኢዜማው አቶ ግርማ በበኩላቸው የሰላም ሒደቱ እንዲሳካ ከተፈለገ የሕወሓት ትጥቅ መፍታት ጠቃሚ ቅድመ ሁኔታ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡ ‹‹ሕወሓት መሣሪያ ታጥቆ በምንም ዓይነት ሁኔታ ድርድር ላይ መቀመጥ አይችልም፣ ተገቢም አይደለም፤›› በማለት ነው አቶ ግርማ ከድርድሩ ሊቀድም የሚገባውን ቅድመ ሁኔታ የተናገሩት፡፡

ምዕራባውያኑ አሁን የሰላም ንግግሩ ይጀመር የሚለውን ግፊታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ካልተሟላ የሚሉትን ቅድመ ሁኔታም ለማስቀመጥ ሲቸገሩ አይታይም፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ እኩል ሕወሓት ትጥቅ ይፍታ የሚልም ሆነ ሌላ ያሟላ የሚሉት ቅድመ ሁኔታ መኖሩን ሲናገሩ አለመሰማቱ ብዙዎችን ያስገርማል፡፡

በሌላ በኩል የኤርትራን በጦርነቱ መካፈል ልክ እንደ የውጭ ጣልቃ ገብነት እያቀረቡት የሚገኙት ምዕራባውያኑ፣ እነሱ በድርድሩ ሒደት የሚያንፀባርቁትን አቋም እንደ የውጭ ጣልቃ ገብነት አለማየታቸው አስገራሚ እንደሆነ ነው ታዛቢዎች የሚናገሩት፡፡

በአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ስብሰባ ላይ አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት አስተዋይ አስተያየት ሲሰጡ መታየታቸውን ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡

አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛች አገር መሆኗን ጭምር ጠቅሰው፣ አገሪቱ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እንድትመለስ ከማገዝ በዘለለ ጣልቃ ገብነት እንደማይበጅ ሲጠይቁ ነበር፡፡

አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላትም የአውሮፓ ኅብረት ከአፍሪካ የሚመጣውን ስደተኛ ለማስቆም በሚል ብቻ የኢትዮጵያን ችግር መዳኘት እንደማይኖርበት ሲጠይቁም ተሰምተዋል፡፡ ‹የአፍሪካ ችግርን መፍቻ መፍትሔ ከአውሮፓ ሳይሆን ከራሳቸው ከአፍሪያካውያን መመንጨት አለበት› ሲሉ የተናገሩት አባላትም ተሰምተዋል፡፡ ይሁን እንጂ አብላጫ የፓርላማ አባላት በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲደረግ ከመደገፍ በተጨማሪ፣ የጦር መሣሪያ ማዕቀብ የመጣል ውሳኔን የሚደግፉ አባላት ሳይቀሩ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ነበር፡፡

ዓርብ መስከረም 27 ቀን 2015 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ‹‹HRC51›› የተባለ የውሳኔ ሐሳብ በ21 ድጋፍ፣ በ19 ተቃውሞና በሰባት ድምፀ ተዓቅቦ ፀድቋል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የምክር ቤቱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አጣሪ ኮሚቴ የሥራ ጊዜ እንዲራዘም ፈቃድ መስጠት ነው እየተባለ ነው፡፡

የኢዜማው አቶ ግርማ አሁን ምዕራባውያኑ ሕወሓት ከእነ ትጥቁ ወደ ድርድር እንዲገባ ግፊት እያደረጉ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ቀጥሎ ደግሞ የሚፈልገውን ስጡት›› ወደ የሚል ጫና ያመራሉ በማለትም የምዕራባውያኑ ጫና ወዴት እያመራ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ከሕወሓት ባህሪ በመነሳት ድርድሩ ይሳካል የሚል እምነት እንደሌላቸው የሚናገሩት አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹ለሕወሓት ብለውም ብቻ ሳይሆን ምዕራባውያኑ በራሳቸውም ፍላጎት በድርድሩ ሒደት ገንቢ ሚና አይጫወቱም፤›› ይላሉ፡፡

ምዕራባውያኑ ከፍተኛ ግፊት እያደረጉበት ያለው ይህ የሰላም ሒደት በሌሎች ምክንያቶች ሊደናቀፍ የሚችልበት ዕድል መኖሩን ከወዲሁ የሚናገሩ ብዙ ናቸው፡፡ በተለይ ሁለቱ ተደራዳሪ ኃይሎች ወደ ሰላም ንግግሩ ይዘዋቸው የሚገቡት የመደራደሪያ ነጥቦች የሚያቀራርቡ ካልሆኑ ንግግሩ ቢጀመርም፣ ብዙም ርቀት ሳይኬድ እንደሚሰናከል የሚናገሩ በርካቶች ናቸው፡፡

ይህን የሚደግፍ አስተያየት የሚሰጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው አሰፋ (ዶ/ር)፣ ‹‹ሕወሓቶች ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረው ሁኔታ ሁሉም ነገር እንዲመለስ ይላሉ፡፡ የወልቃይት ሁኔታ ወደ ነበረበት ይመለስ ይላሉ፡፡ ይህንን የሚሉ ከሆነ እነሱም በማይካድራ፣ በጭና፣ በሰሜን ዕዝ፣ በጋሊኮማ፣ በራያና በቆቦ ያደረሱትን ጭፍጨፋ ወደ ነበረበት ይመልሱልን፡፡ በአማራ ክልል የወደመውን ወደ 500 ቢሊዮን ብር ንብረት ጨምሮ ያጠፉትን ሕይወት ወደ ነበረበት ይመልሱልን፤›› ብለዋል፡፡

የመንግሥት ወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ ገጽ ዓርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ ስለሰላም ንግግሩ ሒደት መታረም ይገባቸዋል ስላላቸው ነጥቦች ማብራሪያ ሰጥቶ ነበር፡፡ የሰላም ንግግሩ በማን መካከል እንደሚካሄድ በዋናነት ያብራራው መረጃው፣ ንግግሩ የሚካሄደው በአንድ አማፂ ኃይልና በሕዝብ ተመርጦ ሥልጣን በያዘ መንግሥት መካከል መሆኑን ያመለክታል፡፡ ‹‹የትግራይ መንግሥት፣ የትግራይ የውጪ ግንኙነት፣ የትግራይ አስተዳደር ወይም የትግራይ ክልል መንግሥት›› የሚሉ አጠራሮች ሕጋዊ መሠረት የሌላቸውና የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትን የሚፃረሩ መሆኑን አስታውቆ፣ ማንኛውም አካል ስለሰላም ንግግር ሒደቱ ሲጠቅስ እነዚህን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚፃረሩ አጠራሮች ከመጠቀም መቆጠብ አለበት ብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -