በግር ጣራ መርገጥ
ሙዚቃ ሲጋልብ መውጣት መውረድ
መፍረጥ፡፡
ዓይኔን ማገላበጥ
መርበትበት መንቀጥቀጥ
መላጋት መንገድገድ እንደሰከረ ሰው
የናፈቀኝ ይኼ ነው፡፡
ተነስቼ ልዝለል
ቡጊ ቡጊ ልበል፡፡
ቡጊ-ቡጊ-ቡጊ
ከበሮ ሲያጋፋት ሙዚቃ ሲያናፋ
ልብሴን ጥዬ ልጥፋ
ልራቆት አብጄ
ልብረር ካለም ሄጄ፡፡
ሙዚቃ በጥላው ይምጣ ይሸፍነኝ
ሁሉንም ያስረሳኝ፡፡
እንደሳት ቦግ ቦግ
መውለብለብ መንተግተግ
መቃጠል መሞቅ ነው
ይኼ ነው ዳንሱ ይህ ነው፡፡
ልቤን ያነሳኛል
ዛር ይሰፍርብኛል፡፡
- ገብረ ክርስቶስ ደስታ