በበላይ ወልደየስ (ፕሮፌሰር)
ከአርባ ዓመት በፊት ከተለያዩ ውጭ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ ሦስት የኬሚካል ምህንድስና ትምህርት ተምረን የተመለስን እንደ ግብ ያደረግነው፣ ተምረን ያመጣነውን ትምህርት በአገራችን ማስጀመርና የተለያዩ የኬሚካል ፋብሪካዎች በአገሪቱ እንዲከፈቱ ጥናት በማጥናት ለመንግሥት ለማቅረብ ነበር፡፡ በዚህም እኔ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ አሥራት ቡልቡላ (ኢንጂነር)በዚያን ጊዜ የኬሚካል ኮርፖሬሽን የቴክኒክ ክፍል ማናጀርና በዚሁ ክፍል ባልደረባ የሆነ ሌሊሳ ዳባ (ኢንጂነር) ቴክኖሎጂስት ተሰባሰብን፡፡ እኔ የትምህርት ክፍሉን ለመክፈት በምሯሯጥበት ጊዜ እነዚህ ጓደኞቼም እያገዙኝ፣ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ኢንዱስትሪን መቃኘት ጀመርን፡፡ ቅድሚያ መስጠት ያለብን፣ በመጀመርያ በምግብ አገሪቷ ራሷን መቻል አለባት ወደሚለው መደምደሚያ ላይ ደረስን፡፡
ታሪክ እንደሚያስረዳው ኢትዮጵያ ግብርናን ከጀመሩት ጥንታዊ አገሮች አንዱ መሆኗ፣ ለእርሻ የሚሆን ሰፋፊ መሬት የያዘችና አገሪቷ ከሠራችበት ‹‹የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫት›› መሆን የምትችል መሆኗ በጥሩነቱ በአንድ በኩል፣ የግብርና አሠራሯ ኋላ ቀር በመሆኑና በየጊዜው ረሃብ ሲፈታተኗት መቆየቱ ደግሞ በድክመት በሌላ በኩል፣ እየተተረከ ይገኛል፡፡
ወደ ባህር ማዶ ስንሄድ የሠለጠኑት አገሮች ረሃብን ከአገራቸው ያስወገዱት፣ እርሻቸውን ዘመናዊ በማድረግ፣ በከፍተኛ ደረጃ በማዳበሪያ ተደግፈው በመሥራታቸው ነው፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው፣ በአውሮፓ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በረሃብ ምክንያት ብዙ አውሮፓውያን ወደ አሜሪካ መሰደዳቸው የታሪካቸው መጥፎ ነጥብ ሲሆን፣ በሌላ በኩል በጀርመን አገር በመጀመርያ የተመረተውን የናይትሮጂን ማዳበሪያ ወስደው ዘመናዊ እርሻ መጠቀማቸው፣ በዚህም የተትረፈረፈ ምግብ ማግኘታቸውና ስደት መቀነሳቸው፣ ጥሩው ታሪካቸው ሆኗል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል፣ በማዳበሪያ የታገዘ ዘመናዊ እርሻ ማስፋፋት አሌ የሚባል አይደለም፡፡
ይህንንም በመገንዘብ ሦስታችንም በዕውቀታችን ማዳበሪያ በኢትዮጵያ እንዲመረት አጥንተን ለመንግሥት ማቅረብ እንዳለብን ተስማማን፡፡ ለኢትዮጵያ አፈር ዋናዎቹ ተፈላጊ ንጥረ ነገሮች ናይትሮጂን፣ ፎስፌትና ፖታሽ መሆናቸውን ካወቅን በኋላ፣ እነዚህን ንጥረ ነገሮች በኬሚካል ማዳበሪያ መልክ ለማግኘት ዋናው መሠረቱ አሞኒያ (ናይትሮጂንና ሃይድሮጂን) የሚባሉትን ጋዞች ከተፈጥሮ ጋዝ ወይም ከድንጋይ ከሰል እንደምናገኝ አወቅን፡፡ የፎስፌትና የፖታሽ ማዕድናትም በአገሪቷ ውስጥ የት እንደምናገኝ አውቀን ነበር፤ በእዚህ ላይ እንዳለን፣ አሥራት (ኢንጂነር) የሳይንስና የቴክኖሎጂ ኮሚሽነር ሆኖ ተሾመ፡፡ እሱንም በመጠቀም፣ በመንግሥት በኩል ለጥናቱ ገንዘብ ለማግኘት እየጣርን ባለንበት ሰዓት በዚያን ጊዜ ሚኒስትር የነበሩት አቶ አሰፋ አብርሃ፣ የቻይና ኩባንያ የካሉብን የተፈጥሮ ጋዝን ወደ ማዳበሪያ ለመቀየር፣ የፕሮጀክት ንድፈ ሐሳብ ለኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረበውን የሚመረምር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ ዓብይ ኮሚቴ አስተባባሪነት፣ በሥሩ ኮሚሽነር አሥራትን የያዘ በምክትል ሚኒስትሮች የሚመራ ኮሚሽን ሲያቋቁሙ፣ እኔንና ኢንጂነር ሌሊሳን የያዘ ወደ ሃያ የሚጠጉ ቴክኖሎጂስቶችና የሳይንስ ባለሙያዎች በቴክኒክ ኮሚቴው ተካተቱ፡፡
እኔ ቴክኖሎጂውን፣ ሌሊሳ (ኢንጂነር) የኃይል ጥናቱን እየመራን ለሦስት ወራት በሥራ ሰዓት እየሠራን ጥናቱን በማጠናቀቅ ለኮሚሽኑ አስረከብን፡፡ ኮሚሽኑም ቻይናዎቹ ያቀረቡት የ150 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት በቴክኒካል ኮሚቴው አዋጭነት ጥናት መሠረት ተቀባይነት ስላለው መንግሥት ይሂድበት ብሎ ጥያቄውን አቀረበ፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ የተቀማጭ አድራሻ በኒዎርክና በጆሃንስበርግ ያለ ተቋም አዲስ ንድፈ ሐሳብ በዚሁ ከካሉብ ጋዝ ማዳበሪያ አመራረት ለመንግሥት እንዳቀረበ ሰማን፡፡ እንደሰማነው ይህኛው ከቻይናዎቹ እለያለሁ የሚለየው ከማዳበሪያ ሌላ፣ በአካባቢው ላለው ኅብረተሰብ፣ የመሠረተ ልማት ገንብቼ የልማቱ ተጠቃሚ አደርገዋለሁ የሚለውን ማካተቱ ነው፡፡
መንግሥትም እኛን ሳያሰማ አዲሱን ንድፈ ሐሳብ መርምሮ፣ ከወራት በኋላ ያንን ተቋም በኒዎርክና በጆሃንስበርግ ቢፈልግ ወይ የሚል ጠፋ፡፡ ቻይናዎቹም ይህንን ሲሰሙ ፕሮጀክታቸውን አጠፉት፡፡ እኛም ግራ ገባን፡፡ በነገራችን ላይ በዚያን ጊዜ ብዙ ባለድርሻ አካል በመንግሥትም ከመንግሥትም ውጪ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማዳበሪያ ገዝተው የሚያቀርቡ እንደ የግብርና ግብዓት አቅራቢ ድርጅት (AISE. Agricultural Input Supply Enterprise)፣ ያራ ኩባንያ፣ አማልጋሜትድ፣ ዲንሾ፣ ጉናና አምባሰል ወዘተ. የተባሉ ጉምታ ድርጅቶች ነበሩ፡፡ ማዳበሪያ በኢትዮጵያ መክፈት፣ የእነሱን ጥቅም ያስቀረዋል ብለው ቻይናዎቹ እንዳያመርቱ ፕሮጀክቱን አጨናግፈውት ይሆን? የሚለው ከመላምት ወዲህ እስካሁን ያወቅነው የለም፡፡
መልሱ እንቆቅልሽ ነበር፡፡ የዚህ ቴአትር ሦስታችንንም ቢያስደነግጠንም፣ ቢገርመንም፣ መንግሥት ለማካካሻ የሚሆን በኮሚሽነር አሥራት ግፊት፣ የድንጋይ ከሰልና የፎስፌት ማዕድናትን ለማልማት በቻይናና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል በጥቅምት ወር 1988 ዓ.ም. ስምምነት አደረገ፡፡ ይህንንም ተከትሎ በኢትዮጵያ ማዳበሪያ ለማምረት የሚያስችል በየካቲት ወር በ1988 ዓ.ም. የኮል ፎስፌት ማዳበሪያ ኮምፕሌክስ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተቋቋመ፡፡ ይህንንም ድርጅት በሥራ አመራር ቦርድነት እንዲመራ ኮሚሽነር አሥራት ቡልቡላ በሰብሳቢነት በላይ ወልደየስ (ዶ/ር ኢንጂነር)፣ አቶ ከተማ ታደሰ፣ አቶ አየለ አሰፋና አቶ መንገሻ በቀለ የተሰየሙ ሲሆን፣ በዋና ሥራ አስኪያጅነት ሌሊሳ ዳባ (ኢንጂነር) ተመደበ፡፡ የእኔ ድርሻ በዋናነት ቴክኒክ ነገር የሆኑትን መምራት ነበር፡፡ እንግዲህ ሦስታችንም በተለያየ የሥራ መደብ ይህንን ፕሮጀክት መምራት ጀመርን፡፡
የመጀመርያ ሥራ ያደረግነው የድንጋይ ከሰል አሉባቸው ተብለው የሚታወቁትን ቦታዎች ማወቅ፣ መጠናቸውን ማስፈተሽ ወዘተ. ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ የማዕድን ፍተሻ (Ethiopian Geological Survey) ሦስት ቦታዎች ማለትም በደልሞዬና በጭልጋ ከፍ ያለ የድንጋይ ከሰል እንደሚገኝ ተጠቆምን፡፡ በእነዚህም ቦታዎች የከርሰ ምድር ምርመራ እንዲያካሂዱ ለቻይናና ለአገር በቀል ቆፋሪ ድርጅቶች ሰጠናቸው፡፡ በእነዚህ ቦታዎች ከ50 በላይ ጥልቅ ቁፋሮ አስደርገን፣ ለፋብሪካ የሚሆን መጠናቸው በአስተማማኝነት ባልታወቀበት ሰዓት በኢሉባቦር ዞን በያዩ ወረዳ አጨቦና ሰምቦ የገበሬ ማኅበር አካባቢ በቅርብ ምልከታ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው የድንጋይ ከሰል እንደተገኘ፣ የእኛ የቦርድ አባል የሆነውና የኢትዮጵያ የማዕድን ፍተሻ ሥራ አስኪያጅ አቶ ከተማ ታደሰ አስታወቀን፡፡ እኛም ወዲያውኑ የጂኦሎጂ ምርመራ (የከርሰ ምድር ምርመራ) እንዲያደርግልን የሥራ ኮንትራት ለቻይና ድርጅት (China Jiangzi Corporation) ሰጠን፡፡ ውጤቱም ከበፊቶቹ ቦታዎች የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ፣ ትኩረታችንን ወደ ያዩ አደረግን፡፡ የቻይናውን ድርጅት የድንጋይ ከሰሉ መጠን አስተማማኝ ደረጃ እንዲያደርስ ስናስቀጥል፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ፋኩልቲ በእኔ ሰብሳቢነት አንድ ከዩኒቨርሲቲውና ከሚኒስቴሩ የተወጣጡ 17 ባለሙያዎች የያዘ ግብረ ኃይል በአማካሪነት አቋቁመን ሥራውን እንዲቀላቀሉ አደረግን፡፡
ከሦስት ዓመት ጥናት በኋላ በያዩ ከ220 ሚሊዮን ቶን በላይ አስተማማኝ የድንጋይ ከሰል፣ ለማዳበሪያና ለኃይል ማምረቺያ መኖሩን አረጋገጠን፡፡ ይህ ውጤት አጥጋቢ ሆኖ በመገኘቱ በደልቢ፣ ሞዬና በጭልጋ የነበረውን ጥናት አቋርጠን በቻይናና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 13 ቀን 1996 በያዩ ማዳበሪያ ለማምረት፣ ቻይና የቴክኒክ ድጋፍ ለመስጠት ስምምነት አስደረግን፡፡ እኛም አጋዥ በማግኘታችን ተደስተን፡፡ ጽሕፈት ቤታችንን አጠናከርን፡፡ ኮሚሽነር አሥራትና አቶ ከተማ፣ በየጊዜው ከእኛ ጋራ ከውጭ ሆነው ለመሥራት በመስማማት ወደ ሌላ ሥራ ሲሄዱ፣ አዲስ የሥራ አመራር ቦርድ፣ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ፣ አቶ ቶሎሳ ሻጊ፣ አቶ ዋሪዮ ገልገሎና እኔ ተሰየምን፡፡
ለአዲሱ የሥራ አመራር በሥዕል የተደገፈ አንድ ሰዓት ስለቴክኖሎጂውና ስለተደረሰበት ሥራ ገለጻ አደረግሁ፡፡ ወዲያው ቀጣይ የሥራ መርሐ ግብር ዝርዝር አስቀመጥን፡፡ ከእነዚህም የማዕድን ልማት አዋጪነት ጥናት (Mine Development Feasibility Study)፣ የድንጋይ ከሰሉን ወደ ቻይና ልኮ በፋብሪካ ሙከራ ማድረግ (Industrial Bulk Test) በድንጋይ ከሰል ላይ የተመሠረተ የናይትሮጂን ማዳበሪያ (ዩሪያ) ፋብሪካ ኮመፕሌከስ የአዋጭነት ጥናት ማጠናቀቅ ጥናቱ አዋጪ ከሆነ የአካባቢ ደኅንነት ግምገማ ሥራ (Environmental & Social Impact Assessment)፣ ፋብሪካ ለሚገነባ የዓለም አቀፍ ተቋራጭ በመስጠት ግንባታ ማስጀመር ወዘተ. ይገኙበታል፡፡
ከግንባታው በስተቀር፣ ዝርዝር ጥናቱን እንዲያጠኑልን ለቻይና ኩባንያ Complant (Chaina National Complete Plant Importe and Export Corporation) እና በአማካሪነት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ፋኩልቲ የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል እኔን ጨምሮ እንዲሠሩ ሰጠናቸው፡፡ የመርሐ ግብሩን አፈጻጸም ለጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊና ለሚመለከታቸው ሚኒስትሮች፣ በየሦስት ወሩ በሥዕል የተደገፈ ገለጻ ሪፖርት እናቀርብ ነበር፡፡ ከተገኘውም የጥናቱ ውጤት ውስጥ በዓመት እስከ ሁለት ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል በማምረት እስከ 500,000 ቶን የናይትሮጂን ማዳበሪያ (ዩሪያ) ለማምረት የሚያስችል ዝርዝር የከሰል ልማትና የማዳበሪያ ኮምፕሌከስ አዋጭነት ጥናት (Feasibility Study) የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ጥናቶቹ እየተካሄዱ 220 ቶን ከሰል ወደ ቻይና ልከን እኔም በተገኘሁበት ሊቋቋም የታሰበ በፋብሪካ ሙከራ አስደረግን፡፡ በዚህ መሥፈርት መሠረት ከሰሉን የሚያቃጥል (Gasification) መሣሪያ እንዲፈበረክ ተስማማን፡፡ በተጨማሪም፣ የአካባቢ ደኅነት ግምገማ ሥራ ማስጠናት ጀመርን፡፡ በጥናቱም ላይ የተሳሳተ አስተሳሰብ ያላቸው የድንጋይ ከሰል ሲቃጠል ጭስና ብናኝ ስለሚሰጥ ከአካባቢው አልፎ ለዓለም ሙቀት መጨመር ምክንያት ይሆናል ወዘተ. የሚሉ ብቅ አሉ፡፡ ይህንን ሐሳብ ከፍተኛ ባለሥልጣናትም ተጋርተውታል፡፡ ይህንን የሚሉት አልፈው የአካባቢው ደን በዓለም ተጠባቂ ቅርስ ነው የሚል ወረቀት ይዘው መጡ፡፡ እኔ ፕሮጀክቱ ለአገሬም ሆነ ለዓለም የሚፈጥረው አደጋ የለም ብዬ መሞገት ነበረብኝ፡፡
ከማቀርባቸውም ምክንያቶች የምንጠቀመውም ንፁህ ከሰል (Clean Coal Technology) ቴክኖሎጂ መሆኑ፣ እኛ የምናመርተው ከዓለም ደረጃ እዚህ ግባ የማይባል መሆኑ፣ ወዘተ. የሚሉት ይገኙበታል፡፡ አጥጋቢ ሙግት ስላላመጡ በዚያው ቆሙ፡፡ በዚህ ሰዓት ሌሊሳ (ኢንጂነር) ከውጭ ሆኖ እኛን እንደሚያግዝ በመስማማት ወደ ሌላ ቦታ ተዛወረ፡፡ በምትኩም ካሣዬ የሺጥላ (ኢንጂነር) ጽሕፈት ቤቱን እንዲመራ አደረግን፡፡ እንግዲህ እኔ ብቻዬን በመስመር ላይ ቀረሁ፡፡ ከ13 ዓመት በላይ ተከታታይ ጥናት የተደረገበትን የቻይናው ኩባንያ የናይትሮጂን ማዳበሪያ (ዩሪያ) ፋብሪካ በኢትዮጵያ መቋቋም የሚያስችለውን ዝርዝር ጥናት አቀረበ፡፡
በዚህም መሠረት በያዩ በ44 ካሬ ኪሎ ሜትር ውስጥ የሚገኘውን 178 ሚሊዮን ቶን ክምችት በዓመት አንድ ሚሊዮን 200 ሺሕ በማውጣት እንደሚጠቀም በየዓመት 300 ሺሕ ቶን ዩሪያ፣ 30 ቶን ኤታኖል፣ አራት ሺሕ አምስት መቶ ቶን ድኚ (Sulphur) እና 90 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመርት ጥናቱ ካሳየ በኋላ ጥናቱ አዋጭ የሚሆነው ማዳበሪያ 390 ዶላር፣ የኤሌክትሪክ ኃይል 60 ዶላር በሜጋ ዋት ሰዓት ሜታኖል 800 ዶላር በቶን ሲሸጥ ብቻ ነው በማለት ያጠቃልላል፡፡ የድንጋይ ከሰል ማዕድንና የማዳበሪያ ኮምፕሌክስ ለማቋቋም በግምት 787 ሚሊዮን ዶላር የሚፈጅ ሲሆን፣ ከዚሁ ውስጥ ወደ 70 ሚሊዮን ዶላር የሚወጣው ለመሠረተ ልማት ግንባታ እንዲሆን ታስቧል፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 666 ሚሊዮን ከቻይና ባንክ፣ ቀሪውን 121 ሚሊዮን ዶላር ከኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚሸፈን ግንዛቤ ተወስዷል፡፡
የግንባታ ጊዜውም አምስት ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተተንብይዋል፡፡ ይህንን ውጤት ይዘን የፋብሪካ ግንባታ ለማስፈቀድ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ቀረብን፡፡ በስብሰባው ላይ የንግድና የኢንዱስትሪ፣ የገንዘብ፣ የማዕድን ሚኒስትሮች፣ የቦርድ ሰብሳቢውና ሌሎች ከፍተኛ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡ እንደተለመደው የደረስንበት የአዋጭነት ጥናቱንና የቀረው ወደ ግንባታ መግባት ብቻ እንደሆነ በማስረዳት፣ ለአንድ ሰዓት በሥዕል የተደገፈ ገለጻ አደረግሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የተለያየ ጥያቄ አቅርበውልኝ ከመለስኩ በኋላ፣ አስደንጋጭ ውሳኔ አሰሙን፡፡ ውሳኔውም የግንባታው ዋጋ ከፍተኛ ስለሆነ፣ በዚህ ፕሮጀክት ላይ ኢንቨስት አናደርግም የሚል ነበር፡፡ እኔም የግንባታ ወጪው ከምዕራቡ ዓለም የቀነሰ እንደሆነ፣ አዋጪም እንደሆነ ለማስረዳት ሞከርኩ፡፡ በስብሰባው የነበሩ ሚኒስትሮች ምንም ሊተነፍሱ አልፈለጉም፡፡
ከ13 ዓመት በላይ የተለፋ ፕሮጀክትና ከመቶ ሚሊዮን ብር የወጣበት ጥናት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥቂት መስመር ዘጉት፡፡ እኔም ከካሉብ ጋዝ ማዳበሪያ ለማውጣት የለፋሁበት ቁጭቴ ሳይለቀኝ፣ ከድንጋይ ከሰል ማዳበሪያ ለማምረት ያጠፋሁበት ጊዜ ተጨምሮ፣ ማዳበሪያን ለማምረት ምን ዓይነት ድግምት ነው እዚህ አገር ያለው እያልኩ ቤቴ ገባሁ፡፡ ወርኃዊ የቦርድ ስብሰባ ተጠራን፡፡ እኔም የተለፋበት ሥራ ሁሉ ውኃ ስለበላው ቦርዱ መፍረስ አለበት አልኩኝ፡፡ ሰብሳቢው ቦርዱ እንዲቆይ መንግሥት ወስኗል በማለት አሰናበቱን፡፡ በየወሩ ቃለ ጉባዔ ለማፅደቅ እየተሰበሰብን ለጥቂት ዓመታት ካለ ሥራ ቆየን፡፡
አንድ ቀን ቤቴ የምሽት ዜና ስሰማ እኛ የለፋንበትን የያዩ የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ሜቴክ በ11,084,852,000 ብር መፈራረሙን ሰማሁ፡፡ ደነገጥኩ፡፡ ሜቴክ በምን አቅሙ ነው እንደዚህ ያለ ውስብስብ (Complex) ፕሮጀክት የሚገነባው እያልኩ ሌቱን በሙሉ መልስ የሌለው ጥያቄ ስጠይቅ አድሬ፣ በነጋታው የቦርድ አባላቱን የሰሙት ነገር እንዳለ ጠየቅኩ፡፡ እንደኔው ናቸው፡፡ ምንም ነገር አያውቁም፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ የቦርድ ሰብሳቢው ስብሰባ ጠሩን፡፡ ምን እንደሆነ ብንጠይቃቸው እሳቸውም በዜና የተሰማውን በወቅቱ ከነበረው ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን እንደሰሙ ነገሩ፡፡ አክለውም፣ ለሜቴክ ቅድሚያ ክፍያ ሦስት ቢሊዮን ብር እንድንፈቅድ አጀንዳ አስያዙ፡፡
ይህ አጀንዳ ሲቀርብ እጄን በማውጣት እኛ ከሜቴክ ጋር አልተዋዋልንም፡፡ የተዋዋለው አካል ይክፈል እንጂ፣ እንዴት ካለ አግባብ እኛ እንጠየቃለን አልኩ፡፡ ሌሎቹም የቦርድ አካላት በሆነው ደንግጠው ነበርና የእኔውን ሐሳብ በመደገፍ የቀረበውን ክፍያ ሳንቀበል ስብሰባው ተበተነ፡፡ ቦርዱ አይመለከተኝም ያለውን የገንዘብ ሚኒስቴር፣ ንግድ ባንክ፣ ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ እንደሚከፍል አድርጎ፣ እንዲያበድር በማድረግ፣ ለሜቴክ ሦስት ቢሊዮን ብር እንዲሰጠው ተደረገ፡፡ ከሦስት ወር በኋላ መንግሥት የኬሚካል ኮርፖሬሽን የሚል ሙገርንና የማዳበሪያ ፕሮጀክቱን የያዘ ተቋም አቋቋመ፡፡ በዚህ ላይ አዲስ የቦርድ አባለት አቶ ኃይለ መስቀል ተፈራ፣ አቶ አብዱልሃዚዝ መሐመድ፣ አቶ ሳሙኤል ሐላላ፣ አቶ ተፈሪ ደመቀ፣ አቶ ተመስገን ዋለልኝ፣ አቶ ነፃነት ወንድይራድና እኔን (ለአራተኛ ጊዜ ቴክኒኩን ይመራል በሚል ዕሳቤ) ተሰየምን፡፡
እኔም እንደወትሮዬ ቴክኖሎጂውን፣ ምን እንደተሠራና እስከ አለንበት ሁኔታ ሥዕላዊ ገለጻ ለአዳዲሶቹ የቦርድ አባለት ከማድረጌም በላይ በሚያሳዝን ሁኔታ ሜቴክ ይህንን ፕሮጀክት የመሥራት አቅም እንደሌለው ገለጽኩላቸው፡፡ መሥራት ግን ግድ ስለሆነ ኮርፖሬሽኑ ፕሮጀክቱን የመቆጣጠር ብቃት ስለሌለው፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እኔ አሠሪ ስለሆንኩ ሳልገባበት በአማካሪነት እንዲሠራ አደረግን፡፡ ይህንንም ሜቴክ እንዲያውቀው ሲደረግ፣ እኔ የተፈራረምኩት ገንብተህ፣ ፈትሸህ አስተላልፍ (Build – Operate – Transfer (BOT)) ስለሆነና እኔም የመንግሥት መሥሪያ ቤት አካል ስለሆንኩ የመንግሥት መሥሪያ ቤትን ሌላ የመንግሥት መሥሪያ ቤት አይቆጣጠርም፡፡ ስለዚህ ቦርድ የሚባል አልቀበልም አማካሪውንም እንዲህ ብሎ እምቢ አለ፡፡
መንግሥትም አንተ ተቋራጭ ስለሆንክ እኔን የሚወክለው ቦርዱ ስለሆነ፣ የፕሮጀክቱ ባለቤት እሱ ስለሆነ፣ ከእሱ ጋራ ሥራ ብሎ መልስ ሰጠው፡፡ ሜቴክም እየተነጫነጨ ሲሻው በተለይ አማካሪውንና የኮርፖሬሺኑ ሥራ አስፈጻሚዎች እየተሳደበ ቀጠለ፡፡ በሥራውም ላይ የዓመት የሥራ ዕቅድህን አምጣ ስንለው ትልቅ ፕሮጀክት የሚያቀርበውን ጥራቱን የጠበቀ አቀራረብ ሳይሆን፣ የመንደር ሥራ የሚያቀርቡት ተራ አቀራረብ ሆኖ ተገኘ፡፡ እኔ እንደዚህ ዓይነት አቀራረብ አይደለም መቅረብ ያለበት ስል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ድሮስ የትምክህተኞችና የጠባቦች ዋሻ ነው፣ ከናንተ ምን ይጠበቃል ሆነ መልሱ፡፡ እኔም አጣፋውን ስመልስ ቦርዱ በመገላገል ያበርድ ነበር፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ ሥራ አስፈጻሚው ‹‹ሜቴክ ገንዘብ ስላለቀብኝ የሚቀጥለው ክፍያ ይለቀቅልኝ፤›› ብሎ ስለጠየቀኝ ቦርዱ እንዲፈቅድለት ብሎ አጀንዳ አስያዘ፡፡
ቦርዱም በኮንትራቱ መሠረት ይከፈለው እዚህ ለምን ታመጣለህ ብሎ መለሰ፡፡ ሥራ አስፈጻሚውም ኮንትራቱ የሚለው እንደ ማንኛውም ኮንትራት ሜቴክ ሥራ ሲጀምር የወሰደውን ገንዘብ ሠርቶ ሲጨርስ ተተምኖ፣ የሚቀጥለው ክፍያ ይለቀቃል ስለሚል አማካሪው ቡድን ይህንን ሲፈትሽ በቦታው ላይ ያልተጠቀመበትን ቁሳቁስ ጨምሮ፣ ያወጣው ገንዘብ ከአንድ ቢሊዮን ተኩል አይበልጥም፡፡ የተከፈለው ደግሞ ሦስት ቢሊዮን ነው፡፡ በዚህም ከኮንትራቱ ውጭ በመሆኑ ቸገረን አሉ፡፡ እኛም ከኮንትራቱ ውጪ የሚደረግ የለም ብለን መለስን፡፡ ከሳምንት በኋላ የቦርድ ሰብሳቢው ደውለው መንግሥት ኮንትራቱ እንደገና ይስተካከልና ገንዘብ ይከፈለው ስለተባለ ስብሰባ ልጠራ ነው አሉኝ፡፡
እኔም ቅዋሜዬን ነግሬ በተጠራው ስብሰባ ላይ አልተገኘሁም፡፡ እኔ በሌለሁበት ኮንትራቱ ታድሶ ሜቴክ ሌላ የሚፈልገውን ገንዘብ ሳይሠራና ሳያወራርድ፣ ተሰጠው፡፡ሜቴክ እንደፈራነው አቅም አጥቶ በመሯሯጥ፣ ኃላፊነት የጎደላቸው ለገንዘብ ብቻ የሚሠሩ በአገር ውስጥ ያሉ መሐንዲሶችና ምንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች ከውጭ እያመጣ ከአቅም በታች እያሠራ ገንዘቡን መርጨት ጀመረ፡፡ በዚህም ሳይቆም ቻይናዎቹ ዲዛይን ያደረጉትንና ሜቴክም ተቀብሎ ግንባታ የገባበትን ማፍረስ ጀመረ፡፡ ከእነዚህም አንዱ በከሰል ማዕድን ማውጫውና በማዳበሪያው ፋብሪካ መካከል ዕርቀት እንዲኖረው በምክንያታዊነት በመካከላቸው ተራራ አድርገው ቻይናዎቹ ዲዛይን ያደረጉትን እንዲያፈርስ በገንዘብ የሜቴክ ዘመድን ለመጥቀም፣ በአንድ ቢሊዮን ተኩል ብር ተራራ እንዲንድለት ኮንትራት ተሰጠው፡፡ እኔም ይህንን እንደሰማሁ አምርሬ ተቃወምሁ፡፡
የሜቴክ መልስ ግን ከማይምነት ብዙ ያልራቀ ‹‹ድንጋዩን ወደ ፋብሪካ ለመጓጓዝ የሚወጣውን የትራንስፖርት ወጪ ለመቀነስ ነው፤›› የሚል ነበር፡፡ በዚህ ዓይነት ስንጯጯህ ዓመታት አለፉ፡፡ ሜቴክ መስከረም ላይ በስንት ልመና የዓመቱን ዕቅድ ሲያስቀምጥ፣ ፕሮጀክቱን 70 በመቶ አደርሰዋለሁ ይላል፡፡ አፈጻጸሙን ሐምሌ ላይ ስንገመግም ከሁለት በመቶ አይዘልም፡፡ ጠቅላላ ቦርዱ ይንጫጫል፡፡ ሜቴክ ግን ጌታዋን የተማመነች በግ ጅራቷን ውጪ እንደምታሳድረው፣ ‹‹ሰማኋቸው የት ትደርሳላችሁ፤›› ነበር መልሱ፡፡ ሜቴክ በ11 ቢሊዮን ብር ሠርቼ አስረክባለሁ ያለው ፕሮጀክት ወደ ሃያ ቢሊዮን አደረስኩት ይላል፡፡ ንግድ ባንክ፣ ወለዱን ብቻ በሙገር ሲሚንቶ ላይ እየጫነ፣ ገንዘብ ለሜቴክ ይከፍላል፡፡ ግዑዙ ማዳበሪያ ፋብሪካ በዕዳ ይጥለቀለቃል፡፡ የኮርፖሬሺኑ የሥራ አመራር የዩኒቨርሲቲው አማካሪ ለቦርዱ ይጮሃሉ፡፡ ቦርዱም ኃላፊነቱ ከበደው፡፡ ግራ ተጋባ፡፡ ለበላይ ቢጮህም መልስ የሚሰጥ የለም፡፡ ‹‹ውሾቹ ይጮሃሉ፣ ግመሎቹም ጉዞአቸውን ይቀጥላሉ፤›› ሆነ፡፡ እኔ በየቦታው ለማገኛቸው ለሕወሓትና ሌሎች ሚኒስትሮች ጩኸቴን ቀጠልኩ፡፡ የሚገርመው ሁሉም ያነጋገርኩዋቸው “እንዴት እንዲህ ይደረጋል” ነበር መልሱ፡፡ ማናቸውም ሊያስቆሙ አልቻሉም፡፡ የቦርድ ሰብሳቢው ቦርዱ እንደተቸገረ ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያስታውቁና በሚነስትሩ ጠያቂነት አንድ ኮሚቴ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር፣ የመከላከያ ሚኒስትር፣ ጄነራል ክንፈ፣ አቶ ኃይለ መስቀል የቦርድ ሰብሳቢ፣ የዩኒቨርሲቲ አማካሪ ቡድን ሰብሳቢ የያዘ ተሰየመ፡፡
ስብሰባውም፣ በመከላከያ ሚኒስቴር መሆን ሲገባው፣ ሜቴኮች ክብራችንን ይነካል በማለት በእነሱ ዋና ጽሕፈት ቤት እንዲሆን አደረጉ፡፡ የተቋቋመው ሚኒስትሮቹ ያሉበት ኮሚቴ ፕሮጀክቱን ለመደገፍ የተቻለውን ቢጥርም፣ በሜቴክ አቅም ውስንነት ፕሮጀክቱ ፈቀቅ ሊል አልቻለም፡፡ ከሚቴው ሜቴክ አቅም እንደሌለውና ፕሮጀክቱን ሊያጠናቅቀው እንደማይችል ከድምዳሜ ላይ ቢደርስም፣ ሜቴክን አስቁሞ ከፕሮጀክቱ ማስወጣት ግን እንደማይችል ያውቅ ነበር፡፡ ይህ በእንደዚህ እያለ የቄሮ፣ የፋኖ፣ የዘርማ፣ ወዘተ. ንቅናቄ በየቦታው እየተፋፋመ መጣ፡፡
ኢሕአዴግ ውስጥ የሕወሓት የበላይነት ቀርቶ ሌላ ቡድን መጣ፡፡ ይህንንም ተከትሎ፣ የለውጥ ስሜት ከዳር እስከ ዳር ፈነዳ፡፡ አንዳንድ የፓርላማ አባላትም መንግሥትን መተቸት ጀመሩ፡፡ ሜቴክ በስኳርና በያዩ ማዳበሪያ ፕሮጀክቶች ላይ እየፈጸመ ያለውን ሥራ መኮነን ጀመሩ፡፡ በያዩ ፕሮጀክት ለተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ፣ የእኛ የቦርድ ሰብሳቢ፣ አቶ ኃይለ መስቀል ጠንከር ያለ ትችት በሜቴክ ላይ አቀረቡ፡፡ ብዙም ሳይቆይ አዲስ የቦርድ አባላት ተሰየሙ፡፡ አቶ ኃይለ መስቀልን ከቦርድ ሰብሳቢነት አንስተው፣ ተራ አባል አደረጉዋቸው፡፡ አዲሶቹም የቦርድ አባለት አቶ በከር ሻሌ ሰብሳቢ፣ ወ/ሮ ዘነቡ ታደሰ፣ አቶ ኃይለ መስቀል፣ አቶ አህመድ ሺዲ፣ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፣ አቶ ቶሎሳ ደገፋና አቶ ጌታቸው ኃይለ ማርያም ሲሆኑ፣ አቶ ሳሙኤል ሐላላ አዲስ የቦርድ አባልና እኔ ለአምስተኛ ጊዜ አባል በመሆን ተሰየምን፡፡
እንደ ለመድኩትም ለአዲሶቹ ቦርድ አባለት ስለፕሮጀክቱ አካሄድና ያለበትን ሁኔታ በሥዕል የተደገፈ ገለጻ አደረግሁ፡፡ የቦርድ አባላትም የሜቴክ ሁኔታ በለውጡ ምክንያት ያውቁ ነበርና በተቻለ መጠን መንግሥት ግፊት እንዲያደርግና ፕሮጀክቱ እንዲተርፍ፣ የእኔን ጩኸት እየተቀበሉ ለማስተጋባት ሞከሩ፡፡ ግን ገና የሜቴክ ደጋፊዎች በሥልጣን ላይ ስላሉ ብዙም ለውጥ ሊያመጡ አልቻሉም፡፡ የሚዲያ ሰዎች አንዳንድ የፓርላማ አባላት፣ ወዘተ. ለውጡን ተከትሎ የያዩ ፕሮጀክት ለምንድነው የተጓተተው? የሚል ጥያቄ ማንሳት ጀመሩ፡፡ ለሚጠይቁኝ ሁሉ ሜቴክ አቅም ሳይኖረው መንግሥት የፖለቲካ ውሳኔ ወስዶ ፕሮጀክቱን ሰጠው፡፡ ሜቴክ ከድንጋይ የከሰል ማዳበሪያ እንዴት እንደሚመረት አያውቅም፡፡ የሰማው ፕሮጀክቱ ሲሰጠው ነው በማለት መልስ እሰጥ ነበር፡፡ እዚህ ላይ ለመናገር የምፈልገው ሜቴክ ገንዘቡን ለሚፈልገው ሥራ እየፈጠረ የሚሰጠው አላግባብ ነው እያልኩ እቃወም ነበር እንጂ ዓይኑን አፍጥጦ እንደሚዘርፍ አላውቅም ነበር፡፡ አንድም ቀን ሜቴክ ገንዘቡን ዘረፈው ብዬ ተናግሬም አላውቅም፡፡ ሁሌም የእኔ ጩኸት የነበረው፣ ሜቴክ ቴክኒካል ብቃት የለውም፡፡ ሜቴክ ማዳበሪያ ለማምረት የሚያስችሉ የበቃ የሰው ኃይል የለውም፡፡ ምን ምን መሣሪያዎች እንደሚያስፈልጉ አያውቃቸውም ወዘተ ነበረ፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ፣ ሜቴክ ለያዩ ማዳበሪያ መሥሪያ የተያዘውን የድንጋይ ከሰል ለመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ መጠቀሚያ ሲያጓጉዝ ቄሮዎች ያስቆሙታል፡፡ ሜቴክም ይህ የቄሮዎች ሥራ ሕገወጥ ስለሆነ መንግሥት ያስቁምልኝ ብሎ ጠየቀ፡፡ እኛም ቄሮዎቹ ሳይሆኑ፣ ሜቴክ ነው ማቆም ያለበት ብለን ተንጫጫን፡፡ አንዳንድ የፓርላማ አባላትም ጥያቄ ማንሳት ጀመሩ፡፡ በዚህን ጊዜ በፓርላማው ውስጥ የመንግሥት ልማቶች ሚኒስትር የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ የያዩ ማዳበሪያ ኮምፕሌክስ፣ የቦርድ ሰብሳቢ፣ የአማካሪ ቡድኑ ሰብሳቢ፣ የፕሮጀክቱ ሥራ አስፈጻሚዎች በፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ጥሪ ላኩ፡፡ የቦርድ ሰብሳቢውም፣ በመደበኛ የቦርድ ስብሰባ ጥያቄውን አቀረቡ፡፡ በመቀጠልም ሰብሳቢው ከእኛ የበለጠ ይህንን ሊያውቅና ሊያስረዳ የሚችለው ፕሮፌሰር ስለሆነ ቦርዱን ወክሎ ይሂድ ብሎ ወደ እኔ ጠቆሙ፡፡ በዚህን ጊዜ እኔ ተቃወምኩ፡፡ ምክንያቱም ‹‹እኔና ሜቴኮች ጥሩ የሥራ ግንኙነት ስለሌለን ሜቴኮች ደማቸው ስለሚፈላ እኔ አልሄድም›› አልኩኝ፡፡ ቦርድ ሰብሳቢውም፣ ‹‹እስከዚህ እንኳ አትዳረሱም፡፡ ከአንተ ሌላ ብቁ ሰው የለም፡፡ ሂድ ብለው›› አስወሰኑብኝ፡፡ እኔም ፓርላማ በተጠራሁበት ቀን ደረስኩ፡፡ ስብሰባውም ተጀመረ፡፡ የቋሚ ኮሚቴውም ሰብሳቢ (አሁን በፓርላማው የሉም)፣ ለቦርዱ (ለእኔ) በቀጥታ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ጥያቄዎቹም ‹‹ሜቴክ መቼ ነው የሚጨርሰው?››፣ ‹‹ድንጋይ ከሰሉን ሜቴክ ሲያጓጓዝ፣ ቦርዱ ያውቅ ነበር ወይ?››፣ ‹‹ቦርዱ ለመሆኑ ፕሮጀክቱን ይከታተላል ወይ?››፣ ወዘተ. የሚሉ በቦርዱ ላይ ስላቅ ያዘለ ጥያቄዎች ይገኙበታል፡፡ ለፓርላማው የሚገባውን ክብር ጠብቄ መልስ ሰጠሁ፡፡
ከመልሶቹም ውስጥ ‹‹ፕሮጀክቱ መቼ ሊያልቅ እንደሚችል፣ ማንም አያውቅም፣ ከእግዚአብሔር ውጪ፡፡ ሜቴክ የተላከው ፋብሪካ እንዲገነባ እንጂ፣ የድንጋይ ከሰል አውጥቶ እንዲሸጥ አይደለም፡፡ ፋብሪካው ሲቋቋም የድንጋይ ከሰሉ ለ32 ዓመት እንዲበቃ ታስቦ ነው፡፡ አሁን እየተዘረፈ ከሄደ፣ በመሀከሉ ላይ ቢያልቅ ምን ሊኮን ነው፡፡ ይህ ወንጀል ነው፡፡ ፕሮጀክቱን ቦርዱ ይከታተላል፡፡ ሜቴክ ተባባሪ አይደለም፡፡ በሦስት ዓመት ጨርሼ አቀርባለሁ ያለው አሁን ወደ አሥር ዓመት እየተጠጋ ነው፡፡ ፕሮጀክት በታሰበለት ጊዜ ካልተጨረሰ ለሚራዘመው ጊዜ ከፍተኛ ተጨማሪ ወጪ ያስከትላል፡፡መዘግየት ላይ ለፕሮጀክቱ ህልውና ‹‹ቀይ መስመር አለው››፡፡ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ሰብሳቢው ምን ዓይነት መልስ እንደጠበቁ አላውቅም፡፡ ደስ አላላቸውም፡፡ ደስ አለማለት ብቻ ሳይሆን፣ ራሳቸውን መቆጣጠር አልቻሉም፡፡ ለሻይ ዕረፍት ስብሰባውን አቋረጡ፡፡ ከስብሰባው መልስ ሰብሳቢው፣ ከፓርላማ ሥርዓት በወጣ ሁኔታ መልስ ሰጡ፡፡ ከመልሶቹም ውስጥ ‹‹ቦርዱ ሥራውን እንዳልሠራ፣ በትምክተኝነትና በጠባብ አስተሳሰብ እየተመራ ሥራው እንዳይሄድ እንቅፋት የሆነ እንደሆነ፣ የሚሉ የሜቴክ ቃል አቀባይ ዓይነት መልሶች ይገኝበታል፡፡ እኔም የተሰጠው መልስ ‹‹ከአንድ የፓርላማ አባል የማይጠበቅ ነው›› ብዬ መልስ ለመስጠት እጄን ሳወጣ አልቀበልም ብለው ስብሰባውን በተኑት፡፡ እኔም ሳላወራርድ ስብሰባው መበተኑ እየቆጨኝ ከፓርላማው ወጣሁ፡፡
ይህንንም ተመልሼ ለቦርድ አባላቱ ገለጽኩላቸው፡፡ ቦርዱም በቁጣ ምንድነው የተፈለገው ብሎ ዝም አለ፡፡ ከፓርላማ ከተመለስኩ ከጥቂት ቀናት በኋላ ከመንግሥት ልማት ሚኒስቴር ከቦርዱ እንደተነሳሁ በደብዳቤ እንዳውቅ ተደረግሁ፡፡ ከ20 ዓመት በላይ ብዙ ገንዘብ ላገኝበት የምችለውን ሥራ በነፃ አፈር አስምሼ፣ የድንጋይ ከሰል አስገኝቼ፣ የአዋጭነት ጥናት አስጠንቼ፣ የፋብሪካ ዲዛይን አሠርቼ፣ ቻይናዎቹ ማዳበሪያ ፋብሪካ እንዲሠሩ እየተነጋገርን እያለን መንግሥት አቅም ለሌለው ሜቴክ ሰጥቶ እንዲወድቅ ሲያደርግ አይሆንም፣ አገሪቷ ብዙ የሰው ሀብት፣ ዕውቀትና ገንዘብ ፈሶበታል ብዬ ስለታገልሁ የሜቴክ ሰዎች ከመንግሥት ጋራ ተስማምተው በአገሬ ላይ እንደ ሁለተኛ ዜጋ በመቁጠር፣ የማዳበሪያ ቦርድ የሥራ አመራር ሆኜ እንዳልታይ፣ ከአካባቢው እንድርቅ፣ የመሬት ግብዓታቸው ከመፈጸሙ በፊት እኔን ተበቀሉ፡፡ እኔ ከማዳበሪያ ቦርድ የሥራ አመራር ከተወገድኩ በኋላ ሜቴክ ሲወድቅ ብዙ ጉድ ሰማን፡፡ እኛ የምንታገለው የያዘውን ፕሮጀክት ለመሥራት አቅም ስለሌለው ገንዘቡን ያባክናል ነው እንጂ በተቀናጀ መልኩ ይዘርፋል ብለን አልነበረም፡፡
ሜቴክ ሲወድቅ አዲሱ መንግሥትም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያልጠበቁት ከፍተኛ መርዶ ደረሳቸው፡፡ ሜቴክ የያዛቸው ሁሉም ፕሮጀክቶች እንደ ተዘረፉ፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ መዋጮ እየተገነባ ያለው የህዳሴ ግድብም አንዱ ነበር፡፡ አዲሱ መንግሥትም ይህ የአገር ኩራት የሆነው ፕሮጀክት መቋረጥ በሕዝቡ ላይ የሚደርሰውን ሐዘን በመገንዘብ ወዲያው ካለ አቅሙ ሜቴክ የያዘውን ወሰዶ ፕሮጀክቱን ለዓለም አቀፍ ተቋራጭ በመስጠት አስቀጠለ፡፡ ተቋራጩም የህዳሴው ግድብ የአገር ኩራት መገለጫ መሆኑን ተረድቶ፣ ብዙ ዓመት ሜቴክ ሳይሠራው ገንዘብ ሲዘርፍበት የቆየውን ሥራ ተረክቦ አሁን ሁለት ዓመት ባልሞላው ውስጥ የመጀመርያው ሁለተኛውና ሦስተኛ ውኃ በግድቡ ውስጥ በመሙላት ሥራውን ለመጨረስ አስተማማኝ ደረጃ ላይ አድርሶታል፡፡ የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታን ግን እኛ የለፋንበት ሳንጠየቅ ፖለቲከኞች ማዳበሪያን ከከሰል ድንጋይ ለማምረት የሚያነሳ እሱ ውሾ ነው በማለት ደምድመው የያዩ ማዳበሪያ ማምረቻ እንዲዘጋ አደረጉት፡፡
ይህ ውሳኔ ግን ነገሩን በደንብ ካለማወቅ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ መጠን ማዳበሪያ እንደሚያስፈልጋት ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ይህንን በከፊል ለሟሟላት ለማዳበሪያ ግዥ፣ በሌለን ዶላር ከፍተኛ ዋጋ እየተጠየቅን ነው፡፡ በ2012 ዓ.ም. ለማዳበሪያ ግዥ አገራችን 506 ሚሊዮን ዶላር ያወጣች ሲሆን፣ በ2014 ዓ.ም. በእጥፍ አድጎ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር በማውጣት ማዳበሪያ አስገብታለች፡፡ አገራችን ወደ ዘመናዊ እርሻ እያኮበኮበች ስላለች የማዳበሪያ ፍላጎታችን ስለሚመነደግ፣ የሌለንን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ሊጠይቀን ስለሚችል አንድ ሳይሆን በዛ ያሉ ፋብሪካዎች በፍጥነት መገንባት ያስፈልገናል፡፡ ታዲያ! ማዳበሪያ ፋብሪካ እንደዚህ ለአገራችን አስፈላጊ ከሆነ፣ ለምን የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ እንዲቆም ተደረገ የሚለው መልስ ማግኘት አለበት፡፡
እንደሰማነው ባለሥልጣኖቹ፣ ፋብሪካው አንዲቆም የወሰኑበት የተለያዩ ምክንያቶችን ጠቅሰዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ መንግሥት ለማዳበሪያ ፋብሪካ ከባንክ ተበድሮ ያወጣውን ሜቴክ ማጥፋቱና ከድንጋይ ከሰል ማዳበሪያ ማውጣት፣ ዋጋውን ውድ ከማድረጉ በላይ ከድንጋይ ከሰል ማዳበሪያ መውጣት ለአየር ብክለት ምንጭ በመሆኑ፣ እሱን በመተካት ከተፈጥሮ ጋዝ ማምረት ንፁህ በመሆኑ፣ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ለፋብሪካው ከባንክ ተወስዶ ሜቴክ ያጠፋው ሲጀመርም ምንም አቅም ለሌለው ለሜቴክ የተሰጠው የፖለቲካ ውሳኔ ስለሆነ፣ ዕዳውንም መሸፈን ያለበት ፖለቲካው (መንግሥት) ነው፡፡ ስለዚህ የባንኩን ዕዳም ሆነ ብድር፣ እንደማይመለስ ተቆጥሮ (Write off) መሰረዝ አለበት፡፡ የሚገኝ ከሆነ የአጠፉትን በሕግ ከሶ ለማስመለስ መጣር አለበት፡፡
ከድንጋይ ከሰል ማዳበሪያ መውጣት በማንኛውም መመዘኛ ከተፈጥሮ ጋዝ ማዳበሪያ ማምረት፣ ጋራ ሲወዳደር ከዋጋና ከቴክኖሎጂ አንፃር ውድ ነው፡፡ ይህም በቀላሉ ለማየት ድንጋይ ከሰል፣ ከከርሰ ምድር ማውጣትና ጋዝን በቱቦ ማውጣት፣ በዋጋ አይደራረሱም፡፡ ከዚህም በላይ ድንጋይ ከሰሉንም ፋብሪካ ወስዶ፣ ለፍብረካ ማዘጋጀት ከባድ መሣሪያዎችን ይጠይቃል፡፡ የተፈጥሮ ጋዝ ግን በቀላሉ በቱቦ ይመላለሳል፡፡ ቴክኖሎጂውም ከድንጋይ ከሰል ማዳበሪያ ማውጣት፣ ከፍ ይላል፡፡
ጥያቄው ግን የሚመጣው እኛ ከተፈጥሮ ጋዝ ማዳበሪያ ለማልማት ዕድል አለን ወይ ነው፡፡ በንጉሡ ጊዜ በአሜሪካኖች፣ በደርግ ጊዜ በሩሲያኖች፣ በኢሕአዴግ ጊዜ በማሌዢያ ከዚያም በቻይና ተሞክሮ አልተቻለም፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ እንኳ በቻይናዎቹ አስተማማኝ የመሰለው አሁን በዜሮ ነው የተባዛው፡፡ በተጨማሪም በአምስት ቢሊዮን ዶላር ድሬዳዋ ላይ የሞሮኮና የአሜሪካ ጥምር ኩባንያ ከፍተኛ የማዳበሪያ ኮምፕሌከስ እናቋቁማለን ብለው እኛን አማለሉን፡፡ እኔ ራሴ የዚህን ጥምር ኩባንያ ብቃት ለመዳሰስ ወደ ሞሮኮ ሄጄ አጥንቼ የተመለስኩት ኩባንያው ቆይቶ እንዳቋረጠ ሰማሁ፡፡ ስለዚህ ማዳበሪያን ከተፈጥሮ ጋዝ ለማምረት ላለፉት 40/50 ዓመታት የተበተበን ድግምት ስላልተፈታልን ማንም በእርግጠኝነት መቼ ማዳበሪያን ከተፈጥሮ ጋስ ማምረት እንደሚቻል ሊናገር የሚችል ሰው በአገሪቱ የለም፡፡ መንግሥት ከያዩ ማዳበሪያ ማምረት ኪሳራ ነው፣ በእጃችን ያለውን ከተፈጥሮ ጋዝ ማዳበሪያ እናመርታለን ብሎ አስቦ ከሆነ፣ ይህም በዜሮ ማብዛት ነው፡፡ ስለዚህ በእጃችን ያለው አስተማማኝ የሆነውን ማዳበሪያ ከድንጋይ ከሰል ማምረት አማራጭ የሌለው ነው፡፡ ከተፈጥሮ ጋዝ ማዳበሪያ በተዓምር ማምረት ብንችል እንኳ፣ ከድንጋይ ከሰል ማዳበሪያ ያመረትነው ይጠቅማል እንጂ ጉዳት የለውም፡፡ እንደ ምክንያትም የድንጋይ ከሰሉ በምዕራብ የአገሪቱ ግዛት ውስጥ በመገኘቱና አካባቢው የግብርና ቦታ መሆኑ፣ ማዳበሪያን ምሥራቅ አምርቶ ምዕራብ ማጓጓዝ የሚወጣውን የትራንሰፖርት ዋጋ በእጅጉ የሚያንረው መሆኑ፣ ለገበሬው በቀላሉ ተደራሽ መሆኑ፣ ለአካባቢው የልማት በር ከፋች መሆኑ ወዘተ. የሚሉት ሚዛን ደፍተው ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ደጋግመን ማስታወስ ያለብን በአሁን ጊዜ ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት ከድንጋይ ከሰል ማዳበሪያ ለማምረት ሙሉ የጥናት ሰነድ ስላለና ሜቴክ በሚሊዮኖች ብር የገዛው ዕቃዎችና መሣሪያዎች ስላሉ እነዚህን ለመጠቀም በመቻሉ ያዩ ላይ ማዳበሪያን ከድንጋይ ከሰል ማምረት ከተፈጥሮ ጋዝ ከሚመረተው የበለጠ የማዳበሪያ ግኝታችንን በአዋጭነት ያጠናክረዋል እንጂ የሚጎዳው የለም፡፡
ብዙ ምሁራን የአካባቢ ደኅንነት ጥበቃ የሚያወጣውን በመመልከት ከድንጋይ ከሰል ማዳበሪያ ሲመረት የአየር ንብረት ለውጥን የሚያስከትሉ የጋዝ ልቀቶች ከተፈጥሮ ጋዝ ማዳበሪያ ሲመረት ከሚያወጡት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ስለሆነ (Natural Gas Emits Almost 50% less CO2 Than Coal)፣ ከተፈጥሮ ጋዝ ብቻ ነው ማዳበሪያ ማምረት ያለብን የሚሉ አሉ፡፡ እኔ የአየር ንብረት ለውጡ፣ ማለትም የአካባቢ ሙቀት መጨመር እንደሚያሳስበኝ ልክድ አልፈልግም፡፡ ካልተቆጣጠርነው ዓለም ወደ ከፋ ሁኔታ እንደ ሚሄድ ያሳስበኛል፡፡ የአካባቢ ሙቀት መጨመር የመጣውም በአብዛኛው ነዳጅ ለማግኘት ከምናቃጥላቸው ቁሶች (Fossil Fuel) እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ከነዚህም አንዱ የድንጋይ ከሰል እንደሆነ እቀበላለሁ፡፡ ግን አገራችን ለዓለም የአካባቢ ሙቀት መጨመር ተፅዕኖ ፈጥራለች የሚለው ላይ ነው ችግር ያለኝ፡፡ የጋዝ ልቀቶች ማዳበሪያ ከተፈጥሮ ጋዝ ሲመረት በአናሳ ደረጃ መውጣታቸው አይቀርም፡፡ በአጠቃላይ እኛ አፍሪካውያን፣ ለዓለም የአካባቢ ሙቀት መጨመር፣ የምናበረክተው የለም፡፡ ምክንያቱም ቢባል ያሉን ኢንዱስትሪዎች በጣም አናሳ በመሆናቸው ወደ ከባቢ አየር የሚለቁት ጋዞች ለአካባቢ ሙቀት መጨመር የሚያበረክቱት ኢምንት ናቸው፡፡
በተፃራሪው የሠለጠኑት አገሮች ናቸው ለአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትሉ የጋዝ ልቀቶች በከፍተኛ ደረጃ የሚለቁት፡፡ ለምሳሌ ምዕራባውያን አገሮች ጀርመን፣ እንግሊዝ፣ ጃፓን፣ ወዘተ. 40 በመቶውን ኤነርጂ የሚያገኙት የድንጋይ ከሰልን በማቃጠል ነው፡፡ ይህንን ቀንሱ ብሎ ዓለም እየወተወተ ባለበት ሰዓት ይባስ ብለው በሩሲያና በዩክሬን ጦርነት ሳቢያ (ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ የኢኮኖሚ ዕገዳ ሲያደርጉ፣ ሩሲያ በአፀፋው የነዳጅ ዕገዳ ስላደረገች) ጀርመን ያጋጠማትን የነዳጅ እጥረት ለማካካስ ኢንዱስትሪዎቿ ከከሰል ነዳጅ እንዲያመርቱ እየፈቀደች ነው፡፡ አሜሪካ ከ50 ዓመት በፊት ከፍተኛ የድንጋይ ከሰል ተጠቃሚ ነበረች፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅና በሌሎች ቦታዎች ድፍድፍ ዘይትና የተፈጥሮ ጋዝ ሲገኝ፣ በአሜሪካ ግዛት ለሁለት መቶ ዓመት ሊበቃት የሚችለውን የድንጋይ ከሰል ከማውጣት ዘግታ በማስቀመጥ ሊያልቅ የሚችለውን ድፍድፍ ዘይትና የተፈጥሮ ጋዝ እየገዛች ከየአገሮቹ ትሻማለች፡፡ በአጠቃላይ ምዕራባውያን አሁንም ቢሆን በከፍተኛ ደረጃ ለኢንዱስትሪያቸው የድንጋይ ከሰል ይጠቀማሉ፡፡ ስለዚህ ደግ ደጉንና ዕውቀቱን ከምዕራብያውያን በመውሰድ ሌላውን እናንተ አትደጉ፣ የእኛን ምርት እየገዛችሁ ኑሩ፣ ጥሬ ዕቃዎቻችሁን አትጠቀሙ፣ ለአካባቢ ሙቀት መጨመር መንስዔ ነው፣ ወዘተ. የሚሉትን ሞኛችሁን ፈልጉ ማለት አለብን፡፡
ለማጠቃለል አገራችን ማዳበሪያ ካላመረተች ከረሃብ አትወጣም፡፡ ማዳበሪያ ለእኛ የመኖር ያለመኖር ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ማዳበሪያን ለማምረት በቂ የሆነ የድንጋይ ከሰል ስላለን እስካሁን ተብትቦ የያዘንን ድግምት ፈትተን ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በመክፈል ለጥናት ያወጣነውን የጥናት ሰነድ እንደገና ከልስን (Review)፣ ሜቴክ በየቦታው የጣለውን ተረፈ ንብረት አሰባስበን ማዳበሪያ ማምረት አለብን፡፡ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ከተፈጥሮ ጋዝ ማዳበሪያ ማምረት ተብትቦ የያዘንን ድግምት በጣጥሰን ብንጥልና ብናመርት፣ የተመረተው ማዳበሪያው ዕገዛ ይሆናል እንጂ አይትረፈረፍም፡፡ ፋብሪካዎቹንም በአንድ ተቋም በማደራጀት የሰው ኃይል፣ የቴክኖሎጂ፣ የቤተ ሙከራ፣ የማዳበሪያ ዋጋ ወዘተ. ተወራራሽ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል፡፡ አንድ የምንስማማው እንደነዚህ ዓይነቶቹ ፕሮጀክቶች በግል ባለሀብቶች ስለማይሠሩ የግድ ለጊዜው መንግሥት ወስዶ ከተለያዩ ፋብሪካዎች የበለጠ፣ ማዳበሪያ ለኢትዮጵያ ቁጥር አንድ ተቀዳሚ መሆኑን አውቆ በስህተት እኛን ሳያማክር ከተፈጥሮ ጋዝ ማዳበሪያ አመርታለሁ ብሎ ከድንጋይ ከሰል ማዳበሪያ አላመርትም ብሎ የወሰደውን ዕርምጃ ወደ ጎን ትቶ፣ ማዳበሪያ ከዚህ ጥሬ ዕቃ አምርቶ ያለውን ድግምት እንዲፈታ፣ ማዳበሪያ ለማግኘት በሚባዝነው ደሃ ገበሬ ስም እጠይቃለሁ፡፡
ኢትዮጵያ በሁሉም ሕዝቦቿ ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በላይ ወልደየስ (ዶ/ር-ኢንጂነር) የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ስፔሻላይዝድ ያደረጉት ደግሞ በፔትሮኬሚካል ኢንጂነሪንግ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2015/16 የአስተማሪነት ልዕልና ሽልማትን (Distinguished Teaching Award) ተቀብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ መሥራች አባልም ናቸው፡፡ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡