Friday, September 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የፓርላማ ያለህ አንልም ወይ!

ሰላም! ሰላም! ከምሥጋናና ከምሬት፣ ከፀፀትና ከተስፋ፣ ከአገሩና ከከተማው የጦፈ ወሬ ጋር እንዴት ከርማችኋል? ሰበር ዜና አስመሰልኩት እንዴ? ዩቲዩብ በየት በኩል መጣ እንዳትሉኝ አደራ። እንግዲህ ፓርላማው ሥራ ሊጀምር ስለሆነ አንዳንድ ጉዳዮቹን እኛው እናስታውሰው እንጂ፡፡ እኛ ካላስታወስን እኮ ማን ይሰማል ብላችሁ ነው? በአፈጻጸም ጉድለት ከሚንገዳገድ ፖሊሲ፣ በሙስና ከተተበተበ ባለሥልጣን፣ መልካም አስተዳደርን ሕልም ካደረጉ እኩዮች፣ ብራችንን መቀመቅ እየከተቱ ዶላርን ከመቶ ብር በላይ ካስወነጨፉ ወንበዴዎች ጉዳይ ጀምረን አቤት ማለት ካልጀመርን ሰሚ የለም፡፡ ፓርላማው ሥራውን ሲጀምር ለሕዝብ፣ ለሕግና ለህሊናቸው የሚገዙ የፓርላማ አባላት ቢሰሙን ብዬ እኮ ነው። ለምሳሌ ከጨዋታ ሳንወጣ ስለኑሮ መክበድ ማውራት እንዴት ለቀባሪው ማርዳት እንደሆነ ላስረዳ። ዶላር በአየር ላይ እየተቀባበሉ ገበያውን የሚያጦዙብን ወንበዴዎች፣ ከመንግሥት ሹማምንት ጋር አብረው ይሠራሉ የሚለው ጉዳይም ይጣራልን፡፡ ምክንያቱም በየዕለቱ ገበያ ሄደን ምግባችንን ስንሸምት ግብይቱ በዶላር የሆነ ይመስል፣ ወሬው ሁሉ ዶላር እንደ ሮኬት ተተኮሰ የሚል ማጣቀሻ አለው፡፡ ይኼ ሁሉ ማሳሰቢያ የሚተላለፈው መንግሥት በከፈልነው ግብር የሚተዳደር በመሆኑ ነው፡፡ አሊያማ ምን አገባን!

ከዚህ እያበደ ካለ የኑሮ ሩጫ ጋር ሁሉን እየሰማንና እየተሰማን እነሆ እዚህ ደረስን። በመኖር ሐዲድ ላይ የጉዟችን ፍጥነት ሲጨምር የአገረ መንግሥት ግንባታችን የዘገየ መስሎ ይታየኝ ጀመር። መዘየድ አልችል እያልን መዘግየት ተግባራችን ሆነ እኮ፡፡ ‹‹ምንድነው የምትለው? ገና አሁን አይደል እንዴ ሁሉም ነገር የተጀመረው?›› አለኝ ከታዳጊነት ዘመኑ ጀምሮ በድለላ ሙያ ላይ የተሰማራ ጓዴ። ‹‹ሁሉም ነገር አሁን አይደል እንዴ የተጀመረው?›› የሚለውን ሊሰመርበት የሚገባ ዓረፍተ ነገር እንበለው። ‹‹ደግሞ ከዚህ ብሶ አሿፊ ዘመኔ ያስቀኛል ደርሶ›› ብለው ባሻዬ የነገሩኝ ግጥም ትዝ አለኝ። ምሥጋናና ምሬቱ፣ ፀፀትና ተስፋው ከዚህ ከዚህ ነው የሚወለደው ለማለት ፈልጌ ነው። እንዲህ ዙሪያ ጥምጥም እየሄድኩ ነገር የምጠመጥመው ቀጥተኛው መንገድ ስለተረሳ አይመስላችሁም? እውነቴን እኮ ነው። አቋራጭና አማራጭ መንገድ ነው ወሬው ሁሉ። ‹‹አቋራጭና አማራጭ ስንፈልግ ደግሞ ከብዙ ነገሮች ጋር እንላተማለን፡፡ ለምሳሌ ዕድገትን በአቋራጭ ለማምጣት የሚረዱ መላዎችን ለመንግሥት ስንጠቁመውና ምክር ቢጤ ስናቀርብለት፣ “ከእኛ በላይ ለአሳር” ብሎ ቆሌያችንን ይገፈናል…›› አለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፡፡ በአባባሉ እየተገረምኩ የአማራጩ ደግሞ ምን ይሆን ስለው፣ ‹‹እነ አይኤምኤፍን አምናችሁ ብራችንን እያረከሳችሁና ዶላርን እያናራችሁ ኑሮአችንን ከምትገድሉን፣ አንቱ የተባሉ ኢኮኖሚስቶቻችንን ምክረ ሐሳብ ስሙ ስንል አይሰሙም፡፡ በተሠራ ወይም በታቀደ ላይ ስትዘፍኑ ከምትከርሙ እስቲ የእናንተን አማራጭ አቅርቡልን ብለን ምክር ቢጤ ጣል ስናደርግ “አጉል አዋቂ” ብለው ያስደነብሩናል…›› አለኝ፡፡ ‹‹መደማመጥ በሌለበት አገር ውስጥ መካሪ ከመሆን ሱባዔ መግባት ይሻላል…›› ሲለኝ ተስፋ መቁረጡ ታወቀኝ፡፡ በስንቱ ተስፋ ቆርጠን እንዘልቀው ይሆን!

የሚገርመው ይኼን አሁን የማጫውታችሁን ጉዳይ እያወጣሁ አልጋዬ ውስጥ እንዳለሁ እንቅልፍ ይዞኝ ጭልጥ አለ፡፡ በዚህ መሀል ነበር በፓርላማ አዳራሽ ብቻውን የሚያስተጋባው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ድምፅ ጆሮዬ ጥልቅ ያለው። እንቅልፍ ውስጥ ሆኜ ፓርላማው ሥራ ሳይጀምር ለካ እኔ አስጀምሬዋለሁ። እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙዎቻችን የጨነቀ ነገር የገጠመን መሰለኝ፡፡ አይደለም እንዴ? አገር ወዳድነት በሌላ በምን ይገለጻል ታዲያ? “በላ ልበልሃ” አትሉት ወይ ጠበል ፀዲቅ ተሰብስበው ሲበተኑ ችግራችን በወሬ ይፈታ ይመስል በተስፋ ቴሌቪዥን ላይ የምናፈጠውን ቤት ይቁጠረን። ‹‹አንበርብር ለአንድ አገር የፖለቲካ ሥርዓት መጎልበትም ሆነ፣ ለሕዝቦቿ ኑሮ መሻሻል አንድ ጭንቅላት ብቻ አይደለም የሚያስፈልገው። የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት መጥፋት እኮ ለሁሉም ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም…›› ካለኝ በኋላ፣ ‹‹አንዳንዴ የዘመኑን የምክር ቤት ተወካዮች ስመለከት በአንድ ትልቅ የሃይማኖት አባት ምርቃት ተርከፍክፎላቸው፣ የአሜን ድምፃቸውን አሰምተው እንደሚወጡ ምዕመናን እቆጥራቸዋለሁ…›› ያለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው። አያመጣው የለ አትሉም? ‹‹አውራ ዶሮና አውራ ፓርቲ ይመሳሰላሉ፣ ብቻቸውን ጮኸው ያጨበጭባሉ…›› ብሎ ገጠመ አሉ አንድ አዝማሪ። ዝም የማለትን ጭንቅ ከአዝማሪ በላይ ማን የሚያስተጋባ ይመስላችኋል? ማንም!

ከዓመታት በፊት ይመስለኛል እግረ መንገዳቸውን ስለአኗኗራችን የሚናገሩት አዲስ ነገር ካለ ልሰማ፣ በደህና ቀን የገዛኋት የድሮ 21 ኢንች ቴሌቪዥን ላይ ማፍጠጥ ጀመርኩላችሁ። ሰው ሌላ ዓለም ላይ ደርሷል። ሰውማ ያልደረሰበት ምን አለ? እኔም ሳፈጥ የፓርላማ አባላቱ እየፈዘዙ እኔም እንደ እነሱ እያንጎላጀሁ የሚሉትን ሳልሰማ ሰዓቱ ነጎደ። በኋላ ግን ምሁሩ የባሻዬ ልጅ እንዳስረዳኝ የያኔው ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ስለሁኔታዎች መክበድ ትልቁን ንግግር ተናግረው ነበር። ‹‹መቼ?›› ስለው፣ ‹‹አልሰማህም እንዴ ሕዝቡ በማስረጃ የሚከሰውን የመንግሥት ሌባ እኔ በግሌ እስከ ፍርድ ቤት ድረስ እከታተለዋለሁ ማለታቸውን?›› አለኝ እንዴት እንዳልሰማሁ ተገርሞ። ‹‹ታዲያ ይኼ የወንጀል እንጂ የኑሮ ጉዳይ ነው?›› ስለው፣ ‹‹በየሄድንበት የሚያስበረግገን የሕዝብ ቀበኛ በዝቶ እያየህ እንዴት እንዲህ ትላለህ? ኑሯችን ራሱ ሙስና ሆኖ መስሎኝ በየቀኑ ወደኋላ የምንሮጠው?›› ሲለኝ ነገሩን የተመለከተበት አቅጣጫ ገባኝ። ለካስ ቀንደኛው የኑሮ አገሻቢ መንግሥት ጉያ ውስጥ የመሸገው ከሆነ ውሎ አድሯል። ምን ታደርጉታላችሁ? ነገር ሲደጋገም እኮ ይረሳል። ዕርምጃ የማናይበት ችግርና ቅሬታ ስለበዛ “ዴሊት” የምናደርገውም በዝቷል። የሆነው ሆኖ በዚያን ጊዜ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደዚያ ብለው ቃል መግባታቸው ትዝ ሲለኝ አንዳች ተስፋ በውስጤ አጭሮ ነበረ። ግና ምን ያደርጋል ችግሩ አሁንም ድረስ እያሳደደን ያሳብደናል፡፡ ትናንት የተፎከረበት ሌብነት ዛሬ እንደ ታርዛን ሆኖ ያስደነብረናል፡፡ ድንቅ ነው!

በሥራ ዘመኔ እንደዚህ “ቢዚ” ያደረገኝ ሳምንት ነበረ አልላችሁም። “ቢዚ” የምትለዋ ቃል ብቻ “ቢዚ” አታደርግም። አታስተውሉ ይሆናል እንጂ እኮ ሠርቶ “ቢዚ” ከሚሆነው “ቢዚ”ን በመጥራት “ቢዚ” የሆነው ከሕዝባችን ቁጥር በልጧል። በሌላ አባባል ራሱን ደርቦ የሚሮጠው ልቋል ለማለት ነው። ገባችሁ? ኋላ ላይ ከቤቴ ወጥቼ እንደሄድኩ ከጀርመን የመጣ የማተሚያ ማሽን እንዳሻሽጥ ተነገረኝ። የዕለቱ ዕለት ምን ስባዝን ብውልም አልሆን ብሎ በነገታው ማልጄ ተነሳሁ። ገዥ ፍለጋ ልማስን ተጣድፌ ስነሳ ውዴ ማንጠግቦሽ፣ ‹‹ፊትህን እንኳ ሳትታጠብ ነው የምትወጣው?›› አለችኝ ታዝባኝ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሥራዬ ባህሪ የሚያደርገኝን እያየች ጥርስ የነቀልኩበትን ሙያ መጥላት ጀምራለች። ፍቅር ነው ብላችሁ ታልፉታላችሁ እንጂ ምን ልትሉት ኖሯል? የማሻሽጠውን የማተሚያ ማሽን ዓይነት ገባትም አልገባትም ከእነ ሞዴሉ ገለጻ አደረግኩላት። ማንጠግቦሽ አቋርጣኝ፣ ‹‹በል ፈጠን በል የእኔ ጀግና። እኔም በለስ ቀንቶህ ከመጣህ ለአስቤዛ የሚገዛዛውን አስቤ እጠብቅሃለሁ…›› ስትል ከአልጋዋ ሳትወርድ ስቃ ሸኘችኝ። በር ከፍቼ ልወጣ ስል፣ ‹‹ውዴ ሰርቆ ከመብላት ሠርቶ መብላት ነው የሚያምርብን…›› አለችኝ። ገንዘቡ ከመግባቱ መውጣቱ እንደማይቀር ተነግሮኝ አስቤ ሳልጨርስ፣ ደግሞ ሌላ ፖለቲካዊ አሽሙር ስትጨምርልኝ በህልሟ ምን ስታይ አድራ ነው እያልኩ መንገዴን ቀጠልኩ። ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ሁሉም ቦታ ቢከበር እኮ፣ የአንዳችን አስተያየት ለሌላችን መስተዋት ይሆን ነበር ብዬ አሰብኩ። “ስንቱን አስታወስኩት…” እንዳለው አንጋፋው ዘፋኝ እኔ ደግሞ “ስንቱን አሰብኩት” ልበል ይሆን? ለማንኛውም ግራና ቀኝ እያዩ መራመድ ሳያዋጣ አይቀርም፡፡ ሊሆን ይችላል!

በስንት መከራ በጥበቃ ያገኘኋቸው ገዥ በመኪናቸው ይዘውኝ ማሽኑን ልናይ መሄድ ጀመርን። በነገራችን ላይ እነዚህ ሰዎች ቢሮ እገባለሁ አትገባም ከጥበቃው ጋር የነበረው ንትርክ እንዲህ ቀላል አይምሰላችሁ። የአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ዋና ሥራ አስኪያጆች ጥበቃዎቻቸውን ነው የሚመስሉት። ለነገሩ አትፈርዱባቸውም በሽብር ወንጀል ከተሰማራው የሚፈረጀው ስለበዛ ምን ያድርጉ? አንዳንዱ ደግሞ በቅጡ ሳይፈትሽ ወይም መታወቂያ ሳይጠይቅ ‹‹ምን ፈልገህ ነው?›› ይላችኋል ናቅ አድርጎ። ‹‹ጉዳይ ነበረኝ…›› ካላችሁት ተለሳልሳችሁ፣ ‹‹የምን ጉዳይ?›› ተረኛው ጥያቄ ነው። ‹‹ምን አገባህ?›› ማለት ወደ መጡበት መመለስን ሊያስከትል ስለሚችል ቅቤ እንደናፈቃት የዘንድሮ ሽሮ በነገር ድርቀት ተመታችሁ በልምምጥ ወደ መሥሪያ ቤቱ ትዘልቃላችሁ። በነገር መንተክተካችሁ ‹‹ድሮስ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር›› በማለት ማብረድ መብታችሁም ብቸኛ አማራጫችሁም ነው። አንዳንዱ መሥሪያ ቤትማ ‹‹ደንበኛ ንጉሥ ነው›› ከማለት ‹‹ጥበቃው ንጉሥ ነው›› ቢሉ ይቀላቸዋል። በብስጭት የጨጓራ አልሠራችንን ያባባሰው የመልካም መስተንግዶ ዕጦት አሁንም የሚያስታግስላችሁ ‹‹ድሮስ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር?›› የሚለው ዓረፍተ ነገር ነው። መድኃኒቱንማ ከውጭ እየገለበጡ ማስመጣት እንጂ መቼ ማምረት ጀመርን? ስንቱን ገልብጠን እንዘልቀው ይሆን? እንጃ!

ቀጠን አጠር የሚሉት ሽማግሌው ገዥ፣ ‹‹ለመሆኑ በዶላር ገዝቶ በብር የሚሸጠው እንዴት ያለ ዕቃ ቢሆን ነው?›› ብለው ያላሰብኩትን ጥያቄ ጠየቁኝ። ‹‹ዕቃውን እንኳ ማየትዎ አይቀርም። በዶላር ገዝቶ በብር የመሸጡ ምክንያት የአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ ብር ስለሆነ አይመስልዎትም?›› ስላቸው ፈገግ ብለው አዩኝ። ‹‹ቅኔ ተምረሃል ልበል? ብር ሆነ ዶላር ያወጣውን አውጥተህ መግዛትህ አይቀርም የምትል ይመስላል…›› ብለው በአጠቃላይ ስለሥራቸው ያጫውቱኝ ጀመር። ‹‹እዚህ አገር እጅግ ከባድ ሥራ ቢኖር ይኼው የኅትመት ሥራ ነው። ዘመኑ የ“ዲጂታል” ቢሆንም ማሽኑም ተሻሽሎ እጅህ ቢገባ ምንም ዋጋ የለውም። በኅትመት ዙሪያ የመንግሥትም ሆነ የአብዛኛው ሕዝብ አስተሳሰብ “አናሎግ” ነው። ያውም እንዲህ የልማትን አቅጣጫ ከልቧ በሚመስል ሁኔታ የተያያዘች አገር ሕዝቧ ከኅትመት ውጤት በብዙ ሊጠቀምና ሊያተርፍ ሲገባ ተቃራኒውን ማየት ያሳዝናል። የሆነው ሆኖ የቻልነውን መሮጥ አለብን…›› ብለው እንዳበቁ ከሥፍራው ደረስን። ዕቃውን ዓይተው እንደወደዱትና እንደፈለጉት ነገሩኝ። ቀሪው ሒደት በፍጥነት ተጠናቀቀ። ባልተጠናቀቁ ውጥኖች መከፋት ብቻ ለምን? ያሰኛል!

ኮሚሽኔን ተቀብዬ በድካምና በደስታ ስሜት ወደ ሠፈሬ ገሰገስኩ። እኔና የባሻዬ ልጅ በምናዘወትራት ግሮሰሪያችን ደጃፍ በኩል ሳልፍ ድንገት ካለ አልኩና ገባሁ። እሱ ግን ከኋላዬ ሳላስበው መጥቶ፣ ‹‹ብቻ ለብቻ ተጀመረ እንዴ?›› ሲል ብሰማው አስደነገጠኝ። ‹‹እኔማ ካለህ አንተኑ ፍለጋ ነበር መግባቴ…›› ስለው እሱም ከሩቅ ዓይቶኝ እንደመጣ ነገረኝ። ብዙ መቆየት እንደማልችል፣ ማንጠግቦሽ እንደምትጠብቀኝ ነገሬው ያላበው ሁለት ቢራ አዝዘን ተቀመጥን። ‹‹ማንጠግቦሽ ደግሞ ዛሬ ምን ብላ አስቸኮለችህ?›› ብሎ ቢጠይቀኝ ያለችኝን እነግረው ጀመር። ‹‹መከራ እኮ ነው አገኘሁ ስትል ወጪው በዚያው ልክ ነው። ብሩ ሥራው መብረር ነው። እኔስ አዕዋፋትን ዓይተው አውሮፕላን እንደፈጠሩት የብርን አበራረር ቢያጠኑ ደግሞ ሌላ ድንቅ ፈጠራ ዓናይም ብለህ ነው?›› ስለው እየሳቀ፣ ‹‹አይዞህ ለነጣቂና ለሌባ አይዳርግህ እንጂ ሌላው ዕዳው ገብስ ነው…›› አለኝና ብርጭቆአችንን አጋጨን። ስንጨርስ ሒሳብ ከፍዬ ወደ ማንጠግቦሽ ልሮጥ ተነሳሁ። ትዳር ክቡር ነዋ!

ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ቆይ አንዳንድ ደግመን እንሂድ ብሎኝ የሚመጣልንን ቢራ ስንጠባበቅ አንዱ ውኃ ወሰድ ያደረገው፣ ‹‹ሰማችሁ ወገኖቼ?›› ሲለን ቀና ብለን አየነው፡፡ ‹‹…የሰማ ላልሰማ መንገር ስላለበት ነው የምነግራችሁ…›› ሲል ሁላችንም ማለት ይቻላል አንገታችንን ወደ እሱ አሰገግን፡፡ አዲስ ነገር ምን ያሰማን ይሆን እያልን፡፡ ሰውየው ትኩረት ማግኘቱ ደመ ነፍሱ ሲነግረው፣ ‹‹ፓርላማው የአዲሱን ዓመት ሥራ ሲጀምር የመጀመሪያው ጥያቄ መሆን ያለበት ዶላር ለምን በብራችን ላይ እንዲህ ተረማመደ ነው፡፡ እውነቴን ነው የምነግራችሁ መንግሥት ባለበት አገር ውስጥ አልጠግብ ባይ ነጋዴዎች መሸጫ ውስጥ የቆመ መኪና ምንም እሴት ሳይጨመርበት፣ አንድ ሚሊዮን ብር ጭማሪ ሲያሳይ መንግሥት የት ነው ያለው መባል አለበት፡፡ ነገ የምንበላው አጥተን እርስ በርስ ከመበላታችን በፊት መንግሥት ይህንን መረን የለቀቀ ነገር እንዴት እንደሚያስተካክል ፍኖተ ካርታውን ያሳየን፡፡ የምታውቁት የፓርላማ አባል ካለ ይህንን ሐሳቤን ሼር አድርጉልኝ፡፡ ዘንድሮ በእነዚህ ወንበዴዎች ምክንያት መራባችን አይቀርም…›› ሲለን በመገረም እርስ በርስ ተያየን፡፡ እውነት ነው ያስተያያል!

እኔና ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ወደኋላ ሄደን ድሮ የተባለ ነገር ማጠንጠን ጀመርን፡፡ ‹‹ትዝ ይለኛል በ1977 ዓ.ም. አገራችን በድርቅ ተመታ ያ ሁሉ ሕዝብ በረሃብ ሲያልቅ፣ በዕርዳታ የመጣ ስንዴና ሩዝ ነበር ቀድሞ የደረሰው፡፡ በጊዜው ስንዴው ለረሃብተኞች ታድሎ ሩዙን ፈላጊ በመጥፋቱ ለከተማ ነዋሪዎች በዝቅተኛ ዋጋ በቀበሌ ሱቆች አማካይነት በግዳጅ ለሽያጭ ቀረበ…›› አለኝ የባሻዬ ልጅ፡፡ ‹‹ከዚያስ?›› አልኩት፡፡ ‹‹ከዚያማ ሩዝ እንግዳ የሆነበት የአገራችን ሰው ሲተናነቀው ‘ልመደው ልመደው ሆዴ…’ የሚለው የኤፍሬም ታምሩ ዘፈን ስንኙ ተቀይሮ ‘ልመደው ልመደው ሆዴ ሩዙን ብላው በዘዴ’ ተባለ ሲለኝ የነገር ዳር ዳርታው ገባኝ፡፡ ‹‹አሁንስ›› ስለው፣ ‹‹ታሪክ ራሱን ደግሞ ቢርበን እንደ በፊቱ የዋሆች ዞር ብሎ የሚያየን የለም፡፡ በዕርዳታ የመጣው በዚህ ዘመን ጨካኞች ይዘረፋል፡፡ ከታሪክ የማይማር ታሪክን ሊደግመው ይገደዳል እንደሚባለው እኛ በስንፍናችን ምክንያት ከረሃብ ጋር ስንፋጠጥ፣ ሌሎች ደግሞ በላያችን ላይ እያጋበሱ ሕይወታችንን ሲኦል ያደርጉብናል፡፡ አሁንም ሰውዬው እንዳለው ፓርላማው ሃይ ይበለን፡፡ አለበለዚያ ያለንበት ሁኔታ አስፈሪ ነው፡፡ አሁንም የፓርላማ ያለህ እንበል…›› ሲለኝ ነገሩ ከንክኖኝ ወደ ማንጠግቦሽ በረርኩ፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት