Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልክብረ መውሊድ

ክብረ መውሊድ

ቀን:

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችና በመላው ዓለም የሚገኙ ጭምር  ነቢዩ መሐመድ የተወለዱበትን ዕለተ መውሊድን በማክበር ላይ ናቸው። ከሐምሌ 23 ቀን 2014 ጀምሮ የእስልምና አዲስ ዓመት ሙሃረም 1 ቀን 1444 ዓመተ ሒጅራ የገባ ሲሆን፣ አሁን ሦስተኛው ወር ረቢ ዑል-አወል ላይ ይገኛል፡፡

ይህ ወር በስድስተኛው መቶ ዘመን በ571 ዓመት ነቢዩ የተወለዱበት ስለሆነ መውሊድ በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ አንዳንዴም መውሊድ አል ነቢ፣ ሚላድ፣ ኢድ ሚላድ ኡን ነቢ፣ ኢድ አል-መውሊድ በመባል በተለያዩ አካባቢዎች ይታወቃል።

ሚላድ በሦስተኛው የእስልምና ወር ረቢዑል አወል 12 ቀን ላይ የሚውል ሲሆን፣ ምንም እንኳን በትክክለኛ ቀኑ ላይ ልዩነት ቢኖርም (የሺዓ ሙስሊሞች የነቢዩ ልደት በ17ኛው ቀን እንደሆነ ያምናሉ) ነቢዩ መሐመድ በአንድ ወቅት ሰኞን ለምን እንደጾሙ ተጠይቀው፡- ‹‹የተወለድኩበት ቀን እና መገለጡ የተጀመረበት ቀን ነው›› ሲሉ መመለሳቸውን ሊቃውንቱን ጠቅሶ ብሪንግሃምሜይል ዘግቧል፡፡

- Advertisement -

በኢትዮጵያ ዕለተ በዓሉ በፀሐይ መስከረም 28 ቀን 2015፣ በጨረቃ ‹‹ጥቅምት 12›› መዋሉ ባሕረ ሐሳቡ ያሳያል፡፡

ክብረ በዓሉ በትውፊቱ መሠረት በተለያዩ መንፈሳዊ ዝግጅቶች በተለያዩ መድረኮች በጸሎት፣ የነቢዩን ሕይወት በመተረክ፣ የነቢዩ መሐመድ ማወደሻ፣ ማስታወሻ አድርገው በመንዙማ፣ በግጥም፣ በቤተሰብ ስብሰባ በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ በመሳተፍና ልዩ ልመናዎችን በማቅረብ ተከብሮበታል፡፡  

መውሊድ ዓምና ከነበረው በ10 ወይም 11 ቀናት ቀደም ብሎ ይውላል፡፡  ምክንያቱም እስላማዊው ካላንደር ጨረቃን የሚከተል በመሆኑ ለ12 የጨረቃ ዑደቶች የሚቆዩት ለ354 ቀናት ነው፡፡ ስለዚህ በአብዛኛው ዓለም ጥቅም ላይ ከሚውለው የ365 ቀናት በፀሐይ ላይ ከተመሠረተው አቆጣጠር ጋር ልዩነት አለው፡፡

መውሊድ በኢትዮጵያ

የፎክሎር ባለሙያው መሐመድ ዓሊ (ዶ/ር) እንደጻፉት፣ በኢትዮጵያ የመውሊድ ከበራ በአሥራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ እንደተጀመረ ይታመናል። የዚህ መውሊድ መሥራቹም ከ1734 እስከ 1799 እንደኖሩ የሚነገርላቸው የወሎው ሸኽ ሙሐመድ ሻፊ መሆናቸው ይወሳል። ኦፊሴላዊ ክብረ በዓል የሆነውም በደርግ ዘመን ከ1967 ወዲህ ነው፡፡ ከበራውን በተመለከተም ባለሙያው እንደሚከተለው ገልጸውታል፡፡

‹‹በአገራችን የመውሊድ ከበራን በሦስት ቦታዎችና ጊዜዎች የማክበር ልማድ አለ። ቦታን በሚመለከት መውሊድ በመኖሪያ ቤት፣ በመስጊድና በሱፊ ማዕከሎች ይከበራል። የመውሊዱ ጊዜ ደግሞ ባብዛኛው ነቢዩ በተወለዱበት በረቢየል አወል ወር አሥራ ሁለተኛው ቀን፣ ወይም በተወለዱበት ወር ውስጥ በሚገኝ ሰኞ፣ ወይም በማንኛውም ወር በሚገኝ ሰኞ ቀን፣ ወይም በማንኛውም ወርና ቀን ይከበራል።››

ከማኅበራዊ ግንኙነት አንፃር የመውሊድን ፋይዳ የፎክሎር ባለሙያው መሐመድ አሊ (ዶ/ር) በጥናታዊ መጣጥፋቸው ላይ እንደገለጹት፣ በመውሊድ ከበራ ሰደቃ ይካሄድበታል፤ በዚህም ሀብታምና ድሃ ይገናኙበታል፣ ያለው ለሌለው የፈጣሪውን ውደታ ፍለጋ ምጽዋዕት ይሰጥበታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የማኅበራዊ ግንኙነትና ትስስር ይጠናከርበታል የሚሉ ወገኖችም አሉ ይላሉ።

የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪና ደራሲው አቶ ተሾመ ብርሃኑ ከማል እንደሚገልጹት፣ መውሊድ እንደ አንድ ኢስላማዊ እሴት የኅብረተሰቡን ማኅበራዊ ማንነት ማረጋገጫ፣ አንዱ ሙስሊም ከሌላው ሙስሊም ጋር ያለውን ወንድማማችነት፣ የአመለካከት አንድነት የሚያንፀባርቅበትም ነው፡፡

‹‹ወደ መውሊዱ ሥፍራ የሚመጡት በአብዛኛው ኢስላማዊ ዕይታ፣ ራዕይ፣ ዓላማና አመለካከት ይዘው የተለያየ የዕድሜ መጠን፣ የዕውቀት ደረጃና ፍላጎት ያላቸው ሲሆኑ ኢስላምን ባይከተሉም የሚከተሉ ሰዎችን ተከትለው መንፈሳዊና ቁሳዊ ጥቅም የሚያገኙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

በአንድ መጣጥፋቸው እንደገለጹትም፣ የነቢዩ ሙሐመድ የልደት ቀን በብዙ አገሮች መከበር ከመጀመሩ በፊት ሰዎች ነቢዩ ሙሐመድ ራሳቸው ወደ ተወለዱበት ቤት በመሄድ ጸሎት ያደርሱ ነበር፡፡

‹‹ይህም ነቢዩ መሐመድ የተወለዱበት ቤት የኸሊፋ ማህዲ ሚስት በነበረችውና የሐሩን አል ረሺድ እናት በሆነችው፣ በአል ኸይዙራን ወደ መስጊድነት ተቀየረና ብዙ ምዕመናን ተሰብስበው ጸሎታቸውን የሚያደርሱበት ሥፍራ ሆነ፡፡ የልደት ቀናቸው መከበር የጀመረው በግለሰቦች ተነሳሽነት እንደሆነም አንዳንድ መረጃዎች ቢያመለክቱም፣ በረቢ ዓል አወል በ12ኛ ቀን ወይም ከዚያ ቀን ጀምሮ ባለው በዕለተ ሰኞ ይከበራል፡፡

እንደ አቶ ተሾመ ማብራሪያ በኢትዮጵያ ውስጥ የመውሊድ በዓል ከሚከበርባቸው ሥፍራዎች ውስጥ በወሎ ዳና፣ ገታ ንጉሥ፣ በባሌ ሸኽ ሑሴን ባሌ (አናጀና)፣ በሐረር ከተማ፣ በትግራይ ዓዲጉደም፣ ግጀት፣ ራያ (አና) ተጠቃሽ ናቸው፡፡

‹‹መውሊድ ማለት የነቢዩ ሙሐመድ ልደትን አስመልክቶ የሚከናወን ሰደቃ (ድግስ) ነው፤›› የሚሉት ስለ ወለኔና የአካባቢው ብሔረሰቦች ባህሎች መጽሐፍ የጻፉት የሕግ ባለሙያው አቶ አብዱልፈታህ አብደላህ ሸቤ ናቸው፡፡

እንደ እሳቸው ማብራሪያ መውሊድ በሁለት መልኩ ይከናወናል፡፡ አንደኛው በግለሰብ ደረጃ ሲሆን ሁለተኛው በቡድን ነው፡፡ በቀደምት ጊዜያት ትላላቅ ባለሀብቶች በግላቸው አርደውና ደግሰው መውሊድን ያከናውኑ ነበር፡፡ መውሊድ ያበላ ሰው የዲንና የዱንያ ደረጃው ከፍ ያለ ሰው እንደሆነ ይገለጽ ስለነበር ታላለቅ ባለሀብቶች ይህንን ደረጃ (ማዕረግ) ለማግኘት በአመቻቸው ጊዜ ሁሉ መውሊድ ያደርጉ ነበር፡፡ በዚህም ብዙ የአካባቢያቸውን ድሆች፣ ፈላጊዎችንና ችግረኞችን አጥግበው አስተናግደውበታል፡፡

‹‹በወለኔ፣ ጉታዘርና ገደባኖ ቢያንስ ወደ 20 ታላላቅ እስላማዊ የቀደምት ማዕከሎች ላይ ዓመታዊው መውሊድ ይካሄዳል፡፡ በሰይድ ከቢር ሀሚዲ፣ በሰይድ አሊኑር፣ በጋዞ­ሸኽ በርከሌ፣ በጥሮነ፣ በቦኔ… የሚካሄዱት ዓመታዊ የመውሊድ ሥነ ሥርዓቶች ከቀደምት ጊዜያት እጅግ እየቀነሱ ቢሄዱም አልተቋረጡም፡፡

‹‹በእነዚህ የቀደምት ታላላቅ እስላማዊ ማዕከላት ላይ የሚካሄደው መውሊድ ሲቃረብ የመውሊዱ መሪዎች (ቤተሰቦች) ለቅርብና ለሩቅ ወላጆች የማሳወቅና የቅስቀሳ መልዕክቶችን ወደየአቅጣጫው ይልካሉ፡፡ በከተማና በገጠር ያለው ተወላጅም መልዕክቱን ተቀብሎ በቡድን መዘጋጀት ይጀምራል፡፡ የሚዘጋጀውም በመውሊድ ቀን ለጀባታ የሚያቀርበው በሬ፣ ወይፈን፣ ጫት፣ ቡናና ስኳር ነው፡፡ በተለይም ለእርድ የሚሆነው በሬ በግል ስለማይቻል በቡድን አዋጥተው ያቀርባሉ፡፡ በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ተወላጆችም ገንዘብ አዋጥተው ተወካይ በመላክ የሠንጋ በሬ ስጦታቸውን በመውሊድ ቀን ጀባ ይላሉ፡፡

‹‹የመውሊድ ሥርዓት በአብዛኛው ለሦስት ተከታታይ ቀናት ማታ ላይ የሚከናወን በመሆኑ አስደሳች ነው፡፡ በተለይም በሰይድ ከቢር ሀሚዲ፣ በዑጁባይ፣ በጋዞ፣ በቦኔ… የሚካሄዱት የመውሊድ የማታ ሥነ ሥርዓቶች ልዩ ውበት ያላቸው ናቸው፡፡ ይህም የሚሆነው እነዚህ ማዕከላት በጥንት ዘመን የተተከሉ፣ እስካሁንም ማንም ያልነካቸውና የማይነካቸውም ትላልቅ በአገር በቀል ዛፎች የተሸፈኑ በመሆናቸው ነው፡፡

‹‹በማታ ክፍለ ጊዜ በእነዚያ ታላላቅ ዛፎች ሥር በየቦታው እዚህና እዚያ ኩራዝ፣ ፋኖስ፣ በርስ… እያበሩ እሳት እያቀጣጠሉ በቡድን የተቀመጡ ሰዎች ሲታዩ ሁኔታው በእርግጥም ልዩ ነው፡፡ አስደሳች ነው፡፡ በጣም ማራኪ ነው፡፡ ቀልብንም፣ ዓይንንም ይማርካል፡፡

‹‹የመውሊድ በዓል በሚዘጋጅበት ቦታ አስቀድሞ እንግዶችን ለማስተናገድ የሚያስችል ሁኔታ ምክክር ተደርጎ ይመቻቻል፡፡ መውሊድ ወደሚዘጋጅበት ተካፋይ ሰውም አንድም ተጋብዞ ካለበለዚያም ጠይቆ በእግር፣ በግመል፣ በበቅሎና በፈረስ ዛሬ ደግሞ በመኪና ሥፍራው መምጣት ይጀምራል፡፡

መንዙማ በመውሊድ

‹‹መንዙማ ምስጋና (ማወደስ) ማለት ነው፡፡ መንዙማ በይዘቱ በዋነኛነት ከሃይማኖታዊ ዝማሬዎች ይመደብ እንጂ በውስጡ የተለያዩ ማኅበራዊና ፖለቲካ መልዕክቶችንም ያቀፈ ነው፤›› የሚለው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የጥናት መድበል ነው፡፡

‹‹ሃይማኖታዊ ይዘቱም አላህ የሚመሰገንበት፣ ነቢዩ መሐመድ የሚሞገሱበት፣ የእስልምና ትምህርት የሚሰጥበት፣ ታላላቅ ሰዎች (አወሊያዎች) እና መላዕክት የሚወደሱበት፣ ገድላቸውና ተዓምራቸው የሚነገርበት፣ ችግር (ድርቅ፣ ረሃብና በሽታ) የመሳሰሉት ሲያጋጥሙ የተማፅኖ ጸሎት የሚደረግበት ነው፤››  ሲልም ያክልበታል፡፡

መንዙማ ከሚተገበርባቸው በዓላት አንዱ የነቢዩ መሐመድ ልደት በዓል መውሊድ ነው፡፡ በአብዛኛው የመንዙማ ግጥሞች የሚጀምሩት አላህና ነቢዩ መሐመድን በማወደስ ሲሆን፣ የሚጨርሱት ደግሞ አላህን ለማመስገንና ለነቢዩ መሐመድ ሰላምና እዝነትን አላህ እንዲሰጣቸው ነው፡፡

የመንዙማው አቀንቃኝ በተሳታፊዎች ፊት ሲያቀነቅን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የአከዋወን ሥልት በመከተል የተለያዩ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ያሳያል፡፡ ከግራ ወደ ቀኝ ከቀኝ ወደ ግራ ሰውነቱን ያወዛውዛል፣ ታዳሚዎችም አስፈላጊውን አጸፋና ምላሽ በድምፅና በጭብጨባ ይገልጻሉ፡፡

የመንዙማ አጨፋፈር እንደ ዜማዎቹ ዓይነት ይለያያል፡፡ ዝግ ያለ የድቤ መምቻ ያላቸው መንዙማዎች የአጨፋፈር ሥልት ምቱን ተከትለው እየዘለሉና እጅን ከአናት በላይ እያሳለፉ ማጨብጨብ ሲሆን፣ ፈጣን የድቤ ምት ያላቸው መንዙማዎች ደግሞ እያጨበጨቡ ከወገብ በላይ አካላቸውን ወደ ግራና ወደ ቀኝ ማወዛወዝ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...