Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአስተዳደሩ መሥሪያ ቤቶች የማኑዋል ግዥና ሽያጭ እንዳይፈጽሙ የሚከለክል መመርያ ተዘጋጀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር የሚገኙ መሥሪያ ቤቶች የሚፈጽሟቸው የግዥና ንብረት ማስወገድ ሥርዓቶች በኤሌክትሮኒክ ዘዴ እንዲቀየር የሚያደርግ መመርያ የወጣ ሲሆን፣ መሥሪያ ቤቶቹ ከፋይናንስ ቢሮ ፍቃድ ሳያገኙ የመደበኛ (ማኑዋል) አሠራር እንዳይከተሉ በመመርያው ተከልክለዋል፡፡  

በአስተዳደሩ ፋይናንስ ቢሮ የተዘጋጀውና በፍትህ ሚኒስቴር ተመዝግቦ ይፋ የተደረገው የኤሌክትሮኒክ ዘዴ ግዥና የሚወገድ ንብረት ሽያጭ መመርያ፣ ለኤሌክትሮኒክ ሥርዓቱ ለሙከራ ትግበራ በተመረጡ ወይም እንደ አስፈላጊነቱ ሊካተቱ በሚችሉ ባለ ሙሉ ወይም ከፊል በጀት መሥሪያ ቤቶች ግዥና ንብረት ሽያጭ ላይ ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል፡፡

መመርያው በቢሮ፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ በዕጩ ተወዳዳሪዎች፣ ተጫራቾችና አቅራቢዎች፣ በፋይናንስ ተቋማት እንዲሁም እርስ በርስ የሚደረግ ማንኛውም ግንኙነት በኤሌክትሮኒክ ሥርዓቱ በተደገፈ የግንኙነት ዘዴ መሆን እንዳለበት የሚያትት ሲሆን፣ በልዩ ድንጋጌው መሥሪያ ቤቶች ከሥርዓቱ አተገባበር ጋር በተገናኘ  ችግር ሲገጥማቸማቸው በመደበኛው አሠራር ግዥ መፈጸም የሚችሉት ጥያቄያቸውን ለፋይናንስ ቢሮው አቅርበው ሲፈቀድላቸው ብቻ መሆኑን ያስረዳል፡፡

ይህ ብቻም ሳይሆን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶቹ በኤሌክትሮኒክ ሥርዓቱ አጠቃቀምና ተያያዥ ችግሮችን በተመለከተ የሚያቀርቡት ጥያቄ፣ በሥርዓቱ ግዥ ለመፈጸም ወይም ንብረት ለመሽጥ ያልተቻለበትን አሳማኝ ምክንያትና ሰነዶች ያካተተ ሊሆን እንደሚገባ በልዩ ድንጋጌው ያስረዳል፡፡

በመመርው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ እንዲሁም ተቆጣጣሪ አካላት አግባብነት ባለው ሕግና በተዘጋጀው መመርያ መሠረት የተሰጣቸውን ተግባርና ኃላፊነት የኤሌክትሮኒክ ሥርዓቱን ተጠቅመው ለመወጣት እንዲችሉ በኤሌክትሮኒክ ሥርዓቱ ላይ መመዝገብ ይኖርባቸዋል፡፡

ማንኛውም በመንግሥት ግዥና ንብረት ሽያጭ የሚሳተፍ ተጫራች፣ ማናቸውንም ከፋይናንስ ተቋማት የሚቀርቡ ክፍያዎችና ዋስትናዎች በኤሌክትሮኒክ ሥርዓቱ ላይ ተብሎ በተዘጋጀውን ቅጽ በመጠቀም የቀረቡ መሆኑን የመከታተልና ማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበት በመመርያው ተዳሷል፡፡

በመመርያው ማንኛውም ሰነድ የኤሌክትሮኒክ ሥርዓቱን በመጠቀም የቀረበ እስከሆነ ድረስ በሰነድ ላይ መፈረምና ማህተም ማድረግ ሳያስፈልግ ሰነዱ ትክክለኛና የሕግ አስገዳጅነት እንዲሆን ተደርጎ የሚቆጠር ሲሆን፣ ሆኖም ውሉን የማያካትትና በኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን አዋጅ ቁጥር 1205/2012 አንቀፅ ስምንት ‹‹ጽሕፍ››ን በተመለከተ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች እንደተጠበቁ ሆነው የሚደረግ ስለመሆኑ ያትታል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 17/2002፣ እንዲሁም በግዥ አፈጻጸም መመርያ ቁጥር 3/2002 እና በንብረት አስተዳደር መመርያ የተሰጡ ትርጉሞች አዲስ በተዘጋጀው መመርያም ተፈጻሚ ይሆናሉ ብሏል፡፡

የኤሌክትሮኒክስ የመንግሥት ግዥ ሥርዓት የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘዴዎችን በመጠቀም ግዥ ፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ጨረታ በአየር ላይ እንዲያወጡ የሚያደርግና ተጫራቾችም በኦንላይን ዘዴ ተጠቅመው እንዲጫረቱ የሚያደርግ ዘዴ ሲሆን፣ መሥሪያ ቤቶች ጨረታ በኦንላይን ካወጡ በኋላ የመጫረቻ ሰነዳቸውን፣ ቅሬታ ካላቸው ቅሬታቸውን በሲስተሙ ማስገባት የሚችሉበት፣ ኦዲት የሚያደርጉ ተቆጣጣሪ አካላትም በሥርዓቱ ውስጥ ገብተው ኦዲት ማድረግ የሚችሉበት መሆኑ ይነገራል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች