Tuesday, January 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየንግድና ኢንቨስትመንት ምድብ ችሎት በይፋ ሥራ ጀመረ

የንግድና ኢንቨስትመንት ምድብ ችሎት በይፋ ሥራ ጀመረ

ቀን:

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ጉዳይን ትኩረት በማድረግ ያዋቀረውን፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ምድብ ችሎት በይፋ ሥራ አስጀመረ፡፡

በሥሩ 11 ችሎቶችን በመያዝ የተዋቀረው ምድብ ችሎቱ የኮንስትራክሽን፣ የኢንቨስትመንት፣ እንዲሁም የባንክና የኢንሹራንስ ጉዳዮችን ብቻ የሚመለከት ነው፡፡ በምድብ ችሎቱ ሥር ካሉት ችሎቶች ውስጥ አምስቱ የተመደቡት ለንግድ ጉዳዮች ሲሆን፣ የባንክና የኢንሹራንስ ጉዳዮችም አምስት ችሎት ተመድቦላቸዋል፡፡ ቀሪው አንድ ችሎት የተመደበው ከኮንስትራክሽ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለመመልከት ነው፡፡

የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፒያሳ በቀድሞው ‹‹ብሪቲሽ ካውንስል›› ሕንፃ ላይ ያዘጋጀውን ምድብ ችሎት በይፋ ሥራ ያስጀመረው፣ እሑድ መስከረም 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ነው፡፡ ምድብ ችሎቱ ከሰኔ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በሙከራ ደረጃ ባለጉዳዮችን ሲያስተናግድ መቆየቱን የፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ቃል አቃባይ አቶ ተስፋዬ ንዋይ ተናግረዋል፡፡ ምድብ ችሎቱ የተዋቀረው በ14 ዳኞችና በአምስት ረዳት ዳኞች ሲሆን፣ የተመደቡት ዳኞች ቢያንስ የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸውና የትምህርት ዝግጅታቸው በቢዝነስና ኮንስትራክሽን ሕግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ፣ በዚህ ምድብ ችሎት የሚከፈቱ መዝገቦች የዳኛ ምደባ የሚደረግባቸው ‹‹ከሰው ንክኪ ውጪ›› በተዘረጋው የቴክኖሎጂ ሥርዓት አማካይነት ነው፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት ሰው በመሀል ጣልቃ ስለሚገባ የሚከፈቱ መዝገቦች ተከራካሪ ወገኖች ወደሚፈልጉት ችሎት ይሄድ ነበር፤›› ሲሉ የሥርዓቱን አስፈላጊነት አስረድተዋል፡፡

ምድብ ችሎቱ በኮንስትራክሽን፣ በንግድ እንዲሁም በባንክና በኢንሹራንስ ጉዳዮች ላይ የሚመጡ ጉዳዮችን ወደ ክርክር ከማምራታቸው በፊት በስምምነት የሚቋጩበት ‹‹የፍርድ ቤት መር አስማሚ›› ክፍል ተዋቅሮለታል፡፡ ክፍሉ በሦስት ወራት የሙከራ ጊዜው ተሟልተው ከቀረቡለት 50 መዝገቦች ውስጥ፣ 20 መዝገቦች በስምምነት እንዲቋጩ ማድረጉ ተገልጿል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ምድብ ችሎቱ ተከራካሪ ወገኖች በአካል መቅረብ ሳይጠበቅባቸው ባሉበት ሆነው ክርክር እንዲያደርጉ፣ ምስክር እንዲሰማና የተለያዩ ውሳኔዎች እንዲያገኙ የሚያስችል የቴሌ ኮንፈረስ ክፍልም ይዟል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ሆነ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የንግድና ኢንቨስትመንት ምድብ ችሎትን ለብቻው እንዲመደብ ያደረጉት ኢትዮጵያ ለንግድ ሥራ ያላት አመቺነት ደረጃ ዝቅ ያለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ የዓለም ባንክ እ.ኤ.አ. በ2019 ባወጣው ደረጃ በንግድ ሥራ አመቺነት ኢትዮጵያን 159ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ይኼንን ደረጃ አስመልክቶ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰብሳቢነት ሁሉም ባለድርሻ ዘርፎች ስብሰባ አድርገው እንደነበር የተናገሩት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ፣ ሁሉም ዘርፎች ይኼንን ደረጃ ለማሻሻል የመፍትሔ ዕርምጃዎችን እንዲወስዱ ንግግር መደረጉን አስታውሰዋል፡፡ የንግድና ኢንቨስትመንት ምድብ ችሎት ለብቻው የተዋቀረውም በዚሁ አግባብ መሆኑን አክለዋል፡፡

‹‹ለእኛ ማንኛውም ወደ ፍርድ ቤት የሚመጣ ባለጉዳይ በአክብሮት ሳይንገላታ እንዲገለገል እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን እነዚህ ደግሞ ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ሕይወት ጋር የተገናኙ ስለሆኑ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥባቸው ፈልገን ነው፤›› ሲሉም የምድብ ችሎቱ መዋቀር አስፈላጊነትን አስረድተዋል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ተመሳሳይ የምድብ ችሎት ለማዋቀር በዝግጅት ላይ እንደሆነ ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...