Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ውይይት እንደማይቀበሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አስታወቁ

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ውይይት እንደማይቀበሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አስታወቁ

ቀን:

በመንግሥትና በሕወሓት መካከል ሊደረግ የታቀደው የሰላም ንግግር የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል መሆን አይኖርበትም ሲሉ ሦስት ተፎካካሪ ፓርቲዎች አስታወቁ፡፡ የሰላም ንግግር ሊካሄድ መታቀዱንም ሆነ የሰሜኑን ጦርነት ለማስቆም የሰላም ጥረት መጀመሩን ፓርቲዎቹ እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ንግግሩ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ መጣል የለበትም ብለዋል፡፡

አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡት የእናት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አቶ ጌትነት ወርቁ፣ የኢሕአፓ ተቀዳሚ ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት፣ እንዲሁም የመኢአድ ፕሬዚዳንት ማሙሸት አማረ የኢትዮጵያን ጥቅም የማያስጠብቅ ንግግር ቢቀር እንደሚሻል ተናግረዋል፡፡

እናት ፓርቲ ከዚህ ቀደም በራሱ ተነሳሽነት የውጪ ኃይል ሳይገባ እኛው እንታረቅ በሚል አስታራቂ ሽማግሌዎችን ለማሰባሰብ መሞከሩን የፓርቲው ዋና ፀሐፊ ገልጸው፣ ይሁን እንጂ ለሽምግልና ከተጠቆሙ ሰዎች ብዙዎቹ ፈራ ተባ በማለታቸው፣ እንዲሁም ሕወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች ላይ ወረራ በመክፈቱ ሐሳባቸው በጅምር መቅረቱን ጠቁመዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹የእኛ የሰላም ፍላጎት የዛሬ ሳይሆን የሁልጊዜ ነው፡፡ የሰላም ንግግር በመደረጉ ደስተኞች ነን ችግር የለብንም፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ጌትነት፣ ሆኖም የአገር ሉዓላዊነትን አደጋ ላይ በሚጥል መንገድ መሆን እንደሌለበት አክለዋል፡፡ ‹‹ሕወሓትና ብልፅግና ድርድር ሊያደርጉ አይችሉም፣ ጉዳዩ የአገር ነውና፤›› የሚሉት ኃላፊው፣ ድርድሩ በፌዴራል መንግሥትና ከፌዴራል መንግሥቱ ባፈነገጠ ኃይል መካከል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አቶ ጌትነት አክለውም፣ ድርድር የሚካሄድ ከሆነ ‹‹የመደራደሪያ ነጥቦቹ፣ የተደራዳሪዎቹ ማንነትና፣ የድርድሩ ውጤት ሁሉ በፓርላማ መፅደቅ ይኖርበታል፤›› ነው ያሉት፡፡ የድርድሩ ዋና ግብም በትግራይና በኢትዮጵያ የደረሰውን ዕልቂት ማስቆም፣ ኢኮኖሚውንና የአገሪቱን አንድነት ከውድቀት መታደግ መሆን እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሕወሓት ትጥቅ ሳይፈታና ራሱን እንደ መንግሥት እየቆጠረ ድርድሩ መካሄድ እንደማይችል አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ተቀዳሚ ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት በበኩላቸው፣ የምዕራባውያኑን የድርድር ጫና መቀበል የአገር ሉዓላዊነትን የሚጎዳ ነው ብለውታል፡፡ ‹‹ድርድር እኛም እንፈልጋለን፣ ነገር ግን ምን ዓይነት ድርድር?›› ሲሉ የጠየቁት ኃላፊው፣ በምዕራባውያኑ ግፊት የሚደረግ ድርድር የአገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ እንደሚጥል ሥጋታቸውን ጠቁመዋል፡፡

‹‹ኢሕአፓ ከሕወሓት ጋር ከስምንት ጊዜ በላይ ተደራድሯል፡፡ ፓርቲያችን ከመነሻው ጀምሮ የሕወሓትን ከሃዲነት ጠንቅቆ ያውቃል፤›› ያሉት መጋቢ ብሉይ፣ ሕወሓት በባህሪው ለድርድር አመቺ ያልሆነ ቡድን መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

መንግሥት በድርድር ስም ራሱን ወጥመድ ውስጥ መክተት እንደሌለበት ያሳሰቡት መጋቢ ብሉይ፣ ከሕወሓት ጋር የሚደረግ ድርድር በጥንቃቄ መያዝ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ የድርድሩ ሒደት ከአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ መውጣት አይኖርበትም ያሉት ኃላፊው፣ ‹‹ድርድሩ በአጠቃላይ ሕወሓትን ትጥቅ የሚያስፈታ፣ ጦርነቱን  የሚያስቆምና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያስጠብቅ ሊሆን ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚዳንት አቶ ማሙሸት አማረ በበኩላቸው፣ ‹‹አገሪቱ ከፍተኛ የፖለቲካ ችግርና ቀውስ የገጠማት በመሆኑ፣ መመካከርና መነጋገር ነው የሚበጃት፤›› ይላሉ፡፡ አገሪቱ ችግሯ እየባሰ ሄዶ ለመበታተንና ለባሰ አደጋ ከመዳረጓ በፊት መመካከር፣ መደራደርና ችግርን በሰላም መፍታት ይበጃል የሚል እምነት መኢአድ እንዳለውም አስረድተዋል፡፡

‹‹ኢሕአዴግ ሕዝብ ላይ ፈረሰ፡፡ የእርሱ ችግር ደግሞ ብልፅግናና ሕወሓት የሚል የቡድን መከፋፈል ፈጥሮ ወደ ጦርነት ገብተናል፤›› ሲሉ ነው፣ አሁን ላለው ቀውስ ሁለቱን ቡድኖች አቶ ማሙሸት ተጠያቂ ያደረጉት፡፡

አሁን ያለው ውጊያና ጦርነትም ችግሩን ከፈጠሩት ኃይሎች አልፎ፣ የሕዝቡ ዕዳ ሆኗል የሚል እምነት እንዳላቸው የጠቀሱት አቶ ማሙሸት፣ ድርድሩ ሕዝቡን ያማከለና ያሳተፈ መሆን እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

‹‹ተቃዋሚዎች ድርሻ ሊኖረንና ሕዝቡ በእያንዳንዱ የድርድር ሒደት የሚወከልበት መንገድ ሊመቻች ይገባል፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ማሙሸት፣ በማለባበስና በመሸፋፈን የአገሪቱን ሉዓላዊነት ሁለቱ ኃይሎች አደጋ ላይ እንዳይጥሉ ጠይቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...