Sunday, January 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአገራዊ ምክክሩ “የወጣቶችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ” የሚሠራ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ተመሠረተ

በአገራዊ ምክክሩ “የወጣቶችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ” የሚሠራ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ተመሠረተ

ቀን:

በኅዳር ወር 2015 ዓ.ም. አጋማሽ ይጀመራል ተብሎ በሚጠበቀው አገራዊ ምክክር፣ የወጣቶችን ተሳትፎ የማረጋገጥ ዓላማ ያለው፣ “የወጣት ሲቪል ማኅበረሰብ ጥምረት ለአገራዊ ምክክር” የተባለ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ተመሠረተ፡፡

በወጣቶች ላይ የሚሠሩ 52 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን እንደያዘ የተነገረለት ጥምረቱ በትናንትናው ዕለት ጥቅምት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ ምሥረታውን ይፋ አድርጓል፡፡

ጥምረቱን የማዋቀር ኃላፊነትን የወሰዱት በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በሲዳማና በአፋር ክልሎች የሚሠሩ ሰባት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መሆናቸውን የጥምረቱ ጊዜያዊ ኮሚቴ ሰብሳቢና የጣምራ ፎር ሶሻል ዲቨሎፕመንት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ብሩክ ይርጋዓለም ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ብሩክ ገለጻ ጥምረቱ የተመሠረተው የአገራዊ ምክክሩ ተግባራዊ መሆን የሚጀመርበት ጊዜ እየተቃረበ ቢመጣም፣ የወጣቶችን ለምክክሩ በማደራጀትና አጀንዳቸውን በማዋቀር ረገድ ክፍተት በመታየቱ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሔኖክ መለሰ፣ ‹‹ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል ከአገሪቱ ሕዝብ ቁጥር አንፃር ብዛት ያለው ቢሆንም፣ የወጣቱን አጀንዳ ለማቅረብ የተደረገ ዝግጅት አላየንም፤›› ሲሉ ይህንን ሐሳብ አጠናክረዋል፡፡

አደራጆቹ እንደሚያስረዱት የጥምረቱ መመሥረት ዋነኛ ዓላማ፣ ‹‹ወጣቶች ምን ይላሉ? ምን አጀንዳ አላቸው?›› የሚለው ወደ ምክክር ኮሚሽኑ በተበታተነና ባልተቀናጀ ሁኔታ እንዳይሄድ ለማድረግ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግም ወጣቶች በአገራዊ ምክክሩ እንዴት መሳተፍና አጀንዳቸውን ማቅረብ እንዳለባቸው ሥልጠና የመስጠት፣ እንዲሁም የተለያዩ መድረኮችን በማመቻቸት “የሚመለከታቸው አካላትና” ወጣቶች እንዲገናኙ የማድረግ ዕቅድ መኖሩን አቶ ብሩክ ገልጸዋል፡፡

አሁን ጥምረቱን ከተቀላቀሉት 52 ድርጅቶች በተጨማሪ በየክልሎቹ ያሉ ሕጋዊ ሰውነት ያላቸውና በወጣቶች ላይ የሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የማስገባት ዕቅድ እንዳለ የገለጹት አቶ ብሩክ፣ ‹‹ሕጋዊ ሰውነት የሌላቸውና በየቦታው ያሉ አደረጃጀቶች እንዴት ይሳተፉ ለሚለው ስትራቴጂ እየቀረፅን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ድርጅቶቹ ከዚህ ቀደም ሲንቀሳቀሱባቸው በቆዩ ዘርፎች ላይ ያሉ መዋቅሮችን ተጠቅመው ወጣቶችን የማንቀሳቀስ ሥራ እንደሚያከናውኑ አክለዋል፡፡

እስካሁን ባለው አካሄድ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ ጥምረት የተመሠረተው በኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ሥር ሆኖ ነው፡፡ አቶ ብሩክ፣ ‹‹የምክር ቤቱ አባል ሆነው በወጣቶች ላይ የሚረሱትን ነው እያሰባሰብን ያለነው፣ ወደፊት አስገዳጅ ሆኖ ከመጣ ሕጋዊ ሰውነት እንወስዳለን፤›› ሲሉ የጥምረቱን አወቃቀር አስረድተዋል፡፡

የምክር ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሔኖክ፣ ምክር ቤቱ ለወጣቶች ጥምረት ድጋፍ ከማድረግ በዘለለ በአጠቃላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአገራዊ ምክክር “እንዴት ይሳተፉ?” የሚለውን በተመለከተ የተሳትፎ ማዕቀፍ (Engagement Framework) አዘጋጅቶ ማጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ድርጅቶቹ በሚኖራቸው ተሳትፎ ሊከተሉ የሚገባቸውን መርሆዎች የያዘ የሥነ ምግባር ደንብ (Code of Ethics) ማዘጋጀቱንም ገልጸው፣ ‹‹የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተለየ ባህሪና የተሳትፎ ሥልት ስላላቸው፣ ከዚህ አንፃር የሚጠበቁ መርሆዎች በግልጽ ያስቀመጠና ሥራዎቻቸውንም መርሆዎችንም ጠብቀው እንዲሠሩ የሚያስችል ነው፤›› ሲሉም ስለደንቡ ምንነት ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...