Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከሦስት ወራት በፊት የተነሳው የጌጣጌጥ ማዕድናት ዝቅተኛ የዋጋ ተመን በድጋሚ ሊወሰን ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የተቀረፀ ኦፓል ንግድ በ227.73 በመቶ ቢጨምርም የተገኘው ገቢ በ1.5 በመቶ ቀንሷል

የማዕድን ሚኒስቴር የጌጣጌጥ ማዕድናት ግብይት ሰንሰለትን ለማቃለል በሚል በሰኔ 2014 ዓ.ም. ያነሳውን ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ተመን በድጋሚ ሊወስን ነው፡፡

ሚኒስቴሩ ከሦስት ወራት በፊት የወሰደው ዕርምጃ ወደ ውጭ የሚላኩ የጌጣጌጥ ማዕድናት ብዛት፣ በሦስትና በአራት እጥፍ የተቀረፀ ኦፓልና ሳፋየር ማዕድናት ተልከው የተገኘው የውጭ ምንዛሪ፣ ቀድሞ ከነበረው ዝቅ ማለቱን አስታውቋል፡፡ በገቢ ጭማሪ የታየባቸው ማዕድናት ላይም ቢሆን የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ከተላከው ማዕድን ብዛት ጋር እንደማይመጣጠን ገልጿል፡፡

የጌጣጌጥ ማዕድናት ላኪዎች ይህ ውሳኔ ይፋ የተደረገላቸው ሰኞ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም. የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በተገኙበት በሚኒስቴሩ ቅጥር ግቢ በተደረገው ውይይት ነው፡፡ ሚኒስቴሩ ባለፉት ሦስት ወራት የጌጣጌጥ ማዕድናት ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ተመን መነሳቱን ተከትሎ በተለይ በኦፓል፣ በሳፋየርና በኤመራልድ ማዕድናት ግብይት ላይ የታየውን ለውጥ የሚዳስስ ጥናት አቅርቧል፡፡

ዳሰሳው እንደሚያሳየው በ2013 ዓ.ም. ሰኔ፣ ሐምሌና ነሐሴ ወራት ወደ ውጭ ተልኮ የነበረው ያልተቀረፀ ኦፓል 2,723.82 ኪሎ ግራም ነበር፡፡ በሰኔ 2014 ዓ.ም. ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ተመን መነሳቱን ተከትሎ ሰኔ፣ ሐምሌና ነሐሴ ወራት የተላከው ያልተቀረፀ ኦፓል በ463 በመቶ ጨምሮ 15,337.5 ኪሎ ግራም ደርሷል፡፡ ይሁንና በ2014 ዓ.ም. ሦስቱ ወራት ካልተቀረፀ ኦፓል ንግድ የተገኘው ገቢ ከ2013 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር ያሳየው ለውጥ 6.13 በመቶ ብቻ ነው፡፡

በሦስቱ ወራት ውስጥ ላኪዎች አንድ ኪሎ ያልተቀረፀ ኦፓል ወደ ውጭ የላኩበት ተደጋጋሚ ዋጋ 50 ዶላር እንደሆነ በዳሰሳው ተጠቅሷል፡፡

የተቀረፀ ኦፓል የውጭ ንግድም ከተመኑ መነሳት በኋላ የ227.73 በመቶ ጭማሪ ቢያሳይም፣ ከማዕድኑ ሽያጭ የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ1.5 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ በ2013 ዓ.ም. ሦስቱ ወራት የተገኘው ገቢ 538,526 ዶላር የነበረ ሲሆን በ2014 ዓ.ም. ከተመኑ መነሳት በኋላ ወደ 530,293 ወርዷል፡፡

በ2013 ዓ.ም. ሦስቱ ወራት ተልኮ የነበረው የሳፋየር ማዕድን 4.47 ኪሎ ግራም ወደ 86.44 ኪሎ ግራም አድጓል፡፡ ይሁንና በ2013 ዓ.ም. የተገኘው 21,549.2 ዶላር ገቢ ወደ 15,570.5 ዝቅ ብሏል፡፡

ከሰኔ እስከ ነሐሴ 2014 ዓ.ም. ባሉት ወራት ከኤመራልድ ማዕድን ንግድ የተገኘው ገቢ በኦፓልና በሳፋየር ንግድ ከተገኘው የተሻለ ቢሆንም፣ ከተላከው የማዕድን ብዛት ዕድገት ጋር የሚመጣጠን እንዳልሆነ ዳሰሳው አሳይቷል፡፡ በሦስቱ ወራት የተላከው ኤመራልድ ማዕድን በ384 በመቶ ሲያድግ ያገኘው ገቢ በአንፃሩ ያደገው በ82 በመቶ ብቻ ነው፡፡

በውይይቱ ወቅት የቀረበው የሚኒስቴሩ ዳሰሳ ከአገር በወጣው ማዕድን ልክ የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ ላለመግባቱ ምክንያት ይሆናሉ ያላቸውን ሦስት ምክንያቶች ጠቁሟል፡፡

ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ተመን ከተነሳ በኋላ 57 በመቶ የሚሆነው ምርት የተላከው ወደ ህንድ መሆኑን፣ እንደ አሜሪካ ያሉ የቀድሞ ገዥዎች የገበያ ድርሻቸው መቀነሱ እንደ አንድ ምክንያት ተጠቅሷል፡፡ አብዛኛው ምርት ወደ አንድ አገር መላኩ ከአገራት ስብጥር የሚገኘውን ገቢ እንዳሳጣ፣ ከዚህም ባሻገር ላኪዎቹ “በዕውቀትና ፋይናንስ እጥረት” ምክንያት ዋጋ ተቀባይ እንጂ ተደራዳሪ እንዳይሆኑ እንዳደረገ ዳሰሳው አሳይቷል፡፡ በላኪዎች መካከል ያለው “ጤናማ ያልሆነ” ውድድርም፣ ላኪዎቹ የተሰጣቸውን ዋጋ ብቻ እንዲቀበሉ አድርጓል ሲል ሚኒስቴሩ ባቀረበው ዳሰሳ ላይ ጠቅሷል፡፡

ባለፉት ሦስት ወራት የተላከው ምርት ጥራት ዝቅተኛ መሆኑም ለተገኘው ተመጣጣኝ ያልሆነ የውጭ ምንዛሪ በምክንያትነት ቀርቧል፡፡

‹‹የተገደበ የሆነውና በብዛት ወደ ህንድ የዞረው የገበያ መዳረሻ የዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ተመን አስፈላጊነትን አሳይቷል፤›› ሲልም ዳሰሳው ድምዳሜውን አመላክቷል፡፡

ከዚህ ድምዳሜ በመነሳት ከሦስት ወራት በፊት የነበረውን አሠራር የመመለስ ውሳኔ ያሳለፈው ሚኒስቴሩ ለስድስት የማዕድን ዓይነቶች አዲስ ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ተመን ለውይይት አቅርቧል፡፡ የተቀረፀ ኦፓል፣ ያልተቀረፀ ኤመራልድና ያልተቀረፀ ሳፋየር እያንዳንዳቸው በኪሎ ከአንድ ሺሕ ዶላር በታች እንዳይሸጡ ብሏል፡፡ ያልተቀረፀ የወሎ ኦፓል በኪሎ 150 ዶላር፣ ያልተቀረፀ የሰሜን ሸዋ ኦፓል በኪሎ 50 ዶላር፣ ክሪስታል ኦፓል ደግሞ በኪሎ 80 ዶላር ዝቅተኛ የዋጋ ተመን ተቀምጦላቸዋል፡፡

ይህ ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ተመን በአዳራሹ ለተገኙት ማዕድን ላኪዎች ከቀረበ በኋላ አስተያየት እንዲሰጡበት ጥያቄ የቀረበ ሲሆን፣ ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ተመን በድጋሚ መቀመጡን በተመለከተ ተቃውሞ አልተሰማም፡፡ ተመኑ በድጋሚ ሲወጣ የጌጣጌጥ ማዕድናት ላይ ተሻሽሎ የነበረው የኮንትሮባንድ ንግድ ወደነበረበት ሊመለስ ይችላል የሚል ሥጋት ከአንድ ላኪ በኩል ተሰምቷል፡፡

የአብዛኛዎቹ ላኪዎች አስተያየቶች ያተኮሩት በተመን አሠራሩ ላይ ሊሻሻሉ ያሏቸው ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ ከእነዚህ አስተያየቶች መካከል በብዙዎች ዘንድ የተነሳው ማዕድናቱ በጥቅል ዋጋ ከሚወጣላቸው ይልቅ በጥራታቸው ተከፋፍለው የተለያየ ዋጋ እንዲወጣላቸው የሚጠይቅ ነው፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ጥራት ያላቸው የጌጣጌጥ ማዕድናት የሚሸጡበት ዋጋ ከተቀመጠው ዝቅተኛ ተመን በብዙ ከፍ ያለ በመሆኑ፣ ጥራት ላላቸው ማዕድናት የሚወጣው ዝቅተኛ መሸጫ ዋጋ ከፍ ተደርጎ እንዲቀመጥ ጠይቀዋል፡፡

እነዚህን አስተያየቶች ካዳመጡ በኋላ፣ “እኛ የገባንን ያህል ነው የሠራነው፤” ያሉት የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ (ኢንጂነር)፣ ፍላጎቱ ያላቸው ላኪዎች የዋጋ ተመኑን የማዘጋጀት ሥራ ላይ እንዲሳተፉ ጠይቀዋል፡፡ በዚህም መሠረት የሦስቱም ማዕድናት ላኪ የሆኑ ከ15 በላይ ላኪዎች ፈቃደኝነታቸውን አሳይተው ተመርጠዋል፡፡

ታከለ (ኢንጂነር) የተመረጡት ላኪዎች ከሚኒስቴሩ ባለሙያዎች ጋር በመሆን የተሰጡትን አስተያየቶች ያካተተ የዝቅተኛ መሸጫ ዋጋ ተመን፣ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንዲያዘጋጁ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች