Tuesday, April 16, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለአገር ህልውና ሲባል ሰላም ሰፍኖ ኢኮኖሚው ይረጋጋ!

የአገር ሰላም ተናግቶ ኢኮኖሚው በከፍተኛ ደረጃ በተጎዳበት በዚህ ወቅት፣ የመንግሥት ዋነኛ ትኩረት መሆን ያለበት ሰላም ማስፈንና ኢኮኖሚውን ማረጋጋት ነው፡፡ ይህ የመንግሥት ኃላፊነት በተጨባጭ ተግባራዊ ሊደረግ በሚችል ዕቅድ ተደግፎ አፈጻጸሙ የሰመረ እንዲሆን፣ ከላይ እስከ ታች ያለው የመንግሥት መዋቅር ሥራውን በአግባቡ የሚያከናውንበት ቁመና ላይ መገኘት አለበት፡፡ ለዚህ ማሳሰቢያ መነሻ ምክንያት የሚሆነው የመንግሥት መዋቅር አቅም እጅግ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መገኘቱ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ብዙዎቹ መንግሥታዊ ተቋማት ከፍተኛ የሆነ ሪፎርም የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፣ በብቁ አመራሮችና ባለሙያዎች መመራት ይኖርባቸዋል፡፡ መንግሥታዊ ተቋማት ከማንኛውም ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት በነፃነት ሥራቸውን ማከናወን የሚችሉት፣ ተቋማቱ የፓርቲና የመንግሥት ሥራ ሳይደበላለቅባቸው ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሥራቸውን ማከናወን ሲችሉ እያንዳንዱ ዕቅድና አፈጻጸም በሪፖርት እየተቀባባ አይቀርብም፡፡ ዕቅድ ሲወጣ ቁጥጥርና ግምገማ የሚደረግበት ሲሆን፣ አፈጻጸሙም ቢሆን በተግባር ውጤት የሚታይበት ይሆናል፡፡ የመንግሥት ሥራ ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሚረጋገጠው በሐሰተኛ ሪፖርቶች ማደናገር ሲቆም ነው፡፡ ሰላም ማስፈንና ኢኮኖሚውን ማረጋጋት የሚቻለውም በዚህ መንገድ ነው፡፡

ከአውዳሚው ጦርነት ውስጥ በፍጥነት መውጣት ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ ነው፡፡ ሰላም ለማስፈን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የማክበርና የማስከበር ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፡፡ ለሰላም የሚደረጉ ንግግሮችም ሆኑ ድርድሮች የኢትዮጵያን ህልውና ችግር ውስጥ የሚከቱ መሆን የለባቸውም፡፡ መንግሥትም ሆነ ከመንግሥት ጋር ጉዳይ አለን የሚሉ ማናቸውም ወገኖች፣ ከምንም ነገር በላይ የአገርን ህልውና የሚፈታተን ማንኛውንም ነገር ማስወገድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት መንግሥት የአገርና የሕዝብን ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ሲኖርበት፣ ሌሎች ወገኖችም ይህንን ዓላማ የማክበር ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡ ሰላም ለማስፈን በሚደረግ ጥረት በአገርም ሆነ በሕዝብ ስም ማጭበርበርም ሆነ ማደናገር ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላማዊና ሕግ አክባሪ በመሆኑ በስሙ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም አካላት፣ ከምንም ነገር በፊት ሕግ አክባሪና ሰላም ፈላጊ መሆናቸውን በተግባር ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ግጭቶች ተፈተው ሰላማዊ ድባብ የሚፈጠረው ከጉልበት አምላኪነትና ከሴረኝነት በመላቀቅ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስፈልገው ከተንኮል የፀዳ ሰላም ነው፡፡

ዜጎች በሰላም ወጥተው ለመግባት ሰላም ያስፈልጋቸዋል፡፡ ፖለቲከኞች ዓላማቸውን በነፃነት ተንቀሳቅሰው ለማሳካት ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለ እንከን የሚከበሩት ሰላም ሲሰፍን ነው፡፡ መንግሥት በሕግ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ሕግና ሥርዓት የማስከበር ኃላፊነቱን ሲወጣ፣ ዜጎችም በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ የሚጠበቅባቸውን ተግባር መፈጸም አለባቸው፡፡ ሕግ ሲከበር መንግሥት እንዳሻው የሚፈነጭበት ብልሹ አሠራር አይኖርም፡፡ ግለሰብ ባለሥልጣናት በሥልጣን አይባልጉም፡፡ የመንግሥትና የፓርቲ ሥራ አይደበላለቅም፡፡ መንግሥታዊ ተቋማት በብቁ አመራሮችና ባለሙያዎች እየተመሩ ጠንካራ ይሆናሉ፡፡ ሊፈጸም የማይችል የዘፈቀደ ዕቅድ አይኖርም፡፡ በሥርዓት የታቀደው በአግባቡ ይፈጸማል፡፡ ሰላም ለማደፍረስም ሆነ አገር ለመዝረፍ የሚፈልጉ ሰዎች አደብ ይገዛሉ፡፡ በብሔርና በእምነት ወይም በዝምድናና በጥቅም ትስስር እየተቧደኑ መስረቅም ሆነ፣ ሕዝብን ማንገላታት መሞከር የማይታሰብ ይሆናል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የሞራልና የሥነ ምግባር እሴት እየጎለበተ ሲሄድ፣ ለጠብም ሆነ ለግጭት የሚያነሳሱ ሰበቦች ይወገዳሉ፡፡ ኢትዮጵያና ሕዝቧ እስካሁን እየተሰቃዩ ያሉት ለሕግና ለሥርዓት ተገቢው ክብር ባለመሰጠቱ ነው፡፡ ሕግና ሥርዓት ሲከበር ግን ግጭት ተወግዶ ሰላም ይሰፍናል፡፡

የኢኮኖሚው ጉዳይ በጣም ያሳስባል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ለተከታታይ አራት ዓመታት ያጋጠሙ በርካታ ግጭቶች፣ ጥቃቶች፣ እንዲሁም ላለፉት ሁለት ዓመታት ያህል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ኢኮኖሚውን መዝብረውታል፡፡ ከግጭቶቹ በተጨማሪ የኮቪድ-19 ወረርሽኝና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያጋጠመው ድርቅም፣ በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይ በሩሲያና በዩክሬን ጦርነት ምክንያት በምግብና በነዳጅ ዋጋ ላይ የታየው ከፍተኛ ጭማሪ፣ በኢትዮጵያውያን ኑሮ ላይ ያደረሰው መቃወስ በጣም ከባድ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚስተዋለው ችግር በቀላሉ የሚገለጸው፣ ገበያ ውስጥ በሚታየው ምስቅልቅል ነው፡፡ ኢኮኖሚው ከገጠመው ፈተና ለማገገም የሚያስችል ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ነገር ሳይታይ፣ በጥቁር ገበያው ውስጥ የሚስተዋለው አደገኛ እንቅስቃሴ በየቀኑ የሸቀጦችን ዋጋ ከማናሩ ባሻገር ነገ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን የሚል ሥጋት እየተፈጠረ ነው፡፡ የምርት አቅርቦት እጥረቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ተመርቶም ሆነ ከውጭ ተገዝቶ የሚገባው ምርት ዋጋ የሚወሰነው የግብይት ሥርዓቱን በወረሩት ሕገወጦች ነው፡፡ የአቅርቦት ሰንሰለቱን የተቆጣጠሩትን እነዚህ ኃይሎች መቆጣጠር ባለመቻሉ፣ ገበያው የሥርዓተ አልበኞች መፈንጫ ሆኗል፡፡

መንግሥት ገበያውን በመቆጣጠር ዋጋ መወሰን ባይኖርበትም፣ የአቅርቦት ሰንሰለቱን መቆጣጠርና በየዘርፉ የትርፍ ህዳግ ምጣኔ ማውጣት ለምን እንደማይፈልግ ግራ ያጋባል፡፡ የምግብ ምርቶች፣ የግንባታ ቁሳቁሶች፣ ተሽከርካሪዎችና የመሳሰሉት አቅርቦቶችና አገልግሎቶች በተደራጁ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር እንዴት ሊውሉ እንደቻሉ መገንዘብ የሚቻለው፣ ይህ ጉዳይ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት በብቁ አመራሮችና ባለሙያዎች ሲመሩ ነው፡፡ ድንገት እየተነሱ መደብር ማሸግ፣ መጋዘን ውስጥ ያሉ ሕጋዊ ዕቃዎችን እንደ ሕገወጥ ክምችት መውረስና በጥናት ላይ ያልተመሠረቱ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ኃላፊነታቸውን የተወጡ የሚመስላቸው ተቋማት ከጥቅማቸው በላይ ጥፋታቸው ነው የሚልቀው፡፡ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት ከሚወሰዱ በርካታ ዕርምጃዎች መካከል ቅድሚያ ማግኘት ያለበት የዋጋ ግሽበቱን ማርገብ ነው፡፡ ዜጎች አንዳችም የገቢ ጭማሪ ሳይኖራቸው እንደ ሰደድ እሳት የሚንቀለቀለውን የኑሮ ውድነት መቋቋም እየተሳናቸው ነው፡፡ የምግብ፣ የቤት ኪራይ፣ የትራንስፖርት፣ የልጆች ትምህርትና ልብስ፣ እንዲሁም ሌሎች ተደራራቢ ወጪዎች ኑሮን እያከፉት ነው፡፡ የኢኮኖሚ ጠቢባንም ሆኑ የሌሎች ባለሙያዎች ዕገዛ ታክሎበት፣ ኢኮኖሚው ከገባበት ማጥ ውስጥ መውጣት ካልቻለ መጪው ጊዜ ከባድ ነው፡፡

የሰላሙም ሆነ የኢኮኖሚው ጉዳይ በአገር ዕጣ ፈንታ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በሰላም መደፍረስ ምክንያት ከሚደርሰው ዕልቂትና ውድመት በተጨማሪ፣ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው የዕርዳታ ያለህ የሚሉ ሚሊዮኖች ጉዳይ ያሳስባል፡፡ ጦርነቱ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እየበላ ለተፈናቀሉ ወገኖች ዕርዳታ ማቅረብ በጣም ከባድ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ዕርዳታ ለማቅረብ ያለው አቅም እየቀነሰ ሲሆን፣ ዕርዳታ የጣልቃ ገብነት ፖለቲካ ማስፈጸሚያ መሣሪያ እየተደረገ በአገር ላይ አደጋ እየደቀነ ነው፡፡ ከዚህ አውዳሚ ጦርነት ውስጥ በፍጥነት ወጥቶ ተረጂዎችን መልሶ በማቋቋም ወደ አምራችነት መመለስ ካልተቻለ፣ ሊከተል የሚችለው ቀውስ ከሚታሰበው በላይ ነው፡፡ በዚህ ወሳኝ ወቅት የመንግሥት ኃላፊነት እንደ ሁኔታው ተለዋዋጭ የሆኑ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን መቅረፅ ነው፡፡ ለምሳሌ ሰላም ለማስፈን የሚጠቅሙ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መፈተሽ አንዱ ሲሆን፣ ለኢኮኖሚ ልማቱ ደግሞ በጥናት ላይ ተመሥርቶ ችግር ፈቺ መፍትሔዎችን መፈለግ ሌላው ነው፡፡ አገር አጣብቂኝ ውስጥ ሆና መዘናጋት ስለማይገባ፣ ሰላም ሰፍኖ ኢኮኖሚው እንዲረጋጋ ጥረት ይደረግ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

ስለዘር ፖለቲካ

በሀብታሙ ኃይለ ጊዮርጊስ  ‹‹በቅሎዎች ዝርያችን ከአህያ ነው እያሉ ይመፃደቃሉ›› የጀርመኖች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይዳፈን ጥንቃቄ ይደረግ!

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር አሁንም ጤና አልባ ሆኖ የተለመደው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ሊሻሻል ያልቻለው የፖለቲካ ምኅዳር ሰሞኑን አዲስ...