ከሱዳን የገቡ ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ በኩል ጥቃት መክፈታቸው ተነገረ፡፡ ሰኞ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በመተማ ወረዳ በሬ፣ እንዲሁም ሻሮ በሚባሉ ተራሮች አቅጣጫ ውጊያ ከፍተው የነበሩት የቅማንት ኃይል ከሕወሓት ኃይል ጋር በመጣመር እንደሆነ ወረዳው አስታውቋል፡፡
በተጠቀሱት ቦታዎች ሁለቱ ኃይሎች ከሌሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ ጥቃቱን እንዳደረሱ የተናገሩት የመተማ ወረዳ የሚዲያ ልማት ቡድን መሪ አቶ ልሳነወርቅ ፀጋዬ፣ በጥምር ጦሩ ተመተው መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ፅንፈኛው የቅማንት ኃይልና ሕወሓት በቅንጅት ጥቃቱን የከፈቱት ወደ መሀል መሻገሪያ ለማበጀት አስበው ነበር፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
አካባቢውን የሚቆጣጠረው የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻን ያቀፈው ጥምር ጦር፣ ጥቃት አድራሾቹን ከመመከት ባለፈ በአካባቢው ሠርተውት የነበረውን አንድ ምሽግ ማስለቀቁንም አቶ ልሳነወርቅ ጠቁመዋል፡፡
‹‹ሱዳን በጥቃቱ አለችበት ወይም የለችበትም ለማለት የሚያስደፍር ነገር የለም፡፡ ሆኖም ግን ቦታ ሰጥታቸዋለች፣ እዚያ ነው ተጠለልው ያሉት፤›› በማለት ስለአጥቂዎቹ መነሻ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ በመተማ በኩል በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ጥቃቶች ከሱዳን በሚነሱ ኃይሎች እንደሚቃጣ ያስረዱት አቶ ልሳነወርቅ፣ በጥምር ጦሩ ጥረት እንደሚከሽፉ ገልጸዋል፡፡ በጥቃቱ ስለደረሰው ሰብዓዊም ሆነ የንብረት ጉዳት ኃላፊው ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡
የሰሞኑ ጥቃት የተፈጸመባቸው አካባቢዎች ለገንዳ ውኃ፣ እንዲሁም ለመተማ ዮሐንስ ከተሞች ቅርብ መሆናቸው ተነግሯል፡፡
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ነሐሴ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. አውጥቶት በነበረ መግለጫ፣ ‹‹ያለ ጦርነት መኖር የማይችለው ሕወሓት በዋግ፣ በወልቃይት አቅጣጫና በሱዳን ድንበር አካባቢ ወረራ ከፍቷል፤›› ሲል ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሦስተኛው ዙር የሰሜኑ ጦርነት እንደ ቀጠለ ሲሆን፣ የሰሞኑ የመተማ ጥቃት የጦርነቱ አካል መሆን አለመሆኑን ከመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት መረጃ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡