Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየደቡብ ሕዝቦች ክልል ሕዝበ ውሳኔን አስመልክቶ በተጠራ መድረክ የክልሉ ወኪሎች አለመገኘታቸው ምርጫ...

የደቡብ ሕዝቦች ክልል ሕዝበ ውሳኔን አስመልክቶ በተጠራ መድረክ የክልሉ ወኪሎች አለመገኘታቸው ምርጫ ቦርድን አስቆጣ

ቀን:

የመጨረሻ ውጤት በአርባ ምንጭ ይፋ ይደረጋል

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሕዝበ ውሳኔ የጊዜ ሰሌዳንና ሒደቱን አስመልክቶ በተጠራ የውይይት መድረክ ላይ የክልሉ አስተዳደር ወኪሎች አለመገኘታቸው ምርጫ ቦርድን አስቆጣ፡፡

ምርጫ ቦርድ ትናንት በኢንተርሌግዠሪ ሆቴል የሕዝበ ውሳኔውን አፈጻጸም በተመለከተ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ባደረገው የውይይት መድረክ፣ ሁነቱ የሚከናወንበት ክልል አስተዳደር ወኪሎች እንዲገኙ ጥሪ ያቀረበ ቢሆንም፣ ‹‹የክልሉ ፕሬዚዳንት ሌላ ሥራ እንዳዘዟቸውና እንዳይመጡ እንደነገሯቸው›› መግለጻቸውን የተናገሩት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ይህ የምንቀበለው ነገር አይደለም ብለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከዚህ ቀደም የመራጮች ምዝገባ ሲካሄድ ከሁለት ሳምንት በኋላም የምርጫ ጣቢያዎች ሳይከፈቱ እንደቆዩ በምልሰት ያስረዱት ሰብሳቢዋ፣ ይህም መንግሥት የመተባበር ግዴታውን በዋናነት ካለመወጣቱ ጋር በተያያዘ መሆኑን ገልጸው፣ የአስተዳደር አካላት ወኪሎቻቸውን ልከው አለመሳተፋቸው ጥሩ አመላካች አይደለም ብለዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል በስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች የሚካሄደውን ሕዝበ ውሳኔ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ለማካሄድ ማቀዱን ያስታወቀ ሲሆን፣ ለሕዝበ ውሳኔ ማስፈጸሚያ የሚውል 541.2 ሚሊዮን ብር በጀት ጥያቄ ለመንግሥት ማቅረቡን  አስታውቋል::

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በደቡብ ሕዝቦች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ሥር በስድስት ዞንና አምስት ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ የጋሞ፣ ጎፋ፣ ወላይታ፣ ጌዲዮ፣ ኮንሶና ደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የቡርጂ፣ አማሮ፣ ደራሼ፣ ባስኬቶ፣ አሌ ልዩ ወረዳዎች ላይ የሕዝበ ውሳኔ በማደራጀት ቦርዱ በአብላጫ ድምፅ መደገፉን በማረጋገጥ ውጤቱን እንዲያቀርብ መጠየቁ ይታወሳል።

በሕዝብ ውሳኔው ላይ ከ3.1 ሚሊዮን በላይ መራጮች ይሳተፉበታል የሚል ቅድመ ግምት የተቀመጠ ሲሆን፣ በአንድ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት፣ 11 የዞንና ልዩ ወረዳ የሕዝበ ውሳኔ ጽሕፈት ቤት፣ 29 የማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶች፣ 3,756 የምርጫ ጣቢያዎች፣ 38 የሕዝበ ውሳኔ ውጤት የሚያዳምሩ የዞንና ልዩ ወረዳ አስፈጻሚዎች ሒደቱ ለማከናወን ዝግጅት እያደረግ እንደሚገኝ ቦርዱ ገልጿል፡፡

በቀረበው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የመራጮች ምዝገባ ሒደት ማስጀመሩ ከታኅሳስ 6 ቀን እስከ ታኅሳስ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ሲከናወን፣ የተለያዩ አማራጮችን (መድረኮችና ቴሌቪዥን) በመጠቀም የሚደረገው የምርጫ ቅስቀሳ ከጥቅምት 7 ቀን እስከ ጥር 24 ቀን 2015 ዓ.ም. የሚከናወን ይሆናል ተብሏል።

በዞን ቢሮዎች ወይም በማዳመሪያ ማዕከል የውጤት ማዳመርና ማሳወቅ ሒደት ከጥር 30 እስከ የካቲት አራት ቀን እንደሚደረግ የታወቀ ሲሆን፣ የተገኘውን ውጤት የማረጋገጥና የማሳወቅ ሥራ ከየካቲት አምስት እስከ ስምንት ተከናውኖ፣ የተረጋገጠው የመጨረሻ ውጤት በአርባ ምንጭ የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ እንደሚደረግ የቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ ያሳያል፡፡

በውይይት መድረክ ላይ የተገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ከአስፈጻሚዎች ገለልተኝነት ጋር በተያያዘ፣ በአካባቢዎቹ ላይ የፀጥታ ሁኔታ፣ በሕዝብ ውሳኔ ተሳታፊ ይሆናል ተብሎ ከተገመተው የሕዝብ ቁጥር አነስተኛነትን በተመለከተ እንዲሁም የምርጫ ቦርድ ሒደቱን የማስፈጸም አሁናዊ አቅም ጋር የተያያዘ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡

ወይዘሪት ብርቱካን እንዳስረዱት፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላን በተመለከተ በስድስተኛው ዙር አገራዊ ምርጫ በአፈጻጸም የተሻሉትን፣ ገለልተኛና ፍቃደኛ የሆኑትን በድጋሚ የመምረጥ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ በሒደቱ የግልጽነት ችግር እንዳይነሳ ምልመላና አሠራሩ በአንክሮ የሚተገበር ስለመሆኑ አስምረውበታል፡፡

በሕዝበ ውሳኔ የተገመተው መራጭ ሕዝብ ስሌት የስድስተኛውን ዙር አገራዊ ምርጫ መሠረት አድርጎ የተሠራ ሲሆን፣ በወቅቱ በነበረው አኃዝ ላይ ለመራጭነት ዕድሜ የደረሱ ዜጎችን ታሳቢ በማድረግ እንደተዘጋጀና፣ ከታቀደው በላይ መራጮች ቢመጡም አዳዲስ ጣቢያዎች በማቋቋም የመራጮች ምዝገባ ሒደቱ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተመላክቷል፡፡

የፀጥታ ችግር አለባቸው በተባሉት አካባቢዎች ከፀጥታ ችግር ነፃ መሆናቸው ተረጋግጦ ሒደቱ ተፈጻሚ እንደመሆኑ መጠን፣ የሕዝበ ውሳኔ ክንውኑ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ ዕውን እንዲሆን የመንግሥትና በየደረጃው ያለ የሕግ አስፈጻሚ አካል የሚጠበቅበትን ማድረግ እንደሚጠበቅበት ወይዘሪት ብርቱካን አሳስበዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...