Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ዩክሬንን እንዲጎበኙ ጥያቄ ቀረበ

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ዩክሬንን እንዲጎበኙ ጥያቄ ቀረበ

ቀን:

  • በመካከለኛው ምሥራቅና አፍሪካ የዩክሬን ልዩ መልዕክተኛ ከአቶ ደመቀ መኮንን ጋር ተወያይተዋል
  • የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ስለጉዳዩ የሚያውቀት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል

ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባች ስምንት ወራት የሆናት የዩክሬን መንግሥት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ዋና ከተማዋን ኪዬቭን እንዲጎበኙ ጥሪ አቀረበ፡፡

በመካከለኛው ምሥራቅና በአፍሪካ የዩክሬን ልዩ መልዕክተኛ ማክሲም ሱብህ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር፣ በአዲስ አበባ ከተማ መነጋገራቸውን ተናግረው፣ የአገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን መልዕክት በማስተላለፍ ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊዎች አገራቸውን እንዲጎበኙ ጥሪ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡

ሰኞ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት አዘጋጅነት የተካሄደውን የምግብ ደኅንነትና አመጋገብ ከፍተኛ ኮንፈረንስ ለመሳተፍ ኢትዮጵያ የመጡት ልዩ መልዕክተኛው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሌላው የጉብኝታቸው ዋነኛ ምክንያት አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የጋራ ግንኙነት ማጠናከርና ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ተገናኝቶ መነጋገር ነበር፡፡

በተጨማሪም የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቭሎድሚር ዘለንስኪ የአፍሪካ መሪዎች አገራቸውን እንዲጎበኙላቸውና ያለውን ሁኔታ እንዲመለከቱላቸው ተስፋ እንደሚያደርጉ ልዩ መልዕክተኛው ገልጸው፣ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትም ዩክሬንን እንዲጎበኙ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ አሁን ባለው ሁኔታ ወደ አፍሪካ የመምጣታቸው አጋጣሚ በጣም የጠበበ ቢሆንም፣ ነገር ግን ሁኔታዎች ሲረጋጉ ጉብኝት ማድረጋቸው እርግጥ ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ልዩ መልዕክተኛው አገራቸው ከምሥራቅ አፍሪካ በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ንግዱን ጨምሮ ጥሩ የሚባል መሆኑን፣ ይህንንም ለማጠናከር እንደሚሠሩ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ባለፈው ዓመት ከኢትዮጵያ ጋር ያደረግነው የንግድ ግንኙነት ወደ 300 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ነበር፡፡ ይህንንም የበለጠ ለማጠናከር ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የሕግ ማዕቀፎችን እያዘጋጀን፣ በበለጠ የተለያዩ የንግድ ውሎችን መፈራረም እንዳለብን ተወያይተናል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

በዩክሬን ዩኒቨርሲቲዎች 50 ያህል ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ይገኙ እንደነበር የተናገሩት ልዩ መልዕክተኛው፣ ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተማሪዎቹ ሁኔታዎች ሲረጋጉ ተመልሰው ወይም በርቀት መማር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መንገራቸውን አስረድተዋል፡፡

በአፍሪካ ኅብረት መሰባሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው ስብሰባ ልዩ መልዕክተኛው የአገራቸውን መልዕክት ለተሳታፊዎች ያስተላለፉ ሲሆን፣ ይህ የእሳቸው ጉብኝትም የአገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች ያደረገው የመጀመርያው ጉብኝት ነው ብለዋል፡፡ አገራቸው ዩክሬን በዓለም ላይ ለተፈጠረው የምግብ ቀውስ ተጠያቂ እንዳልሆነች በስብሰባው የጠቀሱት ልዩ መልዕክተኛው፣ በቱርኪዬ ኢስታንቡል ከተማ ባለፈው ሐምሌ ወር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ቱርኪዬ ጦርነት ውስጥ ያሉትን ሁለቱን አገሮች በምግብ አቅርቦት ላይ ማስማማታቸውን አስታውሰዋል፡፡ ለኢትዮጵያና ለሶማሊያ ለምግብ ድጋፍ እንዲሆን ዩክሬን 50 ሺሕ ቶን የሚሆን የስንዴ ምርት መልቀቋንም ልዩ መልዕክተኛው በንግግራቸው አክለው ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ሐምሌ ወር በፕሬዚዳንት ዘለንስኪ የመካከለኛው ምሥራቅና የአፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት ማክሲም ሱብህ፣ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ባደረጉት ውይይት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት እንደምትደግፍ መግለጻቸውን፣ ኢትዮጵያም የዩክሬንን የግዛት አንድነት መርህ እንድትደግፍ መጠየቃቸውን ለሪፖርተር ጠቁመዋል፡፡ በቅርቡም አገራቸው በኢትዮጵያ አምባሳደር እንደምትሾም ማሳወቃቸውን አስረድተዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለሰ ዓለም (አምባሳደር) በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ፣ ልዩ መልዕክተኛውና አቶ ደመቀ መገናኘታቸውን እስከ ማክሰኞ ጥቅምት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ እርግጠኛ አለመሆናቸውን በመግለጽ፣ ለበለጠ መረጃ በደብዳቤ ጥያቄው ቀርቦ እሳቸውም መረጃ ሰብስበው እንደሚመልሱ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ልዩ መልዕክተኛው በተጨማሪም በአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት የኅብረቱን ምክትል ሰብሳቢን ከሞኒክ ሳንዛባጋንዋ (ዶ/ር) ጋር የኅብረቱንና የዩክሬንን ግንኙነት ማጠናከር ላይ ከመከሩ በኋላ፣ እሳቸውም በዩክሬን ጉብኝት እንዲያደርጉ ግብዣ አቅርበውላቸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...