Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊብሔራዊ ሁለገብ የአረጋውያን ማዕከል ሊገነባ ነው

ብሔራዊ ሁለገብ የአረጋውያን ማዕከል ሊገነባ ነው

ቀን:

ብሔራዊ ሁለገብ የአረጋውያን ማዕከል በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚገነባ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የዘንድሮው የአረጋውያን ቀን ጥቅምት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ማዕከሉ በሚገነባበት ቦታ በተከበረበት ወቅት ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፣ የማዕከሉን ግንባታ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ፣ ሲኤምሲ ፀሐይ ሪል ስቴት ጎን በ6418 ካሬ ሜትር ላይ ለማስጀመር እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡

በዓሉን አስመልክቶ አስቀድሞ መግለጫ የሰጡት ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ አየለች እሸቴ፣ የማዕከሉ የዲዛይን ሥራው መጠናቀቁን፣ ይሁን እንጂ ግንባታው ከፍተኛ መዋለ ንዋይ የሚጠይቅ በመሆኑ ከመንግሥት ጥረት ባሻገር ባለሃብቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ተቋማትና የሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ክፍሉ በበኩላቸው፣ በአገሪቱ እየተካሄደ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴን ተከትሎ የአረጋውያን ጉዳይ ትኩረት ማግኘቱን ገልጸዋል፡፡ ሚኒስቴሩ ማኅበሩ ለሚያከናውናቸው ተግባራት ስኬታማነት እያደረገ ላለው ድጋፍ በማኅበሩ ስም አመስግነዋል፡፡

የቦርድ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ማዕከሉ ዕውን ሲሆን፣ በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ አረጋውያን በማዕከሉ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ማዕከሉ ሆስፒታል፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ጅምናዚየምና የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚካተቱበት ይሆናል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሚቋቋመው ማዕከል አረጋውያን የሠሯቸውን ሥራዎች ከትውልድ ትውልድ ለማስተላለፍ ያለመ ጭምር መሆኑን የአረጋውያንና የቤተሰብ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ሮበሌ ተናግረዋል፡፡

‹‹ማዕከሉ በተለያዩ ችግር ውስጥ የሚገኙ አረጋውያን መንፈሳቸውን የሚያድሱበትና የተለያዩ አገልግሎቶች የሚያገኙበት ነው፤›› ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፣ እነዚህንም አገልግሎቶች ተግባራዊ ለማድረግ ማኅበሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ የማዕከሉን ግንባታ ለመፈጸም ባንኮች፣ ባለሀብቶች እንዲሁም ሌሎች ተቋማት ቃል መግባታቸውን፣ ግንባታውንም ለመጀመር እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በበዓሉ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የአገር ባለውለታ ለሆኑ አረጋውያን ተገቢውን ትኩረት፣ ክብር፣ ድጋፍና ክብካቤ መስጠት ይገባል ያሉ ሲሆን፣ በመንግሥት በኩል እየተደረገ ካለው ጥረት ባሻገር የአረጋውያንን ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሁሉም እንዲሳተፍና የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የአረጋውያን ቀን ‹‹የአረጋውያን የኢትዮጵያዊነት አሻራ ለትውልድ አደራ!›› መሪ ቃል ማክበር ያስፈለገበትን ምክንያት ያብራሩት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

አረጋውያን በልማት፣ በባህል፣ በዕውቀት፣ በመከባበር፣ የበለጸገ የቤተሰብ እሴቶችን በመፍጠር፣ የአገርን ታሪክና አንድነትን ጠብቆ በማቆየትና ለአዲሱ ትውልድ በማሸጋገር የከፈሉትን መስዋዕትነት ለመዘከርና ለትውልድ ለማስተላለፍ በማለት ገልጸውታል፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ማኅበረሰብ አቀፍ የድጋፍና እንክብካቤ ድርጅቶች ለልዩ ልዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ አረጋውያን ክብርና ሰብዕናን የጠበቀና የወደፊት ተስፋ ሰጪ የሆኑ የመሠረታዊ አገልግሎቶችን ድጋፍ እንዲያገኙና በተስፋ እንዲኖሩ ያለሳለሰ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የገለጹት የሄልፕ ኤጅ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በላቸው ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...