Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የዘመናዊ የመመርመርያ መሣሪያዎች ትሩፋት

ካለፉት አሥር ዓመታት ወዲህ በጤናው ዘርፍ አንዳንድ መሻሻሎች እየታዩ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከተመዘገቡትም መሻሻሎች መካከል ዘመኑን የዋጁ ልዩ ልዩ የምርመራ መሣሪያዎች አገር ውስጥ መግባትና ጥቅም ላይ መዋላቸው ይገኙበታል፡፡ በአገር ውስጥና በውጪ አገር የሠለጠኑ ሰብ-ስፔሻላይዝድ ሐኪሞች ቁጥር ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱ ለተገኙት መሻሻሎች አንድ ማሳያ ናቸው፡፡ ዘመን አመጣሽ የሆኑ መሣሪያዎች ከሚገኙባቸው ድርጅቶች መካከልም አንደኛው ፓዮኔር ዲያግኖስቲክ ሴንተር ይገኝበታል፡፡ አቶ ብሩክ በፍቃዱ የሴንተሩ ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ በመመርመርያ መሣሪያዎቹና ተያያዥ በሆኑ ጤና ነክ ጉዳዮች አስመልክቶ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ፓዮኔር ዲያግኖስቲክ ሴንተር ምን ዓይነት የሕክምና ምርመራ የሚያደርግ የጤና ተቋም ነው?

አቶ ብሩክ፡- ፓዮኔር ዲያግኖስቲክ ሴንተር ኤሚጂንግ የጤና ምርምር ተቋም ነው፡፡ ኤሜጂንግ ማለት የሰውን የውስጥ አካል እንደ ፎቶ የሚያነሳ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን የሚያከናውነው ይህ ሴንተር፣ የተለያዩ ዓይነቶችና ለየት ያሉ ማሳያ አድቫንስድ የሆነው ልዩ ልዩ የሕክምና መሣሪያዎች አሉት፡፡ እነዚህም መሣሪያዎች ከኤክስሬዩ አንስቶ አልትራ ሳውንድ፣ ማሞግራፊ፣ ሲቲ ስካንና ኤምአርአይ የተባሉት ናቸው፡፡ ታካሚዎች ወይም የምርመራ አገልግሎት የሚሹ ሰዎች ወደ ሴንተሩ የሚመጡት ከተለያዩ የጤና ተቋማት ሪፈር ተደርገው ነው፡፡ እነዚህን አገልግሎት ፈላጊዎች ከፍ ብለው በተጠቀሱት መሣሪያዎች አማካይነት ተገቢውን ምርመራ ካደረግንላቸው በኋላ የምርመራ ውጤቱን እያንዳንዱን ወደየመጡበት ተቋም እንመልሳቸዋለን፡፡

የመንግሥት ጤና ተቋማት ያለውን ባላውቅም አንዳንድ የግል ጤና ድርጅቶችና እንደ እነዚህ ዓይነት መሣሪያዎች ሊኖራቸው ይችላል፡፡ አብዛኞቹ ድርጅቶች ግን የላቸውም፡፡ በተለይ ሲቲ ስካን፣ ኤምአርአይ፣ ማሞግራፊ የተባሉት መሣሪያዎች የሚጠይቁት ኢንቨስትመንት የትየለሌ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በሴንተሩ የሚገኙ ሁሉም የሕክምና መሣሪያዎች በዓይነታቸው ለየት ያሉና ስፒሲፊኬሽናቸውም ላቅ ያሉ ምርመራዎችን የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መሣሪያዎቹ የሚያመጡትን ውጤቶች አብረው ሪፖርት የሚጽፉ ባለሙያዎች (ሬዲዮሎጂስት) በሙያቸው ሰብ-ስፔሻላይዝድ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በዓይነታቸው ለየት ያሉ ናቸው ስለተባሉት መሣሪያዎችና ዓይነታቸው ቢያብራሩልን?

አቶ ብሩክ፡- በዓይነታቸው ለየት ስላሉት መሣሪያዎች ማሞግራፊንና ሲቲስካንን ብቻ በተመለከተ ላብራራልህ፡፡ ሌላውንም የዚያኑ ዓይነት አድርገን ለማየት ያስችላል፡፡ በተለይ ማሞግራፊ የተባለው የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ የሚደረግበት ነው፡፡ የእኛን ጨምሮ በሁሉም ስሪ ዲ ዲጂታል ማሞግራፊ አለ፡፡ የእኛ ደግሞ ለየት የሚያደርገው ከስሪ ዲ ዲጂታል ማሞግራፊ ከሴንተሩ በስተቀር ሌላ ድርጅት ውስጥ አይገኝም፡፡ ይህ ዓይነት ሲስተም ያለው ስሪ ዲ ማሞግራፊ የጡትን ምስል በተለያየ ስላይስ ያመጣል፡፡ በዚህም የሆነ ግኝት ወይም የሚያጠራጥር ነገር ካለና ናሙና (ሳምፕል) መውሰድ ካስፈለገ ጋይድ አድርጎ ሲስተሙን ይወስዳል፡፡ የሚወሰድ ሲስተም አለው፡፡ ከዚህም ሌላ ሲቲስካን ከሌላው መደበኛ ሲቲስካን ወጣ ያሉ ምርመራን ማካሄድ የሚቻል ነው፡፡ ወጣ ያለ የሚያደርገውም የልብ አንጂኦግራፊ ምርመራ ማካሄዱ ነው፡፡ የልብ አንጂኦግራፊ ምርመራ በልብ የደም ቧንቧ ውስጥ ያለውን የካልሲየም ክምችት ይፈትሻል፡፡ የደም ቧንቧው የመደፈን ወይም የመጥበብ ነገር ይታይበታል? ወይስ ውስጡ ንጹህ ነው? በደንብ ይንሸራሸራልን የሚለውን ይመረምራል፡፡ ሰዎች በልብ በሽታ (ኸርት አታክን) እና በስትሮክ ለሕልፈተ ሕይወት ከመዳረጋቸው በፊት የተጠቀሱት ችግሮች መኖራቸውን በቅድሚያ ያሳውቃል፡፡

ሪፖርተር፡- የምርመራ ውጤቱን አንብበው ሪፖርት የሚያደርጉ ባለሙያዎች አቅምና ብዛት ሊነግሩን ይችላሉ?

አቶ ብሩክ፡- ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት የተለያዩ የምርመራ መሣሪያዎች መርምረው የሚያወጡትን ውጤት አንብበው ሪፖርት የሚያደርጉ ራዲዮሎጂስት ይባላሉ፡፡ በመንግሥት ጤና ተቋማት ውስጥ ስላሉት ምንም ዓይነት መረጃ ባይኖረኝም በግል ጤና ድርጅቶች ያሉት ግን ጄኔራል (ጠቅላላ) ራዲዮሎጂስቶች ናቸው፡፡ ይህም ማለት ማንኛውንም የሲቲስካንና የማሞግራፊን የምርመራ ውጤቶችን የሚያነቡ ናቸው፡፡ ይህም ሆኖ በእያንዳንዱ የጤና ድርጅት ጄኔራል ራዲዮሎጂስቶች አሉት፡፡ የሴንተሩ ራዲዮሎጂስት ሁሉም ሰብስፔሻላይዝድ ራዲዮሎጂስቶች ናቸው፡፡ ይህም ማለት በየሰውነት ክፍሉ ተጨማሪ ትምህርት ተምረው የተመረቁና በዚያ ላይ የሚሠሩ ማለት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የነርቭ ነገር የሚያነብ ራሱን የቻለ ወይም ነርቭ ላይ ብቻ ይሠራል፡፡ የአጥንት መገጣጠሚያዎችን ብቻ የሚያይ ባለሙያ ደግሞ ይህንኑ ብቻ ይከታተላል፡፡ እንደ እነዚህ ዓይነት ከፍተኛ ባለሙያዎች በሴክተሩ ውስጥ የሚሠሩት በሙሉና በትርፍ ጊዜያቸው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፓዮኔር ዲያግኖስቲክ ሴንተር ለኅብረተሰቡ ያለውን ተደራሽነት ምን ይመስላል?

አቶ ብሩክ፡- ቦሌ ከሚገኘው ከዋናው ሴንተር በተጨማሪ በአዲስ አበባና በሁለት ክልሎች ውስጥ ስድስት ቅርንጫፎች አሉት፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥ ያሉት ቅርንጫፎች አራት ሲሆኑ እነሱም ሃሌሎያና ሳንቴ አጠቃላይ ሆስፒታሎች እንዲሁም ሬዲዮ ፋና አጠገብ በሚገኘው ቪዥንና ፒያሳ አካባቢ ባለው አርሾ ክሊኒኮች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ሌሎቹ ሁለት ቅርንጫፎች የሚገኙት በአማራ ክልል ደብረ ብርሃንና በደቡብ ክልል ቡታጅራ ከተሞች ውስጥ ነው፡፡ ከእነዚህ ቅርንጫፎች የሚመጡት የምርመራ ውጤቶች በሙሉ በሴንተሩ ባለው ኮምፒውተር ሰርቨር ውስጥ ገብተው ከፍ ብለው የተጠቀሱት ባለሙያዎች በሰውነት ክፍል የተሠራውን ምስል እንደየሙያቸው አንብበው ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ ሴንተሩ እንደ ዓላማ ይዞ የተነሳው ቅድመ ምርመራ ማካሄድ ላይ ቢሆንም ታሞ የሚመጣውን እናክማለን፡፡ ሥራውንም የተሟላ ለማድረግ በእኔ ባለቤትነት የሚመራ ረዳት ክሊኒክ አለን፡፡ ሴንተሩ አጠገብ የሚገኘው ይህ ክሊኒክ ለታካሚዎች የምክር አገልግሎት ከመስጠትም ባሻገር ቤት ለቤት እየተዘዋወረ የሕክምና አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በተጠቀሱት የሕክምና መሣሪያዎች ምርመራ ማድረግ የሚያስፈልጋቸውንም ወደ ሴንተሩ ይመራቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በጥቅምት ዓለም አቀፍ የጡት ካንሰር ወር ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይህንን ምክንያት በማድረግ ሴቶች የጡት ካንሰር እንዳይዛቸው ለማድረግ ምን መክራችኋል?

አቶ ብሩክ፡- ከኢትዮጵያ ውስጥ በጡት ካንሰር ለሕልፈተ ሕይወት የሚዳረጉት ሴቶች በርካታ ናቸው፡፡ ይህንን መከላከል የሚቻለው ችግሩን በእንጭጩ በመቅጨት ነው፡፡ መቅጨት የሚቻለውም የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ በማድረግና ተገቢውን የሕክምና ክትትል በማድረግ ነው፡፡ ስለሆነም ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች ሁሉ በዓመት አንድ ጊዜ ይህ ዓይነቱን ምርመራ ማድረግ አለባቸው፡፡ ይህም ቢሆን ግን ምርመራ ሲያደርጉ አይታዩም፡፡ ወደ ጤና ተቋም የሚሄዱት በሽታው ስር ሰዶ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ሲደርስ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሕክምናውን ፈታኝ ከማድረጉ ባሻገር የመዳን ሁኔታውም የመነመነ ይሆናል፡፡ ለዚህም ብቸኛው መፍትሔ የታመመውን ጡት ቆርጦ ማውጣት ብቻ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በአንዳንድ ሴቶች ላይ የመገለልና ከማኅበራዊ ተሳትፎ የመራቅ ስሜት ያሳድርባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኅብረተሰቡ በተለይም ሴቶች የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ የማያደርጉት ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ምን ለመሥራት አስባችኋል?

አቶ ብሩክ፡- አዲሱን ዓመት (2015 ዓ.ም.) አስታከን ‹‹ስለ ጤና ምን ያህል ያውቃሉ?›› የሚል ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና ሥልጠና ለመስጠት ዳር፣ ዳር እያልን ነው፡፡ በዚህ ላይ ትልቁን ድርሻ የሚሰጣቸው መገናኛ ብዙኃን ስለሆኑ በቅንጅት የምንሠራበትን እያየን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከውጭ የመጡት የምርመራ መሣሪያዎች ሲበላሹም ሆነ እክል ሲያጋጥማቸው የት ነው የሚታደሱት?

አቶ ብሩክ፡- መሣሪያዎችን የሚያስመጣና የሜንቴናንስ ሥራ የሚያከናውን ‹‹ኢንፍኒቲ›› የሚባል እህት ኩባንያ አለን፡፡ በዚህ እህት ኩባንያ ውስጥ 30 ኢንጂነሮች አሉን፡፡ ኩባንያው ለሴንተሩ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሆስፒታሎችም ዕቃ ያቀርባል፡፡ ኢንጂነሮቹ በሥራ በቂ ዕውቀትና ልምድ በማካበታቸው የተነሳ ወደ ሌሎች አገሮች እየሄዱ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ በቅርቡ እንኳን ኬንያ ሄደው አገልግሎት ሰጥተው የተመለሱ ኢንጂነሮች አሉ፡፡ በተረፈ ኩባንያውን ካቋቋምን 15 ዓመት ሆኖናል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ አንድም ቀን እንኳን ቢሆን ከኩባንያው ኢንጂነሮች አቅም በላይ ሆኖ ከጄኔራል ኤሌክትሪክ ኩባንያ የመጣ ኢንጂነር የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ዕቅዳችሁ ምንድነው?

አቶ ብሩክ፡- ከሦስት ወር በኋላ የኑክሌር ሜዲስን የሚባል ሕክምና እንጀምራለን፡፡ ይህንንም ፓዮኔር ዲያግኖስቲክና ረዳት ክሊኒኩ አንድ ላይ ሆነው ይሠሩታል፡፡ ይኼም ሆኖ ግን አሁንም በአገራችን ገና ያልወጡ ምርመራዎች አሉ፡፡ አቅም በፈቀደ መጠን ለማስመጣትም እየተንቀሳቀስን ቢሆንም የውጪ ምንዛሪ እጥረት ጫና እየፈጠረብን ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...

‹‹የኤድስ በሽታ ከ10 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ባሉ ልጆች በሁለት እጥፍ እየጨመረ ነው›› ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ዘርፍ...

የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ከቦታ ቦታ ቢለያይም እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዷ ናት፡፡ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ ጤና...