Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየሰላም ንግግሩም ሆነ ድርድሩ አክራሪነትን ያስወግድልን

የሰላም ንግግሩም ሆነ ድርድሩ አክራሪነትን ያስወግድልን

ቀን:

በገለታ ገብረ ወልድ

ባለፉት ስድስት ዓመታት አገራችን ከፍተኛ ሕዝባዊ እንቢተኝነት፣ የሕዝብና የግለሰቦች ሀብት ውድመት፣ በውስጥና በውጭ ኃይሎች ትግል የሥርዓት ለውጥ፣ በሒደትም ከፍተኛ ማንነት ተኮር ግጭትና ጦርነት ስታስተናግድ ነው የቆየችው፡፡ ሥርዓተ አልበኝነትና ከዚህ ጋር የተያያዘ የፖለቲካ እስራትም መከሰቱ ተደጋግሞ የታየ ነው፡፡ በእነዚህ ያልተረጋጉና ፈታኝ ዓመታት በርከታ ዜጎች ሙትና ቁስለኛ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ ተፈናቃይና ተሳዳጅ የሆነው ሕዝብ ቁጥር ትንሽ አይባልም፡፡ የአገራችን ገጽታም ከሚገባው በላይ ጠልሽቷል፡፡

እነሆ አሁን ደግሞ አገራችን በነውጠኞችና በአማፂ ኃይሎች የገጠማትን ፈተና በከፍተኛ መስዋዕትነት ለመቀልበስ ከመታገሏ ባሻገር፣ በተለይ ነፍጥ አንስቶ ጥቃት የከፈተው ሕወሓትና መንግሥት ለመነጋገርና ለመደራደር ጥረት እየጀመሩ ይመስላል፡፡ ይህንን ሁነት በደፈናው የሚቃወም ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ምክንያቱም ከግጭት፣ ከጦርነትም ሆነ ከትርምስ ጥቂት ስግብግቦች እንጂ አገር ልታተርፍ አትችልምና፡፡ ይሁንና በዚህ መልካም አጋጣሚ መሠረታዊው ቀውስና የአገራዊ ጉዞው እንቅፋቶች እንዲቀረፉ አስቦ ዘላቂ መፍትሔ መፈለግ ከሁሉም ኃይሎች የሚጠበቅ ይሆናል፡፡ ቀዳሚው ጭብጥ በሁሉም ኃይሎች በኩል ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ ከመደበኛው መከላከያ ኃይልና ፖሊስ በስተቀር፣ ሌላ የተደራጀ ሕገወጥ የታጠቀ ኃይል አለመኖሩ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ምናልባት ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ይኑሩ ቢባል እንኳን በክልል መንግሥታትና በማዕከላዊው የፀጥታ ኃይል ሥር፣ የአካባቢ ደኅንነት ለማስጠበቅ ብቻ ታጥቀውና ተደራጅተው ሊሠሩ ይገባል፡፡

እንደሚታወቀው አሁን ያለው መንግሥታዊ ሥርዓት ከሞላ ጎደል አሳታፊና ሰላማዊ በተባለ ምርጫ ሥልጣን የጨበጠ (አንዳንድ ትግራይን የመሰሉ ምርጫ ያልተካሄደባቸው አካባቢዎች ቢኖሩም) እንደ መሆኑ፣ ለሁሉም የአገሪቱ ሕዝቦች ኃላፊነት የሚወስድበትና ተጠያቂነት ያለበት መሆኑ ቅቡልነት ሊያገኝ ይገባል፡፡ የጎደለውን ሞልቶ ይህንኑ መተግበርም ነው ለሕዝቡ ዋስታና የሚሰጠው፡፡ እንጂ አሁን እንደሚታየው በኢመደበኛ መንገድ የታጠቀና በኃይል መደበኛውን ጦር እየተዋጋ፣ ንፁኃንን እያሰቃየ ያለ ኃይል በምንም መለኪያ በየትኛውም አገር አሠራር ተጨማሪ ዕድል ሊሰጠው አይገባም፡፡

ሁለተኛውም የመግባቢያ ጭብጥ ሊሆን የሚገባው የማንነት፣ የወሰንና የፖለቲካና የአስተዳደር አከላል መዘበራረቅና ንትርክን በዘላቂነት ለመቅረፍ ከወዲሁ በድፍረትና በግልጽነት መነጋገርን ማስቀደም፡፡ ይህ አጀንዳ ቀላል ባይሆንም አሁን በተለይ ሕወሓት መራሹ የትግራይ ኃይል ከአማራና ከአፋር ክልሎች፣ እንዲሁም ከኤርትራ ጋር ያፋጠጠው አንዱ ምክንያት ይህ ጉዳይ ነው፡፡ ሰላማዊ በነበረው ደቡብ ክልል ውስጥ የሰላም ማጣት ምክንያት የሆነው ይህ ችግር መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ አሁን ፈዘዝ ያለ ቢመስልም በአፋርና በሶማሌ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በአማራ ክልሎች፣ በኦሮሚያና በርከት ባሉ አካባቢዎች፣ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ፣ ወዘተ. ጉዳይ የጋራ መግባባት የተያዘበት ስምምነት አልተጨበጠም፡፡

እነዚህን መሠረታዊ ጉዳዮች በማስተካከል በጋራ ጎዶሎአቸውን ለመሙላትና የአገረ መንግሥት ግንባታውን ለማጠናከር ደግሞ፣ ከሁሉ በፊት ሕገ መንግሥቱን መፈተሽና ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር መጀመር ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ አሁን ከምንገኝበት ፈተናና አጣዳፊ ሁኔታ አንፃር ግጭት የማስቆሙ ተግባራትን ማስቀደም ግድ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ሄዶ ሄዶ ድርድሩ ከመሠረታዊ ጭብጦችና ከአገራዊ የለውጥ ማሻሻያዎች ካልጀመረ ከዳር ሊደርስ አይችልም፡፡

ከእዚህ አንፃር በሁሉም ወገኖች በኩል (በጊዜያዊ አዋጅ ወይም ሕግ ተደንግጎም ቢሆን) የሚያስፈልገን በልዩነት መነታረክና በታሪክ መወናበድ ሳይሆን፣ ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝሙን በማጠናከር አብሮነትና ሁለንተናዊ ትብብርን ማሳደግና በፍትሐዊነት አገራችንን መገንባት ላይ ማተኮር ግድና አስፈላጊ ነው። ይህን ለማድረግ በአጭር ጊዜ ከኖርንበት ፅንፈኝነት፣ የጥላቻ ትርክትና የትሕነግ/ኦነግ አንቀልባ ላይ አልወርድ ብለው የዜጎችን መከራና ሥቃይ ለማራዘም የሚሹ ኃይሎች በየብሔሩ ማስቸገራቸው ባይቀርም፣ ብርቱ ሕዝባዊ ትግል መጀመር ያስፈልጋል፡፡

እነዚህን ወገኖች በአንድ በኩል ድርድሩም ሆነ ብሔራዊ ምክክሩ ጥቅማቸውን የማይነካና ሥጋት እንደማይሆንባቸው በማስረዳት፣ በሌላ በኩል እየተከተልነው ያለው መንገድ ከግጭት አዙሪት የማያወጣ የቀውስ መንገድ መሆኑን በተጨባጭ በማሳየትና በማስተማር ጭምር ማረቅ ይቻላል፡፡ ከዚህ አልፈው ከመስመር ሲወጡም በሕግ እያረሙ በመሄድ ማስተካከል ይበጃል። በአንድ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) ለዋልታ ቲቪ እንደገለጹት ፌዴራሊዝሙ ከመቀንጨር መላቀቅ አለበት፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ በድፍረት ወደ ብሔራዊ ምክክር ባህሩ ፈጥኖ መግባት ይገባል፡፡

እስካሁን በቆየንበት በአዲስ ትውልድና በተቀየረ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ውስጥ ትናንት በነበረ ትርክት ላይ ተመሥርቶ የተዘራን የተሳሳተ የጥላቻ ፖለቲካ እያጋነኑና እያመነዠኩ፣ ሕዝቦች አብረው የማይኖሩበትን የቂም በቀል ዘር ከሥሩ ለመንቀልም ጥረት መጀመር አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ አለመተማመንና ጫፍ ረገጥነትን ማስወገድ፣ የፖለቲካ አስተሳሰብን በሕዝቦች ላይ ከመጫን መታቀብ፣ እንዲሁም ገለልተኛና የወል ተቋማትን ማጠናከር ይኖርብናል፡፡

በዚያው ልክ እንደ አገር እኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ ፉክክርና የእኛና የእነሱ ጨቅጭቁም መገራት አለበት። ትናንት በሴራ ሕዝቦችን ለማቃቃር የተቀነበበን ወሰንና የማንነት ጥያቄ በግብታዊነት እየመዘዙ በሕግና ሥርዓት ከማስተካከል ይልቅ፣ በፀብና በግጭት ለመፍታት መሞከርም እያስከፈለ ያለው ዋጋ ብቻ ሳይሆን ነገን እንደሚያጨልም ተደማምጦ መረዳት ይገባል፡፡

ስለሆነም ሁሉም ጉዳዮች ከአገርና ከሕግ በታች እንደ መሆናቸው እውነታውን እየተጋፈጡ፣ የሕዝቡን ውሳኔ እያዳመጡ በመነጋገር ወደ አዲስ ምዕራፍ መሻገር ነው የሚጠበቅብን። እንደ ፖለቲከኛም ሆነ እንደ ሕዝብ ምክንያታዊነትም ማበብ  ይኖርበታል፡፡ ትሕነግና የ60ዎቹ ትውልድ መራሹን አክራሪ ብሔርተኝነትና የዛገውን አስተሳሰብ እናስወግድ ሲባል፣ የብሔረሰቦችን ማንነትና ታሪክ እየገነቡ የየትኛውም መብትና ጥቅም ሳይገፈፍ ጠንካራ የጋራ አገር በሚገነባበት አኳኋን መሆን ነው ያለበት። ለዚህ ደግሞ የፖለቲካና የአስተዳደር ወሰንና የማንነት አጀንዳዎቻችን በወጉ መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡

በመሠረቱ ፌዴራሊዝም ራስን በራስ ለማስተዳደር፣ ለመዳኘትና ለመጠበቅ የሚያስችል፣ ትውልድን በራስ ቋንቋ ለማስተማር የሚያግዝ፣ የአናሳውንም ሆነ የብዙኃኑን ባህል፣ ታሪክና ማንነት ለማጎልበትና ለማሳደግ የሚረዳ ሥርዓት ነው፡፡ የእምነትና የሃይማኖት ወይም የባህልና የማኅበረሰብ ልማዶችን ለይቶ ለማጉላትና ለማሳደግ የሚያመች፣ የታሪክና የቅርፅ ፀጋዎችን ለላቀ ጥቅም ለማብቃት የሚያግዝ ሥልት ነው፡፡ የልማት መሠረት አሳታፊና ፍትሐዊ ብልፅግና አምጭነቱም ላይ ጥርጥር የለም፡፡

ሥርዓቱ ዋስትና ባለው ዴሞክራሲና በጠንካራ ሰላማዊነት ከታጀበ ደግሞ፣ የዕድገትና የብልፅግና  መሠረት መሆኑ ተደጋግሞ የተባለ ነው፡፡ ታዲያ ይህን መልካም ጅምር በጠንካራ አብሮነትና አንድነት ብሎም መደማመጥ ማጠናከር ለምን ይከብዳል ብለን ስንጠይቅ፣ በቀዳሚነት ዘውግ መራሽ ፌዴራሊዝም የዘረጋብንን ሕገ መንግሥት ከመነቅነቅና ከመፈተሽ የቀደመ ተግባር ሊኖር አይችልም፡፡

ከዚህ በተቃራኒው ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት እንደሆነው በስመ ፌዴራሊዝም ሥርዓቱን ለአከራር ዘውጌያዊነትና የብሔር ንትርክ ለማዋል ከተሞከረ፣ በጥገኛ መንገድ የብሔረሰቦችና የክልሎችን ሀብትና ንብረት ለመበዝበዝ የፖለቲካ ሥልጣንን መንጠልጠያ ማድረግ ከታሰበ ውድ ዋጋ የሚከፈልበት መሆኑ አይቀርም፡፡ የአገሪቱን ሉዓላዊነትና አንድነት ጠብቆ ለመቆየት ማሰቡም በፈተና የታጠረ ነው፡፡ አካሄዱ ዕድሜ ካገኘ አኩራፊው ኃይል እንደ አማራጭ የወሰደውን ሁሉ ቀርቶ፣ አሁን አገር በመምራት ላይ ባለው የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፎች መካከልም አወዛጋቢ ተግባራት መከሰታቸውም አይቀሬ ነው፡፡

እውነት ለመናገር ከአንዴ ሁለት ሦስት ጊዜ እየተዳማን ቀርቶ፣ በትናንቱ ሥሌትም  በውስብስብና በአወዛጋቢ የታሪክ ትርክት፣ እንዲሁም በእምነት፣ በብሔር፣ በታሪክና በቋንቋ ለዘመናት የተሰባጠረ ብዝኃነትን ለአደጋ በሚያጋልጥ ጥላቻ ለመበስክሰክ መሞከር አብሮ ሊያኖረን አይችልም፡፡ በመሠረቱ የትኛውም ክልል ቢሆን የሚያወጣው ሕግ፣ የሚከተለው የአስተዳደር ሥልት ወይም ሌላ የልማት አቅጣጫ ከራስ አካባቢ ባሻገር ለአገርና ለሌሎች ክልሎች ያለው ፋይዳ፣ ተስማሚነትና ተቀባይነት ያለውን ትርጉም እየመረመረ ነው መሥራት ያለበት፡፡ ሕግጋቱም ሊያስገድዱት ግድ ይላል፡፡ በዚህ ሁሉ አገራዊ ፈተና መሀል በማይበጀው የፉክክርና የእልህ መንገድ፣ ለወራት ያህል እንኳን ለመራመድ መሞከር ግን ከአገራዊ ኪሳራ አያወጣም፡፡

በሁሉም ወገኖች በኩል መታመን ያለበት እውነታ ፌዴራሊዝም የአብሮነትና የአንድነት ፀረ አለመሆኑን ነው፡፡ ለአብነት ያህል በፌዴራሊዝም የዳበረ ሥርዓት ተጠቃሽ አገር የሆነችውን ጀርመን ብንወስድ፣ ከአስከፊ ጦርነትና ከተበታተነ የመሳፍንት አገዛዝ የሚያላቅቅ ማዕከላዊ መንግሥት የሚያቋቁም ሕገ መንግሥት የተቀረፀላት እ.ኤ.አ. በ1871 ነበር፡፡ ከዚህ ዘመን በፊት በአገሪቱ ውስጥ ከ30 በላይ የየራሳቸውን አስተዳደር ዘርግተው የነበሩ የአካባቢ ንጉሦች ነበሩ፡፡ ፌዴራሊዝሙ ይህንን የተበታተነ አስተዳደራዊ ሥርዓት በአንድ ሉዓላዊ ግዛት ሥር ጠቀለለው፡፡ እስካሁንም ጀርመን ብርቱ አገር መሆን የቻለችው በዚህ መንገድ ነው፡፡

ጀርመኖች አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦች ቢሆኑም የባህል፣ የተለያዩ ልማዶችና ማንነቶች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ በባባሪያዎች፣ በሽባበኖች፣ በፍራንከኖች፣ በሳክሰኖች፣ ወዘተ. ቢጠሩም ጀርመን እስካሁንም ጠንካራዋ ጀርመን ነች፡፡ ሕዝቦቿ ቢጋጩም፣ አጋዛዞች ሁሉ ቢፋለሙም ተደማምጠው በመነጋገራቸውና በመደራደራቸው፣ ሦስት ጊዜ ሕገ መንግሥቷን ማሻሻልና መቀያየር ችላለች፡፡  በሒደትም ጠባብነትና ዘረኝነት አይደለም የመደብ ልዩነትም እየጠበበ፣ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ እያደገ በመሄዱ በሁለመናዋ የዓለም ኃያላን ተርታ ተሠልፋለች፡፡

ኢትዮጵያ ለዘመናት ከዘለቀው የአሀዳዊ ፀረ ዴሞክራሲ አገዛዞች በፊትም ሆነ በኋላ የየራሳቸው አስተዳደር፣ ሕዝብና ወሰን ያላቸው ነገሥታትና መሪዎች ያሏቸው ቦታዎች ስብስብ ነበረች፡፡ ሌላው ቀርቶ የዘመነ መሳፍንትን የመበላላት ክስተት ብንመረምር፣ አንዱ ሌላውን ለማስገበርና ለመጠቅለል ከፍተኛ ፍልሚያ ተካሂዷል፡፡ አሀዳዊ ሥርዓት ከ125 ዓመታት ወዲህ ተጠናክሮ የአሁኗን ኢትዮጵያ ቅርፅ አካቶ በአዲስ መልክ ሲዋቀርም፣ በኃይልና በጦር አቅም በመጨፍለቅ ብቻ ሳይሆን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ማንነትንም በማስቀየር ጭምር መሆኑ የቅርብ ጊዜ የታሪክ ትውስታ ነው፡፡

በእኛ አገር የፖለቲካ ኢኮኖሚ ትግል ውስጥ ክፍተቱ የተፈጠረው ግን፣ ገዥ መደቦችንና የሥርዓቱ ቀንደኛ መሪዎችን ከጭቁን ዜጎች ጋር በመቀላቀል ለማየት በመሞከሩ ነው፡፡ በተለይ የአማራና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዩ ወገን የቀድሞ አገዛዞች መሣሪያ አድርጎ የመሣሉ አካሄድ፣ የጠላትና የወዳጅ ፍረጃ ፈጥሯል፡፡ በተለይ ‹‹ለዘመናት ተረስተን ኖርን›› የሚለው የአገራችን የኅብረተሰብ ክፍልና ‹‹የብሔር ጭቆናን›› የፖለቲካዊ ትግሉ ዋነኛ መሣሪያ አድርጎ የዘለቀው (የኦነግና የሕወሓት አተያይ አቀንቃኝ) ልሂቅ፣ በየፊናው ሲጻፍለት የነበረውን ይህ ዓይነቱ የተዛባ ትርክት ሲያመነዥክ ነበር የኖረው፡፡ ቢያንስ እንዲህ ዓይነት ግድፈቶችን ቁጭ ብሎ በመነጋገር በሚዛናዊነት ማረም ግድ የሚል ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል ሥርዓቱ በተለይ በእኛ አገር ቋንቋና ብሔር ተኮር መሆኑ፣ ‹‹በአስተዳደር የየራሳቸው ሉዓላዊ ሥልጣንና መዋቅር ያላቸው ክልሎች በጋራ የሰየሙት አንድ ፌዴራላዊ መንግሥት ይኖራቸዋል›› ከሚለው ወደ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የመምጣት ዕሳቤ ይልቅ፣ መለያየትና ራሱን የቻለ መንግሥት ለመሆን የሚቋምጥ ‹‹አካል›› እንዲበረክት ማድርጉም የሚቃናበት መንገድ መታየት አለበት፡፡ እዚህ ላይ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 ላይ የተሰነቀሩ አሻሚና አጠራጣሪ ድንጋጌዎችን ከመፈተሽ መጀመሩ መተማመንን ሊገነባ ይችላል፡፡

በመሠረቱ የአስተዳደር ክልልና ወሰን ልሂቃኑ ካሳደሩት የሥልጣን፣ የሀብትና የመሬት መቀራመት ዕይታ አንፃር ሳይሆን መሆን ያለበት ከሕዝቦች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት አንፃር ነው፡፡ የትኛውም ጉዳይ ከአገር አንድነትና ከሕዝቦች ጥቅም አኳያ ብቻ አተኩሮ መታየት የሚገባው ሲሆን፣ በተለይ ኅብረ ብሔራዊ ማንነት ያለውና በየዋና ከተማው የሚኖረውን ወገን የት እናሳርፈው ብሎ መጨነቅም ግድ ይላል፡፡ ይህ ደግሞ ከሕወሓት ዕይታ ወጣ ብሎ አዲስ ፈለግና አታያይ ዕውን ማድረግን ይፈልጋል፡፡ ጦርነትና ትርምስን ሊያስቀር የሚችለውም ይህ ዓይነቱ ሰላማዊ የትግል መድረክ ነው፡፡

በአገራችን የተጀመረው ፌዴራሊዝም እስካሁን ለተጣበቀበት የብሔር ፍጥጫ ሌላም መገለጫ አለው፡፡ ለዘመናት ተቃቅፎ የኖረውና በሕወሓት ከፋፍለህ ግዛው አስተዳደር እንኳን በአንድ ክልል ውስጥ የቆየው ደቡብ፣ አብሬ አልኖረም በሚሉ ካድሬዎች ጭንቅላቱ እየዞረ ነው፡፡ በዚህ ክልል ከ50 በላይ ብሔረሰቦች እንዳሉ ይነገራል፡፡ አብዛኞቹ ተቀራራቢና በአንድ የቋንቋ ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙ ማንነትም ያላቸው ናቸው፡፡ በባህል፣ በወግና በታሪክም የሚቀራረቡ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ግን መነጣጠል እንጂ መሰባሰብና ኅብረት ቦታ እያጡ ነው፡፡ ለዚህም ነው እርማቱ መጀመር ያለበት በተጋጩት ወገኖች ብቻ ሳይሆን፣ ገና ግጭት በሚያሠጋቸው መሀልም መሆን ያለበት፡፡

እንደ አገር ከእነ ጉድለቱም ቢሆን ባለፉት 32 ዓመታት የተጀመረውን የአገር ልማትና የግል ባለሀብቱን ሰፊ እንቅስቃሴ ለማጠናከር እየገደበ የሚገኘውን የመነጣጠል አስተሳሰብ በየትኛውም መንገድ ለማስተካከል መዘጋጀት የሚቻለው ሰላም፣ የላቀ ዴሞክራሲና የተጠናከረ አንድነት ሲገነባ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በየትም ዓለም ሠርተው፣ ተበድረውና አሰባስበው ሀብት ያመጡ ባለሀብቶችና የውጭ ኢንቨስተሮች ጭምር በዋና ከተማዋና በአንዳንድ ክልሎች እንደፈለጉ  እንዳያለሙና አገር እንዳይለውጡ የሚያውኩ ያልተጻፉ ሕግጋትና መገፋፋቶች መስተካከል ይኖርባቸዋል፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን በታሪክ አጋጣሚ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ተበትነው፣ ተዋልደውና ተግባብተው ኑሯቸውን የመሠረቱ ዜጎችና ወገኖች፣ ሴቶችና አቅመ ደካሞች ሳይቀሩ በዘርና በእምነታቸው ምክንያት ብቻ የሚጠቁበትና ዋስትና የሚያጡበት አካሄድ የሚገታው፣ ይህንኑ እውነታ የምክክሩ ቀዳሚ አጀንዳ በማድረግ ነው፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ገደማ በለውጥ ስም በተለያዩ አካባቢዎች፣ ኢትዮጵያዊ ሆኖ በኢትዮጵያ ላይ ይህን ሁሉ ግፍና ጥፋት እስከ ማድረስ የሚያስጨክነውን በሽታ ለይቶ ማከም ባለመቻሉ ልሂቃን ሊፀፀቱ ይገባል፡፡

ሰላም ለማስፈን መስማማት ቅድሚያ ይሰጠው እንጂ፣ በዚህች ታሪካዊትና ሰፊ አገር የተጀመረው ፌዴራላዊ ሥርዓት በሽታው ዘውግ ተኮር ከመሆኑ የሚመነጭ ብቻ ነው ማለትም አዳጋች ነው፡፡ ይልቁንም በነፃ ምክክርና መግባባት ሕዝቦች እንደ ወርድና ቁመታቸው፣ እንደ ተሳትፎና አስተዋጽኦአቸው፣ ብሎም እንደተጋመዱበት መስተጋብር በፍትሐዊነት የሥልጣን ባለቤትነትና የዕድገት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሥራትም ይገባል፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ ተወደደም ተጠላም በመደራደርና በመወያየት ብቻ ነው፡፡

ሲጠቃለል ፌዴራሊዝም የሚበጀንና እያደገ መቀጠል ያለበት ሥርዓት ነው፡፡ በመሆኑም ወቅታዊውና ብቸኛው መፍትሔ እንከኖችን እየነቀሱ ከፍጥጫና ቀስ በቀስ ከሚደፈርስ አገራዊ የሥጋት ስሜት ሊያወጣ የሚችል ምክክርና ድርድር ማድረግ ግድ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ቀዳሚዎቹ ተወያዮች አማፅያኑና የፌዴራሉ መንግሥት ይምሰሉ እንጂ፣ አካታችና ሁሉን አቀፍ ውይይትና የጋራ ማሻሻያ ነው ዘላቂው መፍትሔ፡፡

ማንኛውም ፖለቲካዊ ሥርዓትም ይሁን አገር ከሁሉ በላይ የሰላምና የሕዝብ ደኅንነት፣ እንዲሁም ያለ እውነተኛ ዴሞክራሲ አይረጋምና ለሰላምና ለዴሞክራሲ ማበብ ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡ እነዚህ መሠረታዊ የሕዝብ ጥቅሞች ለድርድር ሳያቀርቡ በፅናትና በጥልቅ መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሰላም ድርድሩም ሆነ ምክክሩ የብሔር፣ የሃይማኖትም ሆነ የእኔ እኔ ባይነት አክራሪነትን ያስቀርልን፡፡ ምኞታችን ይኸው ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን  እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...