Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የድሬዳዋ አስተዳደር የሚገለገልበትን ሕንፃ ለባለንብረቶቹ ባለመመለሱ ውዝግብ ተፈጠረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከአዋጅ ውጭ ተወርሶ የነበረው የድሬዳዋ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና ከኢትዮጵያ የጫት የእርሻ እርባታና ኢንዱትሪ ውጤቶች ላኪና አስመጪ ማኅበር ጋር በጋራ ያስገነቡት ባለአራት ወለል ሕንፃ እንዲመለስ የፌዴራሉ መንግሥት በ2007 ዓ.ም. የሰጠው ትዕዛዝ ሊፈጸም ባለመቻሉ በፍርድ ቤት ተፈጻሚ እንዲሆን ተጠየቀ፡፡ 

ሕንፃው በደርግ ዘመን ከአዋጅ ውጭ የተወረሰ በመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ለባለቤቶቹ እንዲመለስ ወስኖ ይህንንም ውሳኔ የቀድሞ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ (በአሁኑ ወቅት የመንግሥት የልማት ድርጅት ይዞታና አስተዳደር) ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ያስታወቀው ነሐሴ 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ነበር፡፡ ሆኖም ንግድ ምክር ቤቱና አክሲዮን ማኅበሩ በተሰጠው ውሳኔ መሠረት ሕንፃቸውን መረከብ ባለመቻላቸው እየተጉላሉ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የአክሲዮን ማኅበሩና የንግድ ምክር ቤቱ ኃላፊዎች ንብረቱ እንዲመለስ በፌዴራል መንግሥት የተሰጠው ትዕዛዝ ሊፈጸም ያልቻለው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የፌዴራል መንግሥት የሰጠውን ትዕዛዝ ባለመቀበሉ እንደሆነ ገልጸዋል። 

ከዓመታት በፊት አክሲዮን ማኅበሩና የንግድ ምክር ቤቱ በጋራ በጻፉት ደብዳቤ መንግሥት በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ከአዋጅ ውጪ የተወረሰባቸው ንብረት ሊመለስላቸው እንዳልቻለ በወቅቱ ሥልጣን ላይ ለነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አቤቱታ አቅርበው ነበር። የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤትም አቤቱታቸውን ተመልክቶ የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የተጠቀሰውን ንብረት በታዘዘው መሠረት እንዲመለስ አሳስቦ ነበር። ይሁን እንጂ አሁንም ባለንብረቶቹ በትዕዛዙ መሠረት ንብረታቸውን ማግኘት እንዳልቻሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል። ሕንፃው ያለአግባብ በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ተይዞ መቆየቱ ያደረሰባቸውን ጉዳት በመጥቀስም አቤቱታቸውን በድጋሚ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ማቅረባቸውንም ገልጸዋል። የመንግሥት ይዞታና አስተዳደርም ለድሬዳዋ ምድብ ፍትሐ ብሔር ችሎት መስከረም 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ በመንግሥት የተሰጠውን ትዕዛዝ እንዲያስፈጽም መጠየቁን ሪፖርተር ከተመለከተው የሰነድ ማስረጃ ለማወቅ ችሏል። 

በመሆኑም ጉዳዩን ወደ ሕግ በመውሰድ በፍርድ ቤት እንዲፈጸምላቸው አቤቱታ ማቅረባቸውን ገልጸዋል። 

የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ንብረቱን እንዲመልስ የተሰጠውን ትዕዛዝ መፈጸም ለምን እንዳልቻለ ለመጠየቅ ሪፖርተር ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም። 

ነገር ግን የተመለከትናቸው የደብዳቤ ልውውጦች እንደሚያስረዱት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እንዲመልስ በታዘዘው ሕንፃ ይዞታ ላይ ተጨማሪ ወጪ በማውጣት ማስፋፊያ አከናውኖ ለድሬደዋ ከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤትና ለድሬደዋ ኤፍኤም ሬዲዮና ድሬ ቴሌቪዥን ጣቢያ መገልገያነት እያዋለው መሆኑን በመጥቀስ ለባለንብረቶቹ ካሳ ከፍሎ ንብረቱን የከተማ አሰተዳደሩ እንዲያስቀረው ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ አቅርቦ ነበር። በዚሁ ጥያቄ መሠረትም የፌዴራሉ መንግሥት ባለንብረቶቹ ለማስፋፊያ የወጣውን ተጨማሪ ወጪ ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከፍለው ሕንፃው እንዲመለስላቸው፣ ክፍያውን መክፈል የማይችሉ ከሆነ ደግሞ አስዳደሩ ተገቢውን ካሳ ክፍሎ ከሊዝ ክፍያ ነፃ ተለዋጭ የሕንፃ መሥሪያ ቦታ እንዲሰጥ መወሰኑን ከደብዳቤ ልውውጦቹ ለመረዳት ተችሏል።

በዚህ ውሳኔ መሠረትም ባለንብረቶቹ የከተማ አስተዳደሩ ለማስፋፊያ ያወጣውን ተጨማሪ ወጪ ከባንክ ተበድረው የከፈሉ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል። ይሁን እንጂ የከተማ አስተዳደሩ ክፍያውን ተቀብሎም ንብረቱን አስካሁን አልመለሰም።

የመንግሥት የልማት ድርጅት ይዞታና አስተዳደር ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለድሬዳዋ ምድብ ፍትሐ ብሔር ችሎት በጻፈው ደብዳቤ ሕንፃው ለባለንብረቶቹ እንዲመለስ በመርህ ደረጃ መወሰኑን ጠቅሶ ውሳኔውን እንዲስፈጽም ጠይቋል።

በደብዳቤው አክሎም ችሎቱ ውሳኔውን የማስፈጸም ሥልጣንና ውክልና በአዋጅ ቁጥር 110/1987 አንቀጥ 4 ንዑስ አንቀጽ 2(ሐ) እና በፍ/ሰ/ስ/ቁጥር 372 መሠረት የተሰጠው መሆኑን በመግለጽ ለውሳኔ ይረዳ ዘንድ የፌዴራል መንግሥት የሰጠውን ውሳኔ የሚያስረዱ የሰነድ ማስረጃዎችን ልኳል። 

አሁን አፈጻጸም እየጠበቅን ነው የሚሉት ንግድ ምክር ቤቱና አክሲዮን ማኅበሩ ከዚህ ቀደም በተሰጠው ውሳኔ መሠረት መከፈል ያለበትን ክፍያ ሁሉ መፈጸማቸውን ገልጸዋል፡፡ ቢሮ እያላቸው በኪራይ ሥራቸውን እየሠሩ እንደነበር በመግለጽም አሁንም የተሰጠው ትዕዛዝ ተፈጻሚ ይሆንልናል ብለው አንደሚያምኑ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ይህ ባለአራት ወለል ሕንፃ እየተቀመበት ያለውን የከተማ አስተዳደሩ ሲሆን፣ ለማስረከብ ይህንን ያህል ዓመት ለምን እንደወሰደበት ለማወቅ አልተቻለም፡፡ 

   

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች