Wednesday, February 28, 2024

የፕሬዚዳንቷ የፓርላማ የመክፈቻ ንግግርና የፖለቲካ ፓርዎች ዕይታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌደሬሽን ምክር ቤት ሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን የሁለቱም የምክር ቤት አባላትና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጨምሮ የመንግሥት ሹማምንት፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ዲፕሎማችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ሰኞ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በፕሬዚዳት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተከፍቷል፡፡

ፕሬዚዳንቷ በመክፈቻ ንግግራቸው ያለፈውን የ2014 ዓ.ም. የመንግሥት ዕቅድ አፈጻጸምና የተጀመረውን የ2015 ዓ.ም. ዕቅድ በተመለከተ ለምክር ቤቶቹ አቅርበዋል፡፡

በተጠናቀቀው የ2014 በጀት ዓመት አገሪቱ ትልልቅ የሚባሉና በመጥፎም ይሁን በመልካም ሊጠቀሱ የሚችሉ ሁነቶችን እንዳስተናገደች የገለጹ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካካል የአዲስ ምዕራፍ ማብሰሪያ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተካሂዶ፣ አዲስ መንግሥት መመሥረቱንና ምርጫው ከእነ ጉድለቱም ቢሆን አገሪቱ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መንግሥት መመሥረት መቻሏ፣ ከአቅጣጫ ቀያሪ ኩነቶች መካከል የሚጠቀስ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ በዓመቱ ውስጥ እንደ ስኬት ሊቆጠሩ የሚችሉ ትልልቅ ክንውኖች የመኖራቸውን ያህል፣ ‹‹ሕዝባችንን በሐዘንና በጭንቅት ውስጥ የከተቱ ተግዳሮቶች›› መስተዋላቸውን አውስተዋል፡፡ ይህ መሰናክል የበዛበት ጉዞ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ተግዳሮት የሚደጋገምባት አገር፣ በሌላ በኩል ፈተና የማይበግራት የፅናት ተምሳሌት እንድትሆን አድርጓታልም ብለዋል፡፡

‹‹2014 ዓ.ም. በፖለቲካ፣ በኦኮኖሚና በዲፕሎማሲ ዘርፎች ከዕቅዳችን አኳያ በጣም ተስፋ ሰጪ ውጤት ያገኘንበት ቢሆንም፣ ግጭትና መፈናቀል ካልተሻገርቸው ችግሮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነትና በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች በንፁኃን ዜጎች ላይ የደረሰው የጅምላ ጭፍጨፋዎች፣ በአሉታዊ ጎናቸው የሚታወሱና የበርካቶችን ልብ የሰበሩ ክስተቶች መሆናቸውንም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት የሰላምን ዋጋ በሚገባ የተረዳ በመሆኑ ግጭት ጨርሶ እንዲያበቃ ከማንኛውም ወገን ያለ ምንም ቅድም ሁኔታ ለመደራደርና ልዩነቶችን በሰላምና በውይይት ለመፍታት ሐሳብ ማቅረቡን በመግለጽ፣ ይህንን ዕድል ስለትግራይ ሕዝብ ሲል ሕወሓትም የሰላም ጥሪውን በመቀበል ለድርድር እንዲቀመጥ በተደጋጋሚ ጥሪ ስለመቅረቡም አስታውሰዋል፡፡ አክለውም በአጠቃላይ ሲታይ መንግሥት መቼም ቢሆን የሰላም በሮችን እንደማይዘጋ ግልጽ ማድረጉን፣ ማናቸውንም ልዩነቶች በመነጋገር ለመፍታት አስፈላጊ መሆኑን በማመን ያለ ቅድመ ሁኔታ ለመወያየት ጥሪ አቅርቦ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም መንግሥት አካታች የፖለቲካ ምኅዳር ለመፍጠር፣ እንዲሁም በሁሉም የሐሳብ ልዩነቶች ላይ አገራዊ ምክክር እንዲደረግና አገራዊ መግባባት እንዲመጣ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አክለው ገልጸዋል፡፡

የተጀመረው የ2015 ዓመት አገሪቱን ሲፈትናት የነበረው ጦርነት በሰላም የሚቋጭበት ጊዜ እንዲሆን የሁሉንም ጥረት እንደሚፈልግ የገለጹት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፣ በአፍሪካ ኅብረት በኩል ሲደረግ የቆየው የሰላም ጥረት መልካም መሆኑንና ኅብረቱ በልዩ መልዕክተኛው በኩል እያደረገ ያለውን ጥረት በመቀጠል፣ ‹‹ለሰላም ያለውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት እምነቴ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹እንደ አገር አለመግባባትና ልዩነትን፣ ደም አፋሳሽነትን ቂምና ቁርሾን፣ አለመግባባት ልዩነትን እያሰፋ የሚፈጥረውን የግጭት አዙሪት በመስበር አገራችን እየተመላለሰ ከሚጎበኛት የህልውና ሥጋት መጠበቅ መቻል አለብን፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በ2014 ዓ.ም. ሰፊ ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ተግዳሮቶች በኢኮኖሚው ላይ ያሳደሩት ጫና እንዳለ ሆኖ የተመዘገበው የኢኮኖሚ ስኬት ትልቅ ግምት የሚሰጠው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም የኮሮና ወረርሽኝ ጥሎት ባለፈው ጠባሳ፣ ጦርነቱ በፈጠረው የኢኮኖሚ ውድመት፣ እንዲሁም የጎርፍና የድርቅ ክስተቶች በፈጠሩዋቸው አሉታዊ ተፅዕኖዎች ኢኮኖሚው ሳያሽቆለቁል ዕድገት ማስመዝገቡን አስረድተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ ካነሷቸው ስኬቶች መካከል የወጪ ንግድ ዕድገት መጨመር፣ የአገልግሎት ዘርፍ ገቢ ዕድገት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የታክስ ገቢ መጨመር ይጠቀሳሉ፡፡ በተቃራኒው ደግም በዋጋ ግሽበት የተባባሰው የኑሮ ውድነት በዜጎች ላይ ከፍተኛ የኑሮ ጫና መፍጠሩን፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ማክሮ ኢኮኖሚው ዋነኛ ማነቆ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት በትኩረት በመሥራት፣ አነስተኛና ቋሚ ገቢ ያለውን ማኅበረሰብ ካላስፈላጊ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት በተጀመረው በጀት ዓመት የሰላምና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን አንገብጋቢነት በመረዳት ቆራጥ ውሳኔ ባሳለፈው መሠረት፣ ከሕወሓት ጋር የአገሪቱን ጥቅም ባስከበረና በዘለቄታዊ መንገድ ድርድር እንዲደረግ የተቻለውን ሁሉ ጥረት በማድረግ እንደሚገፋበት ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ሰላም አማራጭ በመርገጥ ለሚደረግ ማንኛውም ትንኮሳ፣ አስፈላጊው የማስታገሻ ዕርምጃ የሚወሰድ መሆኑ ሊሰመርበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት ዓለም አቀፉን የዲፕሎማሲ ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብና የአገሪቱን ጥቅም በሚያስከበር መንገድ ከውጭ ወዳጅ አገሮች ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ፣ እንዲሁም የታላቁ ህዳሴ ግድብ በታሰበለት የጊዜ ሰሌዳ እንደሚጠናቀቅና ከግድቡ ጋር የሚነሱ ማናቸውም ዓይነት ጥያቄዎች ከአገሪቱ ተጠቃሚነትና ፍትሐዊነት ጋር በመመርመር ‹‹አስፈላጊውን ውይይትና ድርድር ማድረጋችንን እንቀጥላለን፤›› ብለዋል፡፡

በፍትሕ ዕጦት ወይም መዘግየት በከፍተኛ ደረጃ የሕዝብ እሮሮና አለመርካት የሚስተዋል መሆኑን በመረዳት፣ ሕዝቡን ያሳተፈ ተቋማዊ ሪፎርም በማድረግ ሥነ ምግባርና ክህሎት ያለው ባለሙያ በማፍራት እንዲሁም ቀልጣፋና ግልጽ አሠራር በመዘርጋት፣ መንግሥት የተገልጋይ ማኅበረሰቡን የፍትሕ ጥማት ለማርካት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

የመልካም አስተዳዳር ችግር በመንግሥት ተቋማት ላይ ሥር የሰደደ ችግር መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፣ ይህንንም መንግሥት የሚረዳ በመሆኑ ሰፊ፣ ጥልቅና ተግባር ተኮር ሥራ በማከናወን የችግር ምንጭ የሆኑ አሠራሮችንና ሠራተኞችን በመለየት የማስተካከያ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ጠቁመዋል፡፡

የመንግሥት በጀት ድህነትን በፍጥነት ሊቀንሱ የሚችሉ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዘርፎች ላይ እንያዲተኩር እንደሚደረግ፣ የመንግሥት ኢንቨስትመንት አስተዳደር ሥርዓትን በአግባቡ በመተግበር የተጀመሩ የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቁ እንደሚደረጉና መንግሥት በተያዘው በጀት ዓመት የሚያተኩርባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ በምክር ቤቶቹ ዓመታዊ የመክፈቻ ፕሮግራም የመንግሥትን አፈጻጸምና ዕቅድ አስመልክተው ያቀረቡትን የመክፈቻ ንግግር ይዘት በተመለከተ አስተያየት እንዲሰጡበት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር)፣ የመንግሥትን የቀጣይ ዕቅድ በተመለከተ በተደረገው የመክፈቻ ንግግር መነሳት ከነበረባቸው ጉዳዮች መካከል በሁሉም የአገሪቱ አቅጣጫዎች በአሸባሪነት በተሰየሙ ድርጅቶች በዜጎች ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶችና የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም በተመለከተ በበቂ ሁኔታ አለመጠቀሱን ተናግረዋል፡፡ ለአብነት እንኳ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ብዙ ሕዝብ መፈናቀሉንና ጉዳት እንደደረሰበት ዋና ሰብሳቢው ጠቅሰዋል፡፡

በሌላ በኩል የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት መንግሥት ሙስናን ለመዋጋት እያደረገ ያለው ጥረት በቂ አለመሆኑን ያምናል የሚሉት መብራቱ (ዶ/ር)፣ ሙስናን በተመለከተ ሊሰጠው የሚገባው ትኩረት በተገቢው ሁኔታ በፕሬዚዳንቷ አለመነሳቱን አስረድተዋል፡፡ እንዲሁም የፖለቲካ ባህልን ለማሳደግ የመገፋፋቱ ፖለቲካ ቀርቶ የመቻቻል፣ የመነጋገር፣ በውይይት ችግሮችን የመፍታት አዝማሚያዎችንና የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ሊኖራቸው የሚገባውን ሚና በተመለከተ በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በተገቢው ሁኔታ ሲገለጽ መስማት ይፈልጉ እንደነበር አክለው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በአጠቃላይ የኢኮኖሚውን ዘርፍ በተመለከተ በመክፈቻ ንግግሩ የተገለጸው ዘርዘር መደረግ የነበረበት ቢሆንም፣ ምናልባት በሌሎች መድረኮች ይገለጽ ይሆን እንደሆነ እንጂ በፕሬዚዳንቷ የተነሳው በቂ አይደለም ብልዋል፡፡

የእናት ፓርቲ ፕሬዚዳንት ሰይፈ ሥላሴ አያሌው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የፕሬዚዳንቷ የመክፈቻ ንግግር ዋና ዋና ነገሮችን በመጥቀስ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ  በመሆኑ፣ ትልቁ ጉዳይ በቀጣይ ፓርላማው አፈጻጸሙን እንዴት በዝርዝር ይከታተለዋል የሚለው እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ንግግር መጠቀስ ነበረባቸው ካሏቸው ጉዳዮች መካከል፣ በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ ስለሚጠበቀው የአካባቢ ምርጫና እስካሁን ምርጫ ያልተከናወነባቸውን ቦታዎች በተመለከተ ምንም ዓይነት ነገር አለመባሉ አንደኛው ጉዳይ ነው፡፡

በተመሳሳይ በሰሜን ኢትዮጵያ ስለቀጠለው ጦርነት ያደረጉት ንግግር የ‹ጨረፍታ›  እንደሆነ የገለጹት ሰይፈ ሥላሴ (ዶ/ር)፣ በዚህ ጦርነት የተነሳ አገር እጅግ በጣም ብዙ በሚባሉ ችግሮች ውስጥ እያለፈች በመሆኑ ጠንከር ያለ ንግግር መደረግ እንደነበረበት አስረድተዋል፡፡

በሰሜኑ ጦርነት የተነሳ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ የትግራይ ክልል ሕዝብ እያለፈበት ያለውን መከራ ለመግታት አጽንኦት ተሰጥቶና ረገጥ ተደርጎ፣  የመንግሥትን ትክክለኛ አቋም ሊያሳይ የሚችልና ጠንካራ መልዕክት መተላለፍ እንደነበረበት አክለው ገልጸዋል፡፡

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች አገሪቱ ውስጥ በተፈጠረ ቀውስና ምስቅልቅል ምክንያት ከመኖሪያና ከቀዬአቸው ተፈናቅለው የሰው እጅ ጠባቂ ከመሆናቸውም በላይ፣ አምራች የነበረው ይህን ያህል ዜጋ የሰው እጅ ጠባቂ ሲሆን ይህን ተከትሎ የሚመጣ ኢኮኖሚያዊ ጫና እንዴት መፈታት እንዳለበት አጽንኦት ተሰጥቶት መገለጽ እንደነበረበትም ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ ግን መንግሥት በቀጣይ በአገር ፀጥታና ሰላም ላይ ግንባር ቀደም በመሆን በአንክሮ መሥራት እንዳለበት የገለጹት ሰይፈ ሥላሴ (ዶ/ር)፣ አዲስ አበባ ከተማ በሰላም ወጥተን ስለገባን አገር ሰላም ላይ ነች ማለት አይቻልም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አክለውም በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እየተማገዱ ያሉና ሕወሓት እንደ ማገቻ አድርጎ የያዘው ሕዝብ ሲታይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የወደቀ ትልቅ መከራ፣ ሸክምና ዕዳ በትልቁ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በኦነግ ሸኔ የሚፈጸመውን ግድያ በተመለከተ ያለውን ችግር ለመፍታት፣ መንግሥት ራሱን መፈተሽ እንዳለበትና በዚህ ችግር ውስጥ የመንግሥት አካላት እዚህ እንቅስቃሴ ላይ ላለመኖራቸው ዋስትና የለም ብለዋል፡፡ በመሆኑም በተጀመረው በጀት ዓመት መንግሥት የትኩረት አቅጣጫ አስቀምጦ ሳይዘገይ በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለበት፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ ሊያበጅለት እንደሚያገባ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል አገርን ከጦርነቱ ባልተናነሰ ትልቅ ቀውስ ውስጥ ሊከቱ የሚችሉና የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ መሆን ይገባቸዋል ያሏቸውን ጉዳዮች ሲያብራሩ የኢኮኖሚው ሁኔታ፣ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት፣ ሥራ አጥነት፣ በየቦታው ተፈናቅለው የሚገኙ ዜጎችና የፀጥታ ሁኔታን ጠቃቅሰዋል፡፡

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) ሊቀመንበርና  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር  አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣  ከጥቂት ጊዜ በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ እናሳትፋለን በሚል ቃል ገብተው ነበር ብለው፣ በፕሬዚዳንቷ ንግግር አለመነሳቱን ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም በአገራዊ የሰላም ድርድር ሒደትና በትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ‹‹የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ›› እንደሚባለው፣ የየአካባቢው የፖለቲካ ፓርቲ በየአካባቢው ጉዳይ ላይ ሊመክር ይገባል እንጂ በአንድ ፓርቲ ብቻ በአንድ አቅጣጫ መወሰን ስለሌለበት ይህ ጉዳይም በፕሬዚዳንቷ መነሳት እንደነበረበት ጠቁመዋል፡፡፡

አረጋዊ (ዶ/ር) የሕወሓት አመራሮችን በተመለከተ አጉል መራወጥ፣ ሕዝቡን ማደህየት፣ ሕፃናት ልጆችን ያለ ዕድሜ ወደ ጦርነት መጋበዝ የማይጠቅሙ መሆናቸውን ያሳየበት ነው ብለዋል፡፡ ይህንን ማንነት ሕወሓትን ባለፉት 27 ዓመታትና ከዚያም በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያውቀው፣ የትግራይ ሕዝብም ተሰቃይቶበታል እንጂ አንድም ቀን አልፎለት እንደማያውቅ፣ ስለዚህ መንግሥት ይህንን ትኩረት አድርጎ ችገሩን በፍጥነት ሊፈታ ይገባል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -