Tuesday, March 5, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአርብቶ አደር አካባቢዎች ያለው አካታች የፋይናንስ ተደራሽነት ሊሰፋ ይገባል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከጠቅላላው የአገሪቱ ሕዝብ ብዛት ከ12 እስከ 14 በመቶ ድርሻ ባላቸው የኢትዮጵያ አርብቶ አደር አካባቢዎች ያለው አካታች የፋይናንስ ሥርዓት ተደራሽነት ሊሰፋ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ አርብቶ አደር ልማት ፎረም ጥቅምት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በይፋ ሲመሠረት በቀረበ የዳሰሳ ጥናት እንደተመላከተው፣ በአገሪቱ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ያለው የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት ዝቅተኛ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ለአብነትም በአዲስ አበባ ከተማ አንድ የባንክ ቅርንጫፍ ለ1,490 ሰዎች አገልግሎት ሲሰጥ፣ ነገር ግን የአርብቶ አደር አካባቢዎች መገኛ በሆነው የሶማሌ ክልል ወደ 53 ሺሕ ለሚጠጉ ሰዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡

በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙት ባንኮች ጠቅላላ ከሰጡት ብድር 80 በመቶ የሚሆነው የተወሰደው በርካታ የባንክ ቅርንጫፍ ባለበት አዲስ አበባ ሲሆን፣ በአንፃሩ የአርብቶ አደር አካባቢ መገኛ በሆኑት ክልሎች የተወሰደው የብድር ድርሻ በአማካይ 1.6 በመቶ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ምንም እንኳን ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር የተወሰደው በአዲስ አበባ ቢሆንም፣ ይህ ገንዘብ በሌሎች አካባቢዎች ልማት ላይ ሊውል እንደሚችል ታሳቢ ሊደረግ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል ማይክሮ ፋይናንሶች ለግብርናው ዘርፍ የሚያቀርቡት ብድር ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ዕድገት ቢታይበትም፣ ነገር ግን በተለይም ለአርብቶ አደር አካባቢ ነዋሪዎች ያላቸው የተደራሽነት ድርሻ ዝቅተኛ መሆኑን የብሔራዊ ባንክ መረጃ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ወ/ሮ ፍሬአለም ሽባባው በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ አካታች የፋይናንስ ሥርዓት እንዲሁም የፖሊሲ ማዕቀፎች አገሪቱን ወደ ተሻለና የሚናበብ የኢኮኖሚ ሥርዓት የሚወስድ ሥርዓት ነው ብለዋል፡፡ መንግሥት ለአርብቶ አደር ክልሎች አካታች የሆነ የብድር ሥርዓት (ወለድ አልባ ብድር) ለማመቻቸት ያደረገውን በርካታ የመመርያ ማሻሻያ የተናገሩት ኮሚሽነሯ፣ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አተገባበሩ ግን ብዙ ሥራዎች የሚፈልግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ኮሚሽኑ በአዋጅ ከተቋቋመበት ዓላማ አንዱ በገጠርና በከተማ የሚኖረው ሕዝብ በአካባቢው ሀብት ላይ በመመሥረት የተለየ ዓይነትና ደረጃ ባላቸው የኅብረት ሥራ ማኅበራት በማደራጀት የሚገጥመውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግር በጋራ እንዲፈታና በራሱ እንዲተባበር ማድረግ መሆኑን ወ/ሮ ፍሬአለም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አርብቶ አደር ልማት ፎረም በይፋ በተመሠረተበት መድረክ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን በአርብቶ አደር አካባቢዎች በእንስሳት ዕርባታ ላይ ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን የመልማት አቅም በማገናዘብ ወደ ሰብል ምርት ማሸጋገር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የአርብቶ አደሩን የቁጠባ ባህል በማሳደግ በዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ ሚኒስቴሩ ከብሔራዊ ባንክ ጋር እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ፎረሙ በኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ሐሳብ አመንጪነትና አስተባባሪነት በአርብቶ አደሩና በከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ያሉ የልማት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚሠራ አገር አቀፍ ግብረ ኃይል ስለመሆኑ ተነግሯል።

የአርብቶ አደር ልማት ፎረሙ ገበያ መር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት፣ አካታች የፋይናንስ አገልግሎትን በማጠናከርና የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎችን በማሻሻል በአርብቶ አደሩና በከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የሚኖሩ ማኅበረሰቦችን ኑሮ ከማሻሻል ባሻገር ለአገር ኢኮኖሚ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደሚሆን በመድረኩ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ በአርብቶ አደርነትና ከፊል አርብቶ አደርነት ተለይተው የሚታወቁ 220 ወረዳዎች ሲኖሩ፣ ከእነዚህ ውስጥ 173 ወረዳዎች በአፋር፣ ሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙ ናቸው። ከዚህ ባሻገር 47 የሚደርሱት ደግሞ በደቡብ ምዕራብ፣ በደቡብ ብሔርና ብሔረሰቦች ሕዝቦች፣ በጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ይገኛሉ ተብሏል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች