Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአምስት አካባቢዎች ላይ የብረት ክምችትና ጥራት እየተጠና መሆኑ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የተለያዩ አምስት አካባቢዎች ላይ ያለውን የብረት ማዕድን ክምችት፣ የጥራት መጠን (concentration of iron ore) እና የኢኮኖሚ አዋጭነት እያስጠና መሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት መሪነት የሚካሄደው ጥናት በሰሜን ኢትዮጵያ አማራ ክልል የሰቆጣ ቀበቶ፣ ምዕራብ ኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ጊምቢ አከባቢ፣ በኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ  ክልሎች አጎራባች አካባቢ፣ በጅማና በቦረና ያቤሎ አካባቢዎች የሚደረግ ነው፡፡ ይኼንን ጥናት በማጠናቀቅ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ፣ የአገር ውስጥ አምራቾች በጋራ እንዲሁም የውጭ ኩባንያዎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ የማድረግ ዕቅድ ያለ ሲሆን፣ ይኼንን ለማድረግም የጥናቱ መጠናቀቅ እየተጠበቀ መሆኑን የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ማዕድን ሚኒስቴር ከአንድ ወር በፊት መስከረም 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የብረታ ብረት ፋብሪካዎችን ለማቋቋም የሚያስችል የአዋጭነት ጥናት ለማድረግ ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች፣ ፍላጎታቸውን እንዲገልጹ ዓለም አቀፍ ማስታወቂያ አውጥቶ ነበር፡፡ ይሁንና ለሚኒስቴሩ ፍላጎታቸውን ያቀረቡ ብዙዎቹ ኩባንያዎች ‹‹በሚፈለገው ልክ አቅም የሌላቸው›› በመሆኑ ለሁለተኛ ጊዜ የፍላጎት መግለጫ ማስታወቂያ መውጣቱን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

‹‹የፈለግናቸው ኩባንያዎች የፍላጎት መግለጫ አላስገቡም›› ያሉት ታከለ (ኢጂነር)፣ ‹‹እኛ ግን በራሳችን እየሄድ ነው›› በማለት በመንግሥት ተቋም የሚመራ ጥናት እየተከናወነ መሆኑ አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለውን የብረት ክምችት አስመልክቶ ከዚህ ቀደም የተደረጉ ጥናቶች የብረት ክምችት መኖሩን እንጂ መጠኑንና ጥራቱን በትክክል የሚያሳዩ እንዳልነበሩ ገልጸው፣ የንግድ አዋጭነታቸው በትክክለኛው መንገድ ባለመቀመጡ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ አቅም ያላቸውን ኩባንያዎችን አስገብቶ ማምረት አለመቻሉን  አስታውሰዋል፡፡

ጥናት ከሚደረግባቸው አካባቢዎች ውስጥ አንዱ የሆነው የሰቆጣ ቀበቶ እስከ ሽሬ ድረስ የሚዘረጋ ቢሆንም፣ አሁን ጥናቱ የተጀመረው በሰቆጣ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ጊምቢ የሚገኘው የብረት ክምችት ከዚህ ቀደም ተጠንቶ፣ የብረቱ የጥራት መጠን የተቀመጠ ቢሆንም፣ በአካባቢው ያለው ክምችት ‹‹ለምን ያህል ጊዜ ያገለግላል?›› የሚለው ያልታወቀ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

‹‹ይኼ ጥናት ሲጠናቀቅ ማንኛውም ኩባንያ መጥቶ ኢንቨስት ቢያደርግ፣ የኢትዮጵያ የብረት ክምችት በብዛትም ሆነ በጥራት አዋጭነት አለው ወይ የሚለው በላብራቶሪ ይረጋገጣል፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ለዚህም ሲባል የጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ላብራቶሪን የማደስና የቴክኖሎጂ አቅም የማሳደግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የዕድሳቱ ሥራ በቅርብ የሚጠናቀቅ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ታከለ (ኢንጂነር) በአገር ውስጥ ላብራቶሪ ምርመራ ለማደረግ ያስፈለገበትን ምክንያት ሲያስረዱ፣ በአንድ ጊዜ ለምርመራ ወደ ውጭ የሚላከው ‹‹በሚሊዮን ቶን›› የሚሆን ብረት መሆኑንና የይኼንን ለማጓጓዝና ለምርመራው የሚወጣው የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ፣ ‹‹ምርመራ የሚያደርጉት አገሮች ተገቢውን ውጤት ላይሰጡን ይችላሉ፣ ብረት የሚያመርቱትና ወደ እኛ የሚልኩት ናቸው ላብራቶሪም ያላቸው፣ የጥቅም ግጭትም አለበት፤›› ሲሉ ዓርብ ጥቅምት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚኒስቴሩ ቅጥር ግቢ በተሰጠው መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡

እንደ ሚኒስቴሩ ገለጻ በላብራቶሪው ውስጥ በሚደረገው ጥናት በሚቆፈረው አንድ ቶን ድንጋይ ውስጥ ምን ያህል ብረት ይወጣል የሚለው ይረጋገጣል፡፡ ከአንድ ቶን ላይ እስከ 40 በመቶ የሚሆን ብረት ከወጣ ለኩባንያዎች አዋጭ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹ሌላ ጥናቱ የሚያሳየው እነዚህ አምስቱ ቦታዎች ላይ ፋብሪካ መትከል ነው የሚሻለው፣ ወይስ ጥሬ ዕቃውን ወደ ማዕከል ወስዶ ፕሮሰስ ማድረግ ነው የሚለውን ነው” ያሉት ታከለ (ኢንጂነር)፣ ብዙ ጊዜ የተለመደው እዚያው ጥሬ ዕቃ ያለበት አካባቢ በግማሽ የተጠናቀቀ ብረት (ቢሌት) ለፋብሪካ ማቅረብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ኮርያ ያሉ አገራት ሌላውን አማራጭ በመከተል የብረት ማዕድኑ የወጣበት አካባቢ ላይ ግዙፍ ፋብሪካ የመገንባት አማራጭን እንደተከቱ በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡

የብረት ማዕድን ተገኝቶ ወደ ምርት ለመግባት የሀይል ምንጭ እንደሚያስፈልገውና ለዚህ የሚውለውን የከሰል ድንጋይ በኢትዮጵያ ውስጥ ለማምረት እየተሰራ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ሌላኛው አስፈላጊ ግብዓት የሆነው የኖራ ድንጋይም እንዲሁ በአገር ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ብረት ለማምረት የሚቋቋም ኩባንያው ከፍተኛ የሆነ ውኃ የሚያስፈልገው በመሆኑ ፋብሪካ የሚተከለው ውኃ ባለበት አከባቢ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በዚህ ልክ የሚቋቋም ኩባንያው በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ብቻ የሚቻል እንዳልሆነ የሚያነሱት ታከለ (ኢንጂነር)፣ በቅርቡ 27 የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ይዞ በአንድ መቶ ቢሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ‹‹ትልቅ ድርሻ›› እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡ አገር ውስጥ አምራች ኩባንያዎችም በጋራ አቅማቸውን በማደራጀት የማምረት ሥራው ውስጥ እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡

የውጭ ኩባንያዎች ደግሞ ያላቸውን የቴክኖሎጂ አቅም በመያዝ እንደሚቀላቀሉ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እያነጋገሩን ነው፣ ከቱርክ፣ ሩስያ፣ መካከለኛው ምሥራቅ የመጡ ኩባንያዎች አሉ፣ የተሻለ ቴክኖሎጂ፣ ካፒታልና ልምድ ያለውን እያማረጥን ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ኩባንዎቹ እየጠበቁ ያሉት ይኼንን ጥናት ነው፣ ይኼ ጥናት እንደተጠናቀቀ ምርጫው የእኛ ነው፣ የፈለግነውን እናስገባለን፤›› ሲሉም ከጥናቱ በኋላ ያለውን ዕቅድ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች